በመንገደኞችና በአየር መንገዱ ሠራተኞች ላይ የሚደረገው የኮሮና ቫይረስ ምርመራና ቁጥጥር ደካማ ነው ተባለ

አየር መንገድ ላይ ያለው ቁጥጥር አሁንም ደካማ ነው ተባለ
****
ሲራራ – በቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በመንገዶኞችና የአየር መንገዱ ሠራተኞች ላይ የሚደረገው የኮሮና ቫይረስ ምርመራና ቁጥጥር አሁንም በሚጠበቀው ደረጃ ያልተጠናከረ መሆኑን የሲራራ ምንጮች ገለጹ፡፡
የቫይረሱ ስርጭት ቀድሞ ከተከሰተባቸው እንደ ቻይና ካሉ አገሮች ሳይቀር የሚመጡ የአውሮፕላን ካፕቴኖች እና ሌሎች የመስተንግዶ ሠራተኞች በለይቶ ማቆያ ውስጥ መቆየት ሲገባቸው እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በአገራችን እየተተገበረ እንዳልሆነ የሚገልጹት ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየታቸውን የሰጡ የበረራ አስተናጋጅ፣ “አየር መንገዱ እንደፈለጋችሁ ብሎ ቢለቀንም እኛ ግን ራሳችንን ለይተን መቀመጡን መርጠናል ይላሉ፡፡”
አየር መንገዱ ወረርሽኙን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ያደረገው ሥራ በጣም ደካማና የሚያስጠይቅ መሆኑን የሚገልጹት የአየር መንገዱ ሠራተኞች፣ እንኳን ለሌላው ሕዝብ ለራሱ ሠራተኞችም ሲያደርግ የቆየው ጥንቃቄ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ከውጭ ከመጡትና ለ14 ቀናት ስካይ ላይት፣ ግዮን፣ አዳማ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች ለይቶ ማቆያ ስፍራዎች ከሚገቡት መንገደኞች መሀከል አንዳንዶች ለጥበቃዎችና የሆቴል ሠራተኞች ገንዘብ በመክፈል እየወጡ መሆኑን የማኅበራዊ ሚዲያው ካጋለጠ በኋላ የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ በበኩሉ በለይቶ ማቆያ ውስጥ መግባት ሲገባቸው የመንግሥትን መመሪያ ተላልፈው በሚገኙ መንገደኞች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ ባወጣው መግለጫ ማስጠንቀቁ አይዘነጋም፡፡
Source – ሲራራ