የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በግማሽ መቀነስ አለበት – ጌታቸው አስፋው (የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ለቀጣይነቱ፣ ለሰላምና ለማኅበራዊ መረጋጋት እንዲሁም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሲባል፣ እስካሁን ከሚያስመዘግባቸው የዐሥርና ዐሥራ አንድ በመቶ ዕድገት መጣኞች በግማሽ ቀንሶ ለተወሰኑ ዓመታት ወደ አምስትና ስድስት በመቶ የዕድገት መጣኞች ዝቅ ማለት አለበት፡፡

የአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ይቀንስ ሲባል ያማል ነገር ግን ታሞ ከስቃይ መዳን የሚቻል ከሆነ፣ እየተሰቃዩ ለረጅም ጊዜ ከመኖር ለጥቂት ጊዜ ታሞ መዳን ይሻላል፡፡ እየተራብን እየታረዝን መጠለያ አጥተን የፍጆታችን መጠን ከዓለም የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ በዕድገት ከዓለም አንደኛ ነን ብለን መፎከር፣ ሥቃያችንን አምቀን ይዘን በዕድገታችን ከእኛ የሚስተካከል አገር የለም ማለት አላዋጣንም፡፡

በሁለት አሃዝ ማደጋችንን ለዓለም ሕዝብ ለማውራት ፈልገን በዓለም ዐቀፍ ድርጅቶችና ለአንድ ቀን በጎበኘን ፈረንጅ የምናስመሰክረው የጉራ ወሬ ማኅበራዊ መሠረታችንን አናጋው ሰላማችንን አደፈረሰው፡፡

ማንኛውም ነገር የዕጦት ወጪ (Opportunity Cost) አለው፤ ለመዋዕለንዋይ በወጣ ወጪ ብዙዎች ፍጆታ ቀርቶብናል፡፡ በተሠሩት ሕንጻዎች ልክ በተዘረጉት መንገዶች ልክ በተከፈቱት ዩኒቨርሲቲዎች ልክ ዜጎቻችን ተርበዋል፣ ታርዘዋል፣ መጠለያ አልባ ሆነዋል፤ ተሰደዋል፤ በበረሃ በባሕርና በወንበዴዎች እጅ ሞተዋልም፡፡ የሚታዩትን ሕንጻዎች፣ መንገዶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ እየቆጠርን የማይታዩትን የተራቡ አንጀቶች፣ የታረዙ ገላዎች፣ መጠለያ ያጡ ነፍሶች፣ በኑሮ ሁኔታ የተሰደዱና እስከዘላለሙ ያሸለቡ ወጣቶቻች ሕይወት ሳንቆጥር በዕድገታችን እንኩራራለን፡፡

የብራችን ሸቀጥን የመግዛት አቅሙ እና ከውጭ አገሮች ምንዛሪዎች ጋር የመመነዛዘሪያ አቅሙ ቁልቁል ወርዶ ወጣቶች በአገር ውስጥ ሠርቶ ከመኖር በውጭ አገር ሰርቶ መኖር በብር ተመንዝሮ የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አስልተው በበረሃና በባህር እየሞቱም ወደ ውጭ ለመኮብለል ልባቸው እስከሚሸፍት ድረስ የአገር ውስጥ ግብይይታችን ዝቅተኛ ሆኖ ተመሰቃቅሏል፡፡

የዩኒቨርሲቲዎች ብዛት እየቆጠርን የምናስተምራቸው ወጣቶች ተመራምረው አገር የሚያሳድጉ ሳይሆኑ ለባዕዳን ሎሌ ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸውን እንዳናይ ዐይናችን ተጋርዷል ልባችን ደንድኗል፡፡ አንዱ የሚበላው አጥቶ ጦሙን ያድራል ሌላው አጠገቡ በሊሞዚን ጋብቻ ይፈጽማል፡፡ ይህ ሁሉ የዐሥርና ዐሥራ አንድ በመቶ እድገቶች ያመጡት ጣጣ ነው፡፡ በእርግጥ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ይቀንስ ማለት ዝም ብሎ በስሜት የሚናገሩት ነገር አይደለም በቂ ትንታኔና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በምን ያህል ይቀንስ የሚለውም የብሔራዊ ኢኮኖሚ ተንታኞችን፣ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንታኞችን የዕድገት ሞዴሎች ባለሙያዎችን እና የሌሎችንም ብርቱ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ በባለሙያዎች ተጠንቶ ዕድገቱ ከግማሽ በታች ሊሆንም ይችላል፡፡ ጥናቱን የማጥናቱን እና የማስጠናቱን ጉዳይ ለምሁራንና ለመንግሥት ትቼ እኔ በበኩሌ ዕድገቱ መቀነስ አለበት የምልበትን አንዳንድ አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

አንደኛ፡- የሁለት ቢልዮን ዶላር የኤክስፖርት ሸቀጥ ሽጠን የዐሥራ ስድስት ቢልዮን ዶላር የኢምፖርት ሸቀጥ በመግዛት በየዓመቱ ዐሥራ አራት ቢልዮን ዶላር የሚደርስ የኤክስፖርትና ኢምፖርት ጉድለት ፈጥረናል፡፡ ጉድለቱን ለመሙላት ከተሰደዱ ልጆቻችን እና ከውጭ መንግሥታት የሚላክልን የእርዳታ ዶላርም ተጨምሮ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሂሳባችን የሰባትና የስምንት ቢልዮን ዶላር ጉድለት ያሳያል፡፡ ይህን ጉድለት የምንሸፍነው ከውጭ በመበደር የውጭ ኢንቬስተሮች እንዲመጡ በመለመን የካፒታል ሂሳብ እና ካለችው የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ ላይ በመቀነስ ነው፡፡

ኤክስፖርትን በማበረታታት፣ ጉድለቱን ለማስወገድ የተደረጉት ሙከራዎች ስኬታማ አልሆኑም፤ የውጭ እርዳታውም ቀንሷል፤ በተበደርነው ልክ ክፍያ ስላልፈጸምንም አዲስ ብድር ማግኘት ተስኖናል፤ የውጭ ኢንቬስተሮች መምጣትም እየተንገዳገደ ነው፡፡ ስለዚህም ኢኮኖሚያችንን የምናስተካክልበት ሌላ ዘዴ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡

በብሔራዊ ኢኮኖሚ ስሌት መሠረት በውጭ ኢኮኖሚ የተንቀሳቃሽ ሂሳብ ጉድለትና በአገር ውሰጥ ኢኮኖሚ የቁጠባና መዋዕለንዋይ ጉድለት እኩል ስለሆኑ፣ የአንዱን ጉድለት በሌላው በማጣፋት ማስተካከል ይቻላል፡፡ በአገር ውስጥ ቁጠባና መዋዕለንዋይ ሲመጣጠኑ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሂሳብ ጉድለት ይወገዳል፡፡ ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ የሆነው መዋዕለንዋይ በቁጠባ ልክ እንዲሆን መቀነስ ካለበት ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሲባል የኢኮኖሚው እድገት ቀንሶ የውስጡና የውጩ ኢኮኖሚ መስተካከል አለባቸው፡፡

በአገራዊ የፍጆታና የመዋዕለንዋይ ድምር የሸመታ ወጪ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መካከል ባለው ልዩነት ልክ በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የተንቀሳቃሽ ሂሳብ ጉድለትም ስለሚኖር አገራዊ የሸመታ ወጪውን በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ልክ በማድረግ በውስጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሂሳብ ጉድለቱን ማረምም ይቻላል፡፡

ኹለተኛ፡- ምርታማነት ሳያድግ የአንዳንድ ሰዎች ደሞዝ በዐሥር ዓመት ውስጥ ከአምስት ሺሕ ተነስቶ ሰላሳ እጥፍ በማደግ መቶ ሐምሳ ሺሕ ደረሰ፤ ከዚህ በታች የሚያገኙትም ቢሆኑ ከምርታማነታቸው ጋር የሚመጣጠን አይደለም፡፡ እያንዳንዳችን ምን ሰርተን ምን አገኘን ብለን ብንጠይቅ ራሳችንን በራሳችን ሳንታዘብ አንቀርም፡፡

ሕንጻ ላይ የፈሰሰ ካፒታል ለባለቤቱ በሚልዮኖች የሚቆጠር የወር ገቢ ቢያስገባም ለአገር ግን ምርታማነቱ ዝቅተኛ ነው፣ የንግድ ትርፍ ለነጋዴው ከመቶ በመቶ በላይ ገቢ ቢያስገኝም በምርታማነት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ የብዙዎቻችን ምርታማነት ከሸሚዛችን በላይ ያጠለቅነው ከራቫታችንን እንኳ አያክልም ገቢያችን ግን በወርቅ አምባርና ሀብል አጥለቅልቆናል፡፡

ከሦስት ዓመት በፊት ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን በሚል ባሳተምኩት መጽሐፍ ውስጥ እንደ መፈክር የደጋገምኩት፣ “ከምርታማነታችን በላይ በምናገኘው የግለሰብ ገቢ ልክ አገሪቱን እያከሰርን የመጪውን ትውልድ ተስፋም እያጨለምን ነው፤” ስንኝ ዛሬም ድረስ ትክክል ሆኖ ነገም ለከርሞም ትክክል ሆኖ ይቀጥላል፡፡

የግለሰብ ገቢ ከምርታማነት በላይ መሆን በሸቀጦች ዋጋ ማሻቀብም እየታየ ስለሆነ በዋጋ አወሳሰን ሥርዓት አምራቹ ብቻ ሳይሆን ሸማቹም ዋጋ የመወሰን አቅም እንዲኖረው በዋጋ አወሳሰን አቅርቦትና ፍላጎት እኩል ሚና እንዲኖራቸው ከምርታማነት በላይ ያደገው የግለሰብ ገቢ መቀነስ ስላለበት ለዚህ ሲባል የኢኮኖሚው እድገት መገታት አለበት፡፡

ሦስተኛ፡- ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ለመቀነስ ያለልፋትና ለሌሎች ጥቅም የሚሰጥ አገልግሎት ሳይሰጡ በሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ኪራይ (Economic Rent) ጥቂቶች ከበሩ ብዙዎች ደኸዩ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ኪራይ ማለት ለሌላው የሚጠቅም ሥራ ሳይሰሩ ሳይለፉ የሚያገኙት ገቢ ማለት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ኪራይ የሚፈጠረው ሰዎች የአገሪቱን ሀብት አተልቀው ከትልቁ ለየአንዳንዱ የሚገኘውን ጥቅም አብዝቶ ለመከፋፈል ከመሞከር ይልቅ ካለው የአገሪቱ ሀብት ውስጥ የራሳቸውን ድርሻ ለማተለቅ ሲጥሩ ነው፡፡

የዐሥርና ዐሥራ አንድ በመቶው ዕድገት በሰፊው ሕዝብ ጥረት ድካምና ላብ የተፈጠረ ተጨማሪ እሴት ቢሆንም፣ በኢኮኖሚያዊ ኪራይ መልክ ጥቂቶች የሚሰበስቡት ስለሆነ፣ ዕድገቱ ቢቀንስ ሰፊው ሕዝብ አይጎዳም፤ የጥቂቶቹ ኢኮኖሚያዊ ኪራይ ገቢ ነው የሚቀንሰው፡፡

አራተኛ፡- የካፒታል ክምችት መዛባትን ለመቀነስ፡፡ በመሠረቱ በኢኮኖሚ ጥናት የተረጋገጠው ሐቅ፣ ድሃ ገቢውን ለፍጆታ ያውላል ሀብታም ግን ቆጥቦ መዋዕለንዋይ ያፈሳል የሚል ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ግን ድሃው በ“ባጃጅ ትሸለማለህ” እየተማለለም እንዲቆጥብ ይደረጋል እንጂ ሀብታም አይቆጥብም፡፡ ሀብታም የድሃውን ቁጠባ ወስዶ ፎቅ ቤት ይሠራበታል፡፡ በአኢስ አበባ የተገነቡት ሕንጻዎች ሁሉ የተሠሩት ከድሀው አንጀቱን አስሮ በተገኘ ቁጠባ ነው፡፡

ለገጠሩ ቆጣቢዎች በሚከፈለው ከዋጋ ንረት ያነሰ የቁጠባ ወለድ መጣኝ ምክንያት ንብረቱ በየጊዜው ስለሚቀንስ፣ የገጠሩ ሀብት ተሟጦ ወደ ከተማ ሸሽቶ በሕንጻ ግንባታ ላይ ስለፈሰሰ ለገጠሪቱ ኢትዮጵያ እድገት መሠረት የሚሆን የካፒታል ክምችትም በገጠር አልተፈጠረም፡፡ ግብርናው ሳያድግ ኢንዱስትሪው ስለማያድግም ገበሬው በቁጠባው እንዳይከስርና የገበሬው ገቢ እንዲጨምር የቁጠባ ወለድ መጣኝ ቢያንስ ከዋጋ ንረት በላይ መሆን አለበት፡፡ የቁጠባ ወለድ መጣኙ መስተካከል መዋዕለንዋይን ስለሚገታ የከተማው ሕንጻ ግንባታ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መቀነሱ አይቀርም፡፡

አምስተኛ፡- የዋጋ ንረትን ለመግታት፣ የዋጋ ንረት ማለት መንግሥት በየአንዳንዳችን ኪስ ውስጥ ብዙ ጥሬ ገንዘብ አስቀምጧል ማለት ነው፡፡ ብዙ ብሮች ጥቂት ሸቀጦችን ያሳድዳሉ ማለት ነው፡፡ በደርግ መውደቂያ ዓመታት ነጠላ አሃዝ ቢልዮን ቁጥር የነበረው የጥሬ ገንዘብ መጠን ዛሬ አምስት መቶ ቢልዮን ደርሷል፡፡ ጥሬ ገንዘቡ እንዲበዛ የሚያደርጉት ብሔራዊ ባንኩ በሚያሰራጨው ምንዛሪዎች (ብርና ሣንቲሞች) እና ንግድ ባንኮች ብሮቹን አርብተው ስለሚያበድሩ ነው፡፡

ለኢኮኖሚው የሁለት አሃዝ ዕድገት ሲባል፣ መንግሥት የበጀት ጉድለት ውስጥ መግባቱ የፊስካል ፖሊሲ እና ኢኮኖሚውን ለማስፋፋት በገበያው ውስጥ የተሰራጨው የጥሬ ገንዘብ ብዛት አስፋፊ ሞኒተሪ ፖሊሲ የሥራ አጥነትን ችግር ሳያስወግዱ በዋጋ ንረት ላይ ብቻ ተጽዕኖ የፈጠሩና በመፍጠር ላይ ያሉም በመሆናቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ አስከትለዋል፡፡ ለ2011 በጀት ዓመት የቀረበው ሐምሳ ቢልዮን ብር የበጀት ጉድለት ያለበት ሦስት መቶ አርባስድስት ቢልዮን ብር የመንግሥት በጀት የቁጠባና መዋዕለንዋይ ክፍተትን ብሎም የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሂሳብን ጉድለት ከማስፋት ምርታማ ባልሆነ ሥራ የግለሰቦችን ገቢ ከማሳደግ፣ ኢኮኖሚያዊ ኪራይን ከመፍጠር፣ አልፎ ተርፎ በእርግጠኛ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ዕድገት አይኖርም፡፡

ለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲባል በዓመት በአማካይ በሃያ ስምንት በመቶ የሚያድገው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትም የዋጋ ንረትን ፈጥሮ የሀብት ክፍፍሉን ከድሃው ወደ ሀብታሙ አሸጋገረ እንጂ ለሕዝብ የሚጠቅም የኢኮኖሚ ዕድገት አላመጣም፡፡

ስለዚህም መንግሥት ከሁለቱ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ስም ሕዝብን የሚጎዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚመስሉ ግን ያልሆኑ ድርጊቶች እንዲቆጠብ የኢኮኖሚ ምሁራን ምክራቸውን ሊለግሱት ይገባል፡፡

ስድስተኛ፡- መንግሥት መር ልማታዊ ኢኮኖሚ ማለት የግድ ደርጅቶች የመንግሥት ይዞታ ይሆናሉ ማለት ሳይሆን፣ ማምረቻ ሀብት በግል ይዞታም ይሁን በመንግሥት የኢንዱስትሪ ዕድገቱን፣ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓቱን እና የሀብት ድልድሉን ለገበያው ከመተው፣ በዕቅድ ጣልቃ በመግባት በቅድሚያ ሊያድግ የሚገባውን ኢንዱስትሪ መርጦ ፖሊሲውን ስትራቴጂውን እና ዕቅዱን ለዚያ ተግባር ያውላል ማለት ነው፡፡ ይህን የልማታዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ከሀብት ይዞታ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ከሀብት ይዞታ ጋር የሚገናኝ ቢሆን ኖሮ ሶሻሊስታዊ ወይም ካፒታሊስታዊ ወይም ከፊል ካፒታሊስታዊና ከፊል ሶሻሊስታዊ የኢኮኖሚ አስተዳደር ይባል ነበር፡፡

በመንግሥት ይዞታ ሥር መሆን የሚገባቸው ድርጅቶች ከልማታዊ መንግሥትነት ውጪ የሆነ ታሪካዊ አመጣጥ አላቸው ከዚህም ውስጥ አንዱ ገበያው ለኅብረተሰቡ ሊያቀርባቸው የማይችላቸው ወይም ቢችልም ኅብረተሰቡን በዋጋ አወሳሰን ሊበዘብዝባቸው የሚችሉ ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡ በቅርቡ በመንግሥት ለግል ባለሀብት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲሸጡ ከተወሰኑት ድርጅቶችም ከፊሎቹ በገበያ መር ኢኮኖሚ ቢተዳደሩ የሚመረጥና ከፊሎቹ መንግስት መር ሆነው በዕቅድ ቢተዳደሩ የሚመረጡ ሊሆኑ ይችላሉ የቱ በየትኛው የሚለው በእያንዳንዱ ላይ ጥልቅ ጥናት ተደርጎ የሚወሰን ነው፡፡

ከዚህ አለፍ ሲልም፣ ኢኮኖሚያዊ አስተዳደርም ከጊዜው ጋር ስለሚለዋወጥ በዚህ ዘመን በብዙ ልማታዊና ገበያ መር አገራት የሚታመንበት የኢኮኖሚ አስተዳደር መንግስትም ሆነ የግል ባለሀብት በተናጠል በግላቸው የኅብረተሰብን ፍላጎት ማርካት ስለማይችሉ በሽርክና ሊሰሩባቸው የሚችሉ በርካታ መሠረተልማቶች እንዳሉ የታመነበት ጊዜ ነው፡፡

በአየር ምንገዱ የሚጓጓዘው ሀብታሙ የኅብረተሰብ ክፍል ነው፣ መብራት በዝቅተኛ ዋጋ ሊቀርብ የሚገባው ግን ለድሀው ኅብረተሰብ ነው፡፡ በይዞታ አስተዳደር ወግ ሳይሆን በልማታዊ መንግስት የኢንዱስትሪ እድገት ዕቅድ ተኮር ወይስ ገበያ ተኮር ምርጫ ከአምራቹ አንጻር ብቻ ሳይሆን የዋጋ አወሳሰን ሥርዓትን እና ተደራሽነትን ማዕከል አድርገው ከሸማቹ አንጻር ሊታይም ይገባል፡፡

ሆኖም ግን መንግሥት ጥልቅ ጥናት ሳይደረግ፣ የውጭ ምንዛሪ ስለቸገረው ብቻ ይህንን እርምጃ ወስዶ ከሆነና ዋናው ምክንያትም የኢኮኖሚውን የሁለት አሃዝ ዕድገት ለማስቀጠል የተደረገ መንገታገት ከሆነ፣ በዚህ ጊዜያዊ እርምጃ ብቻ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በዘላቂነት መፍታት ስለማይቻል ስህተት ነው፡፡ የውጭ ኢኮኖሚ ጉድለትን በውስጥ ኢኮኖሚ ማስተካከያ ማረም ብቻ ነው ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው፡፡

ሰባተኛ፡- ከኢኮኖሚው የሁለት አሃዝ ዕድገት በላይ ሊያስጨንቁን የሚችሉ በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውብናል፡፡ ኢኮኖሚያችን የሚፈጥረው ማኅበራዊ ቀውስ አድጎ ሳይበታትነን በፊት ጊዜ መሻማት አለብን፡፡

ኢኮኖሚውን ለማስተካከል በኢኮኖሚስቶች ተጠንተው የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ሊያስተካክላቸው ይችላል የሚባሉት የገበያ ኢኮኖሚው እንዲሠራ ነጻ በማድረግ፣ የገበያ ኢኮኖሚ ጉድለት አለበት በተባለበት ቦታም የሸማቹን አቅም በሚገነቡ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲና የአምራቹን አቅም በሚገነቡ የግል አምራች ድርጅቶች ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለአገር እድገት ይጠቅማሉ የሚባሉ በሌሎች አገራት ተግባራዊ የተደረጉ ሥር ነቀል እርምጃዎች ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተገናዝበው መወሰድ አለባቸው፡፡

ለምሳሌም ዝቅተኛውን የሠራተኛ ክፍያ ደሞዝ ወለል በሕግ መወሰን፣ የትርፍ ህዳግን በሕግ መወሰን ቁሳዊ ሀብት በማያፈራና ለባለቤቱ ብቻ የትርፍ ገቢ በሚያመጣ፣ እንደ ሕንጻ በመሳሰለ ሀብት ላይ አዳጊ የሀብት ግብር (Progressive Property Taxation) እና አዳጊ የአከራይ ተከራይ ግብር መጣል የመሳሰሉት እርምጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

እነኚህ የሀብት ሥርጭት ፍትሐዊነትን የሚያሰፍኑ ፖሊሲዎች ሲቀረጹ የኢኮኖሚውን ዕድገት እንደሚቀንሱት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡