የኮሮና ቫይረስን አቅልሎም ሆነ አክብዶ መመልከት ለአደጋ ያጋልጣል-ተባባሪ ፕሮፌሰር ትዕግሥት ውሂብ

የኮሮና ቫይረስን አቅልሎም ሆነ አክብዶ መመልከት ለአደጋ ያጋልጣል-ተባባሪ ፕሮፌሰር ትዕግሥት ውሂብ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰር ትዕግሥት ውሂብ (ዶ/ር)፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የመረበሽ ስሜት እና ነገሮችን አቅልሎ የማየት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል።
ይህ ደግሞ ከሥነ ልቦና ዝግጁነት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ችግሩን በልኩ ተመልክቶ ተገቢው የጥንቃቄ እና የመከላከል እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጥ እና መረጃን ተደራሽ የማድረግ ተግባራት ሊከናወኑ ይገባል ብለዋል።
በሽታው አዲስ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ተገቢው መረጃ ከሌለው እና ግንዛቤ ተፈጥሮለት የስነ ልቡና ዝግጅት ካላደረገ በተለያዩ አገሮች ከሆነው እና እየሆነ ካለው ጋር በማያያዝ የመረበሽ ስሜት ውስጥ ሊገባ ይችላል ሲሉ ዶ/ር ትዕግሥት ተናግረዋል።
በአንጻሩ በሌሎች አገራት ያለውን ሁነት በኢትዮጵያ ካለው ጋር በማነጻጸር የተከሰተውን ነገር አቅልሎ የማየት እና ችግሩ በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት እንደማያደርስ አድርጎ የመመልከት አዝማሚያ ውስጥ መግባት በከፍተኛ ሁኔታ ለቫይረሱ ተጋላጭ ያደርጋል በማለት አስጠንቅቀዋል።
የኮሮና ቫይረስን ከልክ በላይ አግዝፎም ሆነ አቅልሎ መመልከት በሀገራችን በስፋት እንደሚታይ የጠቀሱት ባለሞያዋ፣ ችግሩን ከሚገባው በላይ አግዝፎ በማየት እና በጣሙን በመረበሽ በሥራ አካባቢም ሆነ በሌሎች ማኅበራዊ መስተጋብሮች ውስጥ የሚገለጽ ትልቅ የፍራቻ ስሜት ተፈጥሯል ብለዋል።
ዶ/ር ትዕግሥት መጠንቀቁ ተገቢ ቢሆንም የበዛ ፀጥታ እና ነገሮችን ሁሉ ከኮሮና ጋር አያይዞ ማየቱ ትልቅ የሥነ ልቦና ጫና ፈጥሯል።
በአንጻሩ ችግሩን አቅልሎ ከማየት እና እኛ/እኔ ጋር አይከሰትም ብሎ በማሰብ ብዙ የግዴለሽነት ተግባራት ይስተዋላሉ፤ ይህ አመለካከት ችግሩን የማባባስ እና ራስንም ሆነ ሌሎችን ለበሽታው ተጋላጭ የማድረግ አካሄድ መሆኑ መታወቅ ይገባዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ ሳይረበሽም፣ ግድየለሽ ሳይሆንም ተገቢውን ግንዛቤ ፈጥሮ ችግሩን የመከላከል አካል በመሆን ራሱንም፣ ሌላውንም እንዲጠብቅ ማስቻል ያስፈልጋል ሲሉ ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል።
ምንጭ:- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት