በወረርሽኙ ምክንያት የገባንበት ፈታኝ ሁኔታ ጠንካራ የፖሊሲ ማስተካከያ ይፈልጋል

“በወረርሽኙ ምክንያት የገባንበት ፈታኝ ሁኔታ ጠንካራ የፖሊሲ ማስተካከያ ይፈልጋል” – ሲራራ
****
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅኗል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተ ቀውስ ለመቋቋም ምን ማድረግ ይገባታል? ኢኮኖሚው ካለበት ድቀት የበለጠ እንዳይሽመደመድ ምን ዓይነት የመፍትሔ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል? ባልደረባችን ይስሐቅ አበበ በእነዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የኢኮኖሚክስ ባለሙያውን አቶ ጌታቸው ተክለ ማርያምን አወያይቷቸዋል፡፡ ውይይቱን እነሆ፡-
****
ሲራራ፡- [ጊዜያዊ] መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም ላይ የኮሮና ቫይረስ ግማሽ ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ አጥቅቷል፡፡ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችም ሕይወታቸውን አጥረዋል፡፡ ወረርሽኙ ከሰው ሕይወት አልፎ የዓለምን ኢኮኖሚም እያናጋው ይገኛል፡፡ በእርስዎ አስተያየት በወረርሽኙ ምክንያት በኢኮኖሚው ላይ ሊደርሱ የሚችሉት አደጋ ምንድን ናቸው?
አቶ ጌታቸው፡- ይህ ትልቅ የሚባል ዓለም ዐቀፍ ቀውስ ነው፡፡ እንደ ቀውሱ የጉዳት መጠንና ግዝፈት በዓለም ላይ ሌላ የኢኮኖሚ ቀውስ ማምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ የተፈጠረው ቀውስ ብዙዎቹ አገሮች ያልተዘጋጁበትና ያልተገመተና ያልተጠበቀ ክስተት ነው፡፡ በተለይ እንደኛ አገር የተዳከመ ኢኮኖሚ አቅም ላላቸው አገሮች የቀውሱ ተጽዕኖ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ እነዚህን አገሮች በበርካታ መንገድ ነው የሚጎዳቸው፡፡ ቀውሱ ከአገሮች ድህነት ጋር ተደማምሮ ለከፋ ችግር ተጋላጭ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ በነዚህ አገሮች አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በድህነት ውስጥ የሚኖር በመሆኑ ተጽዕኖውን መቋቋም በጣም ከባድ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ የሆኑ አገሮች ተቋሞቻቸው እና የኢኮኖሚ አደረጃጀታቸው ደካማ ነው የሚሆነው፡፡ የኢኮኖሚያዊ ቅንጅት ያልፈጠሩ አገሮች፣ በዓለም ዐቀፍ የምርት ሰንሰለት ውስጥ የወጭ ንግዳቸው ዝቅተኛ የሆኑ አገሮች፣ በመሠረተ ልማት፣ በአገልግሎት ዘርፍ አሰጣጥ ደካማ የሆኑ አገሮች በተጽዕኖ ክፉኛ ሊጎዱ ይችላሉ፤ እየተጎዱም ነው፡፡ ከነዚህም ውስጥ የኢሲያ አገሮች አብዛኛዎቹ፣ የአፍሪካ አገሮች፣ የተወሰኑ የላቲን አሜሪካ አገሮቸ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በግልጽ እንደሚታየው አሁን የተፈጠረው ቀውስ የዓለም ዐቀፍ የንግድ ግንኙነቱን አውኮታል፡፡ በዚህ ቀውስ ይህኛው ኢኮኖሚ ዘርፍ ይድናል የሚባል ነገር የለም፡፡ የመጠኑ ሁኔታ ሊለያይ ይችላል እንጅ ይተርፋል ብዬ የማስበው የኢኮኖሚ ዘርፍ የለም፡፡
ሌላው፣ አገሮች የገጠማቸውን ቀውስ ለመፍታት የሚያስችል በቂ አቅም አላቸው ወይ? የሚለው ጥያቄ በደንብ መታየት ያለበት ነገር ነው፡፡ አገሮች ያላቸው ኢኮኖሚያዊ አቅም ከጉዳቱ በምን ያህል ጊዜ (ፍጥነት) ይወጣሉ የሚለውን የሚወስን ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ ኢኮኖሚው የተለያዩ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ መቀዛቀዞች ይታያሉ፡፡ ይህ ሲባል ሁሉም ዘርፎች እና ሁሉም አገሮች በእኩል መጠን ይጎዳሉ ማለት ግን አይደለም፤ ሊሆንም አይቻልም፡፡ የጉዳት ጡንቻው የሚጠነክርባቸው አገሮች እና ዘርፎች አሉ፡፡ በተለየ መልኩም በቀውሱ የሚጎዱ ግለሰቦችም ይኖራሉ፡፡ ይህም ከመከላከልና መቆጣጠር ችግር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ደካማ ኢኮኖሚ ያላቸው አገሮች በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዱ እንደሚችሉ መገመት ግን አይከብድም፡፡ በጥቅሉ ግን ወረርሽኙ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ትልቅ ኢኮኖሚው ቀውስ የፈጠረ እና እየፈጠረም ያለ ነው፡፡
ሲራራ፡- በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳትስ ምንድን ነው?
አቶ ጌታቸው፡- ወረርሽኙ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ በቅርብ ዓመታት ገጠሙን ከምንላቸው ቀውሶች ትልቁ ቀውስ ሊባል የሚችል ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ በፊት የገጠሙንን ቀውሶች ለመቃኘት ሞክሬያለሁ፡፡ በታሪካችን እንዲህ ዓይነት ኢኮኖሚውን ሊፈትን የሚችል ክስተት ገጥሞን አያውቅም፡፡ ይህ ክስተት ትልቅ መጠን ያለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያመጣል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ ጉዳቱ ከዓለም ዐቀፍ ገበያ መቀዛቀዝ የሚመነጭ ነው፡፡
በቅርብ ጊዜያት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ገጠመው የሚባለው የኢኮኖሚ ቀውስ በ2008 ዓ.ም. የተከሰተው የፋይናንስ ተቋማት ቀውስ ነው፡፡ ይህም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተ ነው፡፡ ተጽዕኖ ወደ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚመጣበት መንገድ የሚታወቅ በመሆኑ በተወሰነ መልኩ ለመቆጣጠር የሚቻልባቸው መንገዶች ነበሩ፡፡ ለመቋቋምም ተሞክሯል፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ አብዛኛው ከዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ዘርፍ ጋር ያለው ግንኙነት ጠንካራ የሚባል ባለመሆኑ በዘርፉ ላይ ያን ያህል ጉዳት አላመጣም ነበር፡፡ ሙሉ በሙሉ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አልነበረም ማለት ግን አይቻልም፡፡ በወቅቱ ባጠናነው ጥናት የአገሪቱ ጥቅል ምርት ላይ እስከ 2.8 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ የወጭ እና ገቢ ንግዳችን ችግር ውስጥ የገባበት ሁኔታ ተፈጥሮም ነበር፡፡ ያም ከዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የፍላጎት መቀዛቀዝ ጋር ተያይዞ የመጣ ነበር፡፡ በጊዜው አገሮች የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ሥራዎችን ሲሠሩ የኢትዮጵያም ችግር አብሮ የተቀረፈበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ አሁን የገጠመን ችግር ግን ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች የባሰ የሚባል ችግር ነው፡፡ ችግር በሁሉም በሚባል የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ የገጠመ ነው፡፡
እውነት ለመናገር ሁሉም ሰው ያለ ልዩነት ከመንግሥት ጎን ቆሞ ችግሩን ለማለፍ መረባረብ አለበት፡፡ ይህ ያለ ምንም ልዩነት መሠራት ያለበት ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ በአውዳሚነቱ በታሪክ ሊጠቀስ የሚችል ጉዳት አድርሶብን የሚሄድ ቀውስ ነው፡፡ አሁን የዜጎችን ሕይወት ለማዳን እና ኢኮኖሚው ላይ ሊደርስ የሚችለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም በአንድ መቆም ያለብን ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡
በዚህ ጊዜ ማድረግ ያለብን የመከላከል ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ በኢኮኖሚው ላይ የሚከሰተውን ተጽዕኖ ሊከላከል የሚያስችል ሥራ መሥራት ይገባናል፡፡ ጉዳቱን ለማቃለል በትኩረት መሥራት ይገባል፡፡ እኛ እንዳደጉት አገሮች ድንበሮቻችን ዘግተን መቆየት አንችልም፤ ያን ለማድረግ አቅሙ የለንም፡፡
አየር መንገድ ለምን ቀድሞ በረራውን አላቆመም የሚል ውሃ የማያነሳ ክርክር እሰማለሁ፡፡ በዚህ አገር ኢኮኖሚ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትልቅ ተጽዕኖ አለው፡፡ የገቢ እቃዎችን ከማንቀሳቀስ ጀምሮ በኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው፡፡ የዜጎችን የካፒታል ምርት እንቅስቃሴ የሚወስን ትልቅ ተቋም ነው፡፡ አየር መንገዱ አንደኛው እና ወሳኙ ከውጭ ዓለም የምንገናኝበት መስመራችን ነው፡፡ በብዙ መልኩ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሰው አየር መንገድ ለምንድን ነው የማይዘጋው ተብሎ ክርክር መኖር ያለበት አይመስለኝም፡፡ የእኛ አየር መንገድ እንደ ገልፍ አገሮች አየር መንገዶች አይደለም፡፡ እነሱ ከነዳጅ በሚያገኙት ዶላር በቀላሉ ችግሮችን ተቋቁመው መቆየት ይችላሉ፡፡
ትልልቆቹ አየር መንገዶች የቻይና፣ የእንግሊዝ እንዲሁም የፈረንሳይ አየር መንገዶች የሚገጥማቸውን ችግር ከመንግሥት በሚያገኙት ድጎማ በቀላሉ መፍታት የሚችሉበት አቅም አላቸው፡፡ በእኛ አገር ግን ያንን መድረግ ያስቸግራል፡፡ አየር መንገዱን ለመደገፍ ሀብቱን ከየት እናመጣዋለን? የእኛ አየር መንገድ በኢኮኖሚው የሚደገፍ ሳይሆን ኢኮኖሚውን የሚደግፍ ነው፡፡ ተቋሙ የሚበዙትን የኢኮኖሚ ጉድለቶች የሚሞላልን ነው፡፡ ሌላውን ትተን በሥሩ ቀጥሮ የያዘውን 22 ሺሕ ሠራተኞች እና በሥራቸው የያዙትን ቤተሰብ ብናሰላ፣ ቀላል የሚባል ቁጥር አይደለም የያዘው፡፡ የአየር መንገዱ ሙሉ በሙሉ ሥራ ቢያቆም 100 ሺሕዎች ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ አየር መንገዱ በቀላሉ የተገነባ አይደለም፤ ለመገንባት ብዙ ዐሥርት ዓመታትን የፈጀ ተቋም ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ወረርሽኝ ትልቅ ቀውስ ነው የገጠማት፡፡ ኢኮኖሚው በጣም ነው የሚፈተነው፡፡ ችግሩ በአንድ ዘርፍ ብቻ የመጣ አይደልም፡፡ አንድን ዘርፍ ብቻ አጥቅቶ የሚሄድ አይደለም፡፡ ጠንካራ የሚባል የፖሊሲ ማስተካከያ የሚፈልግ ነው፡፡ የመንግሥት አስተዳደር ችግሩን ለመፍታት ያለው አማራጭ በጣም ጠባብ ነው፡፡ አሁን ያለው አማራጭ በሽታው የሚያደርስውን ጉዳት መቀነስ የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ ነው፡፡ የዓለም አገሮችም ቅድሚውን ሰጥተው እየሠሩ ያሉት በዚያ ላይ ነው፡፡ በእኛም አገር ሕዝብም መንግሥትም፣ የማኅበረሰብ አንቂ ግለሰቦች፣ የግል እና የመንግሥትም ተቋማት ተባብረው በትኩረት መሥራት ያለባቸው እዚያ ላይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደዚያ አድርገንም ካልተሳካልን ግን በጣም አስከፊ ሁኔታ ነው የሚፈጠረው፡፡
ሲራራ፡- በኢትዮጵያ ቫይረሱ መከሰቱን ተከትሎ የሸቀጦች ዋጋ እየጨመረ ነው ያለው፡፡ መንግሥትም ገበያውን ለማረጋጋት የቁጥጥር ሥራ እየሠራ ነው፡፡ የሸቀጦች ዋጋ መናር ለማረጋጋት መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች ምንድን ናቸው?
አቶ ጌታቸው፡- በአገራችን የሰዎችን ፍላጎት መናር እና መቸገርን እንደ ጥሩ ዕድል አድርገው የሚጠቀሙ ነጋዴዎችን እየታዘብን ነው፡፡ የአንድ ሰሞን የማኅበረሰብን ችግር ተጠቅመው ሰማይ ለመድረስ እና የኅብረተሰብን ችግር ተጠቅመው መክበር የሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎች በታሪክ አጋጣሚ ፈጥረናል፡፡ የታሪክ ባለሙያ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን በአገራችን ታሪክ እንዳሁኑ ስግብግብነት አድጎና ጎልብቶ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡ ይህ ሕዝብ ከድህነቴ ኩራቴ ይሻለኛል ብሎ የሚያስብ የነበረ፤ ለማተቤ፣ ለእምነቴ እኖራለሁ የሚል ማኅበረሰብ ያለበት አገር ነበር፡፡ አሁን የምናየው ስግብግብነት ግን ከየት እንደ መጣ ለመናገርም ለመተንተንም በጣም ከባድ ነው፡፡ ምን ዓይነት ስግብግብነት እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ባለፉት ኹለት ዐሥርት ዓመታት በአቋራጭ የመክበር ዝንባሌ ማደጉ የፈጠረው ሂደት ይመስለኛል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሳሙና አቅጥኖ ከመሸጥ ጀምሮ፣ እስከ ምንነቱ ያልታወቀ ምርት ሳኒታይዘር ብሎ መሸጥ ድረስ ያላየነው የስግብግብነት ጥግ የለም፡፡ አሁን ላለው የተረበሸ ገበያ አንደኛው ምክንያት እሱ ነው ብዬ አስባለሁ።
ሌላው ችግር ድንጋጤ የወለደው ግዥ (ፓኒክ ፐርቼዚንግ) መፈጠሩ ነው፡፡ ሰዎች ችግር ይገጥማል ብለው ሲያስቡ በአንዴ ወደ ገበያ ይወጣሉ፡፡ ይህ በዓለም ዐቀፍ ቢሆን የሚታይ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ ሰዎች ከገበያው ውስጥ የሚያስፈልጋቸውንም የማያስፈልጋቸውንም፤ ሊያስፈልገኝ ይችላል በሚል ስጋት ገዝተው መከማቸትን አማራጭ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ደግሞ ገበያው ያልተዘጋጀበት ፍልጎት በአንዴ ሲመጣ ገበያው ላይ እጥረት ይፈጠራል፡፡ ነጋዴውም ዛሬ ከምሸጠው ነገ ልሽጠው በሚል እሳቤ ምርት ይደብቃል፡፡ ዋጋ ይጋሽባል፡፡
ከማክሮ ኢኮኖሚ አንጻር የእኛ አገር ገበያ ቀድሞውም የአቅርቦት ችግር ያለበት ነው፡፡ ሰፊ የሆነ የምርት እጥረት ያለበት ገበያ ነው ያለን፡፡ የአገሪቱ የምርት አቅርቦት አገራዊ ፍላጎት ጋር የሚደራረስ አይደለም፡፡ አቅርቦት አነስተኛ በሆነበት ሁኔታ ከፍተኛ የመግዛት ፍላጎት ሲኖር ገበያው ውጥረት ውስጥ ይገባል፡፡ በእኛ አገር ማምረት አቅም እጥረቱንም በአጭር ጊዜ ውስጥ መሙላት አይቻልም፡፡
ቻይናን ብንመለከት አብዛኛው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎቿን የአፍ መሸፈኛ እንዲያመርቱ ነው ያደረገችው፡፡ አሜሪካም ለአምራች ዘርፉ የተለያዩ ማበረታቻዎችን በመስጠት ምርቶችን በብዛት እንዲያመረቱ እያደረገች ነው፡፡
እኛ ግን አሁንም ምርት አስገቢዎች ነን፡፡ ኢኮኖሚያችን የተንጠለጠለው በገቢ ንግድ ላይ ነው፡፡ የምናስገባው መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ሳይቀር ነው፡፡ ስንዴ፣ ስኳር፣ ዘይት… ብዙውን ምርቶች ከውጭ አስገብተን ነው የምንጠቀው፡፡ አሁን እንደ ድሮ ምርቶችን በቀላሉ ገዝትን ማስገባት አንችልም፡፡ ለእኛ የሚልኩት አገሮች ራሳቸው ተጎጂ ናቸው፡፡ ዓለም ዐቀፍ ንግዱም ቆሟል፤ እንደ ቀድሞው ምርት መስገባት ቀላል ነገር አይደለም፡፡
የበሽታውን ስርጭት መከላከል ካልቻልን ሁኔታው ከባድ ነው፡፡ አሁን ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በጣም መደነቅ ያለባቸው ናቸው፡፡ ትልልቅ ውሳኔዎችን እና በኢኮኖሚው ላይም ትልቅ ተጽዕኖ ያላቸው ውሳኔዎቸን ነው እየወሰኑ ያሉት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እርጋታ እና ውሳኔዎችን ሳናደንቅ ማለፍ አይቻልም፡፡ ውሳኔዎቹ ቀላል የሚባሉ አይደሉም፤ ተጽዕኗቸውም ከባድ ነው፡፡ ግን ውሳኔዎቹ መታገዝን የሚፈልጉ ናቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ እያገዘው ነው ብዬ አላስብም፡፡ መጀመሪያ ወረርሽኙ በቻይና ሲከሰት ችግሩ የቻይና ብቻ ተደርጎ ነበር የተወሰደው፤ ዓለም በቻይና ሲሳለቅ ነበር፡፡ ቆይቶ ግን ሁሉንም አገሮች አዳርሷል፡፡ በአገሮች ሁሉ የመጀመሪያዎቹ 100 ሰዎች እስኪያዙ ድረስ ትኩረት የሰጠው አልነበረም፡፡ ቁጥሩ ሲጨምር ነው ሰው ተደናግጦ መጠንቀቅ የጀምረው በእኛም አገር አሁን ላይ ከፍተኛ መዘናጋት ነው ያለው፡፡ አሁን በብዛት እየመረመርን ስላልሆነ ብዙ ቁጥር ያለው ሕመምተኛ እያገኘን አይደለም፡፡ በደንብ ስንመረምር ብዙ ሕመምተኛ የምናገኝ ነው የሚመስለኝ፡፡
መንግሥት መደነቅ ያለበን ችግሩ በጣም ሳይስፋፋ ነው የመፍትሔ እርምጃዎችን እየወሰደ ያለው፡፡ ይህ በብዙ መንገድ መንግሥትን የሚያስመሰግነው ጉዳይ ነው፡፡ በተወሰኑ ውሳኔዎች ተግባራዊነት ላይ የኅብረተሰቡ ተባባሪነት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በኅብረተሰብ ደረጃ ያለው መዘናጋት ለመፈጠሩ አንደኛው ምክንያት ችግሩን አለመረዳት ነው፡፡ በሌላ በኩል የተወሰኑትን ውሳኔዎች መተግበር የማይችል ማኅበረሰብም አለ፡፡ አኗኗራችን በድህነት የተሞላ በመሆኑ መንግሥት የሚላቸውን ውሳኔዎች ተቀብሎ ወደ ተግባር ለማስገባት በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ የአቅም ዝግጁነት ያለው ማኅበረሰብ በጣም ጥቂት ነው፡፡
ሲራራ፡- በወረርሽኙ ምክንያት የውጭ መዋለ ነዋይ ፍሰት እየተዳከመ ነው፡፡ ያለውም ከዓለም ዐቀፍ ንግድ እንቅስቃሴ መገታት ጋር ተያይዞ ወደ መዘጋት እያመራ ነው፡፡ አብዛኛውም የሠራተኛ ቅነሳ እያደረገ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት የሠራተኞች ከሥራ መፈናቀል የሚያመጣውን ተጽዕኖ እንዴት ያዩታል?
አቶ ጌታቸው፡- ቅደም ብለን እንዳነሳነው ነው፡፡ አሁን የገጠመን ፈተና በአንድ በኩል ብቻ የመጣ አይደለም፤ ሌላኛው የጉዳት ጎኑ የሥራ አጥ ቁጥሩን መጨመሩ ነው፡፡ ወረርሽኙ የወጭ ኢንቨስትመንትን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ አገሮች አሁን ላይ በውጭ ለሚኖሩ ዜጎቻቸው ወደ አገራቸው እንዲገቡ ጥሪ እያቀረቡ ነው ያሉት፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ተሰማርተው ያሉ የውጭ አገር ባለ ሀብቶች ወደ አገራቸው ሊገቡ ይችላሉ፡፡ የእነሱ መሄድ ደግሞ ሰዋዊ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ችግር በሰው አገር ማንም መቆየት አይፈልግም፡፡ ለሥራ ነው የመጡት፡፡ ሥራው ሲቀዛቀዝ ዘግተው ወደ አገራቸው ይሄዳሉ፡፡ በዚህም የሚሠሩት ዜጎች ሥራ አጥ የመሆን ዕድል ሊገጥማቸው ይችላል፡፡
የአበባን እርሻዎችን ብንመለከት ምርቱ በባሕሪው የሚበላሽ ነው፤ ብዙ ጊዜ የሚቆይ አይደለም፡፡ በወቅቱ ወደ ገበያ ካልቀረበ ኪሳራ የሚያመጣ ነው፡፡ ዓለም ዐቀፍ ገበያውም እንደሚታየው ነው፡፡ ይህ በሥራቸው ለሚሠሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ከሥራ መፈናቀልንም ያመጣል፡፡ ከፍተኛ የሰው ኀይል ቀጣሪ የሆኑ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን ያሰናብታሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሰው ውጥንቅጥ በሞላበት ሰዓት፣ ዋጋ ግሽበት በተከሰተበት ጊዜ፣ ሰዎች ተጨማሪ ምርት በሚፈልጉበት ሁኔታ፣ ለጤና መጠበቂያ ከፍተኛ ወጪ እያወጡ ባሉበት ወቅት ከሥራ መሰናበታቸው በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁን መንግሥት የመካላከል ሥራው ላይ ትኩረት እናድርግ የሚለው ይህን ሁሉ ቀውስ ለመካላከል ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ይህን ሁሉ ተረድቶ ከመንግሥት ጎን መቆም መቻል ነው ያለበት፡፡ ቀጣዩ ጊዜ ብዙ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የምናስተናግድበት ጊዜ ነው፡፡ መንግሥት ይህን ተረድቶ ዝግጅት ማድረግ መቻል አለበት፡፡ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሲራራ፡- ችግሩን ለመቋቋም ለንግዱ ከማኅበረሰቡ የሚጠበቀው ምንድን ነው?
አቶ ጌታቸው፡- አሁን ከገባንበት ቀውስ ለመውጣት መንግሥት በየቀኑ እየገለጻቸው ያሉ የመፍትሔ እርምጃዎች አሉ፡፡ አሁን ማሸጋሸግ ያለብንን ሀብት አሸጋሽገን ይህን ችግር ማለፍ አለብን፡፡ ዓመታዊ በጀታችን ወደ 3.7 በመቶ ጉለት እንዳለበት የሚያሳይ ነው፡፡ በጀታችን አሁንም በአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ብድር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን ከፍተኛ የሆነ የእዳ ጫና ያለበት ኢኮኖሚ ነው፡፡ ማክሮ ኢኮኖሚው የተረጋጋ አይደለም፡፡ ባለፉት አራት እና አምስት ዓመታት በአገሪቱ የነበሩት አለመረጋጋቶች ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አምጥተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ፈተና ያለበት ኢኮኖሚ ነው ያለን፡፡ በአስቸኳይ ኢኮኖሚውን መደገፍ የሚችሉ ፖሊሲዎች መዘጋጀት መቻል አለባቸው፡፡ የተቀናጀ መልስ መስጠት የሚችል ዕቅድ ሊኖር ይገባል፡፡ የመንግሥት ፖሊሲ አውጭዎች እንቅልፍ አጥተው መሥራት መቻል አለባቸው፡፡
አሁን ላይ የመንግሥት ባለሙያዎች ቁጭ ብለው በጀታቸውን ማስተካከል ይገባቸዋል፡፡ ከፍተት ያለባቸውን ዘርፎች እየታዩ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ መሠራት ያለባቸው ፕሮጀክቶች በቅደም ተከተል መቀመጥ መቻል አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል፣ ሊከሰት የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቆጣጠር በሚያስችሉ፣ ተጨማሪ አቅም ሊያመጡ የሚችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ በጀት ግን እንደ አዲስ መስተካከል እንዳለበት ሳላነሳው የማላልፈው ጉዳይ ነው፡፡ ጠቅለል ያለ ሁሉም የተቀናጀበት የተቋማት ትብብር መኖር መቻል አለበት፡፡ የግሉም ባለሀብት ከመንግሥት ጋር አንድ ላይ በትብብር መሥራት አለበት፡፡ የተዳከመውን የግል ዘርፍ የሚደግፍ ልዩ በጀትም መዘጋጀት ያለበት ይመስለኛል፡፡ አሁን የሚወሰኑ ውሳኔዎች አብዛኛዎቹ ተፈልገው የሚወሰኑ አይደሉም፡፡ አስገዳጅ ሁኔታዎች ስለተፈጠረ ነው ውሳኔዎች የሚወሰኑት ያም ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ማምጣታቸው የማይቀር ነው፡፡
ይህ ጊዜ ሁሉም ባለሙያዎችና ሁሉም ዜጎች ሊተባበሩበት የሚገባ ጊዜ ነው፡፡ ያለ ርዕዮተ ዓለም ወይም አመለካከት ልዩነት፣ ያለ ዘውግ ወይም ብሔረሰባዊ ወገንተኝነት፣ ያለ ሃይማኖት ወይም ሌላ ማንኛውም የአመለካከት ልዩነት አብረን በትብብር በመሥራት ይህን እጅግ ፈታኝ ጊዜ ማለፍ ይገባናል፡፡
ሲራራ