" /> የህዳሴ ግድብ ግንባታ 72 በመቶ መጠናቀቁ ታውቀ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

የህዳሴ ግድብ ግንባታ 72 በመቶ መጠናቀቁ ታውቀ

የህዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ ሒደት 72 በመቶ መድረሱን መንግሥት አስታወቀየታላቁ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ የግንባታ ሒደት 72 በመቶ እንደሚገኝ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ለሪፖርተር ጋዜጣ አስታውቀዋል። የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎቹ ከ42 ነጥብ 3 በመቶ በላይ የደረሱት የህዳሴው ግድብ፣ እንደ አዲስ እየተገነባ የሚገኘውና በርካታ ችግሮች አጋጥመውት የነበረው የሲቪል ስትራክቸር የግንባታ ሒደትም ከ20 በመቶ በላይ አፈጻጸም ማስመዝገቡን ተገልጿል።የግድቡ ግንባታ እየተፋጠነ ስለሆነ በአሁኑ ወቅት 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ማከማቸት የሚችልበት አቅም ላይ እንዲደርስ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡
ውኃው በክረምቱ ወራት በግድቡ ውስጥ ተጠራቅሞ፣ 700 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚያስችሉ ሁለት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን የመሞከርና የሙከራ ኃይል ማምረት እንደሚጀመር ለሪፖርተር ጋዜጣ አስረድተዋል፡፡ ይህም በመጪው ዓመት የካቲትና መጋቢት ወራት ውስጥ እንዲካሄድ መታቀዱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህን ያህል መጠን ያለው ኃይል ለማምረት የተከማቸ ውኃና የልቀት መጠን ላይ የሚመሠረት ቢሆንም፣ በክረምት ወራት በግድቡ ውስጥ የሚከማቸው ውኃ ከ565 ሜትር ከፍታ ላይ ሊደርስ እንደሚችል ይታሰባል።የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ ሒደት ለግብፅም ሆነ ለሌሎች የተፋሰሱ አገሮች መረጃዎች በግልጽ ቢቀርብላቸውም በግብፅ በኩል ግን ከፍተኛ ተቃውሞና ቅስቀሳዎች ሲደረጉበት መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ግብፅ በቅርቡ በአሜሪካ አድሏዊ የድርድር ዳኝነት አማካይነት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር መሞከሯ ያሰበችውን ውጤት ባለማስገኘቱ መጠነ ሰፊ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ዘመቻ ከፍታለች፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሳሚ ሽኩሪ የተመራ ልዑክ በአፍሪካና በእስያ በመንቀሳቀስ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሞክሯል፡፡ኢትዮጵያም የግብፅን የተሳሳተ አካሄድ የአፍሪካ እና የአውሮፓ አገራት እንዲገነዘቡት ለማስቻል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴንና የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን፣ እነዲሁም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በማሰማራት እውነታውን እንዲያስረዱ በማድረግ ላይ ትገኛለች።

 


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV