ከታሪክ መድረክ – ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትላንትናና ዛሬ -ኀይሌ ላሬቦ

ይሄን ጽሁፍ በፒ.ዴ.እፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

ጽሑፌን የኢትዮጵያ ጠቅላይ መሪ የነበሩት አቶ ኀይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣናቸውን ከመልቀቃቸው በፊት ከተናገሩት ልጀምር።

“ይኸ መሥርያ ቤታችን ዐይነተኛ መረጃ አለን ወይ ውሳኔ ልንሰጥ የሚያስችል ወቅታዊ የሆነ መረጃ አለን ወይ። እኔ ርግጠኛ ነኝ። አሁን በጠቅላይ ሚኒስቴር መሥርያ ቤት ውስጥ [ውሳኔ ሊያሰጥ የሚያስችል መረጃ] አለን ብዬ ለመናገር የሚያስችል አፍ የለኝም። ሰዎች በተናገሩት ላይ ተመሥርቼ ነው እየወሰንሁት ያለሁት እንጂ በጣም ወቅታዊ የሆነ ታች ያለውን መረጃ አግኝቼ በዚያ ላይ ተመሥርቼ ውሳኔ እየሰጠሁ ነኝ ብዬ ለማለት አልችልም። እያንዳንዳችሁም እንደዚያ እንደሆናችሁ ርግጠኛ ሁኜ ለመናገር እችላለሁ። በመሥርያ ቤቱ በምትሠሩት ሥራ በቂ መረጃ ወቅታዊ የሆነ መረጃ እንደዚሁም ደግሞ የመረጃ ሥርዐት የተዘረጋበት ሁናቴ የለም።” (ጠቅላይ አስተዳዳሪ ኀይለማርያም ደሳለኝ)

ከሺዘጠኝመቶስድሳዎቹ ዓ. ም. ጀምሮ በአገራችን የታየው ሁናቴ ይኸንን የጠቅላይ መሪውን ንግግር ያንጸባርቃል ብል የተሳሳትሁ አይመስለኝም። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አብዛኞቻችን ምንም ሳንመረምርና ሳንጠይቅ እንደማያከራክር እውነት አድርገን የተቀበልናቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የሺዘጠኝመቶስድሳዎቹ ተማሪዎች ባልተጨበጠና በምርምር ባልተደገፈ፣ ብዙም ስለአገራችን በቂ ዕውቀት በሌላቸው ባንዳንድ ምዕራባውያን ምሁራን መረጃዎችና ከጥራዘነጠቅነት የማይሻሉ አወናባጅ ጥናቶችና ምርምሮች በመመርኰዝ፣ ወይንም ምንም ባልተረዱት በነማርክስና በነሌኒን ርእዮተ ዓለም ብቻ በመመሠረት፣ እጅግ ከሐቅ ወደራቀ ድምዳሜ ደርሰው፣ አገሪቷን እከፍተኛ ጥፋት ላይ ለመጣል በቅተዋል።፡ በግለሰብ ደረጃ በዚህ መልክ የሚሠራ ሥራ እጅግ ያስነውራል። በአገር ደረጃ ከሆነ ደግሞ፣ የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ምስቅልቅልና ትርምስምስ ይፈጥራል።

 

የሺዘጠኝመቶስድሳዎቹ ተማሪዎች ወጣት ልጆች እንደመሆናቸው አእምሯቸው ብስለትና ሚዛን በተነፈገ፣ ከጫቅላነት ባልተላቀቀ የዕድሜ ጣራ ውስጥ ነበሩ።  በጊዜያቸው ከፍተኛ ተሰሚነትና ተቀባይነት ያለው፣ በየአቅጣጫው ይነፍስ የነበረው፣የግራዘመም ርእዮተ ዓለም ሰለባ መሆናቸው አይገርምም ይሆናል። ችግሩ በሽምግልና ዘመናቸውም ያንኑ የተዛባና የተጣመመ አስተሳሰባቸውን እንደማያከራክር እውነት አድርገው መውሰዳቸውና አለመታረማቸው ነው። አሁንም እንደድሮው፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከመቶ ዓመት በላይ እንዳላለፈ ይተርታሉ፤ የአገሪቷንም ማኅበራዊ አወቃቀር በበዝባዥና በተበዝባዥ፣ በጨቋኝና በተጨቋኝ መከፋፈላቸውን አልተውም። አገሪቷ ትተዳደር የነበረችውና የተመሠረተችው፣አብዛኞቹን ብሔረሰቦች ጨቈኖ ይገዛ በነበረ ባንድ ብሔረሰብ ጉልበት ነው ብለው ማውራቱን እንደቀጠሉ ነው።

ተማሪዎቹ፣ለጭቈናው መፍትሔ ብለው ያቀረቡት፣ ላገሪቷ ባዕድና ፋይዳቢስ የሆነ፣ የግራዘመም ርእዮተ ዓለም በግድ በሕዝቡ ላይ እንዲጫን በመስበክ ነበረ። አጋጣሚም ሆነና፣ የዘውዱን ሥርዐት ገርስሶ የተተካው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት፣ ጩኸታቸውን ቀምቶ ስብከታቸውን በዐዋጅ ኀይል በግብር ላይ ሊያውለው ሞከረ። ግን ምንም ሳይሠራለት ቀረ ብቻ ሳይሆን፣ ከልክ በላይ እየተፋጠነ ይሄድ የነበረውን የአገሪቷን ዕድገትና ልማት ወደመቶ ዓመት ወደኋላ ለመቀልበስ በቃ። ደርግን ደምስሶ የመጣው፣ አሁን በሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሳዊ ግንባር [ኢሕአዴግ] በመባል የሚታወቀው በዳግማዊ ወያኔ የሚመራው አገዛዝ፤ የተማሪዎቹን ኮቴና ፈር በመከተል የመጡት የጐሣ ታሪክ አቀንቃኞች ጥርቅም መሆኑ መረሳት የለበትም። ይኸም አገዛዝ በበኩሉ፣ በተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ወቅት ይነዛ የነበረውን የጐሣ ሥርዐት አንግቦ ብቅ ያለው፣ እንደግራዘመሞቹ ተማሪዎች ምንም ዐይነት ጥናትና ምርምር ያልተደረገበት፣ በታሪክ ሳይሆን በተረትና በጥላቻ ላይ የተገነባ፣የጠላና የቡና ቤት ወሬ እንደማስረጃ አቅርቦ፣ በጦር ኀይል በማሳመን ነው። የርሱም ርእዮተ ዓለም ልክ እንደደርጉ ከኢትዮጵያ ታሪክ የማይጣጣም የፈጠራ ተረት እንደመሆኑ፣ ሥርዐቱ በየቦታው እየተመታና ፍርስርሱ እየወጣ እንደሆነ፣አሁን ጊዜ ሁላችንም እያየን ያለነው ሐቅ ነው። ደርግ የኢትዮጵያን ዕድገት በመቶ ዓመት ወደኋላ ሲቀለብስ፣ ኢሕአዴግ ደግሞ አንድነቷን በመቦርቦርና በማዳከም፣ ወሰኗንና ልዑላዊነቷን በማስደፈር፣ ታሪኳን በማስነወር፣ ማንነቷን በመናድ፣ ከስድስት ሺ በላይ ዓመታት በጋብቻና በአምቻ በመተሳሰር፣ በባሕልና በቋንቋ በመወራረስ፣ በፍቅርና በመልካም ጉርብትና የኖረውን ሕዝብ፣ባሰኘው መልክ በፈጠረው ክልል አደራጅቶ፣ ርስበርስ በማጋጨትና በመከፋፈል፣ በማጣላትና በማጥላላት፣ ከወታደራዊ መንግሥት በከፋ ሁናቴ፣ ቢያንስ በሦስትና በዐራት መቶ ያህል ዓመታት፣ ወደኋላ መልሷታል ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ግፍና ወንጀል ፈጽሟል ማለት ይቻላል።

 

የዛሬው ጽሑፌ ዋና ትኩረት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምንድር ነው በሚለው ላይ ነው። አንድ ሕዝብ ማንነቱን ካላወቀ ነፍሱን እንደሳተ ግለሰብ ነው። የሁሉም መሣለቂያ፣ መዘባቻ ይሆናል። ከየት እንደመጣ፣ ለምንስ ባለበት እንዳለ፣ የትስ እንደሚሄድ ይጠፋበታል። ለኔ ታሪኩን የማያውቅ ሕዝብ የጉዞን መነሻና መድረሻ እንደማያውቅ በባሕር ላይ እንደተንሳፈፈ መርከብ ነው። በየጊዜው በሚነሣው ማዕበልና ነፋስ እየተመታ የመስጠም ወይንም የመዘረፍና የመጥፋት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እንደአገርና ሕዝብ ማንና ምን እንደነበሩ ማወቅ አሁንም ያሉበትን ሁናቴ ለመገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ የወደፊቱንም የአገሪቷንም ሆነ፣ የመጪውን የታሪክ ተረካቢ ትውልድ ዕጣና ዕድል በትክክል ለመተለም ይረዳል። ከዚያም አልፎ ያላቸውን ብሔራዊ የተፈጥሮ ሀብትና የቅድመ አያቶች የኪነጥበብ ቅርስ፣ በደምብ አድርገው ተረድተው፣ የራሳቸው የታሪክ ድርሻ ምን መሆን እንደሚገባው፣ ከሌላውስ ምንና ምንስ ያህል መዋስና አለመዋስ እንዳለባቸው፣ ጥርት አድርገው እንዲያውቁ ያግዛል።

ጽሑፌ አለቅጥ ረጅም ቢሆንም፣ ውድ አንባቢዬ በትዕግሥትና በርጋታ እስከመጨረሻው ከማንበብ እንደማይቦዝኑ ርግጠኛ ነኝ። ካልሆነም ተስፋ አደርጋለሁ። ንግግሬ፣በመጀመርያ ደረጃ የውጭ አገር ጸሓፊዎች ካላቸው ዕይታ በመነሣት፣እነሱ ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያሉትን፣ አንዲሁም ኢዮጵያም ለውጭ አገሮች ያበረከተችውን አስተዋፅዖ ይቃኛል። ቀጥሎም የነዚህን ገለጻና አስተያየት፣በአገር ውስጥ ከነበሩት ሁናቴዎችና ከተፈጸሙት ድርጊቶች ጋር በማነፃፀር ያገናዝባል። ከዚያም፣እንዴት አሁን ወዳለንበት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውነትን ወደመሸራረፍና ወደመሰርሰር ሁናቴ እንደመጣን በአጭሩ ተመልክቶ ይደመድማል።

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያን ታሪክ ማኳሰስ፣ መሬቷን ማንቋሸሽ፣ ምንነቷን መካድ እንደሙያቸው አድርገው በየቦታው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ድርጅቶች እየተራቡና እየበረከቱ ነበሩ ሊባል ይቻላል። እነሱ የሚነጋገሩባትን ኢትዮጵያን የሚደግፉ መዛግብት ግን በየትም በኩል፣ በምንም መልክና ደረጃ እስካሁን ድረስ ብቅ አላሉም። ወደፊትም ይገኛሉ ብዬ ከቶውኑ አላምንም። በውጭ አገር ጸሓፊዎች ስለኢትዮጵያ ብዙ ተብሏል። ግን ከጥንት ጀምሮ ተደጋግሞ የሚነሣ ነገር ቢኖር፣ አገሪቷ እጅግ በጣም ጥንታዊት፣ ነፃነቷንና ልዑልናዊነቷን ጠብቃ የኖረች፣ ረጅምና አስደናቂ ታሪክ ያላት፣ በመሬቷ አቀማመጥና ሀብት አስቀኚ መሆኗ ነው። ስለሕዝቧ ደግነትና ልበሰፊነት፣ ሕግ አክባሪነትና ጀብዱነት፣መንፈሳዊነትና ታታሪነት፣ ስለገዢዎቿ ፍትሕና ርትዕ ወዳድነት፣ እንዲሁም ነገሥታቱ በቅንነታቸው የሚደነቁ፣ ስለአገራቸው ጥበቃና ስለሕዝባቸው ደኅንንት ከማንም ጋር የማይደራደሩ ስለመሆናቸው በሰፊው ይነገራል።

ከጥንት ጀምሮ ከሚነገሩት ዋኖቹ ነገሮች መካከል ዋናው የኢትዮጵያውያን ታላቁ ክብራቸውና ኩራታቸው በባዕድ ቀንበር አለመውደቃቸው ነው። ግን ይኸ ብቻ አይደለም። ራሳቸውን የሥልጣኔ ሁሉ ምንጭ አድርገው የሚያስቡ መሆናቸውንም ይጨምራል። ሌላው ቀርቶ ዓለም እየተደነቀበት ያለው የግብጾች ሥልጣኔ ባለቤቶች፣ የኢትዮጵያውያን ዝርያ መሆኑን አይደብቁም። በአንደኛ ዘመነ ዓለም የነበረ ዲዮዶሩስ ሲኩሉስ የተባለ የጽርዕ ታሪክ ጸሓፊ፣ ይኸንን የኢትዮጵያውያንን ጥልቅ የጋራ ስሜት እንዲህ ሲል ይገልጣል።

የታሪክ ሰዎች እንደሚነግሩን ከሆነ፣ ኢትዮጵያውያን ከሰው ሁሉ የመጀመርያዎቹ ናቸው። ስለዚህ ያለው ማስረጃ ግልጥ ነው ይላሉ። አሁን ወደሚኖሩበት ምድር የመጡት፣ እንደሌላው መጤ ሁሉ ከውጭ አይደለም፤ ታዲያ በመሠረቱ የአገሩ ተወላጆች ናቸው። ሰው ሁሉ እንደሚስማማው፣  ባላገሮች በሚል ትክክል በሆነ መጠርያ የሚጠሩትም ከዚህ የተነሣ ነው። ሌላው ደግሞ፣ ግብጾች በኢትዮጵያውያን የተላኩ ሰፋሪዎች ናቸው፤ አብዛኛውም የግብፅ ባህል የኢትዮጵያ እንደሆነና፣ ሰፋሪዎቹ አሁንም ቢሆን የጥንት ልማዳቸውን እንዳልተው ነው ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪ [ኢትዮጵያውያን] ስለራሳቸው ጥንታዊነትም ሆነ፣ ስለላኳቸው ስለሰፋሪዎቹ ግብጾች የሚናገሩት እጅግ ብዙ ነገር አለ።[1]

ሁላችንም እንደምናውቀው፣ የማንኛውም ሥልጣኔ መሠረቱ ሃይማኖት ነው። አማልክቶቹን ለማስደሰት ሲል፣የሰው ልጅ ለሰማው የሚያስገርም፣ ላየው የሚያስደምም፣ ወደሰማይ የመጠቁ፣ ወደምድር የጠለቁ ሥራዎች ሠርቷል። የግብጾቹ ፕራሚዶች፣ የክርስቲያኖቹ ካቴድራሎች፣ የእስላሞቹ ደማም መስጊዶች፣ የአይሁዶቹ አስቅኚ ምኩራቦች፣ የህንዶቹ አስደናቂ ቤተመቅደሶች፣ የላሊበላ ካንድ ዐለት የተፈለፈሉ ግሩም ድንቅ የሆኑ ቤተክርስቲያኖች፣ የሃይማኖት ፍሬ መሆናቸው አይካድም። ሃይማኖትን መጀመርያ የጠነሰሰው ሰውም ይሁን ሕዝብ፣ የሥልጣኔ ሁሉ ምንጭና መሠረት ነው ቢባል የሚያከራክር አይመስለኝም። ታዲያ እንዲህ የመሰለ በአሳብ የተራቀቀ፣ በአእምሮው የመጠቀ ሕዝብ፣ የትኛው ነበር ብንል፣ዲዮዶሩስ መልሱን በጊዜው ካገኛቸው የኢትዮጵያውያን አፍ ነጠቅ አድርጎ፣እንዲህ ሲል ያሰማናል።

ኢትዮጵያውያን፣ የሰው ልጅ አማልክትን እንዴት መወደስ፣በመሥዋዕት፣በዑደትና በበዓላት፣ እንደዚሁም በሌላውም ሥነሥርዐት እንዴት ማመስገን እንደሚገባው በመማር፣ የመጀመርያዎቹ እነሱ እንደነበሩ ይናገራሉ። ከዚህም የተነሣ፣ መንሳፈዊነታቸው በሁሉም የውጭ አገር ሰው ዘንድ ይታወቃል፤ሰማይን እጅግ በጣም አድርጎ የሚያስደስተው ኢትዮጵያዉኖች የሚያቀርቡት መሥዋዕት ብቻ እንደሆነ በሁሉም ዘንድ ይታመናል። ለዚህም በምስክርነት የሚጠሩት በግሪኮች ዘንድ ምናልባት እጅግ ጥንታዊ የሆነውንና በርግጥ ከፍተኛ አክብሮት ያተረፈውን ባለቅኔውን [ሆሜርን]ነው። ምክንያቱም እሱ በኢሊያድ [መጽሐፉ] ውስጥ፣ ዜውስና አብረዉት የነበሩት አማልክት፣ ለምን ሊገኙ እንዳልቻሉ ሲገልጥ፣ ኢትዮጵያውያን በየዓመቱ ለአማልክቶች ሁሉ ባንድጋ በሚያቀርቡት መሥዋዕትና ድግስ ሊሳተፉ ብለው ወደኢትዮጵያ በመሄዳቸው ነው ይላል[2] [ስለነፃነታቸውም ሲያብራሩ፣] ለአማልክት ካላቸው መንፈሳዊነት የተነሣ፣ በፊታቸው ሞገስ ስላገኙ፣ ከውጭ ለመጣ ወራሪ ተገዝተው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

በዲዮዶሩስ አባባል፣ ኢትዮጵያ የሁሉም ሥልጣኔ ምንጭ ናት። ኢትዮጵያውያን ደግሞ እንደቀረው የሌላው ዓለም ነዋሪ ሕዝብ፣ ከውጭ ፈልሰው ያልመጡ፣ ታዲያ ያገራቸው የመጀመርያዎቹ ሰፋሪዎችና ባላባቶች፣ በባዕድም ተገዝተው የማያውቁ ነፃና ኩሩ ሕዝብ ናቸው።

ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ የሚነሣው ጥያቄ እንደዲዮዶሩስ የመሳሰሉት፣ ይልቁንም የጥንት ጸሓፊዎች፣ ኢትዮጵያ የሚሉት አገር፣ ከአሁኗ ኢትዮጵያ ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት የለውም፤ በፍጹም ልዩ አገር ነው የሚል ነው። ዲዮዶሩስም ሆነ፣ ከእሱ በፊትና በስተኋላ ስለአካባቢው በጻፉት በውጭ አገር ደራስያን ገለጻ መሠረት፣ ከጊዜ ወደጊዜ ቈዳዋ ይሰፋ ወይንም ይጠብብ ይሆናል እንጂ፣ አገሪቷ ግን ከሞላ ጐደል ዛሬም ያንኑ ስም ይዛ የምትገኘው ኢትዮጵያ መሆኗን ነው የሚያረጋግጡት። ዲዮዶሩስ ራሱ ስለ ኢትዮጵያ መልክአ ምድር ሲናገር፣ “የዐባይ ወንዝ የሚመነጭበት፣ አስደናቂ ሐይቅ የሚገኝበት፣ በጣም ተራራማና ለየት ያለ የዝናም ወራት ያለበት ምድር ነው” ይላል። ጥቂት ቈይተን ወደዐራተኛ ዘመነምሕረት መኻል ስንመጣ ደግሞ፣ ከሮማው ቄሳር ወደአክሱም የተላኩት አቡነ ቴዎፍሎስዮስ እንዱስዩስ የተባሉ ጳጳስ፣ከዐረብ አገር ቀጥለው የት እንደሄዱ ቦታውን ሲገልጡ፣ ራሳቸውን ኢትዮጵያውያን ብለው ወደሚጠሩት ወደአክሱሞች[3][3] ዘንድ እንደሆነ ያብራራሉ።  እንግዴህ አክሱሞች ራሳቸውን የሚጠሩት ኢትዮጵያውን ነን በማለት ከሆነ፣ ጥንት ኢትዮጵያ ተብሎ የሚጠራ አገር፣ ከአሁኑ የተለየ ነበር የሚለው አስተያየት ውሃ አይቋጥርም። በሦስተኛ ዘመነምሕረት ላይ የኖረው ዕውቁ የፋርስ ተወላጅ ማኒ (216-276)፣በዓለም ከታወቁት አራቱ ታላላቅ መንግሥታት ናቸው በማለት ከሚዘረዝራቸው ከፋርሶችና ከሮማውያን ቀጥሎ ሦስተኛውን ቦታ የያዘው፣ የነዚህ ራሳቸውን ኢትዮጵያውያን ብለው የሚጠሩት የአክሱማውያን መንግሥት ነው ይላል። እንዲሁም ከዘውድ ቅርፅነቱ የተነሣ የአዱሊስ ዙፋን በመባል የሚታወቀው፣ በሦስተኛ ዘመነምሕረት ላይ ባንድ ስሙ ባልታወቀ ንጉሥ እንደተሠራ የሚገመተው የመታሰቢያ ሐውልት፣አክሱም በጊዜዋ ከመናገሻ ከተማነት አልፋ፣ አብዛኞቹን የዛሬዎቹን የኢትዮጵያ ግዛቶች በምሥራቅ እስከኬንያ ጠረፍ፣ከዚያም ቀይ ባሕር አልፋ የመንንና ደቡብ ዐረብን፣ በሰሜን ደግሞ እስከግብጽ ወሰን ድረስ ትቈጣጠር እንደነበረች ይነግረናል[4]

ዲዮዶሩስ ስለኢትዮጵያ የሚናገረው በዘመኑ የነበረውን ሐቅ እንጂ፣ ፈጥሮ አይደለም። ከሱ በፊት ወደሦስት መቶ ዘመን አስቀድሞ የግብጽን አገር ዙሮ ያየውና፣ በምዕራባውያን ዘንድ የመጀመርያው የታሪክ ጸሓፊ ወይንም “የታሪክ አባት” በመባል የሚታወቀው፣ ጽርኣዊው ሄሮዶቱስ፣የዲዮዶሩስን ምስክርነት ያጸናል። ለምሳሌ ያህል፣ሄሮዶቱስ ከግዝረት ጋር አያይዞ ስለግብጾችና ስለኢትዮጵያውያን ሲናገር፣ “ግብጾች የግዝረትን ልማድ የወረሱት “ቅድመ አያቶቻችን ናቸው” ከሚሏቸው ከኢትዮጵያውያን ሲሆን፣ ሌላው ዓለም ግን ከነሱ ኮርጆ ነው” ሲል ይገልጻል። በዚህም የኢትዮጵያን ጥንታዊነትን ብቻ ሳይሆን፣ ባህላቸው እንዴት ወደቀሪው ዓለም እንደተዛመተ፣ በዓለም ወደር የሌለውን ሥልጣኔ ፈጠሩ የሚባሉት ግብጾች ራሳቸው የኢትዮጵውያን የልጅ ልጆቻቸው መሆናቸውን ያመለክታል።

በውጭ አገር ኢትዮጵያ የሚትታየው የዓለምን ሥልጣኔ ቀያሽ በመሆኗና፣ በማንም የውጭ ኀይል ባለመገዛቷ ብቻ አይደለም። በዘመኑ ከነበሩት አገሮች ተግባርና ከሰዎች እምነት አንጻር ስንመለከት፣ ካገሩ ለተሰደደው መሸሻውና መጠጊያው፣ በጭቈና ቀንበር ሥር እየማቀቁ ላሉት አማራጭ ኀይል፣ የነፃነታቸው ተስፋ፣ የችግራቸው ማስረሻም ማስታገሻ ሁና ትታያለች። ከአገራቸው የተሰደዱትን ተቀብላ በክብር በማስተናገድ፣ ከባህሏ ጋር አዋሕዳቸው ለከፍተኛ ማዕርግና ክብር የበቁት እጅግ ብዙ ናቸው። ይኸም ሁናቴ፣ ከጥንት ተስዐቱ ቅዱሳን ከተባሉት የክርስትና ሃይማኖት አባቶች ጀምሮ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፣ በዘመናችን ሲፈጸም የታየ የማይካድ ሐቀኛ ታሪክ ነው። በስደተኝነት የመጣው ሰው፣ ባህሉንና እምነቱን እንዲቀይር አልተገደደም። ይልቅስ ባለው ሙያና ዕውቀት አገሪቷን እንዲያገለግል መድረኩ ስለተመቻቸ፣ በኢትዮጵያ ግንባታና ነፃነት አሻራውን ያልተወ የውጭ አገር ሰፋሪ የለም ማለት ይቻላል። ዘጠኙ ቅዱሳን ከሮማውያን ግዛት ሸሽተው መጥተው የአገሪቷን የክርስትናን እምነት ከማጠንከር አልፈው፣ አሁን የምናደንቃቸውን ታሪካዊ ቅርሶች ሠርተው ትተውልን ሄደዋል። በወቅቱ ብሔራዊ ቋንቋ የነበረውን ግእዝ ለሥነ ጽሑፍነት አብቅተውት አዳብረውታል። የክርስትናን እምነት ወደምድሪቷ ያስገቡት አቡነ ሰላማ ከሣቴብርሃን በመባል የሚታወቁት ወጣቱ ፍሬምናጦስ ራሳቸው፣ የትውልድ አገራቸው ተብሎ ከሚገመተው ከሶርያ ወደህንድ ሲጓዙ፣ መርከባቸው ቢሰበርባቸው፣ መጠለያ ሰጥታና በእንክብካቤ አሳድጋ ለታላቅ ክብርና ማዕርግ ያበቃቻቸው ኢትዮጵያ ናት። እንዲሁም፣ በግራኝ ወረራ ወቅት፣ብዙ መጻሕፍት ወደግእዝ በመተርጐምም ሆነ፣ የክርስትናን እምነት በማጠናከር፣ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት፣ የመናዊው እስላም ነጋዴ፣ የበስተኋላው የደብረሊባኖስ ዕጨጌ አባ ዕንባቆም ሌላ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። ኢትዮጵያ በዘመናችንም ቢሆን፥ ከፍተኛ ሰብኣዊነት የመላበትንና፣ ሳያቋርጥ በታሪክ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ለጋሥነቷን እንደተጐናፀፈች ናት። ባገራቸው ክፉ ግድያና ጭፍጨፋ ደርሶባቸው፣ በስደት ወደአገራችን የመጡት አርመኖች፣ በተለያየ የልማት ዘርፍ በመሰማራት፣ ለኢትዮጵያ የዘመናዊነት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳበረከቱ፣ሁላችንም እናውቀዋለን ብዬ ስለምገምት ልገፋበት አልፈልግም። በገዛ ራሳቸው ምርጫ ኢትዮጵያን እንደእናት አገራቸው ተቀብለውዋት ለኖሩትም መልካም መስተንግዶ አልተነፈገም። እነሱም ምንም ዐይነት አድልዎ ሳይደረግባቸው፣ ለከፍተኛ ሹመትና ማዕርግ በቅተው፣ በተለያየ ዘርፍ ተሰማርተው፣ በሥነጽሑፍና በሌላም የእምነት ሆነ የፖሊትካ መስክ፣ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች ማስረጃ ናቸው።

ከላይ እንዳልሁት፣ በዚህ ረጅም ስደተኞችን በማስተናገድና ጥገኝነት በመስጠት ታሪክ፣ ወደኢትዮጵያ ሲደርስ፣ ማንም በእምነቱና በትውልዱ ምክንያት አድልዎ የተደረገበት ጊዜና ሁናቴ ያለ አይመስለኝም። ነቢዩ ሙሐመድ ያገራቸው ባለሥልጣናትና ሕዝብ በአዲሱ ሃይማኖታቸው ምክንያት ቢያሠቃዩአቸውና ዕረፍት ቢነሧቸው፣ ባልንጀሮቻቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያሸሹት ወደኢትዮጵያ እንጂ፣ ወደሌላ አገር አልነበረም። በላኳቸውም ጊዜ ስለኢትዮጵያና ሕዝቧ፣ እንዲሁም ስለገዢዋ የተናገሩት፣ ከሳቸው በፊትም ሆነ በኋላ የመጡት በተከታታይ አለማቋረጥ ያስተጋቡትን ድምፅ ነው። ነቢዩ፣ እግዜር ለችግራቸው እልባት እስከሚሰጥ ድረስ፣ ተከታዮቻቸውን ወደኢትዮጵያ እንዲሄዱ ሲመክሯቸው፣ የሰጡት ምክንያት አገሩ ሰው ወዳድ ነው፤ ንጉሡም ምንም ዐይነት ግፍ የማይታገሥ፣ ሕዝቡን ለማንም ሳያዳላ በሰላምና በፍትሕ የሚገዛ ስለሆነ፣ ወደኢትዮጵያ ብትሄዱ እዚህ ከሚደርሳባችሁ ችግር ታመልጣላችሁ የሚል ነበር። ባልንጀሮቻቸው ደግሞ በአካባቢው ካሉት ኀያላን ከተባሉት እንደሮማዊው (ጽርኡ)ና ፋርሱ ከመሳስሉት መንግሥታት መካከል ሁሉ፣ ኢትዮጵያን ነጥለው የመረጡበትና፣ ደስብሏቸውም ወደዚያ የሄዱት፣ “ሐራጥቃነትን ፈርተው ወደእግዚአብሔር ሊሸሹ” ሲሉ ነበር ይላል። እንግዴህ “ሐራጥቃነትን ፈርተው” የሚለው ቃል ሊሰመርበት ይገባል። በነቢዩ ባልንጀሮችና ቤተሰቦች አስተያየት፣ እምነታቸውን ለመካድ ሳይገደዱ፣ ወይንም በመናፍቅነት ሳይከሰሱ፣ከቀረው ኅብረተሰብ ሳይገለሉ፣ ፈጣሪያቸውን ሊያመልኩ የሚችሉበት አገር “ኢትዮጵያ” ብቻ እንደሆነች ነው የምንረዳው። እነሱም እንደዚህ ዐይነት ንግግር እያሰሙ ያሉት፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት የክርስትና እምነት የአገሪቱ መንግሥት ዋና ሃይማኖት መሆኑን ለዓለም በይፋ ካስታወቁ፣ ወደሦስት መቶ ዓመታት አስቈጥሮ በቈየበት ወቅት ነው። የነቢዩ መሐመድና የደቀመዛሙርቶቻቸው ምስክርነት፣ከጥንት ጀምሮ ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያውያን ይነገር የነበረውን ጥልቅ እምነት ደግመው ከማስተጋባት አልፈው፣በማያወላውል መንገድ ያጠናክሩታል። አስተያየታቸው ከስምንት መቶ ዘመነዓለም ጀምሮ፣ በታወቁ በጥንት የቀለም ሰዎች ይነገር ከነበረው፣በምንም መልኩ የተለየ አልነበረም። እንግዴህ፣ ስመጥሩ የጽርዕ ባለቅኔ ሆመር[5]ም ሆነ፣ “የታሪክ አባት” ሄሮዶቱስ የተውልን ማስረጃዎች፣ ከዚህ በላይ እንዳየናቸው፣ የኢትዮጵያን ታላቅነት ብቻ ሳይሆን፣ ልክ ነቢዩ መሐመድ አንዳሉት፣ ሕዝቧም ደግና ተወዳጅ፣ ኑሮው፣ ባህሉና ሥርዐቱ በፍትሕ ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን አጥብቀው ነው የሚመሰክሩት።

ኢትዮጵያ፣ እንደአብዛኞቹ አገሮች በታሪኳ ባላቋረጠ ጦርነት ተዘፍቃ የኖረች አገር ሲትሆን፣ በአውሮጳና በሌሎች አገሮች እንደታየ ሁሉ፣ በሃይማኖት ላይ ብቻ የተመሠረተ ጦርነት ግን አልተካሄደም ማለት ይቻላል። በኢትዮጵያ ታሪክ፣ “ሃይማኖት የግል፣አገር የወል” የሚለው አባባል፣ ዛሬ የተጠነሰሰ ሳይሆን፣ ዘመናት ያስቈጠረ ነው ቢባል ስሕተት አይመስለኝም። ብዙውን ጊዜ እንደሃይማኖት ጦርነት ሁኖ የሚጠቀሰው፣ [ንጉሥ] ግራኝ በመባል በሚታወቁት፣ በእስላሙ ኢማም አሕመድ ቤን-ኢብራሂም አል-ጋዚና በክርስቲያኑ አፄ ልብነድንግል፣ ከዚያም ቀጥሎም በልጃቸው በአፄ ገላውዴዎስ መካከል የተካሄዱት ውጊያዎች ናቸው። እነዚህ ግጭቶች ግን በመሠረቱ የሃይማኖት እንዳልሆኑ የሚያመለክቱ ብዙ ማስረጃዎች አሉ።

በመጀመርያ ደረጃ፣ ንጉሥ ግራኝ ወደጦርነት ሊያመሩ የበቁት አባቴ ሞተብለው አፄ ልብነድንግልን ቢያረዷቸው፣ ሹመትህን አጽድቄልሃለሁ፤ ግብሬን ገብር” የሚለው የንጉሠ ነገሥቱ ትእዛዝ ቢደርስባቸው የለም አልገብርም[6]” ብለው በጉልበታቸው ተማምነው ነበር፤ ዕድሉም ቀንቶላቸው ለድል በቁ። ይሁንና በእስልምና እምነታቸው ተቀስቅሰውና፣ እስላም ስለሆንሁ ለክርስቲያን ንጉሥ ግብር አልገብርም ብለው እንዳልሆነ ግልጥ ነው። ለጦርነቶቹ ሃይማኖት ተገን እንጂ መነሻውና መሠረቱ “መላውን ኢትዮጵያን እኔ ብቻዬን እገዛለሁ” የሚለው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተለመደውና ሥር የሰደደው የሥልጣን ሽኩቻ ነው።

በሁለተኛ ደረጃ፣ ግራኝን የተዋጉት በዘልማድ የክርስቲያን ግዛቶች ነበሩ የተባሉት ብቻ አልነበሩም። የእስልምና እምነት የሰፈነባቸው እንደሐረር፣ ባሌና፣ አሩሲ፣ እንዲሁም ሐድያና ጉራጌ የመሳሰሉ ግዛቶችም ጭምር፣ በጀግንነት ተዋግተዋቸዋል። ግራኝ ራሳቸው የንጉሥነትን ሥልጣን የጨበጡት እስላሞች የነበሩት ዐምስቱ የአዳል ነገዶች ኀይላቸውን ስላልቻሉትና፣ በጦር ሜዳ ድል ከተመቱ በኋላ ነው። ይኸም መነሻቸው ለሥልጣን እንጂ በሃይማኖት ቅናት እንዳልሆነ ይበልጥ ያስረዳናል።

በሦስተኛ ደረጃ፣ ከግራኝ በፊት ወደሁለት መቶ ዓመት አስቀድመው የነገሡትና፣ በተደጋጋሚ ከእስላም ንጉሥ ጋር የተዋጉት ታላቁ ዐምደጽዮን [1314-1334]፣በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረው የመላው እስላም ንጉሥ እኔ እያለሁ ራሱን የእስላም ንጉሥ ነኝ ብሎ ሾመ ብለው ይከሱታል። በወቅቱ ታሪክ ጸሓፊ ንግግር መሠረት፣ የእስላሞቹም ንጉሥ ምኞት የክርስቲያኑን ንጉሥ መንግሥት ወርሼ አገሬ አደርገውና ጫት እተክልበታለሁ፤ የከብቱንም ጠባቂዎች ወደግመል እረኞች እለውጣቸዋለሁ፣” የሚል ነበር[7]። ስለዚህ የክርስቲያኑ ንጉሠነገሥትም ሆነ የእስላሙ አገር ንጉሥ ጠባቸው የመላዋ “ኢትዮጵያ ንጉሥ ለመሆን” ሥልጣንን እንጂ ሃይማኖትን ያማከለ ትግል እንዳልነበር ያመለክታል። እንግዴህ በየጊዜው በክርስቲያኑና በእስላሙ፣ እንዲሁም በኋላ በተመሳሳይ ደረጃና መልክ፣ በክርስቲያኑና በፈላሻው መካከል ይካሄዱ የነበሩት ውጊያዎች ጠባይ፣ ከመላ ጐደል በሃይማኖት በማስታከክና በማሳበብ ይካሄዱ የነበሩ የሥልጣን ጦርነቶች እንጂ በእምነት ላይ የተመሠረቱ ግጭቶች እንዳልነበሩ ይመሰክራል። ሁኖም ከነዚህ ጦርነቶች መታወቅ የሚገባ አንድ በጣም ጠቃሚ ፍሬ ነገር አለ። ተፈላሚዎቹ በሃይማኖት በማሳበብ መላዋን ኢትዮጵያን ለመግዛትና ለመቈጣጠር ሲጥሩና ልባቸውን ሲዳዳው፣ አንዴም እንኳን የዳሩ አገር ከመኻሉ ለመገንጠል ሲል፣ ጦርነት ያካሄደበት ጊዜና ሁናቴ እስከቅርብ ወቅት በታሪክ አልታየም።

ብዙዎች፣ አንዳንድ ታሪክ ጸሓፊዎችንም ጭምር፣ኢትዮጵያን ከክርስቲያን እምነት ጋር አጣምረው የሚያዩ አሉ። እኔም ራሴ ገና በታሪክ ምርምር ዓለም ዳዴ እያልሁ በነበርሁበት ወቅት፣ ባንዳንድ ምዕራባውያን ጽሑፎች ላይ በመመርኰዝ፣ ይኸንኑ አሳብ ተጋርቼ በተደጋጋሚ ያስተጋባሁበት ወቅት ነበር። ዛሬ ግን፣ከፍተኛ ስሕተት መሆኑን መረዳት ብቻ ሳይሆን፣ታሪካችን የተጻፈበትን ቋንቋ መናገር ይቅርና፣ማንበብ እንኳ የማይችሉ፣ ምርምራቸውን ብዙውን ጊዜ በአስተርጓሚ ያካሄዱት፣ የውጭ አገር በተለይም ምዕራባውያን ጸሓፊዎች፣ አሳባችንን ገና በጫቅላነታችን ሳለን እንደሚመርዙ ለመገንዘብ ችዬአለሁ። በኢትዮጵያ የክርስቲያኑ ክፍል የበላይነት ቢይዝም፣ ነዋሪዎቿ ግን የተለያየ እምነትና ባህል አሏቸው።ፓለቲካውም ሆነ ሃይማኖቱ ሕዝቧን ርስበርስ ከመጋባት አላቆሟቸውም። የዚህ ጥሩ ምሳሌ፣የእስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑት የአዳሎቹና የሐድያዎቹ ባላባቶች፣ ክርስቲያኖቹን ሴቶች አሰልመው ሲያገቡ፣ የክርስቲያኖቹ መሪዎች ሚስቶቻቸው በበኩላቸው፣ የእስላሞቹ የባላባቶች ሴቶች ልጆች እንደነበሩ ማየቱ ይበቃል። ከዚያም ባሻገር፣ በዘመነመሳፍንት የክርስቲያኑን መንግሥት በእንደራሴነት ይገዙ የነበሩት የየጁ ወረሼኮች፣ እስላሞቹን ሴቶች እያከረስተኑ ሲያገቡ፣ የአብዛኞቹ የጐረቤቶቻቸው የወሎዎቹ ሙሐመዶች፣ሚስቶቻቸው የሰለሙ ክርስቲያኖች ነበሩ ማለት ይቻላል። ሁናቴው የሚያሳየን፣ በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደጊዜ በሃይማኖት ሽፋን የተካሄደ ግጭት ነበረ ቢባልም እንኳን፣ የያንዳንዱ ሃይማኖትና ባህል በሌላው መወሳሰቡንና መሰበጣጠሩን ነው[8]

መጪውን አለአድልዎ አስተናግዶ ለወግና ለማዕርግ ከማብቃት ባላነሰ መልክ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ እንደረቂቅ መንፈስና አሳብ ሁና ያገለገለችበትም ሁናቴና ወቅትም አለ። ባጭሩ ሁለት ምሳሌዎችን ልጠቅስና ላብራራ እፈልጋለሁ።

አንደኛ፣ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች ጉልበት አግኝተው፣ ዓለምን በጦር ኀይላቸው ባንቀጠቀጡበት ወቅት፣በክርትስና እምነታቸው የሞራልና የሥልጣን አምባገነንነት ይሰማቸው የነበሩትን አውሮጳውያንን ይመለከታል። በጥምቀተ ክርስትና ምርጥ የእግዚአብሔር ልጆች በመደረጋችን፣ የመንግሥተሰማያት ወራሾች እኛ ብቻ ነን እያሉ ይደነፉ የነበሩት አውሮጳውያን፣ በኢየሩሳሌም ቅዱሳት መካናትን የነጠቀባቸውን፣ የሜዲቴራኒያንም ባሕር በመቈጣጠር እንቅስቃሴቸያውን የገታውን፣ የእስላሞችን ኀይል በምንም መልክ ማንበርከክ ሲያቅታቸው፣ አዳኛችን ብለው የጠነሰሱት ፕርስቴር ጆን የሚሉት በቋንቋችን ሲተረጐም “ካህኑ ዮሐንስ” የተባለውን ነበር። በእምነታቸው መሠረት፣ ካህኑ ዮሐንስ እንደቅዱስ መጽሐፉ መልከጼዴቅ፣ የክህነትንና የንጉሥነትን ማዕርግ የተቀባ፣ በፍትሕና በርትዕ የሚገዛ፣ ባንድ ስሙ በማይታወቅ፣ በሩቅ ምሥራቅ አገር የሚኖር “ክርስቲያን” ንጉሥ” ነው። እንደ አ. አ. በ፲፫፻፻፳፱ ዓ.ም. ላይ አንድ የካቶሊክ ቄስ፣ ከህንድ አገር ሁኖ “እጅግ አስቀኚ ነገሮች” በሚል መጽሐፉ፣ “የካህኑ ዮሐንስ አገር ኢትዮጵያ ናት” ብሎ ከመሰከረበት ጊዜ ጀምሮ፣ ቈይተው በ፲፮፻፸ዎቹ ላይ፣ሌሎች ኢትዮጵያን የጐበኙ የካቶሊክ ካህናት ደግሞ፣ ካህኑን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያያይዘው ምንም ነገር የለም ብለው እስካስተባበሉበት ጊዜ ድረስ፣ የካህኑን ዮሐንስ አገር ለመድረስ፣ ከዚያም የጦር ቃል ኪዳን ጓደኛ ለማድረግ በሚል አሳብ በመነሸጥ፣ በአውሮጳውያን እጅግ ብዙ አስደናቂ ነገሮች ተፈጽመዋል። የካህኑ ዮሐንስ አገር ፍለጋ ዘመቻ፣ ተከታታዩን የአውሮጳውያን ትውልድ መንፈስ አነቃቅቷል። አገሩን የማግኘት ምኞት እንደሸረሪት ድር በልባቸው ውስጥ በማድራት፣ ዐይነ-ኅሊናቸውንም በየአቅጣጫው በማወናጨፍ፣ ለሕይወታቸው ሳይሰጉ፣ በዚህም በዚያም በድፍረት ሲያወራጫቸው ቈይቶ፣ እንደአሜሪቃ የመሳሰሉትን አዳዲስ አህጉሮችን እንዲያገኙና፣ ከሌላውም ዓለም ጋር እንዲተዋወቁ ረድቷቸዋል።

ሁለተኛው ምሳሌ፣መላውን ጥቊር ሕዝብ ይመለከታል። በካህኑ ዮሐንስ አገር አሰሳ ስሜት ተቀስቅሰው፣ አዲሱን የአሜሪቃን አህጉር ያገኙትና፣ እዚያው የሰፈሩት አውሮጳውያን፣ አህጉሮቹን ለማልማት ነፃ የሰው ጉልበት ፈልገው ሊያገኙት የቻሉት አፍሪቃውያንን በባርነት ፈንግለው በማስመጣትና፣ ኢሰብኣዊ በሆነ ሁናቴ በግድ በማሠራት ነበር። የባርያ ንግድና የባርነት ኑሮ ሲያከትም ደግሞ፣ ዐይናቸውን ወደአፍሪቃ አዙረው፣ አህጉሩን በሙሉ በቅኝ ግዛትነት ሲይዙት፣ ከዚህ የግፍ ቀንበር ያመለጠችው ኢትዮጵያ ብቻ ነበረች ማለት ይቻላል። በአሜሪቃም ሆነ በአፍሪቃ አህጉራት የነበረው ጥቊር ሕዝብ፣ ከነጭ የጭቈና ግዛትና ሥርዐት ቀንበር ሊላቀቅ ዐቅም ቢያንሰው፣ ዐይኑን የጣለው በኢትዮጵያ ላይ ነበር። ካህኑ ዮሐንስ የአውሮጳውያንን የአሰሳ ወኔ እንደነሸጠ ሁሉ፣ የኢትዮጵያም መንፈስና ረቂቅ አሳብ የጥቊሩን ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት የመጐናፀፍ ተስፋ አነሣሣ። ከአድዋ ድል በኋላ ደግሞ “ኢትዮጵያ” ከአሳብ ደረጃ፣ “ኢትዮጵያዊነት” ወደሚለው የፖለቲካና የሃይማኖት እንቅስቃሴ ወደመለወጥ ደረሰ። ከአሜሪቃ እስከደቡብ አፍሪቃ፣ ከናይጀርያ እስከኬንያ፣ በኢትያጵያዊነት መፈክር ዙርያ ተሰልፎ የተነሣው ሕዝብ፣ የነፃነትና የእኩልነት ትግሉን ድምፅ በያለበት ሲያክላላው፣ ሲያስተጋባው፣ ሲያከለውና ሲያንረው ቈይቶ፣ በመጨረሻም ዓላማውን ለመምታት በቅቷል።

እንግዴህ ኢትዮጵያ በውጭ አገር ዕይታ የተለያየ አስተያየት ቢሰጣትም፣ ባጠቃላይ የተጫወተችው የሙጥኝ፣ የአማራጭ ኀይል፣ የነፃነትና የእኩልነት ፋና በመሆን ነው። ክርስቲያኖቹ አውሮጳውያን፣ የእስላሙ ኀይል ጡንቻ አይሎ ቢታይባቸው፣ ከኢትዮጵያዊው ካህኑ ዮሐንስ ጋር መተባበር በሚለው አሳብ ዙርያ እንቅልፍ አጥተው አለዕረፍት፣ የተለያዩ ከፍተኛ ጀብዱነት ያሳዩበትን፣ አሰሳዎችንና እርምጃዎችን እንዲወስዱ አድርጓቸዋል። የእስልምና እምነት መሥራቾች በበኩላቸው፣ በጠላቶቻቸው እጅ ተጨፍልቀው ከመጥፋት የዳኑት፣ ኢትዮጵያን መጠለያቸው በማድረግ ነው ማለት ይቻላል። የመላው ዓለሙ ጥቍር ሕዝብ በተራው፣ በነጮች የበላይነት ጭቈና ታፍኖ፣ ማንነቱና ታሪኩ በመደፍጠጥ ላይ በነበረበት ወቅት፣ ርጋታውንና መጽናኛውን ያገኘው፣ለነጻነቱና ለእኩልነቱ ተግቶ እንዲዋጋ ያሰባሰበውና፣ በአንድነት ጐራ ያሰለፈው ኀይል፣ የኢትዮጵያነት መንፈስ ነበር። እንግዴህ ኢትዮጵያዊነት ዘርና ቀለም፣ መደብና እምነት፣ ጾታና ዕድሜ ሳይለይ፣ በአገርና በድንበር ሳይታገድ፣ በችግር ላይ ላለ ሁሉ ፈጥኖ ደራሽ መንፈስና ረቂቅ አሳብ ብቻ አልነበረም። በረጅም የታሪክ ዘመኑ ፍትሕ ለተነፈጉ፣ ሰላም ለተነሡ፣ መጠጊያ ላጡ ከለላቸው ሁኖ የኖረ፣ ሁሉንም በክብር ተቀብሎ ዐቃፊም አስተናጋጅም፣ በበጎ እንጂ በሌላ ተግባር የማይታወቅ ኢትዮጵያ የተባለ ያንድ ግዙፍ አገር መለዮውና መግለጫው ነው።

ታሪክ ያነበበ ሰው፣ የካህኑ ዮሐንስም ሆነ ጥቊሩን ሕዝብ ባንድጋ አሰባስበው ለነፃነት ትግል ያሰለፉዋቸው ኀይሎች ትረካዎች ምን ያህል እውነተኝነት አላቸው ብሎ መጠየቁ አይቀርም። ጥያቄዎቹ አገባብ ያላቸው ናቸው። ከርቀትና የጊዜውን ችግር ለመወጣት ሲባል ያልሆነ ገጸባሕርይ ተሰጥቷቸው በበርካታ የፈጠራ ልብስ ስለተሽሞነሞኑ፣ እውነቱን መለየት ቀላል ባይሆንም፣ ታሪኮቹ ከምናብነት አያልፉም ማለት ግን አይቻልም።ካህኑን ዮሐንስን በተመለከተ፣በ፲፪ኛ ዘመነምሕረት መኻል አካባቢ የነገሡት፣የዛጐው አፄ ይምርሐነክርስቶስ በሥርዐቱ ደንብ የክህነት ማዕርግ የተቀቡ ቄስ ስለነበሩ፣ እንደቅዱስ መጽሐፉ መልከጼዴቅ፣ ካህንም ንጉሥም ነበሩ ማለት ይቻላል። በ፲፫ኛ ዘመነምሕረት ላይ

የኖረው፣ አቡጻሊሕ የተባለ የዐረብ ክርስቲያን ጸሓፊ እንደሚነግረን ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት በሙሉ እቤተመቅደስ ውስጥ ገብተው ይቀድሳሉ[9]” ይላል። ይሁንና ከነዚህ መካከል፣ማንም አውሮጳውያን በሰጡት ዮሐንስ በሚል ስም የሚጠራ ካህን ንጉሥ እስካሁን በኢትዮጵያ ምድር አልተገኘም። ግን ርቀትና ጭንቀት ስለተጨማመሩበት፣ አውሮጳውያን ስሙን አዛብተውት ይሆናል። ማንነቱንም በማጋነን ገጸባሕርዩን አኳኲለውት፣ ታላቅነቱን ለማጉላት እንደሞከሩ አይጠረጠርም። አለበለዚያ፣ ለየት ያለ ጠባይ የሌለው መደበኛ ንጉሥ ከሆነማ፣ የእስላሞችን ኀይል ለመጋፈጥ ትብብሩንና ጓደኝነቱን ማግኘቱ ምን ፋይዳ ይኖረዋል። ስለዚህ የካህኑ ዮሐንስ ታሪክም በፍጹም መሠረተቢስ የሆነ ፈጠራ ነው ሊባል አይችልም።

ጥቁሩን ሕዝብ ለትግል ባንድጋ አሰላፊ የሆነችው “ኢትዮጵያ”ም ሆነች፣ በአገሪቷ የመነጨው፣ ጥንታዊው “የክርስቲያን” ሃይማኖትና፣ የዚህም እምነት ጠባቂና አራማጅ ተቋም፣ ማለትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ ታሪክነታቸው እጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ልክ አውሮጳውያን ለካህኑ ዮሐንስ እንዳደረጉት፣ ጥቍር ሕዝብ አንዳንድ አጠያያቂ ገጸባሕርያትን ስላለባበሰ፣ እውነተኛ ምንነታቸው ጥቂት ቢዛነፍም፣ የታሪኩ ባለቤቶች በርግጥ ሕያውና ግዙፍ ማንነት ያላቸው ናቸው።ርቀትና ጭንቀት መደበኛውን ሰማያዊ ገጸ-ባሕርይ ቀባብተው፣ የተለየ ፍጡር ብቻ ሳይሆን፣ ፈጣሪም እስከማስመሰል እንደሚደርሱ፣ በጊዜያችን ታሪክ የተገነዘብነው ነው። የነጮቹ የቅኝ አገዛዝና የባርነት ቀንበር ያንገፈገፋቸው የጃማይካ ጥቍሮች፣ ለብዦታቸው እምነታቸውንና ተስፋቸውን የጣሉት፣ የሃይማኖታቸውና የማንነታቸው መታወቂያና ምሰሶ ሁኖ በቀረው በራስ ተፈሪ ነው። ቈይተውም ከታሪክ ጋር ሲተዋወቁና፣ ግንኙነቱ እየተጠናከረ ሲሄድ፣ ራስ ተፈሪ አፄ ኀይለ-ሥላሴ መሆናቸውን ተገነዘቡ። ከዚያም ራስ ተፈሪ፣ የእንቅስቃሴአቸው ስም ሁኖ ሲቀር፣ኀይለሥላሴን መለኮታዊነትን በማልበስ አምላካቸው እስከማድረግ በቅተዋል። ታዲያ፣ ጃማይካውያን መለኮታዊ ገጸባሕርይ ቢያለባብሷቸውም፣ ራስተፈሪ የበስተኋላው አፄ ኀይለሥላሴ የተባሉ ንጉሠ ነገሥት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ኑረው አያውቁም ተብሎ አይካድም። በዚያው ልክ ደግሞ፣ አውሮጳውያን ስሙን በማዛባት ዮሐንስ ቢለው ቢጠሩትም፣ በኢትዮጵያ ምድር ላይ የክህነትንና የንጉሥነትን ማዕርግ አጣምሮ የለበሰ ገዢ አልነበረም ማለት አይቻልም። ሁለቱም ኑረዋል። “የአፍሪቃ አባት” በመባል የሚታወቁትን አፄ ኀይለሥላሴን ብዙዎቻችን በዓይናችን አይተናቸዋል። ካህኑ ዮሐንስ ስማቸው ቢዛባም፣ታሪካቸው በአውሮጳ በሚናፈስበት ወቅት አካባቢ፣ በሥነሥርዐቱ ተቀብተው፣እንደቅዱስ መጽሐፉ መልከጼዴቅ ካህንና ንጉሥ የሆኑ ገዢ መኖራቸው ሐሰት አይደለም። በሌላው ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት አብዛኞቹ የዲቁና ማዕርግ የለበሱ እንደመሆናቸው፣የቤተክህነት አካል መሆናቸው የሚጠረጠር አይመስለኝም።

በምዕራባውያን ጭቈና ይማቅቅ የነበረው ጥቍር ሕዝብ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ትግሉ ወቅት፣ በኢትዮጵያዊነት ዙርያ በመሰለፍ ብቻ አልነበረም የታገለው። በሰንደቅ ዓላማዋም ነው። ስለሰንደቅ ዓላማ ብዙ የሚባል ነገር አለ። ግን ጨርቅም ቀለምም፣ እንጨትም እንዳይደለ ርግጥ ነው። ባጭሩ፣ ያንድ ሕዝብ የመሬቱ ባለቤትነት፣ የነፃነቱ ርግጠኝነት፣ (የጥሩም ሆነ የመጥፎ) ታሪኩና ርእዮተ ዓለሙ መግለጫ ነው ብሎ ማጠቃለሉ ይበቃል። ኢትዮጵያ ከዐምስት ዓመት ትግል በኋላ፣ፋሽስቶች አገራችንን ጥለው እንደወጡ፣ ለመላው ዓለም ያስታወቀችው፣ ለሕዝቧም ያበሠረችው፣ በመጀመርያ ሰንደቅ ዓላማዋን በመሬቷ ላይ በመትከል ነው። በቀስተደመና ምስል የተሣለው የኢትዮጵያ ባለሦስት ቀለም ሰንደቅዓላማ፣ በጥንታዊነቱም ሆነ ባዘለው ምሥጢር የሚያስደምም ነው ማለት ይቻላል። አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ ቀለማት፣ ትርጒማቸው የአገሪቷን “ምድር፣መንግሥትና ሕዝብ” ሲያመለክት፣ ባሕርያቸው አንድም ሦስትም መሆኑን ያሳያል። ሦስት ፍጽምናን ሲያንፀባርቅ፣ አንድ ደግሞ የሦስቱንም አካላት በዓላማ፣ በአቋምና በግብር ያላቸውን ውሕደትና እኩልነት ያረጋግጣል። በአረንጓዴ የተመሰለችው ምድር፣ የሁሉም ፍሬ ሕይወት ሲትሆን፣የቀዩ ሕዝብ ደግሞ፣ የምድሪቷ ነዋሪዎች ላገርና ለወገን ፍቅር ሲሉ ካስፈለገ ሕይወታቸውን በጀግንነት ሊሠዉ ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ብጫው መንግሥት፣ የምድርና የሕዝብ ጠባቂ፣ የሁለቱም አንድነት ማተብና ሐረግ ሲሆን፣ ሕዝቡን አገር ለመከላከልም ሆነ ለልማት በኅብረት ማሰለፍ ግዴታውና አላፊነቱ እንደሆነ ይነግረናል።

ከአስድናቂው የአድዋ ድል በኋላ፣ ጥቊር ሕዝብ የኢትዮጵያዊነት መግለጫና የማንነቷ መለዮ ሁኖ ለዓለም የተበሠረውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማንም፣ የነፃነትና የእኩልነት ትግሉ ወቅት፣ እንደትእምርተ ኀይልና እንደትእምርተ መዊዕ ያውለብለብ ነበር። የአሳቡ ጠንሳሽ የመላውን ዓለም ጥቊር ሕዝብ፣ ለዚህ ዓላማ ባንድጋ ያሰባሰበው፣ ስመጥሩው የጃማይካው ተወላጅ ማርኩስ ጋርቬይ[10] ነው። አቶ ጋርቬይ፣ በአ. አ. በ፲፱፻፳ ዓ.ም. “ተመልከት ዓላማህን፣ ተከተል አለቃህን” ሲል የጥቊር ሕዝብ ማንነት መግለጫ፣ የትግሉ ተስፋ እንዲሆንለት የሰጠው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማን ቀለማት ነው[11]። ወደሠላሳ ዓመታት ቈይተው፣ ነፃነታቸውን የተጐናፀፉት አብዛኞቹ የአፍሪቃ መንግሥታትም፣ የአገራቸው ክቡርና አኩሪ ታሪክ፣ የነፃነታቸው ማረጋገጫ፣ የመሬታቸው ባለቤትነት ማስመሰከርያ እንዲሆን የመረጡት፣ እነኚሁኑን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሦስቱን ቀለማት በመዋስና፣ መሠረት በማድረግ ስለነበር፣ ዛሬ “የመላዋ አፍሪቃ ቀለማት” በመባል ይታወቃሉ።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍተኛ አድናቆት በዚህ ብቻ አላበቃም። የአድዋ ድል፣ የጥቁር ሕዝብ ተጋድሎ ደጋፊ የነበረውንና በዘመናዊ ፈጠራው የታወቀውን፣ ጋሬት አውጉስቱስ ሞርጋን[12]ን ከኢትዮጵያ ጋር ሊያተሳስር በቅቷል። የመኪናና የተለያየ ተሽከርካሪ በዓለም ላይ ብቅ ማለት፣ መጓጓዣ መንገዶቹን እጅግ በጣም አጨናንቆ፣ ብዙ ሕዝብ ለአደጋ ሲያጋርጥ፣ ለሞት ሲዳርግ፣ ብዙ ቢሞከርም ፍቱን መፍትሔ ሊገኝ አልተቻለም። የተቻለው፣ በአ. አ. በ፲፱፻፳፪ ዓ. ም. ላይ፣ አቶ ሞርጋን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለሞች ለትራፊክ መብራት አገልግሎት በማዋሉ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ፣ ሦስቱ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት፣ ዘመናዊ ተሽከርካሪ በሚጓዝበት መንገዶች፣ በመላው ዓለም ከዳር እስከ ዳር፣ የሰውን ልጅ መመላለሻ ጠባይ ተቈጣጣሪ ሁነዋል። ሦስትዬው ቀለማት የትራፊክ መብራት በያለበት፣ የሕግ አስጠባቂና አስከባሪ ኀይል ብቻ ሳይሆን፣ አገልግሎቱን ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ፣ የብዙውን ሰው ሕይወት ከሞት አድነዋል፤ ትርምስምስና ጭንንቅ ከየመገናኛ መንገዱ አስወግደው ዘርና አካባቢ፣ ቋንቋና ባህል፣ እምነትና የትምህርት ደረጃ፣ መደብና ማዕርግ፣ ዳራና ፆታ ሳይለዩ፣ ሁሉንም በእኩልነትና በትክክል፣ በሥነሥርዐትና በመከባበር እያስተናገዱ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ፣ ለዓለምዐቀፉ ጥቊር ሕዝብ የነፃነት አድማሱን የምታንቀሳቅስ ረቂቅ መንፈስ፣ የመጨረሻ ድሉም ተስፋና አርአያ ብቻ ሁና አልቀረችም። የትግሉን ሕልም እውን ለማድረግ፣ ለአብዛኛው ጥቊር ሕዝብ፣ በተለይም ለአፍሪቃ፣ ወሳኝ አስተዋፅዖም በተግባር አበርክታለች። ከዚህም የተነሣ የአፍሪቃን የነፃነት ትግል በጊዜው በዋናነት የመሩት አፄ ኀይለሥላሴ “የአፍሪቃ አባት” የተባለ ስያሜ ሲሰጣቸው፣ ኢትዮጵያ ደግሞ “የአፍሪቃ እናት” በመባል ትታወቃለች። መናገሻ ከተማዋም የመላዋ አፍሪቃ ድርጅት መቀመጫ ሁና ተመርጣለች።

ኢትዮጵያ ሁሉንም በክብር ተቀብላ በእኩልነትና በነፃነት የማስተናገድና የማዋሃድ፣ የማቻቻልና አብሮ የማኖር ታሪክ ያላት አገር መሆኗን አይተናል። እነዚህ እሴቶች ከውጭ ለሚመጣ ብቻ የሚለገሡ ወይንም ለይስሙላ የተደረጉ አይደሉም። ጩራቸውን ወደውጭ አገር ለማፈናጠር የበቁት፣በአገር ውስጥም የኢትዮጵያዊነት ምንነት ራሱ መግለጫውና መለዮው በመሆናቸው ናቸው። ኢትዮጵዊነት ሁሉንም ዐቃፊና አስተናጋጅ፣ አግባብቶና አቻችሎ በአንዲት አገር ጥላ ሥር፣ በአንድነት፣ በነፃነትና በእኩልነት የሚያኖር፣ ባለረጅም ታሪክ፣ ሁለገብና ውስብስብ ማራኪ ባሕርይ ያለው ረቂቅ ኀይል ነው። ዛሬ የዘውግና የግራዘመም ርእዮተ ዓለም አቀንቃኞች እንደሚሉን፣ ኢትዮጵያ ባንድ ዘውግ ወይንም አንድ ቋንቋና ባህል ባለው ብሔረሰብ የተፈጠረች አገር አይደለችም፤ ሁናም አታውቅም። በተለያየ ጊዜና ምክንያት፣ ሰበብና ወቅት፣ ከልዩ ልዩ አካባቢ በመሳሳብ የተዋሐዱ የብሔረሰቦች ጒንጒን ናት[13]

በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ያለው ልዩነት የቋንቋና የእምነት እንጂ፣ የዘር ወይንም የቀለም አይደለም። ከስድስት ሺ በላይ ዓመታት ጀምሮ፣ ሕዝቡ በወረራና በፍልሰት ሲንሰራራና ሲስፋፋ፣ ሲደበላለቅና ሲዋሐድ ኑሯል። አገሪቷም በየጊዜው የውድቀትና የትንሣኤ፣ የመጥበብና የመስፋት ተመክሮ አጋጥሟታል። እነዚህ ሁናቴዎች በተከታታይ በተፈራረቁባት የረጅም ታሪክ ጉዞ ባላት አገር ውስጥ፣ ለሥልጣን፣ ወይንም ለሀብት፣ አለበለዚያም ለከብት ግጦሽ፣ ወይንም ለፍትሕ ፍለጋ ሲል የሰሜኑ ማኅበረሰብ ወደደቡብ፣ የደቡቡ ወደሰሜን፣ የምሥራቁ ወደምዕራብ የአዜቡ ወደሊባ፣ የመስዑ ወደባሕር፣ በመሃሉ አገር አቋርጦ በማለፍ ፈልሶ፣ በየአቅጣጫውና በየዳር ድንበሩ ሲሰፍር ቈይቷል። በየጊዜው አገሪቷን ያናውጧት የነበሩት የርስ በርስ ጦርነቶችና ግጭቶች፣ ባንድ በኩል አካባቢውን ጐድተዋል ቢባልም፤ በሌላው በኩል ደግሞ አብዛኛውን የኢትዮጵያን ሕዝብ፣ በዚያው ልክ ከማቀራረብ አልፈው፣ አዋህደዉታል። በተለያየ ዘመንና ምክንያት በየወቅቱ የተካሄደው የሕዝብ ፍልሰት በተራው፣ ለሃይማኖቶች መስፋፋት ረድቷል። ለንግድና ለንግደት ከሚደረጉት እንቅስቃሴዎችም ጋር ሁኖ፣ እሱም ልክ እንደጦርነቶቹ፣ በመጨረሻ ላይ ሕዝቡን ወደየርስ በርስ ጋብቻና ወደባህልና ቋንቋ ውርርስ መርቷል። በጠቅላላ፣ እነዚህ ገጠመኞችና ሁኔታዎች፣ በርካታውን የኢትዮጵያን ሕዝብ በታሪክ፣ በደም፣ በቋንቋ፣ በባህል ከማስተሳሰር አልፈው፣ እንደሰርገኛ ጤፍ ደበላልቀውታል ለማለት ያስደፍራል። ከዚህም የተነሣ፣ በዘሩ ጭንጩ የሆነ ዘውግ፣ በርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ አለ ማለት አስቸጋሪ ነው። እውነት ነው፣ እያንዳንዱ ዘውግ ራሱን የሚገልጥበት የተለየ የራሱ ነው መባል የሚችል የአካባቢ ቋንቋ አለው። ይኸ ማለት ግን፣ ሁሉም ቋንቋውን ተናጋሪው ሕዝብም ሆነ ግለሰብ፣ ካንድ እንጅላት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው ማለት አይቻልም። አብዛኛው ለሚኖርበት መጤ፣ አለበለዚያም ከሌላ አገር ከፈለሰ መጤ ጋር የተቀላቀለና የተዋሐደ ነው። ስለዚህም፣ በርካታው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣አንዱ የሌላው የሥጋው ቊራጭ፣ የደሙ ፈሳሽ ነው ቢባል፣ መቼም ከእውነት የራቀ አባባል አይደለም። ድርና ማጉ አንድ ነገድ ወይንም አንድ ጐሣ የሆነ ሰው፣ በኢትዮጵያ ምድር አካቶ የለም ማለት በርግጥ ባይቻልም፣ የብሔርነት ስያሜ የሚገባው ሕዝብ አለ ማለት ግን እጅግ ያጠራጥራል።

ለኢትዮጵያዊነት ስብጥርነት፣ ዋነኞቹ ምክንያቶች የማእከላዊው መንግሥት የመንሰራፋትና፣ ግዛቶቹን ለማስፋፋት ሲል ኩታገጠም አገሮችን የማዋሀድ ጥረት ያስከተሏቸው ጦርነቶች ሆኑ፣የሕዝብ ፍልሰቶች ናቸው ብለናል። እስኪ አጠር ባለ መልኩ ጥቂቶቹን እንቃኝ።

ከክርስቶስ ልደት በፊት የጀመረው የአክሱሞች መንሰራፋት፣ ከዛሬዋ ኢትዮጵያ በርዝመትም በስፋትም እጅግ የሚበልጡ አገሮችንና በውስጣቸውም የሚኖረውን ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ሥር ካጠቃለለ በኋላ፣ በዘጠነኛው ዘመነምሕረት አካባቢ ሲያበቃ፣ እስከ፲፫ኛው ዘመነምሕረት ድረስ ባለው ጊዜ በአገዎች ተተኩ[14]

 

ካርታ ፩።

በሁለቱ ሥርወ መንግሥታት ሽግግር መካከል በነበረው የጨለማና የድብልቅልቅ ዘመን በመባል በሚታወቀው ወቅት፣ በየአካባቢው ከፍተኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝውውርና ፍልሰት ተፈጽሟል ማለት ይቻላል። የአገዎቹ በትረ-መንግሥት ሲያከትም፣ ሥልጣኑን የወረሱት ሰለሞናውያን፣ እስከ፲፮ኛ ዘመነምሕረት ቈዩ[15]። በግዛታቸው ዘመን፣ እነሱ ያልደረሱበት የኢትዮጵያ ምድር፣ ያልተዋጉበት ማእዘን አልነበረም ማለት ይቻላል። ከነሱ ቀጥሎ፣ ተራው የሱማሌዎችና የአዳሎች ሆነ። እነሱም ለተሻለ ኑሮ ሲሉ፣ ከአደን ሰላጤ ተነሥተው ወደሐረር ደርሰው፣ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ተሰማርተው ሲኖሩ፣የእስልምና እምነት አራማጆችና ሰባኪዎች ሁነው፣ ግራኝን በመከተል ከምሥራቅ ወደምዕራብ ዘመቱ[16]። እዚህ ላይ መሰመር ያለበት ዛሬ ሱማሌና ጂቡቲ በመባል የሚታወቁት ሁለቱ ልዑላን መንግሥታት፣ ከአክሱማውያን ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ ግዛት እንደነበሩ ነው። ስለዚህ ግራኝም ሆነ ጦር ሠራዊቱ ኢትዮጵያውያን ነበሩ።

ካርታ ፪

 

ግራኝ ለዐሥራዐምስት ዓመት ያህል ባካሄደው ጦርነት፣ ኢትዮጵያን የመግዛት አሳቡ ቢከሽፍበትም፣ ወረራው ያስከተለው ለውጥ ሥረነቀል ብቻ ሳይሆን፣ጥልቀትና ዘላቂነት ያለው ነበር። በወረራው ምክንያት የአክሱማውያን ውድቀት ካስከተለው ይበልጣል ማለት የሚቻል፣ከፍተኛ የሕዝብ ፍልሰትና ዝውውር ተፈጽሟል[17]። በኢትዮጵያ ላይ ለበላይነት ይታገሉ የነበሩት፣ ሁለቱ የክርስቲያኑና የእስላሙ ኀይል ከልክ በላይ ሲዳከም፣ ተጠቃሚ የሆነው ዘላኑ የኦሮሞ ሕዝብ ነው። በአፈታሪክና በሱም ተደግፈው በየጊዜው በተጻፉት ጽሑፎች መሠረት፣ የኦሮሞ ሕዝብ መነሻው ከደቡብ ከባሌ እንደሆነ ይነገራል። ከዚያ እሱም ተራውን ከብቱን ይዞ ግራውንና ቀኙን እየወረረ እየተጓዘ፣ በ፲፯ኛና በ፲፰ኛ ዘመነምሕረት በአራቱ የአገሪቷ ማእዘኖች ለመንዘራፈጥ በቃ[18]

ካርታ ፫

 

በኢትዮጵያ ታሪክ የአባ ባሕርይን ጽሑፍ በስሕተት በመተርጐም፣ ኦሮሞችን በተመለክተ ሁለት ዐበይት ስሕተቶች ሲደጋገሙ ይታያሉ። አንደኛው፣ ኦሮሞችን እንደመጤዎች የማየት ዝንባሌ ነው። ሐቁ ግን፣ ከዚያ እጅግ በጣም የራቀ ነው። አባ ባሕርይ የጻፉት ስለኦሮሞ ሕዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ መድረክ ብቅ ማለቱ፣ ስለኅብረተሰቡ አወቃቀርና፣ ከሱም ጋር በማያያዝ ፍልሰታⶨው ስላስከተላቸው ብሔራዊ ጠንቆችና ውዝግቦች እንጂ፣ ስለኢትዮጵያዊነት ማንነቱ አይደለም። ኦሮሞች ኢትዮጵያውያንና የአገሪቷም ሕዝብ አካል ስለመሆናቸው፣በፍጹም የሚያጠያይቅ ሁናቴም ጊዜም የለም። በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖር ከነበረው ሕዝብ አንዱ መሆናቸውን፣ በ፲፬ኛ ዘመነምሕረት ላይ የተጻፈ ታሪከ ነገሥት በግልጥ ይመሰክራል። ከ፲፫፻፯ እስከ፲፫፻፴፮ ዓ.ም. የነገሡት፣ ስመጥሩና ገናናው ሰለሞናዊው ንጉሥ አፄ ዐምደጽዮን፣ በደዋሮ አድርገው ሽፍታውን የአዳልን ንጉሥ ሊወጉ ሲሄዱ፣ በ፳፰ ሚያዝያ ላይ በዓለትንሣኤን “በደስታና በሰላም ያከበሩትና”፣የሚወዷቸውንና እጅግ የምትደነቀውን “ባለቤታቸውን ንግሥት መንገሣን” መጀመርያ ትተውአቸው የሄዱት፣ በኋላም በሠኔ ሰባት ላይ ተመልሰው መጥተው የወሰዷቸው፣ “በጋላ”ና “ከጋላ” አገር ነበር[19]። ይኸ በንጉሠነገሥቱ የተፈጸመው ሥራ በማያከራከር ግዛታቸው

 

 

ካርታ ፬

 

ውስጥ መሆኑ አያጠያይቅም። ድርጊቱም የሆነው “ጋላ[20]” የተባለ ሕዝብ ኢትዮጵያን መውረር ጀመረ ከተባለበት ጊዜም ሆነ፣ አባ ባሕርይ መጽሐፋቸውን ከመጻፋቸው ወደሁለት መቶ ዘመን አስቀድሞ ነው።

ሁለተኛው ስሕተት፣ ካንዳንድ ባህላቸው መመሳሰል የተነሣ፣ ኦሮሞችን እንዳንድ ሕዝብ የማየት፣ ወረራቸውንም አንድ ሁነው እንደፈጸሙ አድርጎ የማሰብ ሁናቴ አለ። እውነቱ ግን፣ ከባህልና ከቋንቋ ተመሳሳይነት በዘለለ፣ የተረጋገጠ ምንም ዐይነት ታሪካዊ አንድነት የላቸውም። በታሪክም የሚታወቁት ቱለማ፣ ጃዊ፣ ሊበን፣ ለበቻ በመሳሰሉት እጅግ በጣም በተለያዩ የጐሣ መጠርያቸው እንጂ፣ ኦሮሞ ወይንም “ጋላ” ተብለው አይደለም። የኦሮሞ ዘር አባቶች እንደሆኑ የሚነገሩት በረይቱማና ቦረንም፣ ጥንት አንድ አካባቢ ሲኖሩ አንድ ሕዝብ ሊሆኑ ይችላሉ። ልክ እንደዛሬዎቹ አይሁዶችና ዐረቦች፣ ወይንም ከዚያ ወረድ ሲል የጀርመን ዘር ምንጭ ናቸው እንደሚባሉት፣ እንደኦስትሮጎቶችና ቪሲጎቶች ማለት ነው[21]። የቋንቋቸውና የባህላቸውም ተመሳሳይነት ከዚያ ጋር የተያያዘ ሊሆን ቢችልም፣ የተረጋገጠ ነገር ግን በፍጹም የለም። ይሁንና፣ ያ አዝማናት የቈጠረ፣ የጥንት ታሪክ ነው። የአዳምም ሆኑ፣ ከዚያ ወረድ ስንል የይስሐቅ ልጆች፣ ማለትም የዛሬዎቹ አይሁዶችና ዐረቦች፣ እንዲሁም የእንግሊዞችና የሰሜን ኢጣሊያን ሎምባርዶች፣ ቅድመአያቶች አንድ ቋንቋ ይናገሩ ነበር እንደማለት ነው። ዛሬ ግን፣ ሁሉም እንደየአሰፋፈራቸውና እንደየነገዳቸው፣ በተለያዩ ስሞች ይጠራሉ፤ የሚናገሩትም የየአገራቸውን ቋንቋ፣ ማለትም እንግሊዝኛ፣ እስጳንኛ፣ ኢጣሊያንኛ ወዘተ. ነው።

ወረራቸውን በተመለከተ፣ ባህላቸው ቢመሳሰልም፣ የተለያዩ የኦሮሞ ጐሣዎች ከጥንት መኖርያቸው ከደቡብ ኢትዮጵያ ተነሥተው መኻል አገሩን የወረሩት፣ እንደአንድ ሕዝብ ሳይሆን፣ርስበርሳቸው በከብታቸው ግጦሽ እየተፋጁ ነበር። ላንድ ዓላማ፣ ወይንም የጋራ ችግር ወይንም ጠላት ሊጋፈጡ ሲሉ፣ አብረው የመከቱበትና የዘመቱበት ጊዜ፣ በታሪክ ውስጥ ከቶውኑ የለም። ጐሣዎቹ በታሪክ የሚታወቁት፣ በትብብር ሳይሆን በርስበርስ ለከብታቸው ግጦሽ በመጣላትና በመጨፋጨፍ ነው። የማንነታቸውና የአንድነታቸው መግለጫ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት[22] ነው። ሁለቱንም በገሃድ ያስመሰከሩት በኢትዮጵያና በኢትዮጵዊነት ጥላ ሥር ከሌላው ሕዝብ ጋር አብረው በመኖር፣ ከሱም ጋር ጠላትን በአንድነት በመመከትና፣ አገሪቷን በጀብዱነት በመከላከል ነው። ከዚህ የተለየ ታሪክ ግን፣ የዛሬው የጐሣ አቀንቃኞችና የግራዘመም ርእዮተ ዓለም አራማጆች፣እንዲሁም የ”ብሔረሰባችን ወኪል እኛ ብቻ ነን” ብለው ራሳቸውን በራሳቸው የሾሙት፣ የጠባብ ብሔርተኞች ስብስብ የፈጠሩት ልበወለድ እንጂ፣ ምንም ዐይነት እውነተኝነት የላቸውም። ቀጥለን የሚናየው ታሪክ ይኸንን እውነት በማያወላዳ ሁናቴ ያረጋግጥልናል።

ኦሮሞች ተራቸው ሁኖ ፍልሰታቸውን የጀመሩት፣ ከላይ እንዳልሁት፣ በ፲፮ኛ ዘመነምሕረት መኻል አካባቢ ነው ተብሎ ቢገመትም፣ ግማሽ ዘመን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግን፣ ከውጭ አገር ከመጣ፣ ማለትም ከባዕድ የኢትዮጵያ ወራሪ ጠላት ጋር ሲፋለሙ፣ የኢትዮጵያን ዳርና ድንበር ሲጠብቁና ሲያስከብሩ ይታያሉ። ለአብዛኞቻችን፣ይልቁንም ኢትዮጵያ የመቶ ዓመት ታሪክ አገር ናት እያሉ ለሚያንቋሽሹ፣ የሺ ዘጠኝ መቶ ዐምሳዎቹና ስድሳዎቹ ትውልድ፣ ኢትዮጵያውያን በውጭ አገር ጠላት ላይ የተቀዳጁት ድል ሲነሣ፣ እንደወሳኝና ታሪካዊ አድርገው የሚያዩት፣ በኢጣልያን ላይ የተፈጸመው፣ የቅርብ ጊዜው፣ የአድዋ ድል መሆኑ አይካድም። ከዚያ ግፋ ሲል ሌላ ለትዝታ የሚበቃ ቢኖር፣ ራስ አሉላ በዚሁ በኢጣሊያን ጠላት ላይ አስቀድመው በዶጋሌ፣ አለበለዚያም አፄ ዮሐንስ በግብጽ ላይ በጉራዕና በጉንዴት የተጐናጸፏቸው ድሎች ናቸው። እውነቱ ግን፣ ኢትዮጵያ፣ ዳር ድንበሯን በመድፈር፣ቅኝ ግዛቱ ለማድረግ የሞከረውን ኀይለኛ ባዕድ ወራሪ፣ በልጆቿ ትብብር ጡንቻውን ሰብራ፣ ነፃነቷንና ልዕልናዋን ያስከበረችው፣ በቅርቡ በዘመናችን የመጣውን ጠላት በጀግንነት በመመከት ብቻ አልነበረም። በ፲፭፻፸፩ና በ፲፭፻፹፫ ዓ.ም. ላይ፣ ከኦቶማን ቱርኮች ጋር ሁለት የሞት የሽረት ትግል ተፋልማ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከፍተኛ ድል ለመቀዳጀት በቅቷል። ድሉ ከያገሩ የተወጣጣው የወታደር ኀይል ውጤት ቢሆንም፣ ለመጀመርያ ጊዜ የኦሮሞ ፈረሰኛ፣ ልክ በጊዜአችን በአድዋ እንዳደረገው፣ በዚህም ጦርነት ወሳኝ ሚና የተጫወተበት ጊዜ ነበር ተብሏል። ጦርነቱ ልክ እንደአድዋው፣ ለኢትዮጵያ ህልውና እጅግ በጣም ወሳኝ ነበር። ያኔ አብዛኛውን ዓለም ይገዛ በነበረው በኦቶማን ቱርክ የጦር ኀይል ኢትዮጵያ ብትሸነፍና፣ ሰለባው ሁና ብትቀር ኑሮ፣ ታሪኳና ቅርጿ፣ የሕዝቧም ሥነልቦና፣ እንዲሁም የአገሪቷ ባህልም ሆነ እምነት፣ ዛሬ ከምናየው እጅግ በጣም የተለየ ሁኖ እንደሚቀር አያጠራጥርም። ሌላው ቢቀር፣ በማንም ባልተደፈረ የሕዝቧ የነፃነትና የድል ታሪክ፣ የማይሻር መጥፎ የሥነልቦና ጠባሳ በተወ ነበር። እንግዴህ ኦሮሞኛ ተናጋሪው ኅብረተሰብ፣ ታሪክ ከመዘገባቸው ከነዚህ ሁለቱ ጦርነቶች ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካለንበት ወቅት ድረስ፣ እንደሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እኩል አሻራውን ያላሳረፈበት የጦር ሜዳና ድል በኢትዮጵያ ታሪክ የለም ማለት ይቻላል።

ካርታ ፭

 

ከነዚህ ጦርነቶች ወዲያ፣ ተመሳሳይ እጅግ በጣም ጥልቅ የሆነ የኦሮሞች የውሕደት ሂደት፣ በሌላውም መስክ በጉልህ ሲፈጸም እናያለን። ወረራቸውን ጀመሩ በተባለው በመቶ ዓመታቸው ውስጥ፣ ኦሮሞች ከፍተኛ የቤተመንግሥት ባለሟሎችና፣ ያገር ግዛት አስተዳዳሪዎች ከመሆን አልፈው፣ በከፍተኛ የኢትዮጵያ የቀለም ትምህርትም ደረጃ የመጠቁና የበቁ ግለሰቦች እንደነበሩ፣ ጢኖ በመባል የሚታወቁት ጸሓፈ-ትእዛዝ አዛዥ ተክለሥላሴ [፲፮፻፲፪-፲፮፻፴፪] ጥሩ ምስክር ናቸው። ንጉሠነገሥቱ አፄ ሱስንዮስ፣ “እንደልቤ ታማኝ” የሚሏቸውና፣ ዋናው አማካሪያቸው የነበሩት፣ አዛዥ ጢኖ፣ የኛም የራሳችን ቋንቋ ብለው ከሚመኩበት ከአማርኛ በተጨማሪ፣ ኦሮሞኛን፣ እንዲሁም ግእዝን አሳምረው የሚያውቁ፣ አቀላጥፈው የሚናገሩ፣ ቅኔ የሚቀኙ፣ አንደበታቸው የተባ፣ ብዕራቸው የሰላ ጸሓፊ ብቻ አልነበሩም። በጊዜያቸው፣ በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ የለየላቸው፣ “ምርጥ የቅኔ ምሁራን” በመባል የሚታወቁት፣ ቢቈጠሩ ዐሥር እንኳን የማይሞሉ፣ የቅኔ ትምህርት ዐዋቂዎች ክበብም፣ ዋና አለቃቸው ነበሩ። አድናቂዎቻቸው ኢትዮጵያውያን ብቻ አልነበሩም፤ በጊዜው በአገሪቷ ውስጥ ከፍ ያለ ዕውቀት የነበራቸው አውሮጳውያንም፣ “በማሰብ ችሎታው የረቀቀ፣ በተሰጥዎው የመጠቀ፣ በትምህርቱ የተደነቀ” ሰው ነበሩ ብለው ይመሰክሩላቸዋል።

ኦሮሞች ብዙም ሳይቈዩ፣ እያንዳንዱ ነገዳቸው በየሰፈረበት ቦታ፣ የጥንት አረመኔአዊ ልማዱ[23]ን ትቶ፣ በቋንቋ፣ በባህልና በእምነት ከሰፊው የአካባቢው ሕዝብ ተዋህዶና ተመሳስሎ ይገኛል። በ፲፰ኛ ዘመነምሕረት መጨረሻ ደግሞ፣ ኦሮሞኛ ራሱ ከማንኛውም የዓለም ፊደል አስቀድሞ፣በአገር-በቀሉ በግእዝ ሆሄያት መጻፍ ጀመረ። በቀጣዩ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ደግሞ፣ ቅኔም በኦሮሞኛ ሲቀኝበት ይታያል[24]። የቋንቋውን ፍጹም ኢትዮጵያዊነት በፊታውራሪነት የመራው ግን፣ የፖለቲካው ዘርፍ ነበር። ይኸም በዘመነመሳፍንት ወቅት ስናይ ግልጽ ይሆንልናል።

ዘመነመሳፍንት ማለት ባጭሩ፣ ኢትዮጵያን ከዳር እስከዳር የሚያስተዳድር ማእከላዊ መንግሥት በጠፋበት ወቅት፣“ወሬሸኮች” በመባል የሚታወቁት፣ የየጁ ባላባቶች፣ ነገሥታቱን በዘፈቀደ እንደጉልቻ እንዳሰኛቸው እየቀያየሯቸው፣ ከሸዋ በስተሰሜን፣ ማለትም ከወሎ እስከባሕረ ኤርትራ ያሉትን ግዛቶች በበላይነት ቀጥቅጠው ይገዙ የነበሩበት ወቅት ነው። ታሪክ በስሕተት የጊዜውን አስተሳሰብ በመከተል፣ “የጋላ ግዛት ዘመን” ብሎ ቢጠራም፣ ሐቁ ግን የተለየ ነው። “ወሬሸኮች” አመጣጣቸው ከዐረብ ምድር ነው ይባላል። ስለዚህ የጁዎች ኦሮሞች አይደሉም[25]። ግን ከኦሮሞኛም ሆነ ከአማርኛ፣ እንዲህም ከሌላው ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ ጋር በአምቻና፣ በጋብቻ፣ በባህልና በእምነት እጅግ የተሳሰሩ በመሆናቸው፣ ሥርወ መንግሥታቸው በስብጥርነቱ እውነተኛ የኢትዮጵያዊነት መግለጫ ነው ማለት ይቻላል። ወሬሼኮች ሹመታቸው እንደራሴነት ነው። ግን በዘመነመሳፍንት፣ ለስም ብቻ ንጉሦችን እየሾሙና እየሻሩ፣ከውጭ አገር ጋር በሚያካሄዱት መንግሥታዊ ግንኙነቶችና፣ የጽሑፍ ልውውጦች፣አንዳንዴ ራሳቸውን የሐበሻ [ኢትዮጵያ] ንጉሥ”፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያ “ርእሰ መኳንንት[26]” እያሉ በማስታወቅ፣ የመንግሥትን ሥልጣን ጠቅልለው የያዙት እነሱ ነበሩ።

ዘመነመሳፍንት ራሱ፣ የሁለቱ አዲሶች ኀይሎች፣ ማለትም ባንድ በኩል በእቴጌ ምንትዋብ ሞግዚትነት የሚመራው የቋሮች፣ በሌላው በኩል ደግሞ፣ የኦሮሞ ባላባት ልጅ በነበረችው፣ በእቴጌይቷ ምራትና[27]፣ በደጋፊዎቿ መካከል ይካሄድ የነበረው የሥልጣን ሽኩቻ ውጤት ነበር ቢባል፣ ስሕተት አይመስለኝም። ሁናቴው በግልጥ የሚያሳየን ነገር ቢኖር፣ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት፣ ከበስተደቡብ ወደመኻል አገር ጉዞውን የጀመረው ዘላኑ የኦሮሞ ሕዝብ፣ በጋብቻ፣ በባህልና በኑሮ ከቀረው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተዋሕዶ፣ በከፍተኛ ደረጃ መንግሥትን የመምራት ሥልጣን ለመጨበጥ እንደቻለ ነው። ከዚያም በመቀጠል፣ በ፲፱ኛ ዘመን መኻል በቋራው አፄ ቴዎድሮስ ተጀምሮ፣ በአፄ ምኒልክና የቀኝ እጃቸው በነበሩት በራስ ጐበና በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ የመልሶ አንድነት ምሥረታና ግንባታ፣ እንዲሁም በተከታታዩ የዕድገቷና የልማቷ ሥራ፣ ከመሪነት እስከተራ አላፊነት ባለው ዘርፍ በመሰማራት፣ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ካበረከቱት ዋነኞቹ፣ የኦሮሞነት የአጥንት ዝምድና ያላቸው እንደሆኑ ታሪክ ይመሰክራል።

በኦሮሞ ሕዝብ ላይ በመጠኑ ሰፋ ያለ ገለጣ ለመስጠት የፈለግሁበት ዋናው ምክንያት፣ ፍልሰቱ በኢትዮጵያም ሆነ፣ በኅብረተሰቡ ራሱ ላይ ያመጣውን ሥርነቀል የሆነ ጥልቅና ሰፊ ለውጥ በአጭሩ ለማሳየትና፣በዚያው ልክ ደግሞ፣ የኦሮሞን ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት በመካድ፣ አንዳንድ የብሔረሰቡ ልሂቃንና ድርጅቶቻቸው የሚነዙት ታሪክ መሠረተ-ቢስ እንደሆነ ለማገናዘብ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ የውሕደት ሂደት፣ የሌላውንም የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ሁናቴ ያንጸባርቃል ማለት ይቻላል። ለከብቱ ግጦሽ ፍለጋ ሲል፣ ከበስተደቡብ ከባሌ አካባቢ የተነሣው ዘላን ሕዝብ፣ ግማሽ ዘመን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በየደረሰበት ሁሉ፣ የጥንት ኑሮውን ስልት ትቶ፣ መስፈርና በግብርና መተዳደር ጀመረ። በየሰፈረበትም አካባቢ፣ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በትውልድ መዛመድና መዋሐድ የግድ ሆነበት። በተለያየ የሥራና የሥልጣን ዘርፍ ተሰማርቶ፣ የአገርንና የመንግሥትን ህልውና በመጠበቅና፣ በማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ሊያደርግ በቃ። እንግዴህ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምን መሆኑን፣ ከእንደዚህ ዐይነቱ ታሪክ ለመማርና ለመረዳት አያዳግትም ብዬ አምናለሁ።

ከዚህ በታሪክ ጸሓፊዎች ግምት፣ ቢያንስ ከስድስት ሺዓመታት በላይ የቈየ፣ ይልቁንም የመንግሥትና የሕዝብ የመንሰራፋትና የመስፋፋት፣ የውርስና የቅርስ፣ የአምቻና የጋብቻ ታሪክ፣ እጅግ በጣም አድርገን በከፍተኛ ደረጃ መገንዘብ የሚገቡን ሁለት ጉዳዮች አሉ። እነኚህም፣ ስለኢትዮጵያም ሆነ፣ ስለኢትዮጵያዊነት በተናገርን ቊጥር፣ ተደጋግመው መጉላት፣ በጥብቅ መነገርና መሰመር ያለባቸው ነጥቦች ናቸው ብዬ አምናለሁ። ጉዳዩ፣ ሕዝብንም ሆነ መንግሥትን ይመለከታል። አንደኛው፣በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጸመው በመንግሥት የመንሰራፋትና የመጠናከር ሂደትና ተግባር፣ ከሌላው ተነጥሎ የተለየ ጥቅም ያገኘም ሆነ ሳያገኝ የቀረ፣ የተከፋም ሆነ የተጐዳ የኅብረተሰብ ክፍል የለም ብቻ ሳይሆን፣ ኑሮም አያውቅም። ትላንት ወራሪና አጥቂ የነበረው ኅብረተሰብ፣ ብዙም ሳይቈይ፣ ከጥንቱ ባለጋራው ጐን አብሮ በመሰለፍ፣ ከአዲሱ የውጭም የውስጥም ወራሪ ሲከላከል፣ የአገሪቷን ዳርና ድንበር ሲጠብቅና ሲያስጠብቅ፣ ግዛቷንም ሲያስፋፋ፣ ለራሱም ሆነ፣ ለወገኑና ለአገሩ ደኅንነት ሲል፣ በየጦር ሜዳው፣ በየጢሻው፣ በየበረሃውና በየዱሩ ሲወድቅና ሲዋደቅ፣ አጥንቱን ሲከሰክስ፣ ደሙን ሲያፈስ ይታያል። እንግዴህ ታሪክ ግልጥ አድርጎ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ማንኛውም ኅብረተሰብ በጊዜውና በተራው ጐጂም ተጐጂም ተጠቃሚም መሆኑን ነው።

ሁለተኛው ከፍተኛ ነጥብ፣ በኢትዮጵያ የተካሄደው የመንግሥት መንሰራፋትም ሆነ የሕዝብ ፍልሰት፣ የመጨረሻ ውጤታቸው የሚመሰገንና የሚደነቅ ቢሆንም፣ሂደታቸው የተፈጸመው ግን፣ አብዛኛውን ጊዜ በሰላማዊ መንገድ አለመሆኑን መገንዘብ ነው። አልፎ አልፎ በሰላማዊ መንገድ ቢከናወንም፣ ብዙውን ጊዜ የሚያመዛዝነው ግን፣ ጉልበትና ጥቃት እንደነበር የማይካድ ሐቅ ነው። ይኸም ማለት፣ አንዱ ኅብረተሰብ ከጥንት መኖርያው ተነሥቶ ወደሌላው አካባቢ ሄዶ ሲሰፍር፣ የአገሩ ነባር ሕዝብ፣ መጤውን ከበሮ እየደለቀለት፣ እምቢልታ እየነፋለት፣ ቀይ ምንጣፍ አንጥፎለት፣ ቄጠማ ጐዝጒዞለት፣ ጮቤ እየረገጠ፣ በሆሆታና በእልልታ፣ በሽለላና በዝለላ የተቀበለበት ወቅትና ሁናቴ በኢትዮጵያ ታሪክ መዝገብ ውስጥ ከቶውኑ የለም፤ኑሮም አያውቅም ብል ስሕተት አይመስለኝም። ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ መካከል፣ የፍልሰቱ ታሪክ በውጭም ሆነ ባገር ውስጥ ጸሓፊዎች በሰፊው የተነገረለት ሕዝብ ቢኖር፣ የኦሮሞኛ ቋንቋ ተናጋሪው ክፍል ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ይኸ ኅብረተሰብ ከደቡብ ወደመኻል አገር ፍልሰትና መንሰራፋት እንደጀመረ፣ በወቅቱ በአካባቢው የነበረው ጶርቱጋላዊ ጳጳስ፣ አቡነ ቤርሙዴዝ፣ በመጠኑ መዝግበውታል። በጽሑፋቸው፣ እሳቸው በነበሩበት ወቅት እንኳን፣ኦሮሞች ለከብቶቻቸው ግጦሽ ሲሉ የኢትዮጵያን ሦስት ሰፋፊ ግዛቶቿን ወርረው እቊጥጥሯቸው ሥር ለማድረግ እንደበቁ አቡኑ ይናገራሉ። እነዚህም፣ ስፋታቸው ካስትልንና ጶርቱጋልን የሚያካክሉ የባሌና የደዋሮ አገሮች፣ እንዲሁም ብቻውን ልክ እንደፈረንሳይ መሬት የሚሰፋ የሐዲያ ግዛት ናቸው። ይኸ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ጳጳሱ ሲገልጹልን እንዲህ ይላሉ።

ጋሎች መኖርያቸው በሞቃዲሾ አካባቢ ነው።አገራቸውን ሊያጠፉና አለነዋሪ ባዳ ምድር አድርገው ሊያስቀሩት ብቻ ሲሉ፣ ጐረቤቶቻቸውንም ሆነ ሌላውን ማንኛውንም አገር እየወረሩ የሚኖሩ ጨካኝና ኀይለኛ ሕዝብ ናቸው። አንዱን አገር [በኀይል] ሲይዙ፣ ወንዶቹን በሙሉ ያርዳሉ፤ የልጆቹን አባለዘራቸውን ይቈርጣሉ፤ አሮጊቶቹን ይገድላሉ፤ ልጅ እግሮቹን ደግሞ ለጥቅማቸው ስለሚፈልጓቸው እንዲያገለግሏቸው ሲሉ ይወስዷቸዋል[28]

 

ካርታ ፮

የአቡኑ ምስክርነት የተጻፈበት ወቅት፣ ከፍተኛ የትርምስምስና የብጥብጥ ጊዜ በመሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ ከግል ጥላቻ የጠራ አስተያየት ነው ብሎ ለመቀበል አስቸጋሪ መሆኑ አይጠረጠርም። ሁኖም፣ ከእሳቸው በኋላ ወደሠላሳ ያህል ዓመት ቈይተው የጻፉት፣ ዕውቁ የኦሮሞ ታሪክ ሊቅ አባ ባሕርይም ሆኑ፣ ሌሎችም በተከታታይ በተለያየ ወቅትና ምክንያት ታሪኩን ያጠኑት የውጭና የውስጥ አገር ተመራማሪዎች፣ የጳጳሱን ዘገባ እንዳለ አላንዳች ክርክር ይጋሩታል[29]

የኦሮሞ ብሔረሰብ እስከመሃሉ አገር ሊስፋፋ የበቃው፣ ከፊቱ ያለውን እየተዋጋና እያጠፋ፣ ኀይለኛውን ሕዝብ ደግሞ አልፎት እየሄደ፣ የገበረለትን ኅብረተሰብ ግን ጉዲፈቻ፣ሞጋሳ [ሞገሳ]፣ ገበር የተባሉ ሥርዐቶቹን በመጠቀም፣ በጦር ኀይል ከሥልጣኑ ሥር እያስገባና እያንበረከከ፣ባህሉንና ቋንቋውን ደፍጥጦ፣ ሰብእናውን ጨፍልቆ፣ በኦሮሞነት አጥምቆ፣ ሁለተኛ ደረጃ ዜግነት እየሰጠ መሆኑን ሁላቸውም ይስማሙበታል[30]

እዚህ ላይ መነሣት የሚገባ አንድ አንኳር ነጥብ አለ። ይኸውም፣ አንዳንድ የተዛባ የታሪክ ግንዛቤ ያላቸው፣ ይልቁንም የጠባብ ጐሣነትና የግራዘመም ርእዮተዓለም አቀንቃኞች፣ በአፄ ቴዎድሮስ ተወጥኖ በአፄ ምኒልክ የተደመደመውን የኢትዮጵያን የአንድነት መልሶ ግንባታና ተግባሩን የፈጸሙትንም ሆነ፣ የነሱም ፍሬና ውጤት የሆኑትን፣ “የምኒልክ ሰፋሪዎች” በማለት እስከመወንጀል ደርሰዋል። ከዚህም የተነሣ፣ ቢያንስ ከሰባተኛ ዘመነምሕረት ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግሥትና የሕዝቧ መገናኛና መግባቢያ ቋንቋ የሆነውን አማርኛ የሚናገረውን ሕዝብና ግለሰብ፣ ከያሉበት በግፍ፣ ከወንዛቸውና ከሕዝባቸው እየነጠሉና እያፈናቀሉ በማስወጣት፣ ከፍተኛ ኢሰብአዊ ግፍ እየፈጸሙ እንዳሉ ማየት ዛሬ የተለመደ ሁኗል። መገንዘብ ያቃታቸው ግን፣ “የምኒልክ ሰፋሪዎች” ከ”ጋዳ ሰፋሪዎች”፣ ከ”አዳልና ከሱማሌ ሰፋሪዎች”፣ ከ”አገውና ከትግሬ ሰፋሪዎች” የማይለዩ አለመሆናቸውን ነው። ሁሉም በየጊዜውና በየምክንያቱ ተነሥቶ፣ አጋጣሚውን ተጠቅሞ፣ በኢትዮጵያ የአንድነትም ሆነ የጥቃት ወረራ ተሳትፏል። ሁሉም ከሌላ አካባቢ የመጣ ሰፋሪ ነው።

አማርኛ ከ”ምኒልክ ሰፋሪዎች” ጋር የሚዛመደው፣ ለዘመናት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቋንቋ ሁኖ በመገኘቱና፣ ከተለያዩ አካባቢና ቋንቋ ተናጋሪ ኅብረተሰብ የተወጣጡ፣የኢትዮጵያን የአንድነት መልሶ ግንባታ በተግባር ያዋሉት ጀግኖች አባቶችና ሠራዊታቸው፣ እየተኰላተፉም ቢሆን ስለተናገሩት ብቻ ነው። ጥንት ባንድ ወቅት፣ አምሐራ ወይንም አማራ ከተባለ አካባቢ ጋር ግንኙነት ኑሮት ይሆናል። ቢኖረው፣ ያ አዝማናት ያስቈጠረ ታሪክ ነው። ዛሬ ዋጋ የለውም፤ ምንጩን ማወቁ ግን ጥሩ ነው። ያኰራልና። ዛሬ ግን አማርኛ፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት መሠረታዊ መግለጫና መለዮ ነው። የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች መግባቢያ፣ መገናኛና ጥብቅ መተሳሰርያ ሰንሰለት ነው። ኢትዮጵያውያን፣ በ፲፮ኛ ዘመነምሕረት ቱርኮችን፣ በ፲፱ኛ ዘመነምሕረት ኢጣሊያኖችን ድል ያደረጓቸው፣ አማርኛ በመኖሩ መሆን መረሳት የለበትም። አለበለዚያ፣ ጥረታቸውና ትግላቸው እንደባቢሎን ግንብ ገንቢዎች ባክኖ በቀረ። ያ ቢሆንማ፣ ኢትዮጵያም ኩሩ የነፃነት ታሪኳን፣ ኢትዮጵያውያንም የሥነልቦና ጥንካሬንና አልበገርነትን ከትውልድ ወደትውልድ ለማስተላለፍ ባልታደሉም ነበር። ኢጣሊያንኛ የኢጣሊያኖች፣ እንግሊዝኛ የእንግሊዞች ቋንቋዎች እንደሆኑ ሁሉ፣ አማርኛም የኢትዮጵያውያን ነው። አውሮጳውያን ሴማዊ ቢሉትም፣ ሰባ ከመቶ ያላነሰ ኩሻዊነት አለው። ስለዚህ የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች በሙሉ ለማንኛዉም ሳያዳላ የሚወክል፣ ከማንኛውም ጋር የማይተሳሰር፣ ሲናገሩት ጉሮሮ የማይከረክር፣ ምላስ የማይዶለዱም፣ ገለልተኛ፣ ግልጽና ጥርት ያለ ቋንቋ ነው። ለዕድገቱም አብዛኛው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ አያጠራጥርም። በውስጥም በውጭም ግንኙነት፣መሪዎቹ የተጠቀሙት፣ የአካባቢያቸውን ቋንቋ ሳይሆን፣ አማርኛን ነው። አፄ ዮሐንስ የትግራይ ተወላጅ ናቸው። ግን ሥራቸውን ያካሄዱት በሚቀላቸው ትግርኛ ሳይሆን፣ በአማርኛ ነው። በምዕራብ ኢትዮጵያ በ፲፱ኛ ዘመነ ምሕረት ማቈጥቈጥ የጀመሩት የኦሮሞ ባላባቶች ግዛቶች፣ መሪዎችም ሆኑ፣ በእንግሊዝ ቈስቋሽነት የምዕራብ ኢትዮጵያ የጋላ ባለቃልኪዳን መንግሥታትን ለማቋቋም የቃጡት፣ እንደነደጃዝማች ሀብተማርያም የመሳሰሉት፣ ከእንግሊዝም ከኢጣልያንም የመንግሥት ባለሟሎች የተጻጻፉት በኦሮሞኛ ሳይሆን፣ በአማርኛ ነው። ወደበስተኋላ ገፋ ካልን ደግሞ፣ የዘመነ-መሳፍንት የኦሮሞ ገዢዎችም እንዲሁ። ግራኝ ራሱ አማርኛ ተናጋሪ እንደሆነ፣ የወረራው ታሪክ ጸሓፊው ይገልጥልናል።

አማርኛን ከ”ምኒልክ ሰፋሪዎች” ጋር ብቻ ማዛመድ፣ ከታሪክ ጥራዘነጠቅነትና ከጥላቻ ውጭ፣ ሌላ ምክንያት አይኖርም። የ”ምኒልክ ሰፋሪዎች” ተብዬዎቹ፣ አማርኛ ይናገሩ እንጂ፣ ከመጡበት ብሔረሰብና አካባቢ አኳያ ካየናቸው፣ ደምበኛ ምርምር ተደርጎ ባያረጋግጥም፣ ተጨባጭ ሁናቴው የሚያስረዳን ወደሰማንያ ከመቶው በላይ የኦሮሞ፣ የጉራጌ፣ የትግሬ፣ እንዲሁም የቤኒሻንጉል ኅብረተሰብ አካል ናቸው። በአንድ ቃል፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በጉልህ የሚያንጸባርቁ፣ የተለያዩ ብሔረሰቦች ስብጥር ናቸው ልበልና ወዳቋረጥኹት ወደዋናው ነጥቤ፣ ማለትም ወደመንግሥት መንሰራፋት ልመለስ።

የማእከላዊ መንግሥት መንሰራፋት ጠባይ፣ ከሕዝቡ የፍልሰት ባሕርይ የተለየ አይደለም ማለት ይቻላል። ሁኖም፣ የመንግሥት መንሰራፋት በነፃና ራስገዝ ብሔረሰቦችም ሆኑ፣ አካባቢዎች መካከል የሚከሠቱትን አለመግባባቶችንና ግጭቶችን አስወግዶ፣አንድነትና ስምምነት በማምጣቱ እጅግ የተቀደሰና የሚደነቅ ድርጊት መሆኑ አይካድም። እነዚህ ጉልበታቸውን በርስበርስ ጥቃት በከንቱ ከማባከን፣ ሰላምና ዕርቅ በሰፈነበት ምድር፣ ለራሳቸው ብልፅግናና ዕድገት ሲሉ፣ እናት ለሆነችው አገራቸው ልማት፣ ተባብረውና ተስማምተው እንዲሠሩ፣ መንግሥት ሁላቸውን እንዳንድ አገር ባንድ የግዛት ሥልጣን ጥላ ሥር ቢያመጣም፣ የመንሰራፋቱ ሥራ ግን ራሱን የቻለ አስከፊ ገጽታ እንዳለው መረሳት የለበትም። አንድ አገር ሲመሠረት፣ መንገዱ አልጋ በአልጋ ሳይሆን፣ብዙ ደም የተፋሰሰበት፣ ሕዝብ የወደመበት፣ አካባቢ የተደመሰሰበት ነው። ታሪክን በምስክርነት ከወሰድን፣ በፈቃደኝነትና በውውይት፣ በምክክርና በመግባባት የተመሠረተ መንግሥት፣ ከቶውኑ በዓለማችን ላይ ኑሮ አያውቅም። ሌሎቹን ትተን፣ እስኪ ዛሬ በምግብናዋና በዘመናዊነቷ፣ ከኀያላኖቹ የምዕራብ መንግሥታት አካል አንዷ የሆነችውን፣ ጀርመንን እንመልከት።

ጀርመን፣ ከዐምስት መቶ በላይ ልዑላንና ራስ-ገዝ የነበሩትን፣ ልዩልዩ መንግሥታትን አንድ ጋ በማምጣት፣ እንደአንድ አገር ሁና ከተፈጠረች፣ ወደሁለት መቶ ዐምሳ ዓመታት ልታስቈጥር ቀርባለች። እነዚህ መንግሥታት መሬታቸው ኩታገጠም ከመሆን አልፎ፣ በዘር፣ በባህልና በቋንቋ ያላቸው ልዩነት እምብዛም አልነበረም። ይሁንና በሰላማዊ መንገድ ሁላቸውንም ወደአንድነት ማምጣቱ ለዘመናት ቢሞከርም፣ ጥረቱ ፋይዳቢስ ሁኖ ነው የቀረው። ከአንድነቱ ይበልጥ ይቀናቸው የነበረው፣ ርስበርስ በጦርነት እየተፋተጉና እየተጨፈላለቁ መኖሩ ነበር። በሰላምና በውድ ወደአንድነት ማምጣት ርባና-ቢስ መሆኑን ተረድቶ፣ “በብረትና በደም” ኀይል አንድ ያደረጋቸው፣ አምባገነኑ የፕሩሲያው መሪ ኦቶ ቮን ቢስማርክ ሲሆን፣ እሱም፣ “አንድ አገር እንዴት እንደተመሠረተ፣ ሶሰጅ እንዴት እንደተሠራ መጠየቅ አይገባም፤” የሚል አንድ ድንቅ አባባል ትቶልናል[31]

ኢትዮጵያ፣ ከሦስት ሺ ዓመት በላይ የሚገመት አኩሪ የአንድነትና የመንግሥትነት ታሪክ እንዳላት፣ ምንም የማያከራክር ሐቅ መሆኑን ዐይተናል። በዚህ የረጅም ታሪክ ጒዞ ውስጥ፣ አንድነቷ ከጊዜ ወደጊዜ ፈርሶ የቈዳዋ ይዘት የጠበበበትና የሰፋበት ወቅትም እንደተፈራረቀባት አንሥተናል። በዘመነመሳፍንት የተገረሰሰው አንድነት፣ በዘመናዊ መልኩ ከአንድ መቶ ዓመት በኋላ ተመልሶ ሊገነባ የበቃው፣ በጦርነትም፣ በድርድርም ላይ ተንተርሶ ነበር። ይሁንና ከሌሎች አገሮች ሁናቴ ጋር ሲታይ፣ የኢትዮጵያ የዘመናዊ አንድነት ግንባታ፣ በከፍተኛ ብልህነትና አርቆ-አሳቢነት የተካሄደ ተግባር ብቻ ሳይሆን፣አብነታዊና አድናቆትንም የሚያተርፍ ነው ብል ስሕተት አይመስለኝም። ለምሳሌ ያህል፣ እንደአሜሪቃ በዘርና በቀለም በመበካከል፣ በመደብና በጾታ በመለያየት፣ በዕውቀትና በሀብት በመመሠረት፣ ልዩነትንና አድልዎን ያማከለ፣ ኅብረተሰቡን አንዱን ለማዕርግ፣ ሌላውን ለባርነት፣ ከዚያም ለሎሌነት በይፋ በሕግ የደነገገ አይደለም። ወይንም እንደአብዛኞቹ አገሮች፣ በብሔረሰብነትና በቋንቋ በማመኻኘት፣ ያንዱ ኅብረተሰብም ሆነ ግለሰብ፣ ዕድሉ የተቀጨበት፣ አንዱ ሌላውን የጨቈነበት፣ ደም የተቀባባበት ሁናቴ አልታየም። እንዲሁም፣ በእምነቱ፣ በዘሩ፣ ወይንም በቀለሙ ልዩነት ምክንያት፣ አንዱ ወገን ጌታ፣ ሌላው ባርያ ሁኖ የኖረበት ወቅት አልነበረም። እንደጀርመኖች፣ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አልተካሄደም። እንዲሁም ባህልንና ቋንቋን ስለማይጋራ፣ በቀለም ስለማይመሳሰል፣ በሀብትና በጉልበት ስለማይመጣጠን፣ በጾታና በትውልድ ስለሚለያይ ብቻ ተነጥሎ፣ ለሌላው የተሰጠውን ዕድል የተነፈገ የኅብረተሰብ ክፍል የለም። በአስተዳደር ደረጃ፣ አንዳንድ ጉድለቶች መኖራቸው አይካድም። ግን የኢሕአዴግ አገዛዝ የመንግሥትን ሥልጣን እስከተቈጣጠረበት ወቅት ድረስ፣ ልዩ ዘውግ ወይንም የዘውግ አባል በመሆኑ፣ ወይንም ዘውጉ ከሰፈረበት አካባቢ በመምጣቱ፣ አለበለዚያም ቋንቋውን በመናገሩ፣ ወይንም በጋብቻ ሆነ በሌላ መልክ በመተሳሰሩ ብቻ፣ በይፋም ሆነ በኅቡዕ የተሸለመ፣ ወይንም የተንቋሸሸ፣ የተጨቈነ፣ዜግነቱን ያጣ፣ የሌላው አገልጋይ እንዲሆን ማዕቀብ የተጣለበት፣ በሕግ በልማድም ከሥልጣንም ከዕድገትም የታገደ፣ ግለሰብም ሆነ ብሔረሰብ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አልታየም። ይልቅስ በኢትዮጵያ ታሪክ ማአከላዊ መንግሥት ሲስፋፋ፣ በተደጋጋሚ ጉልህ ሁኖ የሚታይ ነገር ቢኖር፣ የተሸነፈውን ክፍል ወይንም ኅበረተሰብ ለመግዛት፣ ወይንም ለመጨቈን ሳይሆን፣ ሕዝብን ርስበርሱ ለማቀራረብና ለማዋሀድ፣ ከባዕድ ወራሪም በትብብር ለመከላከል ነው ቢባል ይመረጣል[32]። ታሪክ ሲመረመር፣ የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግሥት የአስተዳደር መፈክር በአራት መሠረታዊና አንኳር በሆኑ ነጥቦች ሊጠቃለል ይችላል። አንደኛ፣ወደፈለግህበት ሂደህ፣ በሰላም ኑር። ሁለተኛ፣ ግብር ገብር። ሦስተኛ፣ ነጋዴዬንና ገበሬዬን (የአገር ሀብት ምንጭ እንደመሆናቸው)፣መንገደኛዬንም አትንካብኝ። በመጨረሻ፣ በአካባቢህ ሰላም አትንሣ። መንግሥት ጦርነት የሚያውጀው፣ አካባቢውንም ሆነ ግለሰቡን የሚቀጣው፣ ከእነዚህ መሠረታዊ የዜግነት ግዴታዎች፣ አንዱም ቢሆን ቢፈርስና ሳይሟላ ሲቀር ነው።

የኢትዮጵያን የአንድነት ግንባታ ከሌሎች አገሮችና መንግሥታት የሚለያት ሌላም አስገራሚ ገጽታ አለው። የኢሕአዴግ መሪዎች፣ ክሺዘጠኝመቶስድሳዎቹና ሰባዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ለጥቅማቸው ሲሉ ተበድረው በሚያነበንቡት አርቲቡርቲ ካልተሸነገልን በስተቀር፣ ደጋግሜ እንዳነሣሁት፣ የኢትዮጵያ ሥልጣኔና መንግሥትም ሆነ የአገሪቷ የአንድነት ግንባታ፣ካንድ ከተለየ ብሔረሰብ ወይንም አካባቢ ጋር የተያያዘበትና ተቈራኝቶ የታየበት ጊዜ አልነበረም። ሁኖም አያውቅም። በመጀመርያ ደረጃ፣ በዘመነ-መሳፍንት ፈርሶ የነበረው የሕዝቡና ያገሩ አንድነት ተመልሶ በዘመናዊ መልኩ የተቋቋመው፣ ባንዴ ሳይሆን በሂደት ነው። እንደአንድ አገር የተቋቋመውም፣ ካንድ ከተወሰነ አካባቢ ወይንም ጐሣ በመነጨ ጦርና መሪ ሳይሆን፣ በተለያየ ወቅትና ምክንያት ከየአካባቢው በተወጣጣና በተቀናጀ፣ በመሪነትም ሆነ በሠራዊት ደረጃ፣ ልዩልዩ ብሔርንና ብሔረሰቦችን ባቀፈ ኀይል ነው። ቀለል እንዲልልን እስኪ ዐጠር ባለ መልኩ ወደዝርዝሩ እንግባና እንየው።

ዘመነመሳፍንትን አክትመው ሲያበቁ፣ ያንድነቷን መሠረት የጣሉላት አፄ ቴዎድሮስ የቋራ ተወላጅ ናቸው። የንጉሠነገሥትነት በትር እንደጨበጡ፣ በሰሜን በኩል በተከታታይ ብቅ ባሉት በውጭ አገር ወራሪዎች ጥርስ እንዳትገባ እየተዋጉ፣በመጨረሻም በጦር ሜዳ ላይ ሕይወታቸውን የሠውት አፄ ዮሐንስ የትግራይ ተወላጅ ነበሩ። ከአውሮጳውያን መንጋጋ አድነውት፣ደቡቡን ያቀኑት አፄ ምኒልክ ከሸዋ ሲሆኑ፣ የምዕራቡን ክፍልና ግንባር ያደላደሉት ንጉሥ ተከለሃይማኖት ግን ከጐጃም ናቸው። እያንዳንዱ ንጉሥ በጐኑ፣በጀግንነታቸው እጅግ የታወቁና የተፈሩ፣በጦር ዕቅዳቸው የሚደነቁ፣ቈራጥና ስመጥሩ፣ በሰሜን እንደራስአሉላ አባ ነጋ፣በምዕራብ እንደራስ ደረሶ አባ ጠቦ፣ በመኻል አገር የሸዋው ራስ ጐበና አባ ጥጉ የመሳሰሉ የጦር አበጋዞች ነበሯቸው። ሌላውን የዘር ሐረጋቸውን እግምት ሳናስገባ፣በአባታቸውና በአካባቢያቸው ብቻ ተመሥርተን፣ በትውልዳቸውና አፋቸውን በከፈቱበት ቋንቋ ከሄድን ደግሞ፣ ራስ ጐበና የኦሮሞ፣ ራስ ደረሶ የአገው፣ ራስ አሊ የትግሬ ብሔረሰብ ናቸው ይባላል[33]። እንግዴህ፣ በዚህ መልክ የተቋቋመችውን አገርና ሕዝብ፣ መሪዎቹ ያስተዳድሩ የነበሩት፣ ለማንም ሳያዳሉ፣ ገንዘባቸውና ዐቅማቸው በፈቀዱት መጠን፣ ሁሉንም በእኩልነት ስለነበር፣ አንዱ ዘውግ በተለየ መልክ ተሽሞንሙኖ እንዲኳፈስ፣ ሌላው ተቀፍፎ እንዲኳሰስ፣ የተደረገበት ወቅት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አልነበረም፤ አልታየምም።

እነዚህ የጦር መሪዎችም ሆኑ፣ ነገሥታቱ ለታላቅ ክብርና ማዕርግ የበቁት ደግሞ፣ በኢትዮጵያ በመወለዳቸውና የኢትዮጵያዊነትን ካባ በመልበሳቸው ነው ማለት ይቻላል። ከላይ እንዳየነው፣ የኢትዮጵያዊነት ታላቁ ዕሴትና ምሥጢር፣ ከማንም ተወለድ፣ ከየትም አካባቢ ና፣ ዕጣፋንታህ ከሆነ፣ ችሎታና ብቃት ካለህ፣ ታማኝነት ካሳየህ፣ ለማንኛውም ወግና ማዕርግ ዕጩና ብቁ ነህ የሚል መሠረታዊና የማይካድ እምነት በያንዳንዱ ልብ ለዘመናት ተቀርጾ መኖሩ ነው። በተለያየ ጊዜ ኢትዮጵያን የጐበኙትን ምዕራባውያን በጣም ካስደነቋቸው ነገሮች ዋነኛው፣ የተለያየ አካለጉድለት ያላቸው (ለምሳሌ ያህል ዐይነስውሮች) እንኳን ሳይቀሩ፣ ከፍተኛ ትምህርት ተምረው፣ ለታላቅ ክብርና ማዕርግ በቅተው፣ አላንዳች ማዳላት፣ ከሌላው እኩል ሁነው ማየታቸው ነበር። ይኸ፣ በዚያ ወቅት በምዕራባውያን ዘንድ የማይታሰብ እንደነበር፣ ብዙዎቻችን እናውቃለን። በ፲፱ኛ ዘመነምሕረት ላይ፣ የአፄ ቴዎድሮስ ታማኝ አማካሪ የነበረውን እንግሊዛዊውን ፕላውዴን እጅግ ያስገረመው ነገር ቢኖር፣ በኢትዮጵያ ምድር ሌላው ይቅርና፣ የሚለብሰው ቡትቶ እንኳን በሌለው፣ ባንድ ጭንጩ ድኻ ሥነልቦና፣ ስለገዛራሱ ያለው ጠንካራ አስተያየት ነበር። ፕላውዴን በጽሑፉ፣ የዕድልና ያለመታደል ጉዳይ ሁኖ አንዱ ከሌላው ለጊዜው እኩል ባይሆንም እንኳን፣ በኢትዮጵያ ማንኛውም ሰው በመሠረቱ ያው [እኩል] ነው።እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ራሱን ለታላቅ ዓላማ የተወለደ እንደሆነ አድርጎ ያምናል፤ በፍጹም የማትረባ ፍንጣሪም እንኳን ቢትሆን ይኸንን ምኞቱን ታቀጣጥለዋለች።” ይላል።

በፕላውዴን ትውልድ አገርም ሆነ፣ በቀረው የምዕራብ ዓለም፣ እንደዚህ ዐይነት አመለካከት በሕዝቡ ሥነልቦና ለመቅረጽና፣ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ከፍተኛ ደም ያፋሰሰ ሥርነቀል የሥርዐት ለውጥ ማካሄድ ግድ ሆኖባቸዋል። ኋላ የፈረንሳይ መንግሥት ከፍተኛ መሪ ሁኖ፣ ለታላቅነት የበቃውና፣ መላ አውሮጳን ያንቀጠቀጠው ናፖሊዎን ቦናፓርቴ ዐይነት፣ የፈረንሳይ አብዮት ባይኖር ኖሮ፣ የአንድ አገር መሪ መሆን ቀርቶ፣ ለተራ መኰንንነትም እንኳን ለመታጨት ዕድሉ የመነመነ ነበር። ለምን እንዳልሁ ባጭሩ ላብራራ። ብዙዎቻችን እንደምናውቀው፣ ከፈረንሳይ አብዮት በፊት፣ አብዛኛው የምዕራባውያን ኅብረተሰብ “ቤተክህነት፣ ቤተመሳፍንትና ቤተአልባሌ[34][35]” በተባሉ፣ የየቅላቸው ሰብእናና አገልግሎት ባላቸው፣ በሦስት ማኅበራዊ ዕርከን የተደረደሩ ነበር። በየመንግሥታቱ፣ የበላዮቹ ሁለቱ የየአገራቸው ባላቤቶች ሲሆኑ፣ በ“ቤተአልባሌ” ስም የሚጠራው፣ የሦስተኛው ዕርከን መደብ ግን፣ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ተሰማርቶ፣ ዐሥራት፣ ግብርና ቀረጥ በመክፈል፣ ሁለቶቹን ማገልገል ካልሆነ በስተቀር፣ ሌላ ፋይዳ አልነበረውም። የበላዮቹ ሁለቱ፣ የአገሩ ጠቅላላ ሕዝብ ዐሥር ከመቶ እንኳን የማይሞሉ ቢሆኑም፣ ሥልጣኑንና ማዕርጉን፣ ሹመትንና ዕድገትን፣ አጠቃልለው በእጃቸው ስላደረጉት፣ የቤተአልባሌ ክፍል አባል ምንም ቢተጋና ቢጥር፣ ቢቋምጥና ቢለማመጥ፤ ቢማለድና ቢገዳገድ፣ ከመደቡ ወጥቶ ለወግና ለማዕርግ የመብቃት ዕድሉ የተቀጨ ነበር። የፈረንሳይ አብዮት ሥርዐቱን አፍርሶ ባመጣው፣ አዲሱ ሥርነቀል ለውጥ፣ሹመትንና ዕድገትን ችሎታና ብቃት ላለው ሁሉ ክፍት በማድረጉ፣ ናፖልዎን ከመጀመርያዎቹ ተጠቃሚዎች አንዱ በመሆን፣ ከተራ ወታደርነት ተነሥቶ በሠላሳ ዓመት ያህል ዕድሜው፣ ንጉሠነገሥት በመሆን፣ የአገሩን ከፍተኛ ሥልጣን ለመያዝና፣ አብዛኛውን አውሮጳ ለመግዛት በቅቷል። ድልአድራጊው ሠራዊቱም፣ እግሩ በየረገጠበት የአውሮጳ ምድር፣ አሮጌውን ሥርዐት ገርሰሶ በአዲሱ እየተካ ሄዷል።

በምዕራባውያን ማኅበረሰብ አኳያ፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉም ነገር ተሟልቶና ተስተካክሎ ባይሰጣቸውም፣ በአውሮጳም ሆነ በሌላው ዓለም ሰፍኖ የነበረውን ግፈኛ ሥርዐት ቀምሰው አያውቁም። እያንዳድንዱ ኢትዮጵያዊ፣ ውቃቤው ካልራቀው፣ ችሎታው ካለው የማይመጣጠንለት ማዕርግ፣ የማይታጭበት የሙያ ዘርፍ የለም ብሎ የሚያምን ነው ብል ከእውነት የራቀ አባባል አይደለም። ወጉ፣ አካባቢውና አስተዳደጉ “ሁሉም ይቻላል፤ ግን ያለፋል” የሚል አመለካከት፣ በአብዛኛው ዘንድ እንደማያፋልም የማንነት መግለጫው አድርጎ፣ በአእምሮው ቀርፀውለታል። የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ አወቃቀር፣ እንደአውሮጳ ዐይነት ቢሆን ኖሮ፣ ሁለቱ የቋራውና የተምቤኑ ካሣዎች፣ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ዮሐንስ ለመባል፣ እንዲሁም በአድዋ ጦርነትና በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ከፍተኛ ታሪክ የሠሩት፣ እንደፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስና ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ የመሳሰሉት፣ ዝና ለማትረፍም ሆነ፣ለፊታውራርነትና ለደጃዝማችነት ማዕርግ ዕድል ባላጋጠማቸው ነበር።

የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ብዙዎች ናቸው። ለመዘርዘር ሰፊ ጊዜና ከፍተኛ ትዕግሥት ይጠይቃሉ። እኔ ግን አንዱን ባጭሩ ላነሣ ፍላጎቴ ነው። እሱም ሕግ አክባርነትንና በሕግ ፊት ሁሉም እኩል ሁኖ መታየት እንዳለበት ነው። ግሪካዊው ሄሮዶቱስም ሆነ፣ነቢዩ መሐመድ፣ ከነሱም በኋላ የመጡት ያገር ጐብኚዎች፣የኢትዮጵያን ሕዝብ ለግፍ ስላለው ጥላቻው፣ ስለፍትሕ አፍቃሪነቱ እንደሚወድሱ፣ በተለይም ነቢዩ የኢትዮጵያ ገዢ መደብ “ምንም ዐይነት በደል የማይታገሥ፣ ሕዝቡን በፍትሕና በቅንነት የሚገዛ፣ብሎ እንደገለጠ ቀደም ብለን አይተናል። ንጹሕ በግፍ እንዳይቀጣ፣ ግፈኛው ዋጋውን ሳያገኝ ከፍትሕ እንዳያመልጥ፣በደለኛውን አበጥሮ ለመወሰን በየኅብረተሰቡ ፍቱን ተብለው የሚታመኑ እንደሙግት በተጠየቅ፣ አፈርሳታ፣ ሌባሻይ የመሳሰሉ ባህላዊ ዘዴዎችና ተቋሞች አሉ። በመንግሥትም ደረጃ፣ ከክርስቲያኑ ፍትሐነገሥት ውጭ፣ ከከፍተኛው የዙፋን ችሎት፣ እስከዝቅተኛው የአፈር ወይንም የሥር ዳኝነት ተዘርግቷል።

እነዚህ ባህላዊ ተቋሞች፣ ኢትዮጵያውያን ስለሕግ እጅግ የዳበረ ግንዛቤ እንዳላቸው ያሳያሉ ብዬ አምናለሁ። ግፍንም በብዙ ዘዴና ጐራ፣ የትም ቦታ ቢሆን፣ ወደኋላ ሳይሉና ሳያመነቱ፣ በቊርጠኝነት የሚዋጉ መሆናቸውን፣ አንዳንድ ታሪካዊ ድርጊቶችን ማገናዘብ ይጠቅማል። በአክሱማውያን ዘመን፣ አፄ ካሌብ በየመን አገር፣ ክርስቲያኖች በሃይማኖታቸው ምክንያት በአይሁዳዊ ገዢ ቢሰደዱ፣ ጦራቸውን አደራጅተው በመሄድ፣ ከእምነት ልዩነት የተነሣ ማንም በየትም መሰደድ እንደማይገባው በተግባር አስተምረዋል። አሳዳጁንም ያገሩን ገዢ ወግተው ከሥልጣኑ አባርረውታል። በቅርቡ በፈረንጆች አቈጣጠር በ፲፰፻፰ ዓ.ም. ላይ፣ የኢትዮጵያ መርከበኞች ወደኒውዮርክ ከተማ መጥተው ሊጸልዩ ሲሉ፣ ወደቤተክርስቲያን ጐራ ባሉ ጊዜ፣ በጥቍሮቹ ለተመደበው መደዳ እንጂ፣ ከነጮቹ ጋር ተቀላቅላችሁ መቀመጥ አትችሉም ቢባሉ፣ በእግዚአብሔር ቤተጸሎት ምንም ዐይነት ልዩነት አይገባም ብለው ጥለው በመውጣት፣ሌሎችን ጥቁሮች በማስተባበር አንድጋ ሁነው፣ የመጀመርያዋን “የኢትዮጵያ ምጥማቅ ቤተክርስቲያን[36]” የሚትባለውን በከተማዋ ቈረቈሩ። ይህች፣ በኢትዮጵያ መርከበኞች የተቈረቈረችው ቤተክርስቲያን፣ በአሜሪቃ ለጥቍር ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት በተካሄደው የትግል ታሪክ፣ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተች በግልጽ ይነገራል።

የአፄ ካሌብም ሆነ የመርከበኞቹ ሥራ የሚያስረዳን፣ ኢትዮጵያውያን ግፍ በማየት የሚከፉ ብቻ ሳይሆን፣ በሰው ዘር እኩልነትና መብት ላይ እንደማይደራደሩ ነው። አስተሳሰባቸው ከአውሮጳውያኑ ምን ያህል እንደላቀና፣ ወደፊት የገፋ መሆኑንም ያመለክታል ብል ስሕተት አይመስለኝም። በጽሑፍም ደረጃ ብንመለከተው፣ ይበልጥ ይኸንን አጥብቀን እንረዳለን። በአውሮጳ ታሪክ፣ የዛሬው ዘመናዊ አስተሳሰብና ሥልጣኔ ፈርቀዳጆች፣ በ፲፯ኛና በ፲፰ኛ ዘመነምሕረት ላይ ብቅ ያለው፣ አብርሆ[37] በመባል የሚታወቀው እንቅስቃሴ መሪዎች ናቸው ይባላል። ከመካከላቸው በተለይ ሁለት ፈላስፎች፣ እንግሊዛዊው ጆን ሎክና ፈረንሳዊው ቮልቴር፣ በታላቅነታቸው ይደነቃሉ። ሁለቱም ግን፣ በሰው ልጅ እኩልነት የማያምኑ፣ የሴቶችን ልባምነት የሚክዱ ሲሆኑ፣ ለማትረፍም ሲሉ ገንዘባቸውን በሰፊው ያዋሉት፣ ጥቊሩን ሕዝብ በባርነት በመነገድ ነበር። ከነሱ ወደመቶ ዓመት አስቀድመው በኢትዮጵያ ምድር የታዩት፣ ዘርዐያዕቆብና ወልደሕይወት የተባሉ ሁለት ፈላስፎች ግን፣ ስለሴቶችም ሆነ፣ ስለቀረው የሰው ልጅ እኩልነት፣ ስለጋብቻ ክቡርነት፣ ስለሃይማኖት ትርጒም፣ ከዚያም አልፎ ጥቅምና ጉዳት ብቻ ሳይሆን፣ ባርነት ራሱ ያለመታደልና ያጋጣሚ ጉዳይ ሁኖ እንጂ፣ ባሮቹ ከሌላው የሰው ልጅ እኩል መሆናቸውን አትተዋል። ጽሑፋቸው፣አውሮጳውያን የሚመኩባቸውንና፣ የዘመናዊ ሥልጣኔ ፈርቀዳጆች የሚሏቸውን ከላይ የጠቀስናቸውን ፈላስፎች እጅግ በጣም ያስንቃሉ። የአውሮጳውያን አስተሳሰብ፣ በተራማጅነቱ ከነዚህ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ርእዮተዓለም ጋር ሊመጣጠን የበቃው፣ በጣም ቅርብ ጊዜ ነው ለማለት ያስደፍራል። በኔ እይታ፣ የነዘርዐያዕቆብን አስተሳሰብ ልዩ የሚያደርገው በጽሑፍ መስፈሩ እንጂ፣ እንደ አዲስ ግኝት ሁኖ መታየት ያለበት ነው ብዬ አላምንም። አቋማቸው የሚያንጸባርቀው ከመላጐደል፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ይጋራ የነበረውና፣በኅብረተሰቡ መካከል በሰፊው ይንሸራሸር የነበረውን የቈየና ሥር-የሰደደ አሳብ ነው።

ኢትዮጵያዊነት በሕግ የበላይነት ማመንን ይጠይቃል። ይኸንንም የሚያመለክቱ የተለያዩ ማስረጃዎች አሉ። በየጊዜው ከተራው እስከመኰንኑ፣ ከባለዳባው እስከባለካባው “በሕግ አምላክ፣” “በእግዜር፣” “በጃንሆይ[አምላክ]፣” የሚለው አገላለጽ፣ከዚህ መሠረታዊ እምነት የመነጨ ነው። ንጉሥም ቢሆን፣ የእግዚአብሔር ምድራዊ ምስለኔ ማለትም እንደራሴ እንደመሆኑ መጠን፣ የሕግን የበላይነትና ያገርን ወግ መጠበቅና ማክበር እንዳለበት በሕዝቡ ዘንድ ይጠበቅበታል። እንዲሁም፣ ከሥሩ ያሉት ባለሥልጣኖች ጭምር። እውነቱ እንደዚህ ሁኖ እያለ፣ ከዘውዳዊ መንግሥት መገርሰስ ጀምሮ፣ ስለገዢው ክፍል፣ ይልቁንም ስለነገሥታቱ አምባገነንትና፣ ራሳቸውን ከሕግ በላይ አድርገው ያዩ ነበር በማለት፣ ብዙ ወቀሳ ይሰነዘራል። ክሱ የመነጨው ከስድሳዎቹ የፀረ-ዘውድ ሥርዐት አዝማቾች ቢሆንም፣ ሌሎቹም ዐውቀውም ይሆን ሳያውቁ፣ አሳቡን ሲያስተጋቡት እያየን ነን። አልፈው አልፈው ወቀሳውን የሚደግፉ ክሥተቶች ቢታዩም፣እውነቱ ግን ጠቅላላ አሠራሩንና ለትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን ትውፊትና ልማድ አያንፀባርቅም። የኢትዮጵያ ነገሥታት መፈጸም ከሚገባቸው ታላላቅ አላፊነቶች መካከል እንደዋነኛ ሁኖ የሚቈጠረው፣ “ከመሳፍንት እስከተራ ሕዝብ ያለውን ማንኛውንም ሰው አቅድ ባለው ሕግ ማስተዳደር፣ እንዲሁም ከቁጣ የራቀ፣ አለሕግ ከመቅጣት የተቈጠበ መሪነትን ማስመስከር ነው። የንጉሠነገሥቱም ሆነ የምስለኔዎቻቸው ታላቅነት የሚገለጠው፣ ሥራቸውም የሚደነቀው፣ የማያዳላ ፍርድ በመስጠታቸው፣ አንዲሁም በቅንነትና በፍትሕ በመግዛታቸውና በሕግ አክባሪነታቸውም ጭምር ነው። እነራስ አሉላን፣ እነፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስን፣ እንዲሁም አፄ ምኒልክን የመሳሰሉት መሪዎች በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ያተረፉት፣ ኅብረተሰባቸውን በፍትሕና በርትዕ በማስተዳደራቸውና፣ ማንም ከሕግ በላይ እንዳልሆነ በማሳየታቸው ነው።አፄ ቴዎድሮስ ወደሸዋ በዘመቱ ጊዜ፣ “በፍትሐ ነገሥት ሳያስፈርዱ”፣ በአንዳንድ ከፍተኛ በደል ፈጽመዋል በሚሏቸው ሰዎች ላይ የወሰዱት ጨካኝ ርምጃ፣ ከዚህ በፊት ታይቶ ስለማይታወቅ፣ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ፍራቻና ሽብር ከማሳደር አልፎ በጣም እንዳስወቀሳቸውም፣ የታሪካቸው ደራሲዎች ይናገራሉ። ይኸ ዐይነቱ ወቀሳ ለአፄ ዮሐንስም ተርፏል። ሁኖም፣ አፄ ቴዎድሮስና አፄ ዮሐንስ የሕዝቡ ተቃውሞ በወቀሳ ብቻ በመገደቡ እጅግ የታደሉ ናቸው። እንደነሱ ሥልጣናቸውን አላገባብ በመጠቀማቸው፣ ለብዙዎቹ የደረሰባቸውን ጽዋ አልቀመሱትም። በዚህ ረገድ የበርካታዎቹ ዕጣ ከሥልጣናቸው ውድቀት ውጭ ሌላ እንዳልነበረ ታሪክ ደጋግሞ ይመሰክራል። በዚህ አፄ ተክለጊዮርጊስ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። ንጉሡ ከርሳቸው በፊት ያልተተከለ ግብር በበጌምድር ሕዝብ ላይ ቢጥሉበት፣ በበጌምድር የለ ግብር፣ በሰማይ የለ ዱር፣ በጌምድር ደረቱን ለጦር እግሩን ለጠጠር የሚል መፈክር አንግቦ፣በተቃውሞ ሲነሣባቸው፣ ዙፋናቸውን እንዳጡና፣ ድሮም በውድቀት ላይ የነበረውን ንጉሥነትን፣ ለከፋ ውርደት ስለዳረጉ፣ ስማቸው በተቀጽላ “ተፍጻሜተ መንግሥት ተክለጊዮርጊስ[38]”በመባል ይታወቃል። ሌሎችም እንደነአፄ ዘድንግል፣ አፄ ሱስንዮስ የመሳሰሉት፣ ያገሪቷን ወግና ሥርዐት ጥሳችኋል ተብለው፣ በጦር ኀይል ከዙፋናቸው እንደተወገዱ ታሪክ ይመሰክራል።

ለማጠቃለል ያህል፣ የኢትዮጵያዊነት ፍቹ በቃሉ መሠረት “ፊቱ የጠቈረ” ነው ቢባልም፣ የሚያሳየው በተለያየ ስም የሚጠራና የሚያኰራ ታሪክ ባለቤት የሆነ ሕዝብ የሚኖርበትን አገር ማንነት ነው። አንድ ኢጣሊያናዊ ታሪክ ጸሓፊ፣ ኢትዮጵያን “የሕዝብ ቤተመዘክር” ናት ብሎ ይገልጻል። እውነቱ ግን፣ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም ጭምር “የሕዝቡ ቤተመዘክር” ነው ማለት ይቻላል። እያንዳንዱ በአካላቱ፣ የአብዛኛውን የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ደምና ሰብእና አዝሎ ይዞራል። ይኸም ከስድስት ሺ ዓመት በላይ ባስቈጠረው በተለያየ ሁናቴና አጋጣሚ የተፈጸመው የሕዝብ ከቦታ ወደቦታ መዘዋወርና የማእከላዊ መንግሥት መንሰራራት ከነሱም ጋር ተያይዘው የመጡት ሁናቴዎች ፍሬ ነው። የዘውግና የግራዘመም ርእዮተ ዓለም አራማጆችና አቀንቃኞች የረሱት ነገር ቢኖር፣ ይኸን የኢትዮጵያን ሕዝብ ረጅም የታሪክ ጉዞና እሱም በሂደት ያመጣውን የትውልድና የባህል፣ የቋንቋና የሃይማኖት ትስስርና ውርርስ፣ ውሕደትና አንድነት ነው። ይኸ ሕዝብ በረጅም ጉዞው ሌላው ዓለም ከፍተኛ መሥዋዕት የከፈለባቸውን የሰው ልጅ እኩልነት፣ የሕግ የበላይነት፣የነፃነት፣የፍትሕና የርትዕ እሤቶችን በሥነልቦናው በከፍተኛ ደረጃ አዳብሯቸዋል ማለት ይቻላል።

በመጨረሻ መረሳት የማይገባው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከሌላው የአፍሪቃና የአብዛኛው የዓለም ሕዝብ የሚለዩት የአገሪቷ ጥንታዊነትና ለባዕድ ወራሪ ጥቃት አልበገርነት ብቻ አይደለም። ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የሕዝቧ አንድነትና የአስተዳደሯ አገርበቀልነትም ነው። ቅኝ ገዢዎቹ አውሮጳውያን ዓለምን ሊቀረማመቱና ሊበዘብዙ ሲሉ በየሰፈሩበት ነባሩን ሕዝብ ለጥቅማቸው እንደሚመቻቸው አድርገው በጐሣና በቋንቋ ሲከፋፍሉ፣ ኢትዮጵያ ግን ይኸንን ግፍ አልቀመሰችም። ኢጣልያንም ለዐምስት ዓመት አገሪቷን በያዘችው ወቅት እግብር ልታውለው ብትሞክር አልተሳካላትም። እንግዴህ እውነታው እንደዚህ ከሆነ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሚያራምዳቸው የጐሣና የመለያየት ታሪክ እንዴት መጣ ብለን መጠየቁ ተገቢ ይመስለኛል።

ከኢጣሊያን ይልቅ በኢትዮጵያ አሁን ላሉት ከፍተኛ ጠንቅና ቀውስ መሠረታቸው እንግሊዞች ወዳጅ በመምሰል ዕድሉን በያገኙበት ቊጥር በየጊዜው የፈጸሟቸው መሠሪ ተግባሮች ናቸው ቢባል ግንዛቤው ከእውነት የራቀ አይመስልም። እንግሊዞች፣ መጀመርያ አፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊን ሊወጉ ሲሉ ያገዟቸውን አፄ ዮሐንስን አታልለው በደርቡሾች የተከበቡትን ግብጾች እንዲያድኑ ከተደራደሩ በኋላ፣ የተስማሙበትን ውል አፍርሰው ጣልያኖችን አምጥተውባቸዋል። ኢጣሊያኖችም በእንግሊዝ ርዳታ ከኢትዮጵያ ነጥቀው የወሰዱትን መሬት፣ ኤርትራ የሚል አዲስ ስም ሰጥተው ከኢትዮጵያ ለዩት። በውስጧ ይኖሩ የነበሩት የተለያዩ ዘጠኙ ብሔረሰቦች በየጐሣዏቻቸው ሲጠሩ፣ የጋራ መታወቂያቸው በኢትዮጵያዊነት እንጂ በሌላ ስም አልነበረም። ኢጣሊያ ኢትዮጵያዊነትን እሷው በፈጠረችው ኤርትራዊነት ተካችው። ቀጥላም፣ ኤርትራን እንደአገር ሊታለማት አልሞከረችም፤ ይልቅስ ሕዝቧን ለሎሌነትና ለጠመንጃ ጉርሻ ሲትዳርግ፣ አገሩን ደግሞ የቀረችውን ኢትዮጵያን ለመውረር እንደመፈናጠርያዋ አድርጋ እንደተጠቀመችው ሁላችንም የምናውቀው ታሪክ ነው።

 

የቅኝ ግዛት ፍቅር ያንገበገባቸው እንግሊዞች፣ ለዚህ ዓላማቸው መሰናከል ሊትሆን ወይንም አደጋ ሊታመጣ ትችላለች በማለት ያሠጋቻቸውን ኢትዮጵያን ለማዳከም ያላደረጉት ጥረት፣ ያልሞከሩት ስልት፣ ያልጠነሰሱት ተንኰል የለም ማለት ይቻላል። በ፲፱፻፳ዎቹ መጨረሻ ላይ፣ ኢጣልያ ኢትዮጵያን ሲትይዝ፣ እንግሊዞች ባንድ በኩል በጠላት ባልተያዘው የምዕራብ ክፍል ጦርነቱን ለመቀጠል የታቀደውን፣ የኢትዮጵያን ጊዜያዊ መንግሥት ለማቋቋም ርዳታቸውን ሲለግሡ፣ በዚያው ልክ ደግሞ፣ በተፈጥሮ ሀብቱ እጅግ በጣም ባለጸጋ ብለው ለብዙ ዘመን ይቋምጡ የነበሩትን፣ ይኸንኑ አካባቢ ከሱዳኑ ግዛታቸው ጋር አዋህደው ለመግዛት እንዳቀዱ ይታወቃል። ለዚህም ሲሉ፣ ከያኔው የወለጋው ባላባት ደጃዝማች ሀብተማርያም ጋር ሁነው፣ የምዕራብ ኢትዮጵያ የጋላ ባለቃልኪዳን መንግሥታት[39]  የሚል ግዛት ለመፍጠር ዶለቱ። ያሰቡት የባለቃልኪዳኑ መንግሥታት ግዛት ገና ከጅምሩ ቢጨናገፍም፣ተግባራቸው ግን፣ ጠላትን ሊቋቋም የታሰበውን የኢትዮጵያን ጊዜያዊ መንግሥት አኰላሸ። ቈይቶም፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ለተባለው የጐሠኞች እንቅስቃሴ መነሻው፣ ሕይወቱ በእንጭጩ የተቀጨው የእንግሊዞቹ ጥንስስ የነበረው፣ የጋላ ባለቃልኪዳን መንግሥታት መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

 

የእንግሊዞች ደባ በዚህ አላቆመም። የኢትዮጵያ አጐራብች የሆኑት፣ የራሳቸውና የፈረንሳይ ቅኝግዛቶች፣ ማለትም ሱዳንና የሱማሌ ምድር፣ ጂቡትና ኬንያ፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በደባ ጓደኛዋ በኢጣሊያ ሲያዙባት፣አጥቂውን ለማባረር የበቁት፣ ከኢትዮጵያ አርበኞች ጋር በመተባበር ነበር። ኤርትራውያንንም ለዘመናት “ትመኙ ከነበራችሁ ከእናት አገራችሁ አንድ እንድትሆኑ ንጉሣችሁ ደርሷልና በኢጣልያን ቅኝገዢአችሁ ላይ ተነሡበት” ብለው ሰበኩላቸው። አጋጣሚም ሆነና፣ የኢትዮጵያ ነፃነት ለኤርትራም ተረፈ። እንግሊዞች ግን እንደተለመደው፣ በቃላቸው አልጸኑም። ይልቅስ ሥር የሰደደ ዘረኝነታቸውና፣ ስለጥቊር ሕዝብ ያላቸው ከፍተኛ ንቀት በይፋ ተገለጸ። እንደኢትዮጵያ በዐመጽ በናዚዎች ተይዛ የነበረችውንና፣ በአፍሪቃ ጦር ኀይል ርዳታ ነፃነቷን ሊታገኝ የበቃችውን ፈረንሳይን፣ አለምንም ቅድመሁኔታ ነፃ ባወጧት ጊዜ፣ መሬቷ በፍጹም አልተነካም። ከዚህም አልፎ፣ በናዚዎች ተይዘው በነበሩት፣ በድሮ ቅኝግዛቶቿ ጭምር፣ ፈረንሳይ አምባገነንነቷን መልሳ እንድታረጋግጥ፣በሌለው ኀይሏም ምዕራብ ጀርመንን ከተቀራሙቱት፣ ከአራቱ ኀያላን አገሮች ተቋዳሽ አደረጓት። ወደጦር ጓደኛዋ ጥቁሯ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን፣ ሁናቴው በጣም የተለየ ነበር። ታላቋን ሱማሌ ፈጥረው ሊገዙ ሲሉ፣ለዘመናት የኢትዮጵያ መሬት የነበረውን ውጋዴንን አንለቅም ብለው ቁጭ አሉ። ኢጣሊያንን ሊተኩ ያሰቡ በሚመስል መልኩ፣ ጦር ጓደኛቸውን ኢትዮጵያን፣ በሞግዚትነት ለመያዝ ቃጡ። ኤርትራም ከእናት አገሯ ቢትቀላቀል፣ ጥቅሙ ኢትዮጵያን የሚያጠናከር ሁኖ ስለታያቸው፣ የጦርነት ጊዜ ስብከታቸውን ረስተው፣ በ፲፰፻፹፱[40] ዓ. ም. የኢትዮጵያና የኢጣሊያን መንግሥታት የተዋዋሉትን የአዲስ አበባ ስምምነት በመጣስ፣አገሩን አንለቅም አሉ። ከዚያም ይባስ ብለው፣ በነሱ ሞግዚትነት ሥር ከሱዳን ቅኝግዛታቸው በማዋሀድ አገሩን ሊቈጣጠሩት፣ አለበለዚያም የትግራይን ጠቅላይ ግዛት ከኢትዮጵያ ጐምደው ወስደው፣ ከኤርትራ ጋር በማዋሀድ፣ ትግራይ-ትግርኛ የተባለ፣ አዲስ ነፃ አገር ለመፍጠር ተፍጨረጨሩ። ኢትዮጵያንንና ኢትዮጵያዊነትንም በሕዝቡ ዘንድ ለማስጠላት ሲሉ፣ በሰሜኑ ከፍል በየጊዜው የተንኰል ሥራቸውን፣ በተለያየ መልኩ አቀናጅተው ሥውር ስብከታቸውን አካሄዱ።

 

የእንግሊዞች ዕቅዳቸው በምንም መልኩ ግቡን ለመምታት ባይችልም፣ በየአካባቢው የዘሩት የከፋፍለህ ግዛ ሤራቸው ዘር ግን፣ ሥር ሰድዶ፣በዐመፀኞች ጀሌዎቻቸው አማካይነት አቈጥቊጦ ለፍሬ በቅቷል። የዐመፀኞቹ ዋና መነሻ የሥልጣን ቋመጣ ሲሆን፣ በሕዝብ ፍላጎትም ሆነ፣ በችሎታ፣ ወይንም በብቃት ዕጦት፣ ሊያገኙ ያልቻሉትን፣ ወይንም የተነፈጉትን ሥልጣንና ማዕርግ፣ በነፍጥ ኀይል ለመንጠቅ መከጀላቸው አያከራክርም። በማይወክሉት የሕዝብና የአካባቢ ስም ያካሄዱት የነፃነት ትግል፣ አላስፈላጊ ከፍተኛ የሰው ሕይወት ጥፋት፣ የአካባቢ ውድመት፣ የንብረት ቀውስና የአስተዳደር ነውጥ ሲያስከትል፣ እነሱ ይኸን ሁሉ ያዩት እንደልጆች ጨዋታ ነው። ምንም አልመሰላቸውም። በነሱ ዘንድ በነፃነት፣ በዘር ማጽዳት፣ በርእዮተ ዓለም ስም ያንድ እናት ልጆች በግፍና በጭካኔ መግደል፣ ሰይፍና ጦር መማዘዝ እንደጀብዱ ተቈጠረ። ኢትዮጵያም በገጠሟት የችግሮች ተደራራቢነት፣ የዐቅም ውስንነት፣ አንዳንዴም በአስተዳደር ድክመት ምክንያት፣ በተቀናጀ መልኩ ልትጋፈጣቸው ስላልቻለች፣ እሷን የማዳከም፣ አንድነቷን የማናጋት፣ ታሪኳን የማንቋሸሽ ዓላማ ከመላ ጐደል ለጊዜውም ቢሆን ተሳክቶላቸዋል። ሥልጣንም እንደያዙ፣ የራሳቸውን አረመኔኣዊ ድርጊቶች ሲያስተሠርዩ፣ የባላንጣቸውን ግፍ ለፍርድ ሲያቀርቡ፣ በግልጥ ያሳዩት ነገር ቢኖር ሕጉና ፍርድቤቱ፣ የፖለቲካቸው ደንገጡሮች እንጂ፣ ሌላ ትርጒም እንደሌላቸው ነው።

 

የሚገርመው ከእነዚህ ግለሰቦች፣ የጥቂቶቹ ወላጆች በአገር ክህደት የሚወነጀሉ ቢሆኑም፣ አብዛኞቹ ግን ኢትዮጵያ በታላቅ እንክብካቤ ያስተማረቻቸው፣ አገራቸውን ከነጭ የባርነት ቀንበር አወጥተው፣ በጀግንነት ተዋግተው፣ መልሰው በማቋቋም የገነቧት የአርበኞች ልጆች ናቸው። ጀግኖቹም ራሳቸው የመማር ዕድል ሳያገኙ፣ ትምህርት ቤት አሠርተው፣ አስተማሪ አስቀጥረው፣ ከፍተኛ መሥዋዕት ከፍለው ያስተማሯቸው፣ እነዚህ ልጆቻቸው ከነሱ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩና፣ ኢትዮጵያንም በትምህርት ገበታ ባገኙት ዘመናዊ ዕውቀታቸው ገንብተዋት፣ በሥልጣኔ ከገፉት አገሮች ጋር አስተካክለዋት፣ከተቻለም አስቀድሟት፣ከኋላቀርነትና ከድኅነት ማቅ አላቅቀዋት፣ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስረክቧት በማሰብ ነበር። ግን ያ ሁሉ ሕልም ሁኖ ቀረ። ይባስ ብሎ ደግሞ፣ ልጆቹ እንደጀግኖች አባቶቻቸው መሆኑ ሲያቅታቸው፣ እንደማድነቅ ጠሏቸው። ብዙዎቹ ታሪካቸውን አኰሰሱ፤ ከነሱ በመወለዳቸው ተጸጸቱ፤ ጀብዷቸውን ናቁ። አንዳንዶቹ በግልጥ ባይሉትም፣ ለነጭ ባለመገዛታቸው ተቈጩ።

 

በዚህ መልክ አገርና ወገን በማንቋሸሽና በመበታተን ተግባር በግንባር ቀደምትነት የመሩት የኤርትራ ነፃ አውጭ ድርጅቶችን ያቋቋሙት ናቸው። የኤርትራ ነፃነት ግንባርም ሆነ፣ እሱን የተካው ሻቢያ በመባል የሚታወቅ ባላንጣው የኤርትራ ሕዝብ ነፃነት ግንባር፣ ዓላማቸው ኤርትራን ከኢትዮጵያ መገንጠል ሲሆን፣ ይኸንንም ለማስፈጸምና ለማፋጠን የቻሉት በልኡካኖቻቸውና ኰትኲተው ባሳደጓቸው የጡት ልጆቻቸው መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ከልኡካኑ መካከል አዞ የተባለው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ቡድን፣ ከ፲፱፻፷ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ በኢትዮጵያ በየዘርፉ ለተከሠተው የታሪክ ግንዛቤና የርእዮተዓለም ቀውስም ሆነ ላስከተለው ኢሰብኣዊ ተግባር[41]  በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂ ነው ቢባልም፣የጡት አባታቸውን ሕልም በግብር እውን እንዲሆን ያበቁት ግን ከአብራኩ የወጡት የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)ና የትግራይ አርነት ሕዝባዊ ወያኔ (ሕወኣት) ናቸው ማለት ይቻላል። ኢሕአፓና ሕወኣት፣መጀመርያው በኅብረብሔርነት፣ ሁለተኛው በጐሣነት ላይ የተመሠረቱ የማይጣጣሙ ድርጅቶች መስለው ቢታዩም፣ በዓላማቸውና በርእዮታቸው ግን አንድ መሆናቸው መረሳት የለበትም። የሁለቱም ዓላማቸው ሥልጣን ሲሆን፣የተጠቀሙትም ከበስተጀርባቸው ያሉትን የአሳዳጊያቸውንና የአጋዦቻቸውን የመገንጠል ጥያቄ በኢትዮጵያ የጭቁን ብሔሮች ሽፋን ለማስፈጸም እንደሆነ ድርጊታቸው ይመሰክራል። የሁለቱም አንጃዎች ርእዮተ ዓለም ከ፲፱፻፷ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በተዋሱት፣ “ብሔር፣ብሔረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት እስከመገንጠል” በሚል መርህ ዙርያ የተገነባ ሲሆን፣ ዋናው ልዩነታቸው የትኛው አስቀድሞ ይተግበር በሚለው ላይ ነው። ኢሕአፓ “ትግሉ ሊሠምር የሚችለው በኅብረብሔራዊ ድርጅት ሲመራ ነው” ሲል፣ ሕወኣቶች በበኩላቸው፣ “የለም፤ በቀዳሚነት የተለያዩ ጭቁን ብሔር፣ብሔረሰቦች በየራሳቸው ድርጅት አማካኝነት ትግላቸውን ጀምረው፣ ከዚያ በኋላ የኅብረት ግንባር ሲፈጥሩ ነው” በሚል አቋም ላይ ነው። ስለዚህ ሁለቱም በስልት እንጂ በርእዮተ ዓለም አይለዩም ማለት ተገቢ ነው።

 

ሁለቱም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንቋሽሹ፣ አባቶችንና ታሪክን የሚያዋርዱ፣ በአጉል ትምክህትና ትዕቢታቸው ያበጡ፣ የማይስማማቸውን በጭካኔ ከማረድ ወደኋላ የማይሉ፤ ለሥልጣንና ለገንዘብ ሲሉ አገር ከመሸጥ ወይንም ከጠላት ጐን ተሰልፈው ከመውጋት፣ ዐይናቸውን የማያሹ ስለመሆናቸው፣ በየጊዜው በተለያየ አጋጣሚ የፈጸሙት ድርጊታቸው ይመሰክራል። በምንም አኳያ ቢታዩ፣ ሁለቱም የአገርና የሥልጣኔ ጠንቅ ናቸው ማለት እጅግ የለዘበ አነጋገር ይመስለኛል። ሁለቱም በኢትዮጵያ ጥንታዊነትና ታላቅነት አያምኑም። በነሱ አስተያየት፣ ከዚህ በላይ ደጋግመን እንዳየነው፣ ዓለም የሚደነቅበት፣ የመላው ዓለም ጥቊር ሕዝብ የሚኰራበት፣ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው፣ ከአፄ ምኒልክ ሲሆን፣ ሌላው የደብተሮች ፈጠራ ነው። ከስድስት ሺ ዓመታት በላይ ያስቈጠረውን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የርስበርስ መወላለድ፣ በአምቻና በጋብቻ፣ በባህልና በሀብት፣ በቋንቋና በሃይማኖት መተሳሰር ይክዳሉ። ኢትዮጵያ ለነሱ፣ አንድ አማራ በተባለ ጨቋኝ ብሔረሰብ ወረራ የተቋቋመች፣ መቶ ዓመት የማይሞላ ታሪክ ያላት አገር ናት። በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያ፣ አማራው በሁሉም ዘርፍ የበላይነቱን ይዞ የሚገዛባት፣ አማራ ያልሆነው ብሔረሰብ ግን፣ በግፍና በገፍ የሚማቅባት እስር ቤት በመሆኗ፣ ፈርሳ፣ ጨቋኝና ተጨቋኝ በሌለበት መልኩ፣ በነሱ አምሳል በአዲስ መልክ መገንባት ይኖርበታል ይላሉ።

 

መጠነኛ የማሰብ ችሎታ ላለው ሰው፣ የኢሕአፓና የሕወአት ርእዮተ ዓለምና ስለኢትዮጵያም ታሪክ ያላቸው ግንዛቤ፣ የሕፃናት ቧልት ከመሆን አያልፍም። ከዚህ በላይ ካየነው እውነኛው ሁናቴ ጋር እጅግ አድርጎ ይማታል፣ ይጋጫል። ይሁንና፣ ኢሕአፓ የኢትዮጵያን ፍጻሜ በሚከተለው በምድረገነት ስብከቱ፣ በአገር ፍቅር ስሜት የነደደውን፣ ዘመናዊ ትምህርቱን ከነባሩ ሥርዐትና ወግ ማጣጣም ያቃተውን፣ የቦዘኔውንና የሕልመኛውን፣ እንዲሁም የግልቱንና የገልቱን ወጣት ቀልብ በሰፊው ሊስብ እንደበቃ የማይካድ ሐቅ ይመስለኛል። ሁኖም አብዛኞቹ፣ ድርጅቱ ለሥውር ዓላማው ሲል የፈጠረው ነጭ ሽብር የተባለ የግድያ መፈክሩ ሰለባ በመሆን፣ ለእንግልትና ለእልቂት ሲዳረጉ፣ከመሪዎቹ ራሳቸው በከፈቱት ጦርነት ጥቂቶቹ ቢሞቱም፣ ብዙዎቹ ግን፣ዕቅዳቸው ሲባክንና ሲመክን፣ እንደምንደኛ እረኛ ተከታዮቻቸውን ቀይ ሽብር በተባለ ጠላታቸው እጅ ጥለው፣ ጓዛቸውን ጠቅልለው፣ ወደውጭ አገር እንደፈረጠጡ፣ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ስለሆነ እዚህ መድገም ተገቢ አይመስለኝም።

 

ኢሕአፓ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም፣ ቢቻልም ለማጥፋት፣ ከተነሡት ድርጅቶች አንዱ ቢሆንም፣ ለሥልጣን ግን አልበቃም። በለስ የቀናለት ሕወአት ብቻ ነው። ሕወአት እንደኢሕአፓ፣ በኤርትራ ነፃ አውጭ ድርጅቶች፣ በተለይም በሻቢያ፣ ተኰትኲቶ ቢያድግም፣ ለአፄ ምኒልክ ቤተመንግሥት ያጨው ግን በቀዝቃዛ ጦርነት ፍጻሜ ማግሥት የተከሠተው፣ አዲሱ የዓለም ኀይሎች አሰላለፍ ነው ማለት ይቻላል። ብቸኛዋ የዓለም ዘበኛ ሁና የቀረችው አሜሪቃ፣ ስለኢትዮጵያ ያላት እይታ፣ ሥጋትና ፍራቻ፣ እንግሊዝ የዓለም ጠባቂ ከነበረበት ጊዜ የተለየ አልነበረም። አሜሪቃ በቀይ ባሕር አካባቢ ባላት ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሟ አኳያ ኢትዮጵያን ሲታያት፣ አደገኛ አገር ሁና ነው ያገኘቻት። የገዢዎቿ አገርወዳድነት፣የሕዝቧ ሥራአፍቃሪነትና ታታሪነት፣ የታሪኳ ታላቅነት፣ በመላው ዓለም በይበልጥ ደግሞ በአፍሪቃና በሦስተኛው ዓለም ካላት ዕውቅናና ከፍተኛ ተሰሚነት፣ እንደሌሎቹ የሦስተኛ ዓለም አገሮች በዓለም ባንክ ብድር ሳትጨፈለቅ ምጣኔሀብቷን አስተካክላ ከመጓዛ ጋር ተደራርቦ፣ በቀላሉ የማትገባጠር አገር መሆኗ አሜሪቃን እጅግ ማሳሰቧ እንዳልቀረ መገመት ይቻላል። በአ. አ. ከሺ፱፻፸፫ እስከ ሺ፱፻፸፯ ዓ.ም. በውጭ አገር ጉዳይ ጸሓፊ የነበሩት ዶር. ሄንሪ ክሲንጀር[42] ላገራቸው መንግሥት አቀረቡ የተባለ ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ ኢትዮጵያ ዕድሏ ሁኖ በዘመናዊ ሥልጣኔ ገፍታ ራሷን የቻለች አገር ብትሆን በማንም የማትደፈር መሆኗ አይቀሬ ነው ይላል። ዶር. ክሲንጀር ይኸንን ሁናቴ አስቀድሞ ለመጋፈጥ፣ ከተቻለም ለማጨናገፍ የሰጡት መፍትሔ፣ ሰላም በአገሪቷ እንዳይሰፍን፣ሕዝቧ በጐሣ ሥርዐት ተከፋፍሎ ርስበርሱ እየተጋጨ በማያባራ ሁኬት ተዘቅጦ እንዲኖር የሚረዳ መሆን አለበት” ይላሉ። በሳቸው ዘገባ መሠረት፣ ኢትዮጵያ ሰላም ካገኘች የማትቻል አገር ስለምትሆን፣

 

“አሜሪቃ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ሚና ወደፊት ዋጋ እንዳያጣ፣እንዳያድጉ ማሰናከል ከሚገባቸው በቀይ ባሕር አዋሳኝ ታዳጊ አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆን አለባት። ስለዚህ ከንጉሥ ኀይሌ ሥላሴ በኋላ ኢትዮጵያን የሚመራ መንግሥት ሰላም እንዳያገኝና፣ አገሪቷም እንደዐረብ አገሮች ተከፋፍላና ተነጣጥላ እንድትበታተን [ማድረግ ይገባል]፤ መንግሥታችን [በቀይባሕር የበላይነቱን መጠበቅ የሚችለው] ኢትዮጵያን ከጎረቤቷ ከሱማሌ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከፍለ አገሮቿን ራሳቸውን በሰሜንና በደቡብ ከፋፍሎ፣ ደካማውን ወገን በመርዳት፣ ያላመፀውን ጐሣ እንዲያምፅ በማበረታት፣ ከዳር ድንበሯ ለዘላለም ሁከትና ጦርነት እንዳይለያት በማድረግና፣ ፀረ-መንግሥት ተዋጊዎችን በሲአይኤ አደራጅቶ ሰላም በአገሪቷ በመንሣት ብቻ ነው። — እኛ ያሳደግነው ውሻም ቢሆን ሊነክሰን ቢሞክር ከሥልጣኑ በማስገልበጥ፣ ላንዲት ዘመን እንኳ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሰላም ሳይሰፍን፣ ሰሜንና ደቡብ፣ ማለትም ኤርትራ፣ ትግሬ፣ አማራ፣ ጋላ እየተባባሉ እርስ በርሳቸው እየተነካከሱ ለረጅም ጊዜ ከቈዩ፣ ቀይ ባሕር ለአሜሪቃ መንግሥት ጠቃሚ በር ሁኖ ይኖራል። “[43]

 

አሜሪቃ በርእዮተ ዓለማቸው የሚመሳሰሏትን ግን አገርወዳዶችና ፀረ-ብሔርተኞች የሆኑትን ድርጅቶች በማግለል[44]፣ሕወአትን ለመደገፍ አላስፈላጊ የተፍጨረጨረችበት፣ይኸንን ሥውር ዓላማዋን ለማሳካት ድርጅቱ ታማኝነቱን ስላረጋገጠላት መሆኑ የሚያጠራጥር አይመስለኝም። ግን ያንድ ጐሣ መንግሥት በመባል እንዳይወቀስ በተሰጠው ምክር መሠረት፣ ሕወአት ከኅብረብሔራዊ የፖለቲካ ቡድኖችና ሕዝብ ከጠላውና ዐንቁሮ ከተፋው ከደርግ መንግሥት ጋር ተፋልሞ ድል ከተጐናፀፈ በኋላ፣ በአሜሪቃ ግፊትና፣ ሳያስብበት በተፈጠረው መላ ኢትዮጵያን የመግዛት ዕድል፣ ታላቋን የትግራይ ነፃ ሬፓብሊክ የማቋቋም አሳቡን ለጊዜውም ቢሆን ለመጣል ተገደደ። ከዚያም፣ ለመርሀግብሩ አስፈጻሚ ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን አጋር ድርጅቶች ፈጥሮ የኅብረብሔርነት ሽፋን ለመስጠት ሲል ከየብሔረሰቦቹ ወደመመልመል ዘመቻ ገባ። ኢህአፓ ከመሰሉ ግራዘመም አቀንቃኞች አቋሙን ለማሳመን የበቃውን በመቀላቀል፣ ልግምተኞቹን በመደምሰስ፣ አለበለዚያም ከአካባቢው በማባረር፣ ድርጅታዊ መዋቅር ከሌላቸው ብሔሮች ደግሞ እንደራሱ መለስተኛ የማሰብና የመመራመር ችሎታ ያላቸውን እንደኅብረተሰቦቹ ልሂቃን በመምረጥ ከሰበሰበ በኋላ፣ በአምሳሉ የተፈጠረውን ይኸንን የጐጠኞችና የአገር ካጆች ክበብ ነው ለማለት የሚያስከጅለውን የድርጅቶች ቅንጅት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) በሚል ስም አጠመቀው። ድርጅቶቹን ከበላይ ሁኖ ከሚቈጣጠረው ዳግማዊ ወያኔ በመባል ከሚታወቀው ሕወሓት በተጨማሪ፣ኢሕአዴግ በመነሻው ሌሎች ሦስት የጠባብ ብሔርተኞች ድርጅቶችን ያጠቃልል ነበር[45]። ሥልጣኑንም የተቋደሰው በሻቢያ ችሮታ እየተንቀሳቀሰ ክልሌ ነው በሚልበት አካባቢ በጊዜው የነበረውን የፖለቲካ ቀውስ በመጠቀም፣ ይዞታውን ለማስፋፋት እየተቀላጠፈ ይሯሯጥ ከነበረው ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ነበር። የኦነግ መሪዎች በሥልጣን ድርድር ባለመስማማታቸው ተዋጊ ወታደራቸውን በጦር ሜዳ ለጠላት ትተው በአይሮፕላን ሲፈረጥጡ፣ ኢሕአዴግ ብቻውን ያገሩ ፈላጭ ቈራጭ ሁኖ ቀርቷል።

 

ኢሕአዴግን ራሱን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ብሎ ይጥራ እንጂ፣ በተደጋጋሚ በሥራው ያስመሰከረው ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደማይወክል፣ አብዮታዊነት እንደሌለው፣ የዴሞክራሲም ሆነ፣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ጠላት መሆኑን ብቻ ነው። ኢሕአዴግ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ አጉልቶ ያሳየው ነገር ቢኖር፣ የተዛባውን የሕወአትን ርእዮተ ዓለም ማስፈጸሚያ መሣርያ መሆኑን ነው። ገና ከበረኻ ትግሉ ወቅት ጀምሮ ሕወአት ሁለት ነገር እንደማያፋልሙ ዓላማዎቹ አድርጎ ይዟል። አንደኛ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማጥፋት። ሁለተኛ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጠላትና ጨቋኝ የሚለውን አማራን መደምሰስ።

 

ኢሕአዴግ አማራ ብሎ በሠየመው ኅብረተሰብ ላይ ብዙ ግፍ እንደፈጸመና እንዳስፈጸመ በገፍ ተገልጿል። ተፈጸሙ ከተባሉት ድርጊቶች አብዛኞቹ በሥዕል የተቀረጹ፣ ለሰው መብት በቆሙ ባስተማማኝ ብሔራዊና ዓለም-ዐቀፍ ድርጅቶች የተጠናቀሩ፣ እሙን በሆኑ ያይን ምስክሮች የተደገፉ ስለሆኑ ማስተባበሉ ከመደናቈርና የአትኳራ ግብግብ ከመግጠም ውጭ ሌላ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። የግፎቹ ኢሰብኣዊነትና የፈጻሚዎቻቸውም አውሬነት ለሚሰማ ሁሉ ከመዘግነን አልፎ፣ ሰው ሁኖ መፈጠሩን ራሱን የሚያስጠላ ከመሆኑ የተነሣ፣ ልቦና ያለው ተመልካቺም ሆነ ሰሚ፣ በይስሙላ መንግሥትነት በወያኔ የሚመራውን የኢሕአዴግ ገዢዎች፣ በጀርመንና በኢጣሊያን ምድር ከታዩት፣ ከናዚና ከፋሽስት መንግሥታት መሪዎች፣ በምንም እንደማይለዩ አስመስክረዋል ብል የተሳሳትሁ አይመስለኝም።

 

እንግዴህ እዚህ ላይ ጽሑፌን ባጭሩ ልቃጭ። ኢትዮጵያ ታላቅና ረጅም ታሪክ ያላት ምድር ናት። እሷን የመሰለ ክቡርና ስመጥሩ አገር ማስተዳደር ሰፊ ዕውቀትና ብልህነት ይጠይቃል። የዘውዱን ሥርዐት የገረሰሰው የደርግ አገዛዝ፣ የጥራዘ ነጠቆች ስብስብ እንደመሆኑ፣ በሁለቱም ረገድ አልታደለም። ከባዕዳን የተበደረውን ርእዮተዓለም በብረት ኀይል ቢጭንባት፣ አገሪቷ አልቀበለውም ብትለው፣ ጭካኔና ግዽያ ተጠቅሟል። ኋላም፣ “በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይሞታልና”፣ ደርግ ኢሕአዴግ በተባለ፣ በጉልበተኛ የጐሦች ጥርቅም ድርጅት ከሥልጣኑ ለመባረር በቅቷል። ኢሕአዴግ የተካነው እንደደርግ በገዳይነቱና የኢትዮጵያን ታሪክ በማዛነፍ ብቻ አይደለም። ከዘራፊነት አልፎ የአገሪቷን ሀብቷን በመግፈፍ፣ መሬቷን ሸራርፎ ለባዕዳን በመስጠት፣ ግዛቷን በመገነጣጠልም ነው። አባቶቻችን “አገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል” ያሉት ምሳሌዊ አባባል እውነተኝነት አለው ብለን ካልተቀበልነው በስተቀር፣ በታሪኳ ያልተደፈረች፣ በሥልጣኔዋ የብዙዎች መመኪያና ኩራት የሆነች አገር፣ እንዴት እንደዚህ በመሰለ በባዕድ አምላኪ፣ ለአገሩና ለወገኑ፣ ለታሪኩና ለክብሩ ደንታ በሌለው፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ በወንጀልና በዘረፋ በተሰማራ አገዛዝ ሥር ልትወድቅ በቃች ለሚለው ጥያቄ የሆነ ያልሆነ መልስ በመስጠት ከመቀባጠር ለጊዜው ሊፈታ የማይችል እንቆቅልሽ ነው ብዬ ማለፍ እመርጣለሁ። ካልሆነም መልሱን ለውድ አንባቢዬ እተወዋለሁ።

 

አሁን ባለንበት ወቅት አንድ ነገር ግልጥ እየሆነ ነው። ሕወአት በአጋር ድርጅቶቹ መሣርያነት፣ ኢትዮጵያዊነትን ለመግደልና፣ ከሕዝቡ ጭንቅላት መንቅሮ ለማዉጣት፣ ያልጠመደው ወጥመድ፣ ያልተጠቀመው መሣርያ፣ ያልፈጸመው ድርጊት፣ ያልደነገገው ሕግ፣ ያልፈጠረው ምክንያት፣ ያልፈለገው ዘዴ ባይኖርም፣ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያን አንድነት ሊያጠፋና ሊደመስስ ግን እንዳልቻለ ብዙዎቻችን እያየነው ነው። ለዚሁ ዓላማ ድርጅቱ ተግቶ በሠራ ቊጥር፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈስና ስሜት፣ በአብዛኛው ዘንድ እየተጠናከረ እንጂ፣ እየቀዘቀዘ ሲሄድ አልታየም። ይልቅስ ዛሬ ያለንበት የፖለቲካ ሁናቴ የሚያመለክተው፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ባለፉት ለሠላሳ ዓመት ያህል ሳይታክት የሸረበው ኢትዮጵያን የማፍረስ ደባ ከሽፎበት፣ አሁን በየቦታው በሕዝብ ዐመፅ እየተናወጠ ባለበት ወቅት፣ ከመሪዎቹ መካከል አብዛኞቹ የሥልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም ሲሯሯጡ፣ ሌሎች ደግሞ ቅንነት የተላበሰ በሚመስል መንገድ የሙጥኝ ብለው ታላቂቷንና ኩሩ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በመቈናጠጥ ላይ ናቸው።

 

[1] . Diodorus Siculus, Diodorus of Sicily, ትርጒም በC. H. Oldfather (ከምብሪጅ፣ ማሳ፤ ሃርቫርድ ማተሚያ፣ 1933):3:89, 93, 95

[2] . ዖመርና ዲዮዶሩስ ማንም ሕዝብ ከሚያቀርበው ይበልጥ አማልክትን የሚመስጠው የኢትዮጵያውያን መሥዋዕት ነው ብለው የተናገሩት፣ ዛሬም ቢሆን እውነተኝነት አለው ማለት ይቻላል። የአክሱማውያንን የጣዖት አምልኮ ገርስሶ በቦታው የተተካው የክርስቲያን እምነት እንደሆነ አይጠረጠርም። የዚህ እምነት አራማጅ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን [ኢኦተቤክ] ናት። መንፈሳዊነት በጸሎታት ብዛትና ዐይነት፣ እንዲሁም በፈጣሪ ውዳሴና ምሥጋና በሚጠፋው የጊዜ ርዝመትና የዜማ ስልት ከታሰበ፣የኢኦተቤክ የሚመጣጠናት መንፈሳዊ ድርጅት በዓለም ላይ ያለ አይመስለኝም። ከዜማዎቹ ዐይነቶች የተወሰኑትን ብቻ ብጠቅስ፣ጐላ ብለው የሚታዩት፣ ከመንፈቀ ሌሊት እስከ ነግህ የሚዘመረው ሰዓታት፣ ከዓመት ወደዓመት የሚደረሰው ድጓ፣ በየታላላቆቹ በዓላት የሚዜመው ክሥተት፣ ደራሲውን ያሬድን ራሱን መሠጠው፣ መጠቀው የተባለው አርያም፣ በንባብና በዜማ የሚጸለየው ቅዳሴ፣ ለሙታን በተመላለስ የሚደገመው ምዕራፍ ናቸው። እነዚህን እንደየአገባባቸው፣ ዘማርያኑ በመቆሚያዎቻቸው እየረገዱ፣ በጸናጽሎቻቸው እየገረፉ፣ ማለትም በተለያየ ስልትና ቃና ከከበሮው ጋር እያጣጣሙ ዐቀብ፣ ቊልቊል ግራና ቀኝ እየጸነጸሉ፣ በወረብ፣ በለዘብ ወዲያና ወዲህ እየተወዛወዙ በመረግድና በጽፋት እያሸበሽቡና እያስረግጡ ሲዘምሩ፣ መንፈስ የሚመጥቅ፣ ዐይነ-ኅሊና የሚመስጥ፣ ልብ የሚነሽጥ፣ እጅግ በጣም መታየት የሚገባ ታላቅ ትርኢት ነው ማለት ይቻላል። በዚህ ረገድ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ለሮማውያን ሥልጣኔ የተጫወተችውን ሚና ያህል፣ የኢኦተቤክም በጥንት የሚደነቀውን የአክሱማውያንን የመንፈሳዊነት ቅርስ ወራሽም ጠባቂም መሆኗን የምታረጋግጥ መሆኗ አይካድም።

[3] . ርኢ Yuri M. Kobishchanov, Axum, አርታኢ Joseph W. Michels, ተርጓሚ Lorraine T. Kapitannof (University Park & London: Pennsylvania State University Press, 1979):72::

[4] . ይኸ ከአናቱ ላይ ያለው የንጉሡን ስም የሚገልጸው ወገን ከመግቢያ ተጐምዶ የጠፋበት ጽሑፍ፣ በሦስተኛ ዘመን አካባቢ የተጻፈ ሲሆን፣ ንጉሡ በኻያ ሰባተኛ ዘመነ-መንግሥቱ ሰፊ ድል የሰጡለትን አማልክቱን፣ማለትም ዜውስን፣ ኤራስ [ጨረቃ]ንና፣ ጳሰይዶስን ሊያመሰግን ሲል ባቆመ ባንድ የዘውድ ቅርጽ ባለው ድንጋይ ላይ የተጻፈ ሐውልት ነው። ንጉሥ አስገበርኋቸው የሚላቸው የአገሮች ዝርዝር፣ በቅርብ ጊዜ ሊቀሊቃውንት ላጲሶ ድሌቦ [የድሮው ጌታሁን ድሌቦ] ለኢሳት ሬድዮ ቴሌቭዥን በሰጡት ቃለምልልስ “የአክሱማያን ግዛት ከዛሬው ትግሬና ኤርትራ ክልል አያልፍም ብለው የተናገሩትን ያስተባብላል።ስለቃለምልልሱ ርኢ Professor Lapiso G. Delebo Interview with ESAT Radio on Oromo history, October 7, 2015; ለዚህ ቃለምልልሳቸው ስለወጣላቸው ኂስ ርኢ፤ ESAT Yesamintu Engida Ato Tekle Yeshaw’s Response to Dr. Lapis G. Delebo, October 30, 2015.

[5] . ሆመር በኢሊያድና በኦዴሲ ስለኢትዮጵያውያን በግጥም የጻፈውን ውዳሴ ክቡር አቶ አዲስ ዓለማየሁ እንደሚከተለው አድርገው ተርጉመውታል።

እናንተ ኢትዮጵያውያን፣ ከሰው ዘር ሁሉ እንከን የሌላችሁ፣

ከተንኰል፣ ከክፋትና ከሰው ድክመት ሁሉ ነፃ የሆናችሁ፣

ከቶ ከምን ይሆን የተፈጠራችሁ፣ ምንድርነው ባሕርያችሁ።

አማልክት ትሆኑ፣ ወይስ ሰው ናችሁ።

አማልክት ሳትሆኑ ሰው ከሆናችሁ፣

ምንድር ነው ምሥጢሩ አማልክት የሆኑት ማኅበርተኞቻችሁ፤

ምንድር ነው ብልሃቱ፣ የሰማይ አማልክት ያጓደኟችሁ።

ያ ብልሃት ምንድር ነው፤ ንገሩን እባካችሁ።

እናንተ ኢትዮጵያውያን ከሰው ዘሩ ሁሉ የላችሁ አቻ፣

የላችሁ መሳይ።

አማልክት ይወርዳሉ ከሰማይ፣

ከናንተ ጋ ሊዝናኑ በናንተው አደባባይ።

ሌሎቹ ይቅሩና ዜውስ ታላቁ ንጉሠ ሰማይ

የሁሉም ጌታ ከሁሉም የበላይ፤

ለዐሥራሁለት ቀናት አብሯችሁ ሊል እልል እፎይ፣

በዓል ሲታከብሩ፣ በድግሳችሁ ላይ፣

በደስታ በተድላችሁ፣ ሊሆን ተካፋይ፣

በደመና ተጭኖ፣ በአማልክት ታጅቦ ይወርዳል ከሰማይ፣

እንደሚወዳችሁ፣ እንደሚያከብራችሁ፣ ለዓለም ሁሉ ሊያሳይ።

(ሐዲስ ዓለማየሁ፣ ‘ኢትዮጵያዊነት በኔ አመለካከት፣” በሚል ርእስ በኢትዮጵያዊነት ማኅበር ምሥረታ ስብሰባ ቀን የተናገሩት ንግግር አሳታሚው የኢትዮጵያዊነት ማኅበር፣ ኢትዮጵያዊነት ገ.22::  የእትሙ ቦታ አልተሰጠም።

 

[6] . ታሪክ ጸሓፊዎች የአዳል ግዛት ለንጉሠነገሥቱ ሰባት መቶ ነጭ በቅሎ እንደሚገብር ይናገራሉ:: የአፄ ቴዎድሮስ ዜና ታሪክ (ኢትዮጵያ 257 ሞንዶን 70)።

[7]. የአፄ ዐምደጽዮን ታሪክ ደራሲ ዐመፀኛው ስብረዲን ተናገረ ብሎ የጻፈውን ከተመለክትን፣ፍላጎቱ ሥልጣን እንጂ እምነትን ያማከለ አይደለም። ደራሲው እንደሚነግረን፣ የሸፈተበት ምክንያት፣ “እኔ በጽዮን እነግሣለሁ አለ። አብያተክርስቲያናትን ወደእስላሞች መስጊድ እለውጣቸውአለሁ።… እሱንም [ንጉሡን} ከመኳንንቴ አንዱ አድርጌ እሾመውአለሁ፤ ካልተገዛልኝ ግን ግመሎች እንዲጠብቅ ወርጅ ለሚባሉት እረኞች አሳልፌ እሰጠውአለሁ፤ የንጉሡን ሚስት እቴጌ ዢን መንግሣን ወደወፍጮ ቤት እሰዳታለሁ።” Perruchon, M. Jules, “የአፄ ዐምደጽዮን ጦርነቶች ዜና [የፈረንሳይኛ ትርጒም) Journal Asiatique, vol. ser. 14 (ፓሪስ 1889) ገ. 281-292:: ግግር እውነትነት ካለውታሪከ ዜናው ደራሲ ንግግር ቃል በቃል እን

[8] . ለአብነት ያህል፣ የአፄ ኀይለሥላሴን የዘር ሐረግ ስንመለከት፣ ሰንጠረዡ የያንዳንዱ ግለሰብ ትውልድ በእምነትም በትውልድም ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ አጒልቶ ያሳያል።

[9] . የኢትዮጵያ ነገሥታት ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን በሥርዐቱ መሠረት፣ አብዛኞቹ የዲቊና ትምህርት ይማራሉ። ስለዚህ ዲያቆንነት ስላላቸው እቤተመቅደስ ሊገቡና ሊያስቀድሱ እንደሚችሉ አያጠራጥርም። አቡጻሊሕ ከዚህ ሁናቴ ጋር አማትቶ ሊሆን ይችላል።

[10] . Marcus Mosiah Garvey, 1887-1940.

[11] . ማርኩስ ጋርቬይ (Marcus Mosiah Garvey, 1887-1940) የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት መስለውት፣የመላው ጥቊር ሕዝብና አገር የማንነት መለዮና መግለጫ እንዲሆኑ ያወጃቸው ቀለማት ጥቁር፣ አረንጓዴ፣ ቀይ ናቸው። በኢትዮጵያው ብጫ ቀለም ቦታ በስሕተት ጥቊር መጠቀሙን የተረዳው ቈይቶ ነው ይባላል።

[12] .Garrett Augustus Morgan, 1875-1963. ሞርጋን ብጫ ቀለም እንደማስጠንቀቂያ በመጨመሩ፣ ዘመናዊው ተሽከርካሪ ያደርስ የነበረው አደጋ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ፣ የፍልሰፋውን መብት፣ ጀነራል ኤለክትሪክ ኩባንያ በአ. አ. በ፲፱፻፳፫ ዓ. ም. በአርባሺ የአሜሪቃ ብር ገዝቶት፣ ሦስቱ የኢትዮጵያ  ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት  የመላው ዓለም  ዘመናዊ መጓጓዥ ዋና ተቈጣጣሪ ቀለማት ሁነዋል።

[13] . የያንዳንዱ ግለሰብ የትውልድ ሐረግ ብንመለከት፣ እጅግ በጣም የተወሳሰበና ብዙ ብሔረሰብ ያቀፈ ሁኖ እናገኘዋለን። ለምሳሌ ያህል፣ እዚህ የአፄ ኀይለሥላሴን እስከሦስተኛ የትውልድ ሐረግ ስናይ፣ ከሩሲያ፣ ከአማራ፣ ከትግሬና ከኦሮሞ (በጉዲፈቻ) እንደሚዛመዱ ያመለክታል።

[14] . ካርታ ፩ ይመልከቱ።

[15] . ካርታ ፪ ይመልከቱ።

[16] . ካርታ ፫ ይመልከቱ።

[17] . ካርታ ፬ ይመልከቱ።

[18] . ካርታ ፭ና ፮ ይመልከቱ።

[19] . M. Jules Perruchon, “Histoire des Guerres d’ꜥAmda Şion in Journal Asiatique, vol. series 14, (1889): 294, 305.

[20] . አጋጣሚ አጥቼ ብዙ ጊዜ ላነሣ የፈለግሁት “ጋላ” ስለሚለው ቃል ነው። በአንድ ኢሳት በሰጠሁት ቃለምልልስ ላይ፣ “ጋላ” የሚለውን ቃል ስለተጠቀምሁ፣ ከፍተኛ ውርጅብኝ ደርሶብኝ ነበር። ግን ትክክል አይመስለኝም። “ጋላ” የሚለው ቃል እንደስድብ የሚቈጥር አንባቢ፤ ወደብዙ ዝርዝር ሳልገባ ከተቻለ፣ ይድረስ ለአቶ ሞሪ በሚል ርእስ የጻፍሁትን፣ በየድረ-ገጹ ታትሞ የወጣውን፣ ድርሰቴን ማንበብ ይገበዋል። ጋላ የሚለው ቃል የዘመኑ ተማርን ባዮችና ፖለቲከኞች በተጣመመ ናላቸው በሚሰጡት ትርጒም ካልሆነ በስተቀር፣ በምንም መልኩ ስድብ አይደለም፤ ሁኖም አያውቅም። ግን እዚያ ጽሑፍ ላይ ቦታው ስላልነበረ ያላነሣሁት ነጥብ ቢኖር፣ እንዴት ከጋላ ወደኦሮሞ መጠርያ ሄድን የሚለው ነው። ወደዝርዝር ሳንገባ ባጭሩ ደርግና አጫፋሪዎቹ የነበሩት በነኀይሌ ፊዳ የሚመሩት የመኢሶን ቡድኖች ያመጡት ጣጣ ነው ብዬ ከመለስሁ በኋላ አጭር ማስረጃ ጫርጫር ላድርግ። ኀይሌ ፊዳ በአዲስ አበባ ዩኒቬርሲቲ የሳይንስ ተማሪ በነበረበት ወቅት፣ ጽፎ ለንባብ ባበረከተው የምርምር ወረቀት፣ “ጋላ” ከፈረንሳይ (ማለትም በሮማውያን “ጋኡል = Gaul) ተብሎ ከሚጠራው አገር የመጣ ሕዝብ ነው ሲል ለማስረጃ ያህል በሁለቱም ቋንቋዎች መካከል ተመሳሳይነት ያላቸውን ቃል መዝዞ ቢያቀርብ፣ ሊቀሊቃውንት ፓንክሄርስት (ነፍሳቸውን ይማርና)፣ ተመሳሳይነቱ ያጋጣሚ ጉዳይ እንጂ ትክክል አይደለም ብለው ገልጸውለት ሲያበቃ፣ ምርምሩን ለማሻሻል እንዲጥር ገሠጹት። እሱም ለትምህርቱ ወደፈረንሳይ ሊሄድ የመረጠው፣ ለሳቸው ተግሣጽ በሰጠው መልስ መሠረት፣ ምርምሩን ሊያሻሽል ነበር። ይሁንና ተመልሶ የመጣው እንደአብዛኞቹ የ፲፱፻፶ዎቹ ዩኒቬርሲቲ ተማሪዎች፣ “ምርምሩን አሻሽሎ” ሳይሆን፣ በግራ ዘመም ፖለቲካ ተለክፎ፣ ዐይን ባወጣ ጭፍን የጐሣ ጥላቻ ተበክሎና ታጥቦ ነው ማለት ይቻላል። ከአበሻ ባህልማለትም ከአማራና ከትግሬ ነፃ ለመውጣት በግእዝ ፊደል መጠቀም የለብንምብሎ ኦሮምኛ በተለመደው በኢትዮጵያ ሳይሆን፣ በላቲን ፊደል እንዲጻፍ ሊያስወሰን ሞክሮ ደርግ አሳቡን ሳይቀበለው ቀረ። ሁኖም ፊደሉን በተመለከተ፣ የሱ ርዝራዦች የነበሩት በኢሕአዴግ መንግሥት የኀይሌ ፊዳን ሕልም እውን አድርገውለታል። ኀይሌ ፊዳ “ጋላም” የሚለው ስም፣ እሱ ካለው “ጋኡል = Gaul” አለመምጣቱን ሲያውቅ፣ አውሮጳ ሳለ፣ እንደክራፍ ከመሳሰሉ የምዕራብ ዓለም ወንጌል ጸሓፊዎች በሸወደው ትምህርት መሠረት፣ ቃሉ ስድብ ነው ብሎ፣ ድንፍፉን የደርግ መንግሥት በመወትወት ትክክለኛ መጠርያው “ኦሮሞ” እንዲሆን አስደረገ። እንግዴህ ጋላ ከሚለው ቃል፣ ወደኦሮሞ እንድንሄድ የተገደድነው፣ በፍጹም ባልተረዳው፣ በምዕራባውያን ግራዘመም ፖለቲካ ሰክሮ የነበረው ደርግ ባወጣው አዋጅ ነው። በሥልጣን ያለው መንግሥት ያወጀው አዋጅ በሙሉ እውነተኝነት አለው ማለት ይከብዳል፤ ይልቁንም የዞረበትና ግፈኛ የሦስተኛ ዓለም መንግሥት ከሆነ። ስለዚህ ትክክልም ነው ብለን መቀበል የለብንም። የደርግ ከፍተኛ እዋጅ ኅብረተሰባዊነት ነበር። ከዚህም የተነሣ፣ ሣር ቅጠሉ ሳይቀር፣ በኅብረተሰባዊነት መርህ ይመራ እንደነበር ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ነው። ግን ብዙም ሳይቈይ ከነአካቴው ተደምስሶ በጠባብ ብሔርተኝነት ተተካ። ወራሹም ሆነ ጠፊው መንግሥት እያነበነበ የነበረውና ያለው፣ የግላቸውን ዓላማ ለማሳካት አመቺ ሁኖ በታያቸው እንጂ፣ ዘመኑ በሚጠይቅበት መልክ በምርምር በተደገፈ ጥናት ላይ የተመሠረተ መርህ አይደለም። ለብዙዎቻችን የሚነግሩን ሁሉ ውሸት ነው ማለት ይቻላል። ግን በታጠቁት የጦር ኀይል ብቻ በመተማመን፣ አላንዳች ክርክር እሺ ብለን እንድንቀበል እያስገደዱን ስለሆነ፣ ብዙዎቻችን ምርጫ ላይኖረን ይችላል። ላገርና ለሕዝብ ጥቅም እስካልሆነ ድረስ፣ የማንኛቸውንም ስብከትና ዐዋጅ መቀበል ግን ተገቢ አይመስለኝም።

አባ ባሕርይ፣ የድፍኑ ዓለም ምሁራን በሚያደንቃቸው ድርሰታቸው “ጋላ” በማለት ያስታወቁን ሕዝብ፣ ከዚህ መልክ በተለየ አጠራር ራሱን ሲጠራም ሆነ፣ ሌሎች ሲጠሩት አላየንም። ከሚናገረው ቋንቋ በመነሣት፣ ለመጀመርያ ጊዜ “ኦሮሞ” የተባለውን ስም የሰጠውና፣ ኦሮሞ የሚለውን ቃል የፈለሰፈው፣ በቄሳራዊነት ምኞትና ምትሐት ልቡ ይቃጠልና ይሠቃይ የነበረው፣ ጀርመናዊው ቄስ ዮሐን ክራፍ ነው። የክራፍ ዓላማው “ኦርማኒያ” ብሎ የጠራውን ሕዝብ ማክረስትንና፣ከኢትዮጵያ ደቡብ እስከ ሐሩሩ መኻል አፍሪቃ ድረስ ከጀርመን ሥር ማድረግ ነበር። ግን በሃይማኖት ስብከቱ አማኞችን የማፍራት ሥራው እንደከሸፈ ሁሉ፣ የጀርመን ቅኝ ግዛትም አሳብ ሳይሟላለት ሞተ። ክራፍ፣ “ጋሎች ቋንቋቸውን “ኦርማ” ስለሚሉ በዚያው መሠረት “ኦሮማ” ተብለው ይጠሩ” ሲል ጽፏል። ያኔ በቋንቋ ጥናትና ምርምር የተሰማሩትና የቄሳራዊነት ምኞት ያልነበራቸው፣ የመጠቁና የረቀቁ ምሁራን፣ ጥራዘ-ነጠቁንና ፖለቲከኛውን ክራፍን፣ እጅግ በጣም ስለተቃውመት “ቃሉ” የትም ሳይደርስ ቀረ። ምሁራኑ የተቃወሙትምጋሎችራሳቸውን የሚጠሩትጋላበማለት ነው፤ መጠርያውን ያወጡት ደግሞ ጋሎች ራሳቸው እንጂ፣ ዐረቦችም ኢትዮጵያውያንም አይደሉም ብለው ነው። የክራፍ ታላቁ ስሕተት የአንድ ሕዝብ መጠርያ ከሚናገረው ቋንቋ ይዛመዳል፤ ይመነጫል፣ መጋር አለበት የሚል የተዛባ አስተሳስብ ነው። ያንድ ሕዝብ ቋንቋ፣ ለምሳሌ ያህል ላቲን፣ እንግሊዝኛ ወይንም ዐረብኛ፣ ከዚያም አልፎ ፈረንሳይኛ ቢሆን፣ ሕዝቡ የግዴታ ላቲን፣ እንግሊዝ፣ ወይንም ዐረብ ወይንም ፈረንሳይ ተብሎ ይጠራ አይባልም። ሮማውያን ቋንቋቸው ላቲን ነው፤ ግን ላቲኖች ተብለው አይጠሩም። ጐረቤቶቻችን ኬንያዎች ቋንቋቸው እንግሊዝኛ ነው፤ ግን እንግሊዞች ነን አይሉም። ጂቡቲዎች ፈረንሳይኛ ዋነኛ ቋንቋቸው ቢሆንም፣ እነሱ ግን ፈረንሳዮች መባል አይፈልጉም። ግብፆች ዐረብኛ ቢናገሩም፣ በእምነትም ሆነ በባህል በጣም ተመሳሳይ ሳሉ፣ እኛ ዐረቦች ነን፤ “ዐረቢያ” ተብለን እንጠራ አይሉም። የእስጳንያ ግዛቶች የነበሩት የላቲን አሜሪቃ አገሮች፣ ቋንቋቸው እስጳንኛ ቢሆንም፣ አንዳቸውም በዚያው በቋንቋ ስም አይጠሩም። ሁሉም የሚጠራው፣ በየአካባቢው ስም ነው። እንዲሁም፣ ወደአገራችን ስንመለስ፣ አማርኛ የሚናገር በሙሉ አማራ ከተባለው አካባቢ የመጣና ከዚያም ከመጣ የተወለደ አይደለም። ስለዚህ “ኦርማ” ከተባለ ቋንቋ ተነሥቶ፣ተናጋሪውን ሕዝብ “ኦሮሞ” ማለት ትክክል አይደለም። የአውሮጳውያን ጸሓፊዎች “ወረሞ/አረሞ” ሲሉ ቋንቋውን እንጂ ሕዝቡን አይደለም። ሕዝቡን ጋላ ነው የሚሉት።

[21] . የምሥራቅ ጀርመኖች ኦስትሮጎቶች (የምሥራቅ ጎቶች) ተብለው ሲጠሩ፣ የምዕራቡ የሚታወቁት ቪሲጎቶች (የምዕራብ ጎቶች) በመባል ነው። እነዚህ በዘራቸው አንድ ናቸው ተብለው ቢታመኑም፣ በተለያዩ የአውሮጳ አገሮች ተበታትነው ይኖራሉ። ስማቸውም እንደየጐሣቸውና እንደየአሰፋፈራቸው ይለያያል። ጥቂቶቹን ብቻ ለመጥቀስ ያህል ዛሬ እስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ደንማርክ፣ አይስላንድ፣ እስዊጸርላንድ፣ ጀርመን፣ 0ውስትርያ፣ ሰሜን ኢጣሊያ (ሎምባርዶች)፣ ኔዜርላንድ፣ እንግላንድ፣ ቡርጉንዲ፣ ቫንዳሎች (እስጳኞች) ከነዚህ ሁለቱ ቅርንጫፎች የሠረፁ ናቸው ይባላሉ።

[22] . በኬንያ ላሉት ኦሮሞች የአንድነታቸው መግለጫ ኬንያውነት ነው።

[23] . አሬመናዊ ልማድ ስል፣ በሰፊው የተመዘገበው የወንዱን ብልት፣ የሴቱን ጡት የመቊረጥ ልማድ ነው። ይኸም፣ በአሩሲና፣ በደቡብ በቦረና አካባቢ፣ እስከቅርብ ጊዜ እስከሺዘጠኝ መቶ ሰባዎቹ ድረስ፣ አልፎ አልፎ በይፋ ይከሠት እንደነበር የዐይን ምስክሮች ይገልጣሉ። በቅርቡ የጋዳን ሥርዐት እንደከፍተኛ የሰው ልጅ የሥልጣኔ ዕርከን የማየት ዝንባሌ አለ። በአንደኛ ደረጃ፣ የጋዳ ሥርዐት፣ ያውም አሉታዊ ገጽታውን ሳያካትት፣ በብዙዎች የአፍሪቃም ሆነ፣ የኢትዮጵያ (ለምሳሌ፣ ሲዳማ፣ ዴራሳ፣ ኮንሶ፣ ቡርጂና ጊዶሌ በመሳሰሉት) ኅብረተሰቦች ዘንድ ያለ ባህል ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ኦሮሞች ለብዙ ጊዜ የቈዩት፣ ተመሳሳይ የጋዳ ዐይነት ባህል ካለው ከሲዳማ ሕዝብ ጋር ተቀራርበው በመኖር ስለነበር፣ የትኛው ብሔረሰብ የባህሉ አመንጪ/ዋና ወይንም ተዋሽ መሆኑ በግልጥ በጥናት አልተረጋገጠም። በሦስተኛ ደረጃ፣ ጋዳ ከሰብአ-ትካትነት የኑሮ ደረጃ ጋር የተያያዘ እንደመሆኑ መጠን፣ የኅብረተሰቡ የኑሮ ስልት ሲቀየር፣ ባህሉ፣ እጅግ በጣም በተወሰነ አካባቢ ካልሆነ በስተቀር፣ በአብዛኛው የኦሮሞ ኅብረተሰብ ዘንድ ከሞተ ዘመናት አስቈጥሯል። የሆነ ሁኖ፣ በኦሮሞች ዘንድ የጋዳ ዋናው ደረጃ ሉባነት ነው። በዐሥራሰባተኛ ዘመነ ምሕረት መግቢያ ላይ፣ ስለኦሮሞ ብሔረሰብ በቅርቡ ያጠኑትና፣ ትውልዳቸውም ከዚያው ኅብረተሰብ እንደሆኑ የሚነገርላቻው፣ ደጃች ጢኖ፣ ስለሉባ እንዲህ ይላሉ።

“በሉባነት [ማዕርግ] እስከሚሾም ድረስ የ[ጋላ] ኅብረተ-ሰቡ አባል አይገዘርም ብቻ ሳይሆን፣ ልጅ እንኳ ቢወልድ እንደወላጅ ሁኖ በሥነ-ሥርዐት በማሳደግ ፈንታ፣ እንደውሻ ቡችላ እውጭ ይጥለዋል። በዚህ ሹመት ላይ ባለ ጊዜ ውስጥ፣ ሰው ካልገደለ ደግሞ ፣ ጠጒሩን አይላጭም፤ የግድያ መለዮው ስለሆነ፣ ጒቱም አያሳድግም ፤ ታድያ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ሰው፣ ዘወትር እያለቀሰ፣ በሐዘን ውስጥ ተዘፍቆ ይኖራል እንጂ።”

በዚህ መረጃ መሠረት ካየነው፣ ጋዳ የከፍተኛ ሥልጣኔ ዕርከን መሆን ይቅርና፣ ከዘመናዊነት ጋር የማይጣጣም፣ እጅግ በጣም አጸያፊ ባህል ነው ማለት ይቻላል።

[24] . የታወቀው የጋልኛ ቅኔ ባንድ በአንኮበር ደብተራ በ፲፰፻፺፩ ዓ. ም. ለወህኒ አዛዥ ወልደጻድቅ የተቀኘው ነው።

ናገርሲሲ ከራ ሐዘሎ፣ ዒጃ ምኒልክ ወልደ ጻድቅ

አኒ ቤኬ እንጅሩ ጎፍታኮ፣ ከራ ሐዘሎ ሁንዱማ፤

ዱቢን ኬቲ ዳዲ፣ አፋን ኬቲ ደማ፣

ሌንጫ ጎፍታኮ፣ አርካ ምኒልክ ይልማ፤

ወረሞ አቡልቱ ምስለ ሲዳማ፤

ዒጃ ጎፍታ ኬኛ ኲኖቲ፣ ቢፍቱ ዲረማ፤

አዕይንተ ይሰብር በግርማ። (ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ያማርኛ ሰዋስው (አዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣፲፱፻፵፰)፡፪፻፳፩

[25] . ግራኝ አፄ ልብነ ድንግል በዋሰል ተራራ ላይ መሆናቸን አይተው ሊይዟቸው ሲሉ፣ ወታደራቸውን “የእስላም ሳይሆን [አደሬ]”፣“የየጁ ቋንቋ” እንዲናገሩ ያዟቸዋል። ይኸም የዛሬው አማርኛ መሆኑ አያጠራጥርም(Paul Lester Stenhouse (ትርጒም.) and Richard Pankhurst (ማብራርያ), Futuh Al-Habaša, The Conquest of Abyssinia (Tsehai Publishers, ገ.235-236)።

[26] . ትርጒሙ “የመኳንንት ራስ፣ መሪ” ማለት ነው።

[27] . ብርሃን ሞገሳ በመባል የሚታወቁት እቴጌ ምንትዋብ የአፄ በካፋ (1713-1723) ባለቤትና የአፄ ኢያሱ ብርሃንሰገድ(1723-1747) እናት ናቸው። የልጅ የልጃቸው፣ የአፄ ኢዮአስ (1747-1761) እናት፣ ወለተቤርሳቤሕ (የቀድሞ ስማቸው ውቢት) የሚወለዹት ከወሎ ባላባት ነው። በባላቸው በአፄ ኢያሱ ብርሃንሰገድ ጊዜ በሽሽግ ይቀመጥ የነበረው ልጃቸው ሲነግሥ፣ እቴጌ ምንትዋብ እቴጌ ተብለው ከልጃቸው ኢያሱ ጋር እንደንግሥት ይገዙ እንደነበር ሁሉ፣ እኔም ልክ እንደዚያው የእቴጌነት ማዕርግ ተሰጥቶኝ፣ ከልጄ ጋር በንግሥትነት ልግዛ፣ ልሹም፣ ልሻር በማለት ከልጃቸው አያት፣ ማለትም ከእቴጌ ምንትዋብ ጋር የጀመሩት ፉክክርና ክርክር፣ ቈይቶ ወደዘመነመሳፍንት አመራ።

[28] . R. S. Whiteway (ed. trans.) The Portuguese Expedition to Abyssinia in 1541-1543 As Narrated by Castanhoso, (The Haklyut Society: London, 1802):228-9.

[29]. ፍቱን የታሪክ ተመራማሪዎች መሆናቸው የተመሰከረላቸው አንዳንድ “ኦሮሞ ነን” ባዮች ምሁራንም ይጋሩታል። ለምሳሌ ያህል፣ ሊቀጠበብት ሙሐመድ ሐሰን አሊ [ከጥላቻ የተነሣ ይሁን፣ ወይንም ከዕውቀት ማነስ አይታወቅም፣] የኢትዮጵያን የክርስቲያን እምነትንና ማእከላዊ መንግሥትን የሚያጥላላ፣ የኦሮሞችን “ሌጣ መንግሥት” የሚወድስ ሁኖ ቢታይም፣ የኦሮሞ ኅብረተሰብ እንዴት ወደቀረው የአገሪቷ ክፍል እንደተንሰራፋ ሲነግረን እንዲህ ይላል

“ኦሮሞቹ ከእረኝነት ወደግብርና እንደተሻገሩ፣[የሌሎቹን]ከብታቸውን ለመዝረፍ፣ ነዋሪዎቹን ለባርያ ንግድ ሲሉ፣ አካባቢያቸውንና ጐረቤቶቻቸውን መውረር ዋና ሙያቸው አድርገው ነበር። የባርያ ጥቅሙ ሁለገብ ነበር። በባርያ ጋማ ከብትና ጠመንጃ ይሸመትበታል፤ መድኀኒትና የክት ልብስ ይገዛበታል፤ እንደስጦታ ዕቃም ይሰጣል። ስለዚህ ባርያ ከማንኛዉም ሀብት በላይ የሚፈለግ ብርቅ ዕቃ ነበር። በጐጃም፣ በበጌምድር፣ በምፅዋና በቀይ ባሕር ዙርያና እንዲሁም በሸዋና በሐረር ከዚያም ባሻገር ባሉት አገሮች የሚሸጡት ባሮች፣ ዋናው ምንጫቸው ከነዚሁ አካባቢዎች [በምዕራብ ኢትዮጵያ ከ፲፱ኛ ዘመነምሕረት መግቢያ እስከመኻሉ ድረስ ከጐጃም በታች አቈጥቊጠው የነበሩት የጊቤ ባላባቶች ግዛቶች በመባል የሚታወቁት እነጉማ፣ ጐማ፣ ሊሙ፣ ጌራና ጅማ] መሆኑ ይታወቃል።”

Muhammed Hassen, The Oromo of Ethiopia: A History, 157-1860, (Cambridge: Cambridge University Press, 2003):124-125።

[30] . Muhammed Hassen The Oromo 18-24::

[31] . ብዙዎቻችን እንደሚናውቀው፣ የሶሰጅ ጥሩነቱ ሲበሉት ነው።ደስ ይላል፤ ይጣፍጣል። ከምን እንደተሠራ መመራመር የሚያመጣው መዘዝ፣ ምግቡን ወደመንገፍገፍና መዘግነን ሊያመራ ይችላል። እንዲሁም፣ አንድ አገር ደስ የሚለው ማንነትንና፣ ከሱም ጋር የተሳሰሩ መብቶችን ለማዳበር፣ አብሮ ባንድጋ በሰላም መኖሩና ትብብሩ የሚያበረክቱትን ጥቅማጥቅሞችን ማየቱ ነው። አንድነቱ እንዴት ሁኖ ተደረሰ በሚለው ጥያቄ ላይ ብቻ ማፋጠጥ ግን፣ ባልታሰበ፣ ደም በሚያስገነፍል፣ ጦር በሚያስመዝዝና፣ ያገሪቷን አንድነት በሚያናጋ ጠንቅና ንትርክ ሊከት ይችላል። ሌላው ቀርቶ አንድ እናት እንኳን፣ ዋና አሳቧ በወለደችው ልጇ መሆን ቀርቶ፣ ባሳለፈችው ምጧና፣በቀመሰችው መከራዋ ብቻ ከሆነ፣ መጨረሻው ላያምር ይችላል። ከዘጠኝ ወር በላይ ያዘለችው የሆዷ ፍሬ፣ የደስታና የእልልታ ምንጭ መሆኑ ቀርቶ፣ ለጥላቻና ለሌላም አደጋ እንዳይዳርግ ያሰጋል።

[32] . እኔ ሁሌዬ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር፣ “የዚህ ብሔረ-ሰብ አካል በመሆኔ ተጨቁኜ ነበር፤ ብሔረሰቤም ተጨቊኖ ነበር” ባዮች፣ ጭቆናው በምንና እንዴት መቼስ እንደሆነ፣ እስካሁን ሊያስረዱኝ አልቻሉም። የብሔረሰቡ አባል በመሆናቸው፣ የትምህርት ዕድል የተከለከሉበት፣ በሥራ ሲቀጠሩ አድልዎን ያዩበት፣ በጋብቻ፣ በመኖርያ፣ በሀብት ልዩነት የቀመሱበት አጋጣሚና ሁናቴ ካለ፣ ልነግሩኝ አልቻሉም። አንድ ጊዜ፣ አንድ ኤርትራዊ ብዙ ምሁራን ወረቀት በሚሰጡበት ስብሰባ ላይ ተገኝቶ፣ ስብሰባው እንዳይካሄድ መበጥበጥ ጀመረ (ብዙዎቻችን እንደምናውቀው፣ በሽምቅ ተዋጊዎች ወኪሎች፣ በግራዘመምና በዘውግ ርእዮተዓለም አቀንቃኞች ዘንድ ያኔ በጣም የተለመደ ስልት ነበር)። በመጨረሻ፣ ሊቀ መንበሩ አለሳለሱትና፣ ስብሰባው እንደታቀደው ቀጠለ። ሰውዬው ባንድ ዩኒቬርሲቲ ጥሩ ሥራ ያለው ነበር። በስብሰባው ለተሰብሳቢዎቹ ሊያስታውቅና ሊያስረዳ የሞከረው፣ ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ከልክላ፣ ኤርትራውያንን ከቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለይታ እንዴት እንደጨቈነች፣ እሱም ትምህርቱን ሊማር የበቃው፣ እዚህ አሜሪቃ ከመጣ በኋላ ብቻ እንደሆነ ነበር። ከስብሰባው አዘጋጆቹ አንዱ እኔው ነበርሁና፣ ኋላ እንደተረዳሁት ቅሬታውን ለማሰማት ወደማስተማርበት ትምህርትቤትና ክፍል መጥቶ፣ ካለቃዬ ቢሮ ሲወጣ አገኘሁት። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፣ ‘እኔኮ በትውልድ አገርህ አካባቢ ሠርቻለሁ” አለኝ። በስብሰባው ላይ፣ “ከኤርትራ በቀጥታ መጥቼ፣ እዚህ አሜሪቃ ዕድል አግኝቼ ልማር በቃሁ” ብሎ ስለነበር፣ እኔም ገርሞኝ፣ እንዴት ሄድህ አልሁት። “የአዲስ አበባ ዩኒቬርሲቲ የሦስተኛውን ዓመት የአገልግሎት ግዴታዬን ያሟላሁት ባንተ ከተማ ተመድቤ ነው” ብሎ ቁጭ አለ። ለማመን አልቻልሁም። ኋላ በጉዳዩ ተገርሜ፣ ስለሰውዬው ዳራ ስመረምር፣ ለካስ የአንድ የተከበሩ አገር-ወዳድ ከፍተኛ ኤርትራዊ ባለሥልጣን ዘመድ ስለነበር፣ ይማር የነበረው በአዲስ አበባ ካቴድራል ትምህርትቤት ሲሆን፣ እሱ የሚመላለሰው፣ ቈይቶም ምሳውም በየቀኑ የሚመጣለት፣ በሹፌር በሚነዳ ሊሞስን  እንደነበር አብረው ይማሩ የነበሩት ጓደኞቹና ትውውቆቹ  ነገሩኝ። እንግዴህ፣ ስለብሔረሰብ ጭቈና የሚለፈልፉት የጐሣና የግራዘመም ርእዮተዓለም አቀንቃኞች፣ ይኸ ሰውዬ ከሚያወራው ጭቈና የተለየ ዐይነት ያላቸው አይመስለኝም።

[34] . በቋንቋቸው የነዚህ የታደሉ ሁለቱ መደቦች አካል ያልሆነው፣ ቤተአልባሌው፣ በጠቅላላ “የቀረው ሁሉ” ወይንም “ማንም” በመባል ይታወቃል።

[35] . መቶ በመቶ ትክክለኛ ትርጒም ባይኖረውም፣ ሦስቱን በአገራችን አጠራር “ቀዳሽ፣ ነጋሽ፣ አንጋሽ” ብለን ልንተረጒም እንችላለን። “ማንም” ወይንም “አንጋሽ”፣ በሁለቱ መደቦች ያልተካተቱትን፣ ማለትም ከለማኝ እስከቱጃርና ከፍተኛ ምሁር ድረስ ያለውን ባለሙያን ሁሉ ሁሉ ያጠቃልል ነበር።

[36] .    በእንግሊዝኛ፣ The [First] Abyssinian Baptist Church [in New York] በመባል ትታወቃለች።

[37] . በእንግሊዝኛ ቋንቋ Enlightenment Movement የተባለው እንቅስቃሴን ያመለክታል።

[38] . ትርጒሙ “የመንግሥት መጨረሻ ተክለጊዮርጊስ” ሲሆን፣ በአፄ ኢዮአስ ዘመን የደከመው የንጉሠነገሥቱ ኀይል በጭራሽ መውደቁንና በተቀራኒው ደግሞ የእንደራሴአቸው ሥልጣን እየገንነ መሄዱን ያመለክታል።

[39] . በእንግሊዝኛ “Western Ethiopia Galla Confederation”

[40] ወደአድዋ ጦርነት የመራውን የሚያዝያ ፳፭ ቀን ፲፹፹፩ ዓ. ም. የኢትዮጵያና የኢጣሊያን መንግሥት የተዋዋሉትን የውጫሌን ስምምነት የተካው፣ በጥቅምት ፲፯ ቀን ፲፹፹፱ ዓ. ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተፈራረሙት ዘጠኝ ክፍሎች ያሉት ውል ነው። በዚህ ውል አንቀጽ ዐምስት፣ በኢጣልያን ቅኝ ግዛት ሥር ያለው፣ ኤርትራ በመባል የሚታወቀው አገር፣ የኢትዮጵያ መሬት መሆኑን በሚቀጥለው መልክ ይገልጸዋል። የኢጣሊያ መንግሥት ከዚህ አገር ለማንም ማን መንግሥት መስጠትና መልቀቅ አይቻለውም። ዛሬም የኢጣሊያ መንግሥት በጁ ከያዘው አገር መልቀቅ ያማረውም እንደሆነ ለኢትዮጵያ መንግሥት ይመልሳል።

[41] . “ኢሰብኣዊ ተግባር” ወይንም “አሬመነኣዊ ተግባር” ከሚባሉት እጅግ አፀያፊ፣ ዘግናኝና አሰቅጣጭ የአቶ ጌታቸው ማሩ አገዳደል ነው። አቶ ክፍሉ ታደሰና አቶ ተስፋይ ደበሳይ ሰውዬውን ከገደሏቸው በኋላ፣ ራሳቸውን፣ እጃቸውን፣ እግራቸውንና ሌላውን አካላቸውን ለየብቻው ቈራርጠው በጆንያ ከትተው በመንገድ ይዘውት ሲሄዱ ተይዘው ሁለቱም ሸሽተው እንዳመለጡ ይነገራል። ይኸ ዐይነት ጭካኔ በኢትዮጵያ መሬት ሲፈጸም፣ የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም። የሚያሳየውም፣ የሺዘጠኝመቶስድሳዎቹ ተማሪዎች፣ ወደኢትዮጵያ ያመጡት የአውሮጳን የባህልና የርእዮተ ዓለም ጦርነት ብቻ ሳይሆን መላ ታሪካቸውን የበከለውን ዐመፅና ጭካኔም ጭምር ነው።

[42] . Henry Kissinger, 1923 – .

[43] . ጥቅሱ የተወሰደው ከኮሞዶር ጣሰው ደስታ ሲሆን እሳቸውም ያገኙት አሞራ ከተባለ በአቶ ግደይ ባሕረሹም ከተደረሰ መጽሐፍ መሆኑን ይናገራሉ። በኮሞዶር ጣሰው ትርጒም ላይ አንዳንድ ማሻሻያ አድርጌአለሁ (ኮሞዶር ጣሰው ደስታ፣ የኢትዮጵያ አንድነት፤ ትዝታና ትግል፣ ሃይፖይንት ኖርዝካሮላይና ፲፱፻፺ ዓ.ም ገ. 245-246)።

[44] ኮሞዶር ጣሰው ደስታ “የኢትዮጵያ አንድነት፣ ትዝታና ትግልበሚለው መጽሐፋቸው የአሜሪቃን ስለላ ድርጅት ማለትም ሲአይኤ፣ አንዲት ኢትዮጵያ በሚል መርህ የሚንቀሳቀሱትን የኢትዮጵያ ዴሞክራክ ኅብረትንና ሌሎችን እሱን የመሳሰሉትን ለማዳከምና ለመበታተን፣ የፀረ-አንድነት ኀይሎችን ግን ማለትም የሻቢያን፣ የኦነግንና የወያኔን ጉልበት ለማጠናከር እጅ ከጓንት ሁኖ እስከመሥራት የተጫወተውን ሚና በመጠኑ ይገልጣሉ (ገ. 177-196)።

[45] . ሦስቱ ድርጅቶች የአማራን ሕዝብ ይወክላል የተባለውንና፣ ከተበታተነው ከኢሕአፓ ሠራዊት በሰሜን ቀርቶ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲአያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን)  ስም ሲንቀሳቀስ ቈይቶ፣ ከሕወአት ድል በኋላ ስሙን ወደ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የቀየረውን፣ የኦሮሞ ሕዝብ እወክላለሁ ባዩን የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ)፣ እንዲሁም የተማሩና የተማረኩ የኢትዮጵያ ሠራዊት መኩንኖች ስብስብ (የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መኰንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኢዴመአ) ያካትታል። በኋላ ሕወአት ትውልዳቸው ከደቡብ ሁኖ ሕወአትንና ሻቢያን ሲዋጉ የተማረኩትን የሠራዊት አባላትንና የብሔረሰቦቹ ልሒቃን ብሎ ከየቦታው የለቃቀማቸውን ግለሰቦች በማሰባስብ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዴኢሕዴግ) የተባለ ፈጠረ። ዴኢሕዴግ መጀመርያ ላይ የዘጠኝ ጐሣዎች ድርጅቶች ያካትት ነበር። በኋላ በዚያው በተቋቋመበት ዓመት ውስጥ ሌላ አራት የጐሣ ድርጅቶች ተጨምረውበት፣ አባላቱ ዐሥራአራት ሲሆኑ፣ ቈይቶም ስሙን ከዴኢሕዴግ ወደ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ዴኢሕዴን) ቀይሯል።መረጃ ቲቪን በተሻለ ጥራት እና ፍጥነት እንድናቀርብ እገዛችሁን እንሻለን።
መረጃ ቲቪን ለማገዝ ይህን ሊንክ በመጫን አባል ይህኑ - JOIN Mereja TV