ብሔራዊ የልማት ኢኮኖሚ ዕቅዶች (ጌታቸው አስፋው)

ብሔራዊ የልማት ኢኮኖሚ ዕቅዶች
*****
ጌታቸው አስፋው – ሲራራ
*****
ትልቁ የአገራችን ችግር የዕቅድ አለመኖር ወይም በዕቅድ ያለመመራት ችግር ነው፡፡ ከዚያ በላይ የከፋው ደግሞ ዕቅዶች ቢኖሩም አሳታፊ ባለመሆናቸው የወረቀት ላይ ጌጥ ሆነው መቅረታቸው ነው፡፡ የልማት ዕቅዶች አሳታፊ መሆን ይገባቸዋል፡፡ አሳታፊ ብሔራዊ የልማት ኢኮኖሚ ዕቅድ ልክ እንደ የግል አሳታፊ የልማት ኢኮኖሚ ዕቅድ ከባለሙያው በተጨማሪ ተጠቃሚዎችና ባለድርሻ አካላት ሐሳብ በመስጠትም ሆነ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሚሳተፉበት ነው፡፡
የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የዕቅዱን ማዕቀፍ፣ ጠቋሚ አመልካቾችና፣ የሀብት ክፍፍል በጀት ጣሪያ ደልድሎ ክፍላተ ኢኮኖሚዎችና በስሮቻቸው ያሉ መሥሪያ ቤቶች በተሰጣቸው ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው የየራሳቸውን ዕቅድ አዘጋጅተው የሚልኩበትና የዕቅድ መሥሪያ ቤቱ ከአስፈጻሚ ክፍላተ ኢኮኖሚዎች ጋር በመመካከር የሁሉንም በአንድ ላይ አቀናጅቶ ለመንግሥት አቅርቦ የሚያስፀድቅበት የዕቅድ ሂደት ነው፡፡ ይህ ለይስሙላም ቢሆን ኢትዮጵያ አሁን የምትጠቀምበት የዕቅድ ዓይነት ነው፡፡ ይህን ዓይነት አሳታፊ ዕቅድ የምትጠቀም ይምሰል እንጂ ዕቅዱን በራሳቸው ፍላጎት የሚመሩት ጥቂት የፖለቲካ ሰዎች ናቸው፡፡ ባለሙያው የጽሕፈት አገልግሎት ብቻ ነው የሚሰጠው፡፡
በአሳታፊ ዕቅድም ቢሆን የዕቅድ ባለሙያ ክህሎቱን ተጠቅሞ እንደ ሾፌር ሆኖ ሌሎችን አስተባብሮ በኅብረት ይሠራል እንጂ ሙያን አግልሎ በዘፈቀደ አይታቀድም፡፡ ኢትዮጵያ ግን በዕቅድ አዘገጃጀት አደረጃጀትም ሆነ ያለፉት ዓመታት ተሞክሮዎችዋ እንኳንስ በዕቅድ ባለሙያ ክህሎት ልትጠቀም ይቅርና የዕቅድ ባለሙያዎች እንዳሏት እንኳ አታውቅም፡፡ በዋናው የዕቅድ አዘጋጅ ባለሥልጣን የፕላን ኮሚሽን እንኳ በልዩ ልዩ የኢኮኖሚክስ ሙያ ክህሎት ያላቸውን እንደ የዕቅድ ባለሙያ አድርገው ይቆጥራሉ እንጂ የኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ የለም፡፡
በሥርዓተ ማኅበርና በኢኮኖሚ አስተዳደር መንግሥታዊ ቅርጽ ዓይነት ላይ ተመርኩዞ ዕቅድ በሁለት ዐበይት ዓይነቶች በሶሻሊዝም ሥርዓተ ኢኮኖሚ የእዝ ማዕከላዊ ዕቅድ እና መንግሥት ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ትንበያ ተነስቶ የራሱን ገቢዎችና ወጪዎች በመገመት ለግሉ ዘርፍ የፖሊሲ መረጃ ሰጥቶ ዕቅዱን በመረጃው መሠረት እንዲያስተካክል የሚጠቁምበት መንገድ የካፒታሊዝም ሥርዓት ጠቋሚ ዕቅድ ይባላሉ፡፡
የሶሻሊዝም ዕቅድ በዕዝ ሰንሰለት በማዕከል ደረጃ ምን ያህል እንደሚመረትና እንዴት እንደሚመረት በቁጥር ተገልጾ፣ እያንዳንዱ ድርጅት ለማዕከሉ ዕቅድ የራሱን አስተዋጽዖ አቅዶ የሚያሳውቅበትና ያቀደውንም በግድም በውድ ማከናወን ያለበት መሆኑን የሚያመለክት ዓይነት ዕቅድ ነው፡፡
ይህ ዓይነት ከማዕከል አንስቶ እስከ ዳሩ ድረስ በቁጥር ደረጃ ተናቦ መጠንን የማቀድ ሁኔታ ምናልባት ማዕከሉና ዳሩ በሰከንድ ጊዜ ውስጥ መረጃ ሊለዋወጡ በቻሉበት በዛሬው ቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ቢታገዝ ኖሮ ምን ያህል ውጤታማ ሊኮን እንደሚችል ሲታሰብ ሶሻሊዝምን ጊዜ ከዳው እንጂ ውጤታማ ሊሆን ይችል ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ቻይናንና ጃፓንን የመሳሰሉ እስከ ዛሬም ድረስ በማዕከላዊ ዕቅድ የሚመሩ አገሮች ከገበያ ኢኮኖሚ አገሮች የበለጠ የኢኮኖሚ ዕድገት ውጤት ማስመዝገብ ምክንያትም ለማዕከላዊ ዕቅድ ቴክኖሎጂው ስለጠቀማቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ የሚዘጋጀው በባለሙያዎች ስሌትም አይደለም፡፡ በባለሙያና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎም አይደለም፡፡ በባለሥልጣን ይህን ያህል አድርገው እየተባለ በትዕዛዝ እንደሚታቀድና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በባለሥልጣኖች ምኞት ላይ የተመሠረተ መሆኑን በርካታ ማስረጃዎችን ጠቅሶ መናገር ይቻላል፡፡ አንዱ ዓባይን ልገድብ ካለ ዓባይን ለመገደብ ታቀደ ይባላል፤ ሌለው ግልገል ጊቤን ልገድብ ካለ ግልገል ጊቤን ለመገደብ ታቀደ ይባላል፤ ሦስተኛው ተነስቶ ተከዜን ልገድብ ካለ ተከዜን ለመገደብ ታቀደ ይባላል፡፡
አንዱ ተነስቶ አስር የስኳር ፋብሪካዎች ልትከል ካለ አስር የስኳር ፋብሪካዎች ለመሥራት ታቀደ ይባላል፤ ሌላው የባቡር መስመር ልዘርጋ ካለ የባቡር መስመሮች ዝርጋታ ታቀደ ይባላል፤ ሦስተኛው ተነስቶ ኮንዶሚንየም ቤቶች እሠራለሁ ካለ የኮንዶሚንየም ቤቶች ሥራ ታቀደ ይባላል፤ አራተኛው ተነስቶ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ልገንባ ካለ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ታቀደ ይባላል፡፡ የዕቅድ አውጪዎቹ ባለሞያዎች ሥራ የባለ ርዕዩን ምኞት በቃላት አሳምሮ መጻፍ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን የእያንዳንዱ ዕቅድ ሐሳብ ከየትኛው ባለ ርዕይና ባለሥልጣን እንደመነጨ በስም ሳይቀር ያውቃል፡፡
ዕቅዶቹ የባለሥልጣን ትዕዛዞች መሆናቸውን የምናረጋግጥባቸው ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ በአገር ውስጥ ምርት ዕድገት ድርቅ ቢከሰትም ባይከሰትም፣ ሌሎች ችግሮች ቢያጋጥሙትም ባያጋጥሙትም በየዓመቱ ኢኮኖሚው ዐሥራ አንድ በመቶ እንደሚያድግ መታቀዱ ከላይ በተገለጸው መልክ በባለሙያ በሁኔታዎች ጥናትና በስሌት ያልተሠራ መሆኑን ያረጋግጥልናል፡፡
ኢኮኖሚው ከየትኛው የሙያ ዓይነት ምን ያህል የተማረ ሰው እንደሚፈልግ ሳይጠና ሥርዓተ-ትምህርቱ በትዕዛዝ ወይም ሙያ በሌለው ሰው የታቀደ መሆኑን ለመገንዘብ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ብዛት በአንዳንድ ሙያዎች ሥራ ጠፍቶ ተመራቂዎች አምስትና ስድስት ዓመታት ሥራ ፍለጋ ሲንከራተቱ ኮብልስቶን የማንጠፍ ሥራ ለመሥራት ሲረባረቡ በአንዳንድ ሙያዎች ደግሞ የሠራተኛ ፍልሰት የአሰሪዎችን ናላ እያዞረ መሆኑን መረዳትና ችግሮቹም የዕቅዶቹ ጉድለቶች መሆናቸውን በዓይን በሚታዩ ማረጋገጫዎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ አፈጻጸምን ከዕቅድ እኩል የማድረግ የሐሰት ሪፖርት ብዙ ዓመታት ከተዋሸበት በኋላ በዐይን በሚታዩ የገበያ ውስጥ መገለጫዎች መጋለጥ ስለጀመሩ ከቅርብ ጊዜ አንስቶ የዕቅዶቹ ጉድለት ተደብቆ የአፈጻጸም ችግሮች እንዳሉ መነገር ተጀምሯል፡፡
በጨርቃ ጨርቅ ምርት፣ በቆዳ ምርት፣ በስኳርና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ክንውን፣ በሥራ አጥ ቁጥር ቅነሳ፣ በውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ በዋጋ ንረት ወዘተ… አፈጻጸም ከዕቅድ ጋር የማይመሳሰል መሆኑን ለብዙ ዓመታት ተደብቆ እውነቱን ከመንግሥት ከራሱ መስማት የጀመርነው ችግሮቹ በገበያ ውስጥ በዐይን መታየት ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡
ችግሮቹ አፍጥጠው ባልታዩበትና ሰሚው ምንም ዓይነት ማረጋገጫ ሊኖረው እንደማይችል በሚገምቱበት በቀድሞ ጊዜያት ግን ዕቅዶቹና ክንውኖቹን እኩል አድርገው ሪፖርት ያቀርቡ ነበር፡፡ ከበርካታ የኢኮኖሚው እንቆቅልሾች ውስጥ አንዱ በዚህ መልክ ገበያው የሚነግረንና የባለሙያዎቹ ስታቲስቲክስ የሰማይና የምድር ያህል መራራቅ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ደርግን ከመጣሉ በፊት በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በቢልዮን ብር ሲለካ ዐሥራ ቤት ውስጥ ብቻ የነበረው የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ከሰላሳ ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከመቶ እጥፍ በላይ አድጎ ሁለት ትሪልየን ለመድረስ መቃረቡ በገበያ ውስጥ ካለው ዋጋና የሕዝቡ ኑሮ ደረጃ አለመሻሻል ጋር ተገናዝቦ ሲታይ ሊታመን የሚችል አይደለም፡፡ ሆኖም ይህ መረጃ ትክክል አይደለም የሚል ሰው ካለ ትክክል አለመሆኑን በምን ሊያረጋግጥ ይችላል፡፡ የአገር ውስጥ ምርትን ለመለካት በሺህ የሚቆጠሩ የስታቲስቲክስ ባለሙያዎችን አሰማርቶ መረጃ መሰብሰብ ሊያስፈልግ ይችላል ግለሰብ አጥኚ ደግሞ ይህንን ማድረግ አይችልም፡፡
ሲራራ