የወረርሽኙ መጨመር የሚነካቸው ዘርፎችን ስለሚያበዛ፤ የኢኮኖሚውን ጉዳት የበለጠ ያከፋዋል – ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

‹‹ማህበረሰቡ ኮቪድ 19ን አስመልክቶ መንግሥት የሚለውን ተግባራዊ አለማድረጉ ሁኔታውን አስፈሪ ያደርገዋል›› – ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የኢዜማ ፕሬዚዳንት
(ኢፕድ) – ‹‹ማህበረሰቡ መንግሥት፣ የጤና ባለሙያዎች እና ሳይንቲስቶች ኮቪድ 19ን አስመልክቶ የሚነግሩትን ተግባራዊ አለማድረጉ እና ወረርሽኙን እንደከባድ ጉዳይ አምርሮ አለመውሰዱ ሁኔታውን በጣም አስፈሪ ያደርገዋል›› ሲሉ የኢዜማ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።
Image may contain: 1 person, sitting and beardየኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፤ ማህበረሰቡ ከሳይንስ ይልቅ እምነቶች ላይ በማተኮር ብዙ ሰው እስኪሞት ድረስ፤ በዓይኑ እስኪያይ መጠበቁ ወረርሽኙን እያስፋፋ የሚያዘው ሰው ቁጥር ብዛት እንዲጨምር ያደረጋል። የወረርሽኙ መጨመር የሚነካቸው ዘርፎችን ስለሚያበዛ፤ የኢኮኖሚውን ጉዳት የበለጠ ያከፋዋል።
‹‹የቫይረሱን ባህሪ ጥቅል በሆነ መልኩ ልማዱን መግለጽ አይቻልም። ገና ያልታወቁ ተለዋዋጭ ጉዳዮች አሉ። ቀነሰ ሲባል መልሶ የሚጨምርበት ሁኔታ አለ›› በማለት የተናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ የኢኮኖሚው ጉዳት የሚወሰነው ወረርሽኙ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል? ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ዘርፎችን ይጎዳል? የሚለው ከታወቀ በኋላ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደፕሮፌሰር ብርሃኑ ገለጻ፤ ወረርሽኙ የተከሰተው ከምርት ጊዜ በፊት በመሆኑ እና በገጠር በሽታው ገና በደንብ ባለመግባቱ የእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚው አልተነካም። ጉዳቱ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በገጠሩ ክፍል ወረርሽኙ ከተስፋፋ ግን የሚቀጥለው ዓመት የእርሻ ምርት ላይ መስተጓጎል ሊያጋጥም ይችላል። እርሻ ለኢትዮጵያ ትልቅ የኢኮኖሚ አካል በመሆኑ ጉዳቱም የከፋ ይሆናል።
ህብረተሰቡ የጤናውን ዘርፍ ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ማዳመጡ የኢኮኖሚውን ጉዳት የሚቀንስ ቢሆንም፤ ተወደደም ተጠላ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተወሰነ ደረጃ ከውጭው ኢኮኖሚ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጉዳት እንደማይቀር ማስታወስ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
‹‹ስለወረርሽኙ ሲነሳ የውጭ ምንዛሬ ጉዳይ የሚያመጣው ተፅዕኖ በጣም ከባድ እና ከሌላው ጉዳት የበለጠ ነው›› በማለት ተናግረው፤ ቀውሱ ዓለም አቀፋዊ ስለሆነ የኢትዮጵያ ዋና ዋና የውጭ ምንዛሪ ገቢዎች አደጋ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል። ወደ ውጭ የሚላከው ዕቃ ምንም ዕድገት ያላሳየ ከመሆኑም ባሻገር በፊት የሚላኩት እንደአበባ እና አትክልት የመሳሰሉት ምርቶች በቫይረሱ ምክንያት የውጭ አገራት ገበያ መቀዛቀዝ በመኖሩ ከዚያ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ይቀንሰዋል›› ብለዋል።


መረጃ ቲቪን በተሻለ ጥራት እና ፍጥነት እንድናቀርብ እገዛችሁን እንሻለን።
መረጃ ቲቪን ለማገዝ ይህን ሊንክ በመጫን አባል ይህኑ - JOIN Mereja TV