በዘመናት መካከል ቁመናል – አንዱዋለም አራጌ

(የአንድነት ሃይሉን በጋራ ለማንቀሳቀስና ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሐሳብ ላይ የተመረኮዘ ግላ አማራጭ ለማቅረብ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች፣ አንጋፋው የቀድሞ አንድነት ም/ፕሬዘዳንት የሕሊና እስረኛ አቶ አንዱዋለም አራጌና ፣ የቀድሞ የፓርላማ አባል የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉና በርካታ የቀድሞ አንድነቶች ያሳተፈ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል። በዚህ ወቅት በተደረገው ስብሰባ፣ አቶ አንዱዋለም አራጌ “ በዘመናት መካከል ቆመናል በሚል ርእስ ያደረጉትን ንግግር ከዚህ በታች አቅርበናል።)

——————————–

አጠር ያለውን ንግግሬን ከመጀመሬ በፊት ጥቂት ነገሮችን ለማለት ይፈቀድልኝ፡-

ድንገት ካወቃችሁኝ በብዙዎቻችሁ ዘንድ ከፖለቲከኛነቴ ይልቅ በእስረኛነቴ ይመስለኛል፡፡ በፖለቲካ እስረኛነቴ፡፡ አሁን ከፖለቲካ እስረኛነት ወደ ፖለቲከኛነት ለመሸጋገር የስነ – ልቦና ዝግጅት በማድረግ ላይ እገኛለሁ፡፡ የእስረኛነት ስሜት እንደልብስ በቀላሉ አውልቆ የሚጥሉት አይደለም፡፡ ለተወሰነ ጊዜም አብሮኝ ይቆያል፡፡የህይወቴ አካልም ሆኖ ይዘልቃል፡፡ ብዙዎቻችሁ ስለ እኔና ስለሌሎች እስረኞች እንደ ፀለያችሁ፤ በልባችሁ እንዳነባችሁ፤ በተለያየ መንገድ ስለዕውነት፣ ስለፍቅርና ስለፍትህ እነደታገላችሁ አምናለሁ፡፡ ለፀሎታችሁ ምላሽ የሰጠውን ፈጣሪና በአካል ከእኛ ጋር ባትታሰሩም በመንፈስ ለዓመታት አብራችሁን የታሠራችሁ የሀገሬን የኢትዮጵያን  ልጆች ሳላመሰግን ወደ ውይይቱ ብገባ ተገቢ ሆኖ አላገኘውም፡፡ ከዓመታት በኋላ በዚህ መልክ እንድንገናኝ የረዳ ፈጣሪ ክብር ምስጋና ይግባው፡፡ እናንተም ለዓመታት በተለያየ መንገድ መታገላችሁ ሳያንስ ከእስረኛስ ምን ፍሬ ያለው ነገር ይገኛል ሳትሉ በዚህ ሁኔታ ስለታደማችሁ ከልቤ ዝቅ ብዬ ከፍ ያለ መስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡

ሰማያዊ ፓርቲም ይኽንን የመሠለ ደማቅ፤ መድረክ ወሳኝና ወቅታዊ በሆነ አጀንዳ ላይ በማዘጋጀቱ ታላቅ ምስጋናዬን እናዳቀርብ ይፈቀድልኝ፡፡

የተዘጋጀሁበት ርዕስ – በዘመናት መካከል ቁመናል የሚል ነው፡፡ ይኽን የመሰለውን የመወያያ ሀረግ ብጠቀምም በማስታወቂያው ላይ እንደተመለከትነው በዋናነት ትኩረት የማደርገው የፖለቲካ መስመሮች ላይ ይሆናል፡፡ ምንአልባት በመሳታወቂያው ላይ የተመለከትነው ‹‹የሀሳብ ፖለቲካ›› የሚለው ሀረግ የሚያወያይና አሻሚ ነው፡፡ በብሔር የተደራጁ ወገኞችም ቢሆኑ የቆሙት ወይንም የወከሉት ሀሳብን አይደለም ወይ? የሚል አመክኖያዊ ተጠየቅ ያስነሳል፤ ሊነሣም ይገባዋል፡፡ በብሄር መደራጀትም በራሱ ስርየት የሌለው ሀጢያት ነው ብዬ አላምንም፡፡  ለእኔ ስርየት የሌለው ሀጢያት የህዝብን ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት መብት በሃይል መግሠስ  ነው፡፡ ህዝብ የትኛው አመለካከት ይበጀናል ብሎ እነዳይወስን ማፈን መቼም የቅር ልንለው ማይገባን ደዌ ነው፡፡ አጥብቀን ልንታገለው የሚገባን ነቀርሳ እኔ አውቅላችሁ አላሁ ባይነትነው፡፡

ነገር ንግ በብሔር መደራጅ መብት መሆኑን ብቀበልም፤ ስርየት የሌለው ሀጢያት አይደለም ብዬ ባምንም ፤ እንደየፖለቲካ አስተሳሰብ ግን በጣምም የምነቅፈው በጣም ጎጂ መሆኑን አፅንኦት ሰጥቼ የምታገለው አስተሳሰብ ነው፡፡ የብሔርን አስተሳሰብ ባልደግፍም ህብረ – ብሔራዊ አስተሳሰብ ለማራመድ የተሰለፉ ወገኖች የሚጎናፀፉት መብት ሁሉ ለብሔር መብት አቀንቃኝ ወንድሞቼና እህቶቼ ሁሉ ሊከበርላቸው እንደሚገባ ለአፍታ እንኳን ተጠራጥሬ አላውቅም፡፡ እኔና እኔን መሰል አያሌ ኢትዮጵያውያን የታገልንለት የምንታገልለት ትልቅ ዓላማ ህብረ – ብሔራዊ የፖለቲካ መስመር ነው፡፡

ሀሳቡን ለማፍታት ያህል ይህችን ታክል ካወሳው ውይይታችንን ለማበልጸግ ይረዳን ዘንድ  በወፍ በረር  የኋላውን ታሪካችንን ጨልፈን እንይ፡፡ ከፖለቲካ አደራጃጀት ጋር በተያያዘ ትንሽ መቃኘት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ የወዳጀትን አስፈላጊነት ቀደሞ የተረዳው ገርማሜ ንዋይ ይመስላል፡፡ ከወንድሙ ከጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ጋር የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ከማድረጋቸው በፊት በተደጋጋሚ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው የሚመስሉ ስብስቦችን ለመፍጠር ከሦስት ያላነሱ ሙከራዎችን ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡ ይሁን እንጂ ውጤታማ አልሆነም፡፡ አደረጃጀቱ ግን የየትኛውን ብሔር ጥያቄ ይመልሳል ከሚል ሳይሆን በአጠቃላይ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን ይመስላል፡፡ መፈንቅለ መንግስቱ ከከሸፈ በኋላም በተከተሉት አያሌ ዓመታትም ቢሆን ብዙሃን ተማሪዎች  አደረጃጀቶች ህብረ – ብሔራዊ የአስተሳሰብ መስመርን የተከተለ ነበር፡፡ የተማሪው እንቅስቃሴ የወለዳቸው ዋናዎቹ ፓርቲዎች መኢሶንና ኢህአፓን እንኳን ብንወስድ ህብረ – ብሔራዊ የአሰተሳሰብ መስመርን በመከተል ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ይበጃል ያሉትን ለውጥ ለማምጣት መታገላቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ ዋለልኝ መኮንን የብሄሮች መብት መከበር ጉዳይ ሲያነሣም ተገቢው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አስታውሦ በተለይም ስለዓለማቀፋዊነት እያወሩ በብሔር ተኮር ጉዳይ መታጠሩ ለእርሱም እሩቅ የማይወስድ ሆኖ እንዳገኘው ይገመታል፡፡

ብሄር ተኮር ሀሳብ ቀድሞ ስላልተነሳ ለዘላለም አይነሣ ልንል ግን አንችልም፡፡ ሰዎች ሁሉ የመሠላቸውን ሀሳብ ያራምዱ ዘንድ መብታቸው ነውና፡፡ ዋናው ቁም ነገር ሀሳቡ ምን ያህል አመክንዮአዊና ጠቃሚ ነው የሚለውን የሀሳብ ክር መዞ ማየቱ ነው፡፡

የተማሪው ትግል በደርግ ተመትቶ ሲበታተን የተመታው የተማሪው ትግል ብቻ ሳይሆን ህብረ – ብሐራ አስተሳሰብም ጭምር ይመስላል፡፡ ከደርግ ጡጫ የሸሹት ተማሪዎች ብሔር ተኮር አስተሳሰብን እንደሁነኛ የትግል መሣሪያ ወሰዱት ደርግ ሲወድቅም ስልጣን መንበሩን የተቆናጠጡት በብሔር አስተሳሰብ የቀሰሱ ወገኖች ሆሙ፡፡ የህወሓት ፊትአውራሪዎች ከየብሔሩ ጥቂት ሰዎችን በመመልመል የክርስትና ስም እየሰጡ የየብሄሩ ወኪሎች ናችሁ ብለው ሰደሯቸው፡፡ አፈ – ሙዝ ያነገሣቸው ገዣዎች ብቻቸውን በሚናዝዙባቸው የመገናኛ- ብዙሃን የህብረ – ብሔራዊ አስተሳሰብ ሞቶ እንዲቀበር ያላቸውን ሁሉ ተኮሱበት፡፡  ቀብረነዋል መቃብሩን ፈልቅሎ አይነሣም ሲሉ ፍፁም ታምራዊ በሚመስል ሁኔታ በ1997 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ ህብረ – ብሔራዊ አስተሳሰብ ሰማይ ምድሩን ሞልቶ ቆመ፡፡

ሕብረ – ብሔራ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ለህብረ- ብሄራዊ አስተሳሰብ ያለውን ትልቅ ዕምነት ባገኛት ቲኒሽ የነፃነት መስኮት ለአገዛዙ ብቻ ሳይሆን ለዓለምም ይፋ አደረገ፡፡ አገዛዙ የነፃነት መስኮቷን ጠርቅሞ ዘጋት፡፡ ሕብረ – ብሔራዊ አስተሳሰብ ያላቸው ፓርቲዎች የአገዛዙ ሰይፍ ሰለባዎች ሆኑ፡፡ ፓርቲዎች ከይስሙላ ያለፈ ሚና እንዳይኖራቸው አገዛዙ ወሰነ፡፡ የእግር ቆረጣ ታክቲክ ወደ አንገት ቆረጣ ተሸጋገረ፡፡ ህብረ -ብሄራዊ አስተሳሰብን የሚያራምዱ ፓርቲዎች ከፖለቲካው ገጸ – ምድር ተወገዱ፡፡ ብሔር ድርጅቶች ተኮለኮሉበት፡፡ ኢትዮጵያ በብሔር ፖለቲካ ተሰቅዛ ተያዘች፡፡ በታሪክና በባህል ብቻ ሳይሆን በደምና ስጋ የተገመዱ ኢትዮጵያውያን አንዱ ለሌላው ጠበቃ መሆኑ ቀርቶ አንዱ ለሌላው ስጋት ተደርጎ የሞቄጠርበት እና የኢትዮጵያን መሠረት የሚያናጋ የከፋ አፈፍ ጠርዝ ላይ ቆምን፡፡ የኢትዮጵያን ስምና ታሪክ ከሚጸየፈው የኢህአዴግ መሪዎች ስብስብ ውስጥ ኢትዮጵያን የሚያንቆለጳጵሱ ሰዎች ብቅ አሉ፡፡ ዶ/ር አብይንና አቶ ለማን ማለቴ ስለመሆኑ ማንም አይስተውም፡፡

ከሌሎች የኢህአዴግ መሪዎች በተለየ ስለኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚበጀውን ሀሳብ በሚያማልሉ ቃላት የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ውስጥ የተቀበረውን እውነት መልሰው ነገሩት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ስለነገ እርግጠኛ ባይሆንም ስለመልካም ቃላቶቻቸው ግን ምስጋናን አልነፈጋቸውም፡፡ ይሁን እንጂ ዛሬም እንደ አዲስ ኢትዮጵያውያን ዘር ለይተው እየጠገዳደሉ ነው፡፡ የዘር ፖለቲካ ጠንቅ አሁንም የኢትዮጵያ ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ስለኢትዮጵያውያን በእኩልነት ጥብቅና እንደሚቆሙ ፍኝጭ የሰጡት ዶ/ር አብይ ቢሆኑም እስከ ትናንት ማታ ድረስ ከየአካባቢው ህይወታቸውን በወገኖቻቸው ስለሚነጠቁ፣ በግፍ ስለሚፈናቀሉ ወገኖች እርምጃ መውሰድ ይቅርና በአቋም ደረጃ እንኳን የጠራና ጠንካራ አቋም ሲወስዱ አልተስተዋሉም፡፡

መፍትሄውም ምንም እንኳን መሪ ቢሆኑም ከአንድ  ከእርሳቸው ብቻ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ የብሔር አስተሳሰብን እንደ ችግኝ እያፈላ ኢትዮጵያን የውድቀት አፋፍ ላይ የጣላው ኢህአዴግም ለችግሩ ምፍትሄ ይሆናል በሚል መጠበቁ ተገቢ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚገባውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ሃላፊነት የሚወስድበት እንጂ ቁጭ ብሎ ሌሎችን የሚጠብቅበት አይደለም፡፡ አንባገነኖች ስልጣንን ያለአግባብ ሲጠቀሙ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሁሉ ዜጎችም ኢትዮጵያ በብሄር ፖለቲካ ተሰቅዛ ኢትዮጵያውያን በጥፍራቸው እንዲራመዱ ሲገደዱ ምንም አለመፈየድ ከተጠያቀዊነት አያድናቸውም፡፡ ተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን ነገ ሌሎችን የሚበላው እሳት እነርሱን ስላለመብላቱ እርግጠኛ መሆን አይችሉም፡፡ መፍትሄው ሁሉም ስለአንዱ አንዱ ስለሁሉም መታገል ነው፡፡ ይኽንን ዘርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሸፍጥ ያስከተለውን ችግር ሳይውል ሳያድር የመፍታት ሃላፊነት እያንዳንዳችን ለይ ወድቋል፡፡

ቀደም ብዬ እንደተቀስኩት ስልታዊ በሆነ መልኩ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ውክልና የሞቆም አስተሳሰብ በሀይል ቢመታም የኢትዮጵያውያን ልብ ግን አሁንም ወንድማማችነትን መሰረት ላደረገ ህብረ – ብሔራዊ አስተሳሰብ የተመቸ ስለመሆኑ ከፍ ብለን አይተናል፡፡ የአንዱ መብት መከበር ከሌላው መብት ተቆርሶ የሚሰጥ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን መብት በእኩልነት ሊከበር እንደሚችል ለኢትዮጵያውያን ግልፅ ነው፡፡ መብት የእኛና የእነርሱ ተብሎ የሚተው አይደለም፡፡ የአንዱ መብት መገፈፍ የሁሉም መብት መረገጥ ነው፡፡ አንዱ ከሌላው ያነሠም ሆነ የበለጠ መብት የለውም፡፡ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚደረግ ትግል ለአንድ ወይንም ለሁለት ብሄሮች ብቻ ጥብቅና በመቆም የሌላውን መብት መገፈፍና ሞት እንደከንቱ አይቆጥርም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ የሚፈፀም ጭቆና እያንዳንዳችን ላይ የተፈፀመ ጥቆና ነው፡፡ የሀይማኖት የፆታ የብሔር ወይንም የእምነት ልዩነት ከሰብዓዊነት በላይ አይሆንም፡፡ ለዚህም ነው ዶ/ር ማርቲን ኩተር ኪንግ “ሁላችንም የተጠቀለልንበት ግምጃ ሰብዓዊነት ነው”ያሉት፡፡

አሁን በሀገራችን የብሔር ፖለቲካ የቀፈቀፋቸው ችግሮች ከሰብዓዊነት ጠርዝ የወረዱ ከመሆናቸውም በላይ እየተፈጸመ ያለው ወንጀል በዓለም አቀፍ ህግጋት ማዕቀፍ ስር ሲታይም ትልቅ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ crime against humanity (በሰው ዘር ላይ የተፈፀመ ወንጀል) ነው፡፡ የኢትዮጵያን ህገ – መንግስትም ም ቢሆን በግልፅ የሚጥስ ወንጀል ነው፡፡ የዚህ ወንጀል መሠረቱ ደግሞ ብሄርን መሠረት ያደረገው ፖለቲካ ነው፡፡ ዜጎች በብሔር ሊደራጁ በየብሄራቸው ደጃፍ ላይ ቆመው የላሌውን ወገናቸውን ሞት ያያሉ፡፡ አንዳንዴም እኩይ ሀሳብ ላነገቡ ልሂቃንም መጠቀሚያ በመሆን በወገናቸው  ላይ የሞት መልክተኞች ይሆናሉ፡፡ በየተራና በተናጠል ይጠቃሉ፡፡ ለሚጨቁኑን ሃይሎች ተመቻችተን እንገኛለን፡፡ ሳይጠይቁን ለመጋለብ ተጎንብሰብ እንገኛለን፡፡ ለዚህም ነው ገጣሚው ፡-

ሀገሬ ተባብራ ካረገጠች  እርካብ

ነገራችን ሁሉ የእንቧይ ካብ፤ የእንቧይ ካብ

ያለው ፡፡

የህብረ – ብሔራዊ አስተሳሰብ ሰውን ሰብዓዊ ከሚያስኘው ባህሪው ጋር በእጅጉ ይቆራኛል፡፡ የሌለላው ዜጋ መብት ሲረገጥ ሌላው ሰው የሚያሰኘውን ክብሩን እንደተገፈፈ ይወስዳል፡፡ በመሆኑም በምንም አይነት አጥር ሳይገድብ ይታገላል፡፡

ለሌላ ከመታገል በዘለለ ከሁሉ ለከበረውና ሰው ለሚያሰኘው ማንነቱ ዘብ ይቆማል፡፡  የሌላውን ሰው የስቃይ ጩኽት አለመስማት ኢ -ሠብዓዊነት ነው፡፡ ከዚያም በላይ በሁላችንም እየተቃጣ ያለን ጥቃት አለመከላከል ነው፡፡

በብሔር ላይ የተመሰረተ አስሳሰብ ከትብብር ይልቅ ውድድርን፣ ከመተማመን ይልቅ መጠራጠርን፣ ከአቃፊነት ይልቅ  ገፊነትን አሁን እንደምናየው ደግሞ ከገፊነት ወደ መጠፋፋት አፋፍ የሚገፋ መሆኑን በመከራም ቢሆን እየተማርን ነው፡፡ ትልቁን ሰብዓዊ ነገራችን እየተውን ወደሚያጠፋፋን የቲኒሽነት አዘቅት እየወረድን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያዊነትን ለመደድፈቅ የተደረገ ሁሉን አቀፍ ዘመቻ ውጤት ነው፡፡ ዜጎች ከጎሣ ባለፈ እነዳያስቡ ፤ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብኩ ደግሞ መፈናፈኛ እንዲያጡ በመገደዳቸው ዛሬ ባለንበት ሁኔታ እንድንገኘ ተገደናል፡፡ ይኽንን የአዘቅት መንገድ ተከትለን ወደ ውድቀት ጉርጅ እንውረድ ወይንስ አንዱ ስለሁሉም ሁሉም ስለአንዱ የሚታገልበትን ህብረ -ብሔራ የፖለቲካ ቀመርን ተከትለን ከምንገኘበት የውድቀት አፋፍ ወደ ሰላም፣ ወንድማማችነትና ስበዓዊ ስዕልና ኮረብታ እንውጣ?

ከብዙ ዓመታት ትግልና ከአያሌ ዜጎች መስዋዕትነት በኋላ የተስፋ ጭላንጭል እያየን ነው፡፡ ይኽንን ሁኔታ እንዴት እንጠቀመው? እንደከዚህ ቀደሙ በየቤታችን ሆነን በማዘን ጥቂቶች ታግለው ነፃ እንዲያወጡን በመጠበቅ ወይንስ የምናልማትን ኢትዮጵያን ለመጨበጥ እጅለእጅ ተያይዘን እንታገል? ተለያይተን እንጠፋፋ ወይንስ ተባብረንና ተመካክረን ጠንካራ ሀገር ለልጆቻችን እናርስ? የጠንካራ ሀገር መሠረት፣ የሰብዓዊ ልዕልና ሁሉ ዋስትናና የዘላቂ ሰላም ምንጭ ህብረ – ብሔራ አስተሳሰብ ስለመሆኑ አሁን የምንገኝበት ሁኔታ የማያብል እማኝነቱን ይሰጣል፡፡

ህብረ – ብሔራ አስተሳሰብ ወይንም አደረጃጀት ለአንዱ በሩን ከፍቶ ለሌላው አይዘጋም፡፡ የዘር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የፆታ፣ የመደብ፣ የሞያና ሌሎች አጥሮች አይገድቡትም፡፡ በዜጋው እኩልነትላይ ተመስርቶ ለዜጋው ልዕልና ሁሉም ትግል የሚያደርግበት መድረክ ነው፡፡

እናም ከዚህ በፊትም እንዳልኩት በዘመናት መካከል ቁመናል፡፡ ዶ/ር ማርት ሉተር ኪንግ እንዳሉት እየተጠቃ ላለ ወገናችን ባንደርስለት ምን ይሆናል?ብልለን እንጠይቅ ወይንስ ለእርሱ ደህንነት ጥብቅና ብቆም ምን ይደርስብኛል ? ብለን እንጠይቅ እኔ ጥቃት እየደረሰበት ላለ ወገኔ ባልደርስለት ምን ይሆናል? ለሚለው ጥያቄ መልስ መስጠትን መርጫለሁ፡፡ ምክንያቱም ስለራሴ መብት ዋስትና የማገኘው የወንድሜ መብት ሲከበር ነውና፡፡ ስለአንድነት እያወራን ልዩነትን የማንኮተኩትበት ዘመን ሊሆን ይገባል፡፡ ዶ/ር ኪንግን በድጋሚ እጠቅሳለሁ “የምንከተለው መንገድ የምንደርስበትን ግብ ያህል ንፁህ ሊሆን ይገባዋል”፡፡ አዎ በዘመናት መካከል ቁመናል፡፡  በሰላምና በጦርነት ዘመናት መካከል ቁመናል፡፡ በጭቆናና በነፃነት ዘመናት መካከል ቁመናል፡፡ በግፍና በፍትህ ዘመናት መካከል ቁመናል፡፡  በችጋርና በብልፅጋና ዘመናት መካከል ቁመናል፡፡ በጥላቻና በፍቅር ዘመናት መካከል ቁመናል፡፡ አዎ በዘመናት መካከል ቁመናል፡፡ መጭውን ዘመን የሰላም፣ የነፃነት፣ ፍትህ፣ የአንድነት፣ የክብር ፤ የብልፅግናና የፍቅር ልናደርገው ፈፅመን እንችላለን፡፡

አንዱ ስለ ሁሉም ሁሉም ስለአንዱ የሚታገሉበት ህብረ -ብሔራዊ መንገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ መድህን የሚሆንበትን ዘመን አሁን ነው፡፡ አዎ በዘመናት መካከል ቆመናል፡፡

                   ዘመኑን የሚመጥን ትግል ለማድረግ ሁላችንም እንነሳ

                                         ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ

 

 

 


► መረጃ ፎረም - JOIN US