ጎንደር በብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችና በመከላከያ ሰራዊት ጦር ቀለበት ውስጥ ነች ሲሉ የአማራ አክቲቪስቶች ተናገሩ

ህወሓት ወደ መቀሌ አልሸሸም! ፀረ አማራነቱን የተሸከሙለት ቤተ መንግስት ናቸው። (Getachew shiferaw)
የአራት ኪሎው ቤተ መንግስት ሰው እንጅ አስተሳሰብ አልተቀየረበትም። ትህነግ/ሕወሓት ሕዝብን ሲያሸብር ኖሯል። የሱዳን ጦር የአማራን ገበሬ ሲወጋ ከኋላ ሆኖ ገበሬውን ሲመታ ኖሯል። ከሶስት ቀን በፊት የሱዳን ጦር ሉአላዊ ደንብር ጥሶ ሲገባ ለመመከት የጣረው ሕዝብ ነው። መከላከያ ሰራዊቱ እንደተለመደው ሕዝብ ራሱን እንዳይከላከል ነው መሃል የገባው።
በአንፃሩ የአማራን ሕዝብ ለማሸበር ሲሆን ታንክ ይዞ ይገባል። የፋኖ ጉዳይ በሽምግልና ተይዟል። የአማራ ሕዝብ ሽምግልናውን የሚመርጠው ገዥዎቹ በቃላቸው ስለሚፀኑ አይደለም። የተፈጠረው ተፈጥሮ አማራው እንዲተራመስ ከሚፈልጉት ክፉዎች የተሻለ አስተውሎ መንቀሳቀስ ስለነበረበት ነው። ታዲያ በሽምግልና የተያዘን ጉዳይ በሽብር ለመፍታት እየጣሩ ነው። ይህን የሚያደርጉት ወረርሽኝ በገባበት ወቅት ነው። ይህን የሚያደርጉት አማራው የቅድመ መከላከያ ቁሳቁሶች አጥቶ በወረረረሽኝ ስጋት በወደቀበት ወቅት ነው። በወረርሽኝ ስጋት ያለን ሕዝብ በመውረር ላይ ያለ አካል የምንጊዜም የአማራ ጠላት ነው።
ወለጋ ላይ ለሚገኝ ወንበዴ ኢንተርኔት የለቀቀው የእነ ዐቢይ አህመድ መንግስት ለአማራው የሚልክለት ጥይት ነው። ወረርሽኝ ስጋት የደቀነበትን ሕዝብ ከወረርሽኝ ጋር ተደምሮ እያሸበረው ነው። ይህ መቼም ይቅር የማይባል ጠላትነት እንደሆነ ሊያውቁት ይገባል!
አዴፓ የሚባል መቼም ራሱን ችሎ የማይቆም፣ አራት ኪሎ የገባ ሁሉ የሚጎትተው ድርጅት ከአማራ ሕዝብ ዘንድ ለመጠጋት የነበረውን ተስፋ ቆርጥሞ ጨርሶ አሁን ሕዝብን በማስወረር ላይ ተጠምዷል። ከአማራው ይልቅ ገዥዎቹ የሚቀርቡት ይህ ቡድን በዚህ የወረርሽኝ ወቅት እንኳ ከሕዝብ ዘንድ ለመወገን ቅንጣት ፍላጎት የለውም።
……………………….
በመግለጫም ሊሸውዱን ይሞክሩ ይሆናል! ግን ውሸት ነው!
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንደ ስሙ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ባያገለግልም፣ አማራ ላይ የሚያደርገው ትክክል ባይሆንም ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አለው። ግዴታውም ነበር። ትግራይ “መከላከያ አይውጣብኝ” እያለች አማራው “መከላከያ መጣ” የሚለው አላማውን ስለሚያውቅ ነው። ለበርካታ ጊዜያት መከላከያ ሰራዊቱ አማራ ላይ ያደረገውን መዝግበናል። የትህነግ ዘራፊ ድርጅቶች መሳርያ በማቀባበል ወንበዴ ሲደግፉ ኖረው ሕዝብ ይጠየቁልኝ ሲል በከባድ መሳርያ ተጨፍጭፈዋል። የሱዳን ጦር ድንበር ጥሶ ሲገባ የተከላከሉት ላይ ሲተኩስ ኖሯል። የቅማንት ኮሚቴ የሚባለው ጋር የነበረውን በሚገባ እናውቃለን።
የዛሬው እጅግ የባሰ የሚያደርገው ጊዜ ጠብቀው፣ ሕዝብ በበሽታ እየተረበሸ ባለበት ወቅት የፈፀሙት ታሪክ የማይረሳው ክህደት በመሆኑ ነው። ይህን ሽብር ከአማራ ሕዝብ ውጭ ሌላ ላይ አያደርጉትም። ከአሁን ቀደምም የአማራ ሕዝብ መከራ ሲገጥመው የፈፀሙት ክህደት ተመዝግቧል። ከሚሴና አጣዬ ላይ በወንበዴ ስም ተወርሯል። የሚዲያ ማወናበጃ ተደርጎበታል። ሰኔ 15ን ተከትሎ ለአማራ የቆፈሩለት ክህደት ተመዝግቧል። በሞጣው ጉዳይ እንደ ገዥ ብቻ ሳይሆን እንደ አክቲቪስት ሆነው ሕዝብ ላይ ዘምተዋል። ስንጥቅ ለማስፋት ጥረዋል። በአማራ ሕዝብ ላይ በደል ሲፈፀም ከዝምታ፣ ከመሸፋፈን አልፈው አጋጣሚውን መጠቀምን ሲመርጡ ይህ የመጀመርያው አይደለም።
ሰሞኑን የሱዳን ሰራዊት ድንበር ጥሶ ሲገባ “ለምን?” አላልንም። የሱዳን ሰራዊትማ አማራውን ውረርልኝ የሚለውን ትዕዛዝ ተቀብሎ ድንበር ጥሶ ይገናልና “ከኋላው ያለው ማን ነው?” ብለናል። በትህነግ ዘመን ከኋላው የነበረው ትህነግ ነበር። የሱዳን ወታደር በባለሀብት ሳይቀር የሚዘወር ነው። ትህነግ ስልጣን ከተነጠቀ በኋላም በባለሀብት በኩል በአማራ ላይ አዝምቷል። አሁንም አያደርግም አይባልም። ግን ከሱዳን ሰራዊት በስተጀርባ ከትህነግ ባሻገር ለአማራ ጊዜ የሚጠብቅ ሁሉ አለበት። ከሁለት ቀን በፊት በምዕራብ አርማጭሆ የተጀመረው ሽብር ዛሬ ዳባትም ላይ አለ።
የዛሬውን ሽብር በመግለጫ ሊያስተባብሩ ይችሉ ይሆናል። መከላከያ ሰራዊቱ አዲስ ስምሪት እያደረገ እንጅ ምንም አይነት የለም ሊሉን ይችላሉ። ውሸት ነው። እውነታው ለአማራው ምቹ ጊዜ አገኘንለት የሚል ነው። እውነታውን አማራውን ለመረበሽ፣ ጎንደርን የአማራው ወለጋ ለማድረግ ነው!
በኮሮና ምክንያት እስረኛ እየተፈታ አማራው ላይ ግን ሽብር ተጀምሯል። የወለጋ አሸባሪ ኢንተርኔት ሲለቀቅለት፣ ሌሎች አካባቢዎች የህክምና ቁሳቁስ ሲላክላቸው ለአማራው ከባድ መሳርያ እየተላከበት ያለውን ይህን ሽብር በመግለጫ ሊያስተባብሩት አይችሉም!
ጎንደርና ዳባት ላይ የሚነሱት ጉዳዮች የመንግስት ብቻ ችግር ስላልነበር ነው ለማቀዛቀዝ የጣርነው። ሁሉም በየፊናው ችግሮች ስላሉበት፣ እነዚህ ችግሮች ጎንደር ከተማን እየረበሹ ስለሆነ ነው በሽምግልና እንዲያልቅ የተደረገው። ከሰኔ 15 በኋላ አማራው ላይ ሌላ ደንቃራ እንዳይከሰት ነው ነገሮችን ለማረጋጋት የተጣረው። ፋኖን ግፋ ያለውንም፣ ፋኖን አጥፊ ያደረገውንም ለማረጋጋት የሞከርነው እውነታው ከሁለቱም የተለየ ስለሆነ፣ ለአማራው የሚጠቅመውም እውነታው ስለሆነ ነው። ሆኖም እነዚህ ችግሮች የማይፈቱ አይደሉም። እንነጋገር በተባለው መሰረት ጥሩ ውይይት እየተደረገ ነበር። በኮሮና ወረርሽኝ ቅድሚያ መሰጠት ስለነበረበት ለኮሮና ቅድሚያ ተሰጥቷል። ኮሮናን በቀዳሚነት መከላከል የነበረበት መንግስት ግን ወደ ጎንደር መመርመሪያ መሳርያ ከመላክ ይልቅ ከኮሮና በላይ እያሸበረ የሚጨርስ ከባድ መሳርያ ልኳል። በዚህ ወቅት መከላከያ የሚልኩበትን ምክንያት በመግለጫ ሊያስተባብሉት አይችሉም። እውነታው ሕዝብን ለማሸበር ነው!
የአካባቢው አስተዳደር “ከአቅሜ በላይ ነው” ሊል አይችልም። ከአቅሜ በላይ ነው የሚለው ጉዳይ ቢኖር እንኳ ከአማራ ሚሊሻና ልዩ ኃይል አቅም ውጭ የሚሆን ጉዳይ የለም። ይህ ሁሉ ባይሆን እንኳ በዚህ መጠን ከባድ መሳርያ እያሳዩ የሚያሸብሩበት ችግር የለም። ወቅቱም ለሕዝብ የሕክምና ቁሳቁስ የሚጫንበት እንጅ ከባድ መሳርያ የሚጫንበት አልነበረም። መከላከያ ለመግጠም ሳይሆን ለወረርሽኙ የወጣውን እገዳ የሚያስከብርበት እንጅ ጦርነት የሚጠራበት አልነበረም።
በመግለጫ አይስተባበልም። ክህደት ነው! ገዥዎቹን ከተጣባቸው ፀረ አማራነት የመጣ ነው! የፋኖ ጉዳይ በውይይት የሚፈታ፣ ችግሮቹ በውይይት የሚቀረፉ፣ አማራጭ ተፈልጎለት ወደ ከፋ ሁኔታ እንዳይሄድ መፍትሄ የሚበጅለት ነው። ይህኛው ግን ከፋኖ ጋር የሚደረግ አይደለም። በአማራ ህፃናት፣ እናቶች ላይ የታወጀ፣ ወረርሽኝ ፈርቶ ቤቱ የተቀመጠን ሰላማዊ አማራ ሁሉ የሚያሸብር ተግባር ነው።