የጄኔራሎቹ ቃለ ምልልስ !

የጄኔራሎቹ ቃለ ምልልስ !
(የመጀመርያ ክፍል)
በኮሮና ቫይረስ ሥርጭት ምክንያት እቤት ስንውል ጊዜያችንን በተለያዩ ጠቃሚ ነገሮች እንደምናሳልፋቸው ይገመታል፡፡ ለዚሁ ዓላማ በሚል ከዛሬ ሰባት ዓመታት በፊት በዝዋይ እስር ቤት ቃለ መጠይቅ አድርጌላቸው ሃሳባቸውን በመጀመርያ መጽሐፌ(የነፃነት ድምጾች ላይ) ለንባብ ካበቃሁላቸው የእስር አጋሮቼ ሁለቱ ብ/ጄ/ል ተፈራማሞ እና ብ/ጄ/ል አሳምነው ጽጌ ናቸው፡፡ ጊዜው የቆየ ቢመስልም በወቅቱ የተነሱት ነገሮች ምን ያህል መሰረታዊ እንደሆኑ ያስተዋልኩት መለስ ብዬ ጽሑፎቹን የመመርመር እድል ባገኘሁበት በዚህ ወቅት ነው፡፡
በተለይ መጽሐፏን ማንበብ ያልቻላችሁ ወገኖች አጋጣሚውን ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ በጽሑፉ ርዝመት እንዳትሰለቹ በሚል የሁለቱንም ጄኔራል መኮንኖች ቃለ ምልልስ በሁለት በሁለት ክፍል አቀርብላችኋለሁ፡፡ ሌሎችም ወደፊት በተከታታይ የማቀርብላችሁ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ወገኖች ሃሳብና ተሞክሮ ይኖራል፡፡ (ታዲያ ርቀታችንንና ንጽናችንን እየጠበቅን)
**********//**********
⨳“የሆነው ሁሉ ብዙሃኑን ሕዝብ ይጠቅማል ብለን ጊዜ ወስደንና አስበንበት ያደረግነው በመሆኑ፣ ከሕዝቡ ምንም ነገር መሸሸግ የለበትም ብዬ አምናለሁ፡፡›› በማለት ነበር ስለ 2001ዱ ‹‹የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ›› የሚል
ስያሜ፣ የተሰጠው ክስ ላነሳሁላቸው ጥያቄ መመለስ የጀመሩት፡፡
*“እስኪ ስለራስዎ በአጭሩ ያጫውቱኝ፤ ወደ ትግል መቼ፣ እና እንዴት ገቡ? ከእነማን ጋር ነበሩ? የትግል ሜዳ ልዩ ትውስታዎችዎ ምንድናቸው?” አልኳቸው፡፡
⨳የትግል እንቅስቃሴዬ የተጸነሰው በ1967 ዓ.ም ነበር፡፡ በወቅቱ የትውልድ አካባቢዬ በነበረው ላስታ አውራጃ ውስጥ የደርግን መምጣት ተከትሎ፣ ዓላማቸው የተለያየ ሆኖም ተመሳሳይ መገለጫ ያላቸው የዐመፅ እንቅስቃሴዎች ይካሄዱ ነበር፡፡ ብርሃነመስቀል ረዳ በአየር መንገድ ላይ ጥቃት የሰነዘረውም ያኔ ነበር፡፡ ደርግ ደግሞ ጉዳዩን
ከሥሩ መርምሮ ከመፍታት ይልቅ ጦር ላከ፡፡ ዕድሜያችን 10 ዓመት የሞላ ልጆች ሳንቀር ጫካ ገባን፡፡…”
*‹‹እና ከዚያ ግዜ ጀምሮ በረሃ ነበሩ?››
⨳‹‹አይ …ያ የተደራጀ እንቅስቃሴና ሕዝባዊ ዓላማ ያነገበ ዐመጽ አልነበረም፡፡ ወደ ትግሉ የገባሁት በ1976 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ኢህዴን/ በሚባለው ድርጅታችን ሥር፣ ከሁሉም ብሔረሰቦች የመጡ ኢትዮጵያውያንን አቅፈን እንታገል ነበር፡፡››
*“እስኪ ከታዋቂ ባለሥልጣናት ውስጥ ለዚህ አባባልዎ ማስረጃ የሚሆኑ የተወሰኑ ይጥቀሱልኝ?” ጨዋታው እየሳበኝ ሄደ፡፡
⨳አቶ አዲሱ ለገሰ (የጭሮ ተወላጅ ኦሮሞ)፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ /ሲዳማ/፣ አቶ ያሬድ ጥበቡ (ጌታቸው ጀቤሳ በሚል የበረሃ የትግል ስም ይታወቃል፤ አማራና ኦሮሞ)፣ ታምራት ላይኔ /ጉራጌ/ እና ኩማ ደመቅሳ፣ አቶ አባዱላ ገመዳና ሌሎችም ነባር የኢህዴን ታጋዮች ናቸው፡፡”
*“ክቡር አቶ አባዱላ እና አቶ ኩማ የኢህዴን አባላት ነበሩ? መቼ ነበር የተቀላቀሉት?”
⨳“እንደሚታወቀው ሻዕቢያ ማርኳቸው ለረዥም ጊዜ ቆይተዋል፡፡ ከባድ የጉልበት ሥራ እና ምሽግ ያስቆፍሯቸው ስለነበር ወደ ኢህዴን በድርድር እንዲመጡ በተደረገበት ወቅት… በነገራችን ላይ ከእኛም ይቀድማሉ… የተሻለ አድካሚ
እንቅስቃሴዎችን የመቋቋም ልምድ አዳብረው ነበር፡፡ በእርግጥ ይህ የምሽግ ቁፋሮና የጉልበት ሥራ በሌላ በኩል ወታደራዊ አቋማቸውን አደብዝዞት የላብአደር ባህሪ አላብሷቸው ነበር፡፡ አንዳንዶች ‹ኤርትሮ-ማሲ› ይሏቸው
ነበር፡፡”
*“ምን ለማለት ነው?”
⨳“ኤርትሮ-ኤርትራ ለማለት ሲሆን ‹ማሲ› ደግሞ መማስ ለማለት ነው፡፡ የኤርትራን ምሽግ መቆፈር ወይም መማስ የሚል ቀልድ ቢጤ ነው፡፡… ትግሉ የተለያዩ ስኬቶችን እያስመዘገበ ቀጠለ፡፡ በእርግጥ ውስጣዊ ችግሮችና ራስን ችሎ
የመቆም ጥያቄዎችም መነሳት ጀመሩ በኋላ…”
*“እስኪ ስለዚህ ራስን የመቻል ጥያቄ ይንገሩኝ ምን ነበር?” አልኳቸው ወደ ሌላ ነጥብ ሳይገቡብኝ፡፡
“የህወሓት የበላይነትን የማሳየትና ያላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ነበር መንስኤው፡፡ ለድርጅታችን የሚላኩ ደብዳቤዎች ሳይቀሩ በህወሓት ይጠለፉ ጀመር፡፡ 1978 ዓ.ም አጋማሽ ነው፣ ይህ ሁኔታ የኢህዴንን አመራር እንኳ ለሁለት ከፈለው፡፡ ያሬድ ጥበቡ፣ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሠ እና ዑስማን የተባሉት አመራሮች ጣልቃ ገብነቱን ሲቃወሙ፤
ታምራት ላይኔ፣ ኃይሌ ጥላሁን፣ ታደሰ ካሳ /ጥንቅሹ/ ለህወሓት ተከራከሩ፡፡ ጉዳዩ ጣልቃ ገብነት ሳይሆን ውዥንብር እንዳይከሰት ለመከላከል የተደረገ ነው አሉ፡፡ በኋላ በ1981 ዓ.ም ዳንሻ ላይ የአቅጣጫ ለውጥ የተደረገበት ስብሰባ ተጣራ፡፡ አወያዮቹ መለስ፣ ስዬ፣ ተወልደ፣ አለምሰገድና ዓባይ ነበሩ፡፡…”
“… ኢህዴንም 81 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ‹መስመር ማጥራት› የተባለውን ጉባኤ ዋግ ውስጥ በመጥራት፣ 20 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተመረጡ፡፡ ቅድም የጠቀስኩልህ አቶ ኩማ፣ አባዱላ እና ኢብራሂም መልካም የኮሜቴው አባላት ሆነው
ተመረጡ፡፡ ከጉባኤው በኋላ ክረምት ላይ ኢህአዴግ ተመሠረተ፡፡”
*“ኦህዴድ የተመሠረተው ደራ ላይ ነው የሚባለው እውነት ነው?” ለማጥራት የፈለኩት ግምት ስለነበር ያነሳሁት ጥያቄ ነው፡፡
⨳“በኢህዴን ውስጥ የነበሩትን የኦሮሞ ተወላጆች በዚያው ዓመት ክረምት ላይ አሰባስበው የመሠረቱት ትግራይ ላይ ነው፡፡ ደራ የሚባለው ወደ ኦሮሚያ ክልል ጠጋ ተብሎ ምሥረታው ይፋ የሆነበት ነው፡፡”…
ከብ/ጄ/ል ተፈራ ማሞ ጋር የነበረኝ ቃለምልልስ ሁለተኛና የመጨረሻ ክፍል ቀጥሎ ቀርባለች፡፡ትናንት ካጋራኋሁ ክፍል የተወሰኑ ነገሮች ያገኛችሁ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ የወጋችን ማጠንጠኛ ወደኋላ ሰባት ዓመታትን የሚመልሰን በመሆኑ ወቅታዊ ያለመሆኑ ይሰማኛል፡፡ ቢሆንም ብዙ ባታተርፉበትም አትከስሩበትም በሚል ሁለተኛውን ክፍል ይዤላችሁ መጥቻለሁ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን፤ አሁን የማናነሳቸው ጉዳዮች በተከሰቱ ማግስት(የሆነው ሁሉ ከሆነ በኋላ)፤ የጦሩ ገበሬ የሆኑትን ብ/ጄ/ል ተፈራ ማሞን የውሃ ክፍል ሃላፊ አድርገው ሾሟቸው የሚል ነገር ሰምቼ ስደነቅ ከርሜያለሁ፡፡ ከማሰር የማይተናነስ፤ ወይም በጥንቱ ጊዜ በግዞት ተሾመው ወደሩቅ ቦታ እንደሚላኩ፤ የማይፈለጉ(የሚፈሩ) ዓይነት ሰዎች ውስጠ ወይራ እርምጃ መሆኗ ነው፡፡ በእጅ ያለ ወርቅ እንደመዳብ ይቆጠራል የሚለውንም የሚያስታውስ ነው፡፡ የዓመቱ አስገራሚ ውሳኔ ነው፡፡
ይህ ጉዳይ እንኳ በራሱ አውድ የሚተነተንበት በመሆኑ ለጊዜው ይቆየን፡፡ አሁን ወደወጋችን እንግባ፡፡…
******//*******//******
*‹‹ዝርዝሩ ሰፊና ራሱን የቻለ መድበል የሚወጣው በመሆኑ፣ እያንዳንዱን ጉዳይ ልናነሳው አንችልም ግን ወደ አሁኑ ክሳችሁ ከመምጣታችን በፊት፣ በእርስዎ ግምገማ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መንስኤ ምን ነበር? ትርፍና ጉዳታችን /ኪሳራችን/ እንዴት ይገለፃል?›› ስላቸው የጦርነቱን ትዝታ በጨፈገገ ፊት እያስታወሱ፡-
⨳“የጦርነቱ መንስኤ በቀላል አገላለጽ እናስቀምጠው ከተባለ፣ የኢትዮጵያ ቋት እንዴት ይሟጠጥ የሚለው አላረካቸው ወይም አላጠግባቸው ስላለ ነበር፡፡ ትርፍ የሚባለው ትርፍ ከሆነ ሀገሪቱ በጥምረት ከመበዝበዝ መዳኗ ሲሆን፣ ጉዳቶቹ ደግሞ የሀገሪቱ ልጆች በገፍ ማለቃቸው፣ የባከነው ሀብትና ንብረት እንዲሁም ከዚህ ሁሉ መሥዋዕትነት በኋላ ‹ይግባኝ ላንጠይቅ› ተብሎ ለኤርትራ የተወሰነው የባድሜ ጉዳይ አሁንም ድረስ የተጠመደ ፈንጂ መሆኑ ነው፡፡ ጦርነት ውስብስብና መጥፎ በመሆኑ በመሠረቱ ትርፍ ኪሳራ የሚለው ነገር አጠያያቂ መሆኑንም ግን ያዝልኝ…”
*“አሁን ደግሞ እስኪ ለሕዝብ ብለን አስበንበት ያደረግነው እንቅስቃሴ ነው ስላሉኝ የእስራችሁ መንስኤ ይግለጹልኝ?”
⨳“እንዳልኩህ ታስቦበት የተደረገ ነው፡፡ መንስኤዎቹ ብዙዎች ናቸው ዋናው ግን ሕዝቡ ላይ የተጫነው መከራ ዕለት በዕለት እየተጨመረ፣ እየተደረበ፣ እየባሰ ወገቡን ሊቀነጥሰው የደረሰ መሆኑ ነው፡፡ በጦሩ ውስጥም ሆነ በሲቪል ተቋማት ውስጥ የለየለት የሀብት ምዝበራ፣ አስነዋሪ የብሔር ወገንተኝነትና የሀገሪቱን ቁልፍ ቦታዎች ሁሉ በዚሁ በተሳሳተ ሥሌት አስይዞ፣ ሌላውን የሕዝብ ወገን መግፋት እንዲያም ሲል ከሕግ አግባብ ውጪ ያሉ የማናለብኝ ውሳኔዎችን ማሳለፍና እርምጃ መውሰዱ ቀጠለ፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ለዛም ሆነ የዜግነት ሁለንተናዊ ክብሮች ተረጋገጡ፡፡ በተለያዩ መድረኮች ላይ ጉዳዩን አነሳነው ተከራከርን፤ ጮህን፤ ግን ነገሮች እየባሱ ሄዱ፡፡…”
*“ምን እርምጃ ለመውሰድ አሰባችሁ ታዲያ?”
⨳“የመጀመርያው ነገር ለፍትህ እና ለእውነት የሚቆሙ የጦሩን አባላት በሂደት ማሰባሰብ ነበር፡፡ ችግር ካለ ከችግር ለመላቀቅ የሚፈለግ ጥቂት ሰው እንኳ ቢሆን መሳባሰቡ መቼም ቢሆን አይቀርም፡፡ ኢህአዴግን ይህ የገባው አልመሰለኝም፡፡ በዚህ ከሁሉም ክፍሎች የተደራጀ ኃይል አዘጋጀን፡፡”
*“አሃ… ከ1997 ዓ.ም በኋላ ነው የተባለውስ?”
⨳“ይህቺ’ኳ ስላቅ ናት፤ ችግሩማ የጀመረው እንዲያውም በትግሉ ወቅት ነው፡፡ እዚህ ሲደርስ ግን መዘዙ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ይለበልበው ጀመር፡፡ ያስተማረን፣ ያሳደገን፣ ደግሞም የታገልንለትና የወጣትነት ዕድሜያችንን የሰዋንለት ሕዝብ ነው፣ ዛሬ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ደርሰናልና የራሱ ጉዳይ እንበለው? አይሆንም እንጂ፤ ስለዚህ የክርክር መድረኮቹ ሁሉ ሲከሽፉ ተገድደን የገባንበት የኃይል አማራጭ ነው፡፡”
*“ስለዚህ መንግሥት ያላቸው ነገሮች እውነት ናቸው?” የሚገደሉ ባለሥልጣናት ዝርዝር አውጥታችሁ ነበር?”
⨳በዚህ ጥያቄዬ ጄኔራሉ ያለመርካት ስሜት አሳዩ፡፡
“እየውልህ… ነገሩን እኮ በአመክንዮ ማየት ትችላለህ፡፡ ‹ስም ዝርዝር ማውጣት› የሚለው ራሱ ደካማ መከራከርያ ነው፡፡ ግባችን ግፍና አምባገነንነትን ከሕዝቡ ጫንቃ ላይ ለማውረድ፣ የዚህ ተዋናዮች የሆኑትን አመራሮችና ተቋሞቻቸውን በመቆጣጠር አስገድዶ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ማስፈን ብቻ ነው፡፡ ይህ እኮ ተራ የቂም መገዳደል አይደለም እንጂ የግድያ ዝርዝር አውጥቶ በመንቀሳቀስ፣ ይህን ዓላማ ማሳካት ይቻላል ብሎ የሚያስብ የለም”
*የመጨረሻ ጥያቄዬን አቀረብኩላቸው፡፡ “በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ዘመቻው የተከፈተበት ወገን ምላሽ ጉዳዩን በጠመንጃ አፈሙዝ መፍታት ቢያደርገውስ? መተኮስ አትጀምሩም…?”
⨳ “እንዴ… ወታደሮች እኮ ነን፡፡ ሁላችንም የተሸከምነው እሳት ነው፡፡ ግን ለነፃነት ሲባል በረሃ ገብተን መታገል፣ መጣልና መውደቅ ትክክል ከነበረ፤ አጠገባችን ያሉት ጓደኞቻችን በረሃ የከተተን ሕዝባዊ በደል ሲፈጽሙ አይሠራም የሚባለው በምን ሥሌት ነው? ለዚህ እኮ ነው ከተነጋገርንማ እውነቱ መደበቅ የለበትም ያልኩህ” አሉኝ፡፡
ከብ/ጄ/ል ተፈራ ማሞ ጋር ተጨማሪ ሰፊ ጥያቄና መልሶችን አድርገናል፡፡ ያቀረብኩት ግን በጣም የተወሰኑትን ነው፡፡ ራሳቸው አንድ ቀን በስፋት ይመለሱበታል ብዬም አምናለሁ፡፡
በተመሳሳይ ወቅት ቃለምልልስ አድርጌላቸው የነበሩትን የትግል አጋራቸውን፤
የብ/ጄ/ል አሳምነው ጽጌን አጭር የትግል ልምድና መሰል ዝክር ቃለምልልስ እናያለን፡፡…
 ከብ/ጄ/ል ተፈራ ማሞ እና ከብ/ጄ/ል አሳምነው ጽጌ ጋር በብዙ ጉዳዮች ዙርያ ሃሳቦችን ያነሳን ቢሆንም ‹‹የነፃነት ድምፆች›› በተሰኘችው የመጀመርያ መጽሐፌ ላይ ለንባብ ያበቃሁትን ብቻ ከኮሮና ጋር በተያያዘ በቤትዎ ለሚያደርጉት ቆይታ፤ ለማስታወሻ ያህል እነሆ ብያለሁ፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዤ አንድ ሁለት ነገር ብዬ እንዳልፍ ይፈቀድልኝ፡፡ ሁላችሁም እንደምታውቁት ብ/ጄ/ል አሳምነው ጽጌ አልፈዋል፡፡ በእሳቸው ህልፈት ዙርያ ስምና ፊት አልባ የፌስቡክ መንጋ በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ያሻውን ሲልና አገር ለመበተን ፎቷቸውን ፕሮፋይል ፒክቸር አድርጎ ሲራወጥ አያለሁ፡፡ የሰዎቹን ትክክለኛ ማንነት ለማረጋገጥ፤ ዕድሜ ለቴክኖሎጂ በአካውንታቸው ተገብቶ ሲፈተሸ ግን 99 በመቶዎቹ በ2001ዓ.ም ላይ እሳቸውን ለእስር ያበቃው የሕወሓት ቅጥረኞችና ሰዎቹ መቀሌ ከመሸጉ በኋላ ደግሞ ቀለብ የሚሰፍሩላቸው አማርኛ ተናጋሪ ሕወሃቶች ሆነው ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች ሚና ክልሉን አመሳቅሎ የብዙ ወንድማማቾችን ሕይወት ለጥፋት በመዳረጉ በኩል ቀላል አልነበረም፡፡
ብ/ጄ/ል አሳምነውን በእስር ቤት እያለን ‹‹አሴ!›› እያልን እንደታላቅ ወንድም አንተ ብለን እንጠራው
ነበር፡፡ በዝዋይ ጭለማ ቤት ያሉ እስረኞች ሲጋጩ እኔና እሱ ሽማግሌ ሆነን ያስታረቅናቸው ብዙ ነበሩ፡፡ ፍቅር ካለ ጸብም አለና እኔና እሱም ተኮራርፈን ያስታረቁን አሉ፡፡ ዛሬ እሱ በሕይወት ስለሌለና መልስ ሊሰጥበት ስለማይችል ወደዚያ ውስጥ አልገባም፡፡ የማልረሳለት አንድ ነገር ግን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ወሰን ውስጥ ያሉ ዜጎችን በሙሉ ያለልዩነት የመቀበል፣ ለሁሉም እኩል የመታገልና የጋራ ዕጣችንን በጋራ የመወሰን ዕምነትና ዓላማ ነበረው፡፡ ከእስር መልስ፤… የተረገመው፣ መንጋው፣ ስውር ዓላማ ያነገበው የፌስቡክ ሠራዊት አሴን እያሳሳቀ የወሰደው ይመስለኛል፡፡
እንዴት እና ለምን የሚለውን ምስጢር ብዙዎች ያውቁታል፡፡ ከሰኔ 15ቱ ክስተት በኋላ በስፍራው ሄጄ አሁንም ድረስ በልዩ ሃይሉ ውስጥ እስከ ዓመራርነት ባሉ ቦታዎች ያሉ የጋራ ወዳጆቻችንን አናግሬያለሁ፡፡ ‹‹ወይ ነዶ!›› ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ ግን ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም ሆኖ አታላዩ የፌስቡክ ሠራዊት አሁንም ያሻውን ያቦካል፡፡ ዝርዝሩ ለታሪክ ይቆንና እነአምባቸውን ያሕል አርቆ አስተዋይና እንኳን ፍቅራቸው ቁጣቸው የሚናፍቅ የሕዝብ ልጆች አጥተናል፡፡ እነ አሴንም አጥተናል፡፡ በዚህ የፈነጠዘውና ሜዳ አልበቃ ያለው ግን እነ አምባቸው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መቀሌ የከተቱት ኃይልና በመሐል አገር ቀለብ የሚሰፍሩለት ተባይ ሃይል ብቻ ነው፡፡ በተጨባጭ አንድ መነሻ ያላቸው የአማራና የኦሮሞ ልጆች አንድ ላይ በመቆማቸው ቀን የከዳት ሕወኃት አትርፋበታለች፡፡
ሙሉውን ምስጢር፤ እመኑኝ ከ2013 ዓ.ም አዲስ አመት በፊት በይፋ ታገኙታላችሁ፡፡ ዛሬ በጦሱ እነ ኮሎኔል ፋንታሁን ሙሐባ(ሕወሓት ለዘጠኝ ዓመታት አስራው በሕዝብ ትግል ወጥቶ የነበረ የሕዝብ ልጅ) በባሕርዳር ማረሚያ ቤት ይማቅቃሉ፡፡ ነገር እንዳላበዛ ወደብ/ጄ/ል አሳምነው ጽጌ ቃለምልልስ ልውሰዳችሁ፡፡
*****//******
በተንቀሳቀሱባቸው የውጊያ ቀጠናዎች ሁሉ ከአጠገባቸው ለይተዋት አያውቁም፡፡ የማደርገው ነገር ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ እንድፈትሽ ታሳስበኛለች ይሏታል፡፡ ከቅድመ አያቶቻችን እስከ ልጆቻችን ትውልድ ድረስ፣ የተለያዩ ታሪኮችን እየታዘበች የተውለበለበችው ሠንደቅ ዓላማ፤ ወደ ውጊያ የሚሄድ ተዋጊም ሆነ አዋጊ ከትጥቁ ሊለያት እንደማይገባም ይገልጻሉ፡፡ ‹ዘመቻ ፀሐይ ግባት› በድል ተጠናቅቆ፣ ባድሜ በኢትዮጵያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ስትውል፣ የደም አበላ ጎርፍ በወረደባት ባድሜ ላይ ተሰቅላ ስትውለበለብ በሚዲያ የተመለከትናት ሠንደቅ ዓላማ የእርሳቸው ነበረች፡፡ ጄ/ል አበበ እና ጄ/ል ጻድቃንም በዕለቱ አብረዋቸው ነበሩ፡፡
***ብ/ጄ/ል አሳምነው ወደ በረሃው ትግል የገቡት፣ በ1980 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ የተቀላቀሉትም ‹አዋሽ› ተብሎ የሚታወቀውን የኢህዴንን ክፍለ ጦር ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ወታደራዊ ክፍሎች ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ ዩ.ኤ.አርሚ. ዋር ኮሌጅ› በመግባት፣ በወቅቱ ብቸኛው ከኢትዮጵያ የሄዱ ሠልጣኝ የመሆን ዕድሉን ሲያገኙ፣ ይህ የዘመናዊውን ዓለም የጦር ሠራዊት አደረጃጀትና ዘመናዊ የውጊያ ሳይንስ ጥበብ እንዲቀስሙ አስቸሏቸዋል፡፡
በሀገር ውስጥ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኮማንድነት፣ የባህር ዳር ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ኃላፊ፣ በውጊያው ወቅት ደግሞ የ22ኛ ክፍለጦር የግንባሩ የአስተዳደር መኮንን እና በሌሎችም ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ከመቆየታቸው አንጻር፣ ይህን ሁሉ በግለሰብ ደረጃ ሲታይ ልዩ ዕድልና ምቾት እርግፍ አድርጎ ሕይወት ሊያሳጣ ወደሚችል አደገኛ ህቡዕ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዴት ሊገቡ ቻሉ? ሂደቱ ምን ይመስል ነበር? ዕቅዱ ከሽፎ
የእንቅስቃሴው ተዋነያን በአብዛኛው እንዴት በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ቻሉ? የሚሉትና በመሰል ጥያቄዎች ዙሪያ፣ ሐሳባቸውን ሊያካፍሉኝ ፈቃደኛ በመሆናቸው፣ በድብቅ ማስታዎሻዎቼ ላይ አጫጭር ነጥቦችን ለማሥፈር ችዬ ነበር፡፡
ከጄኔራሉ ጋር ያደርኩት ቆይታ ቀደም ባለ ምዕራፍ ውስጥ የተነሱትን ነጥቦች የሚያጠቃልል፣ ከጄ/ል ተፈራ ሐሳቦች ጋር ተመሳሳይ የሆኑትን በመዝለል፣ ለየት ካለ አቅጣጫ የተነሱ የመሰሉኝን ብቻ ቀጥሎ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ፡፡ ለእርሳቸውም ይህንኑ ከገለጽኩላቸው በኋላ፡-
*“የእንቅስቃሴያችሁ አንዱ ሥልት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ‹መቆጣጠር› እንደነበር ገልጸውልኛል፡፡ በዚህ መንገድ አንድን ሥርዓተ መንግሥት መቀየር የሚቻልበት እውነታ ምንድነው?” የሚል ጥያቄዬን አቀረብኩ፡፡
⨳“በሌሎች ሀገሮች ቢሆን መሪዎች ላይ ያነጣጠረ ዒላማ፣ መንግሥትን ቀይሮ የዴሞክራሲን መንገድ
አያደላድልም፡፡ ይህ የማይሆነው ግን ሀገራቱ በዴሞክራሲ ያደጉና የዘረጉት ሥርዓተ መሰንግሥትም በግለሰቦች ዙሪያ
ያልተዋቀረ ከሆነ ነው፡፡ በነፃ ሕዝባዊ ምርጫ ያለምንም አስገዳጅና አሰቃቂ ሂደት የሚመረጥ መንግሥት መሪ ቢሄድ ይመጣልና መጀመርያውኑ የዚያ ዓይነቱ ነገር አይታሰብም፡፡ ወደ አምባገነናዊ ሥርዓት ስንመጣ ግን የአንድ ቡድን ስብስብ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዕጣ ፈንታ በእጆቹ ጨምድዶ ስለሚይዝ፣ ያንን ስትመታው ሕዝቡን ከመከራው ትፈታዋለህ፡፡ ስለዚህ ዴሞክራሲያዊና ሁሉን አሳታፊ ሲስተም በየተቋማቱ ውስጥ መስፈን ስላልቻለ፣ በተደጋጋሚ ሞክረንም ሰሚ ስላጣን እንቅስቀሴውን ጀመርነው፡፡…”
*“ያደራጃችሁት ቡድን እንደ ድርጅት ደንብና መመሪያዎችን አውጥቶ ነበር? በውጭ ከሚገኙት ከግንቦት 7 አመራሮች ጋር ተገናኝታችኋል የተባለውስ እውነት ነው?”
⨳“እንደሚታወቀው እንቅስቃሴው ህቡዕ ስለሆነ ማኒፌስቶ አዘጋጅተን ልንበትን አንችልም፡፡ ግን በእንቅስቃሴው ውስጥ የነበርነው አብዛኛዎቻችን በአደረጃጀትም ሆነ በምሥጢራዊ የድርጊት አተገባበሮች ልምድ ስለነበረን በዚያ በኩል ችግር አልነበረም፡፡ ሁላችንንም በጋራ ያሠለፈን ኢ-ፍትሓዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ አሠራር ነው፡፡ ያንን ለመቀልበስ ነው ስንሠራ የነበረው፡፡ የተመሠረተው ድርጅት ‹የኢትዮጵያ ነፃነትና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች› የሚል ሲሆን፣ ውጪ ካሉት ጋር ለተባለው በእንቅስቃሴው ውስጥ ኢትዮጵያዊ የሆኑና ለኢትዮጵያ ነፃነት የሚሠሩ ወዳጆቻችንን ሁሉ
አሳትፈናል፡፡”
“በይፋ በሚታወቁ ትልልቅ የውይይት መድረኮች ላይ ጥያቄዎቹ ተነስተዋል፡፡ እዚህ የምታየው ሁሉ…” አብረዋቸው የታሰሩትን አባሪዎቻቸውን በዓይኖቻቸው እያሳዩኝ
⨳“… በእነዚያ መድረኮች ላይ ድምፃቸውን ያሰሙ ነበር እንዲያውም እንድንናበብና በጋራ እንድንሰበሰብ ያስቻለንም ይኸው ነው፡፡ ከዚያ በተረፈ እኔ ለጠ/ሚ/ር መለስ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ በዝርዝር ጽፌ /በግልባጭ ለደኅንነት ሚኒስትሩና ለቅርብ አለቃዬ ለጄ/ል ሳሞራ አሳውቄያለሁ፡፡ ሁኔታው አደገኛ እየሆነ ስለሄደ አጠቃላይ መድረክ ይከፈት፣ መፍትሔም ይሰጥበት ብያለሁ፡፡ በጦሩ ውስጥ ያለው ሁኔታም ሌላው በአግባቡ መፈተሽ የነበረበት ጉዳይ ነበር፡፡”…
ከብ/ጄ/ል አሳምነው ጋር ይህን ውይይት በምናደርግበት ወቅት ደግሞ፣ የኢህአዴግ አመራሮች የደቡብ ሱዳን የሁለት ወገን ተቆራቋሾችን ሊሸመግሉ ላይ ታች የሚሉበት በመሆኑ ተደምመን እንከታተለው ነበር፡፡ የኢህአዴግ አመራሮች በሌሎች ሀገራት የተደረገውን መፈንቅለ መንግሥት “መፈታት ያለበት በፖለቲካዊ መንገድ ብቻ ነው” ብለው ሲሞግቱ፣ በእዚያ ያለፈውን በሺዎች የሚቆጠር የሕይወት እልፈትና ምስቅልቅል ጠፍቷቸው አይመስልም፡፡ ትክክለኛው መድኃኒት ምን እንደሆነ ስለሚያውቁት እንጂ፡፡ ይህን መድኃኒት ግን በሀገራቸው ላይ ስላልተገበሩት አብረዋቸው የዕድሜያቸውን ከግማሽ በላይ ያሳለፉትን የትግል አጋሮቻቸውን ማስታወስ አላስፈለጋቸውም፡፡ ኢትዮጵያን የሚያስር መሪ እንጂ የሚያሽር መድኃኒት እንደማያስፈልጋት የደመደሙ ይመስላሉ፡፡ 2005 ዓ.ም ነበር …