በከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም የመጀመሪያዎቹ ተጠቃሚዎች የሶስት ወር ቅድሚያ ክፍያ እንዲከፈላቸው ተወሰነ

(ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴራል የከተሞቸ ልማታዊ ሴፍቲ ኔት ፕሮጀክት ስቲሪንግ ኮሚቴ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጋር በተያያዘ በዝቅተኛ ደረጃ ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ውሳኔዎችን አሳለፈ፡፡

ኮሚቴው ባካሄደው ስብሰባ ከከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ተጠቀሚዎችና ተጋላጭ የሆኑ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ የሚያጋጥማቸውን ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች አፋጣኝ የሚፈቱበትን ምላሽ ለመስጠት እንዲያስችል ውሳኔ አሳልፏል።

የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ስቲሪንግ ኮሚቴ ሰብሳቢና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ እንደገለፁት የኮሮና ወረርሽኝ በሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተነሳ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረጉ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሰረት በፕሮግራሙ በታቀፉት 11 ከተሞች የሚገኙና በአካባቢ ልማቶች የተሰማሩት የመጀመሪያዎቹ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች የራሳቸውን ኑሮ ለመምራት የሚያስችሉ ደረጃዎች ላይ ቢገኙም ወረርሽኙ በሚያስከትለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳይጎዱ በማሰብ ስራቸውን ሳይሰሩ የሶስት ወራት ቅድመ ክፍያ እንዲከፈላቸው የሚያስችል ወሳኔ ተሰጥቷል፡፡

በከተሞች በምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ ከታቀፉት በተጨማሪ በፕሮግራሙ ያልተካተቱትና ዝቅተኛ ኑሮን የሚገፉ ዜጎችም ለዚህ ወረርሽኝ ተጋላጭና ተጎጂ የሚሆኑበት ሁኔታ ከፍተኛ በመሆኑ በፕሮግራሙ በመታቀፍ የሶስት ወር ቅድሚያ ክፍያ እንዲከፈላቸውም ስቲሪንግ ኮሚቴው ወስኗል፡፡

እንዲሁም በየምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ከሚያገኙት ገቢ በቁጠባ ተቀማጭ ካደረጉት ገንዘብ 50 በመቶውን ያህል በማውጣት ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸውን የኑሮ ጫና ለመደጎም እንዲጠቀሙበት መወሰኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በከተሞች የጎዳና ተዳዳሪዎች በወረርሽኑ ተጠቂ እንዳይሆኑ ከዚህ በፊት በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰሩ ለነበሩ ስራዎች የታሰቡ ሃብቶችን ከወረርሽኑ ጋር በተያያዘ ከተሞች ሊሰሩ ላሰቧቸው ተግባራት እንዲያውሉ ውሳኔ ተላልፏል መባሉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ይህም ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ለወረርሽኙ ይበልጥ ተጋላጭና ተጎጂ ሊሆኑ በሚችሉ 16 ከተሞች የሚኖሩና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችም የሶስት ወር ክፍያ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ውሳኔ መወሰኑም ተጠቁማል።