የተጎጂዎችን ቁጥር ለመቀነስ መንግሥት ተጨማሪ እርምጃዎችን ሊወስድ የሚችልበት ዕድል አለ

መንግሥት ተጨማሪ እርምጃዎችን ሊወስድ የሚችልበት ዕድል አለ
******************************************************

BBC Amharic : ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ባስተላለፉት መልዕክት በሌሎች አገራት እንደተደረገው የሕዝቡን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ለመዝጋት የሚያስችል አቅም መንግሥታቸው እንደሌለው ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል “ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴዎችን ለመዝጋት መንግሥት አቅም የለውም” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ፤ የሚነገሩ የጥንቃቄ ተግባራትን በመፈፀም የተጎጂዎችን ቁጥር ለመቀነስ መንግሥታቸው እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሁሉንም ዜጎች ቤታችሁ ተቀመጡ ማለት የማይቻልበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ ቤት የሌላቸው እንዳሉ፤ ያላቸውም ቢሆኑ የዕለት ጉርሳቸውን የሚያገኙት ከእጅ ወደአፍ በሆነ ሁኔታ መሆኑን በማስታወስ መንግሥት ለእነዚህ ወገኖች ምግብ ማቅረብ ካልቻለ የበለጠ ቀውስ እንደሚፈጠር አብራርተዋል።

ነገር ግን በመጪው ሳምንት የሚኖረውን የወረርሽኙን አዝማሚያ በማጤን መንግሥት ተጨማሪ እርምጃዎችን ሊወስድ የሚችልበት ዕድል እንዳለ አመልክተዋል።

ጨምረውም “ይህንን ወረርሽኝ ከተረዳዳን፣ ከተደማመጥን ዓለም ከዚህ ቀደም ከገጠማት ወረርሽኝ በበለጠ ፍጥነት ለመቆጣጠር እንችላለን” ብለዋል።

መንግሥት ባለው አቅም ሞትን ለመቀነስ በርካታ የማስተማሪያ ስልት ቀይሶ እየሰራ ጠቅሰው፤ ነገር ግን የጥንቃቄ መልዕክቶች አሁንም ተግባራዊ ሲደረጉ እንደማይታይና መዘናጋት እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

የኮሮናቫይረስን በሚመለከት ከአፍሪካ መሪዎችና ከዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወረርሽኙ አሁን ባለው ሁኔታ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ከቀጠለ ያለው የአገሪቱ የመከላከል አቅም በእጅጉ እንደሚፈተንና አደጋውም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ስጋት መኖሩንና ገልፀዋል።

ሕዝቡ ራሱን የሚነገሩትን የጥንቃቄ መልዕክቶች በአግባቡ እየተገበረ ባለመሆኑ “ስጋታችን ከፍተኛ ሆኗል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ምናልባት ችግሩ ከጸና በማለት ለኢትጵያዊያን ቤተሰቦች ጥያቄ አቅርበዋል።

ይህም አንድ ቤተሰብ ለሌላ አንድ ቤተሰብ በቀን አንድ ምግብ ለማቅረብ እንዲዘጋጅ ጠይቀው፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንንም “ማዕድ ማጋራት” ሲሉ ጠርተውታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሆኑት ታከለ ኡማ አዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ የመዝጋት እቅድ እንደሌለ መናገራቸው ይታወሳል።

ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት የበሽታውን መዛመት ለመግታት ሲሉ ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት የሚቆዩ እንቅስቃሴን ሙሉ ለሙሉ የመዝጋት እርምጃ ወስደዋል።