በመተማና ወልቃይት የጦር ሰራዊቱ ድንበር መጠበቁን አቁሟል።

የሀገር አልባዎች ዜና! (በጌታቸው ሽፈራው)

ትህነግ/ኢህአዴግ የቋራን፣ የመተማና ወልቃይትን መሬት ለሱዳን ከሰጠ በኋላ የጦር ሰራዊቱ ድንበር መጠበቁን አቁሟል። የአማራ ገበሬ መከላከያ ሰራዊቱን ተክቶ ዳር ድንበር እያስከበረ ይገኛል።

ዳር ድንበር ሲያስከብሩ ከነበሩት መካከል እውቁ ባሻ ጥጋቡ ይጠቀሳል። የመከላከያ ሰራዊቱ አልፎ አልፎ ብቅ ሲል ሱዳኖቹ የመለስ ጦር መጣ ይላሉ። የባሻን ጦር ደግሞ ያውቁታል።

ሱዳኖቹ ከገዥዎቹ ጋር ቅርበት ያላቸውን ባለሀብቶች ሰብል ሲያቃጥሉ ወይንም ከብት ሲነዱ አልፎ አልፎ መከላከያ ሰራዊቱ ለሱዳን ወደተሰጠው የኢትዮጵያ መሬት ይዘልቃል። ሱዳኖቹም የመለስ ጦር መጣ ይባላል። ጥጋብ ሲሰማቸው ” እንኳን የመለስ ጦር ባሻ ጥጋቡም ይምጣ” ብለው ይፎክራሉ። ከመለስ በላይ ባሻ ጥጋቡ ነበር ድንበር ጠባቂው። ባሻ ጥጋቡ በአነጋጋሪ ሁኔታ ህይወቱ አለፈ። ባሻ አለኝታው የነበረው ገበሬ መንግስት ነው የገደለው ብሎ ያምናል። በማግስቱ የኢትዮጵያ ገበሬዎች ማሳ በእሳይ ጋየ። የሱዳን ጦር የገበሬውን ቤት ሁሉ አቃጠለ። አሁንም ሌሎች ባሻ ጥጋቡዎች ድንበሩን ይጠብቃሉ።

ሆኖም የኢትዮጵያ ጦር ነው የሚባለው የራሱን ሕዝብ እየወጋ ለሱዳን ያግዛል። የሱዳን ከብት ጠፋ ከተባለ ከሱዳን ወታደር ጋር በመሆን ገበሬዎቹን ይወጋል። የሱዳን ጦር ኢትዮጵያ መሬት ላይ ተቀማጭ ሲሆን የኢትዮጵያው ጦር ወደኋላ አፈግፍጎ ሕዝብ ለጠላት ጦር አስረክቧል።

የሱዳን ጦር ደስ ባለው ጊዜ ገበሬውን እያገተ ይወስዳል። ይገድላል። ንብቱን ያቃጥላል። ልጆችና ሚስቱን አፍኖ ይወስዳል። የሚደርስ የኢትዮጵ የሚባል ጦር የለም። ገበሬው በቻለው መንገድ ይከላከላል።

ዛሬም አፈናው ቀጥላል። ትናንት ሰኔ 14/2010 ዓም ደጉ ማሞ፣ ጌጤ ክብረትና ሌላ አንድ ገበሬ በሱዳን ጦር ታፍነው መወሰዳቸው ታውቋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሚባለው አልደረሰም። በሱዳን ጦር ተገድለው ተጥለዋል የሚል መረጃ እየተናፈሰ ነው።

ዳር ደንበር የሚጠብቅ ጦር በመጥፋቱ ራሱንና ሀገሩን እየጠበቀ ያለ ገበሬ ስቃዩ በርትቷል። በደሉ በዝቷል።የሚያስታውሰው አላገኘም። ውርደታችን ከዚህ ደርሷል። መንግስት ነኝ የሚለው ዳር ድንበር መጠበቅ አልተቻለም። የሸጠውን መሬት ማስረከብ የሚችለው በዚህ መንገድ ነው! ዳር ድንበሩ ያልተከበረ ሀገር ሀገር አይደለም። የአማራ ገበሬዎች ባይተዋር ላለመሆን የራሳቸውንና የሀገራቸውን ሉዓላዊነት እያስጠበቁ ቆይተዋል። ከውጭ ወራሪዎች በላይ ግን መንግስት ነኝ የሚለው አካል ነው የሚያስደፍራቸው፣ ባይተዋር፣ ሀገር አልባ የሚያደርጋቸው!