የአስተዳደር ወሰን ሳይሆን የዘር ክልል ነው ያለን #ግርማ_ካሳ

በአዋሳና በወላይታ ሶዶ እየሆነው ያለው ነገር ልብን የሚያዳማ ነው። ማሳዘን ብቻ ሳይሆን አንገትን የሚያስደፋ ነው። አለም የትናየት በደረሰበት ዘመን፣ በጎጥና በጎሳ ተከፋፍለን በዘር መባላታችን መቼ እንደሚቆም አላውቅም። ትንሿ ችግር በቀላሉ ወደ ዘር ግጭት እየተለወጠች ትልቅ ቀውስ መፍጠሯ የተለመደ እየሆነ ነው። ይሄ ላለፉት 27 አመታት በአገራችን የተዘረጋው የዘር አወቃቀር የፈጠረው ችግር ነው። “ይሄ አገር የዚህ ዘር፣ ያ መሬት የዚያ ዘር” እየተባለ አገሪቷ በዘር ተሸንሽናለች። ዜጎች በአገራቸው ለነርሱ ዘር ከተመደበው ቦታ ውጭ ሲሄዱ እንደ መጤ ነው የሚቆጠሩት።

አንድ አካባቢ ብቻ ላይ፣ ከማንም ጋር ሳይደባለቅ የሚኖር ብሄረሰብ አለ ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። በብዙ ቦታዎች ብዙ ብሄረሰቦች በአንድ ላይ ይኖራሉ። ሸዋ፣ ሜኤሶ፣ ባቢሌ፣ ጉርሱም፣ ሞያሌ፣ ጠለምት፣ ጠገዴ፣ ዲላን እንደምሳሌ ብንወስድ አንድ ወቅት በነዚህ አካባቢዎች ዜጎች በሰላም በፍቅር ነበር የሚኖሩት። ተዋልደው። ተዛምደው። ተደባልቀው። በሞያሌ አካባቢ ሰፋ ያለ ቦታ ላይ የሚኖሩ የጋሪ ማህበረሰብ አባላት አሉ። ጋሪዎች ኦሮሞ ነንም ይላሉ፤ ሶማሌ ነንም ይላሉ።ኦሮሞነት ወይንም ሶማሌነት ብቻ በተናጥል አይገልጻቸውም። ሶማሌነትና ኦሮሞነት በጋራ ነው የሚገልጿቸው። ይሄን ማህበረሰብ “ኦሮሞ ነህ ፤ኦሮሞ ክልል ግባ፣ ሶማሌ ነህ ሶማሌ ክልል ግባ” ስትሉት ችግር መፍጠሩ አይቀርም። ችግርም ፈጥሯል። በወልቃይት ጠገዴ ትግሬ፣ አማራ ሳይባባል ህዝቡ ለዘመናት በሰላምና በፍቅር የኖረ ነው። ትግሪኛ ይናገራል፣ አማርኛ ይናገራል።ሲያሻው ጎንደር፣ ሲያሻው ሽሬ ሄዱ ይነግዳል፣ ይሸምታል። ተዋልዷል። ተደባልቋል። የወልቃይት ሰዎች አማርኛ መናገራቸው ተረስቶ፣ ትግሪኛ ስለተናገሩ ብቻ “ትግሬ ናችሁ” ተብለው ወደ ትግራይ እንዲጠቃለሉ ተደረገ። መሬታቸውም የትግሬ ነው ተባለ። “ትግሪኛ መናገራችን ትግሬ አያሰኘንም፣ አማርኛም ተናጋሪዎች ነን፤ አማራ ነን፣ ወልቃይት የአማራ ነው” በሚል ለትግራይ ብሄረተኝነት ምላሽ ይዞ የአማራ ብሄረተኝነት ብቃ አለ።

ከላይ የተጠቀሱት አንድ የነበሩ አካባቢዎች ከተሞች/ወረዳዎች/ዞኖች በዘር ተከፋፍለው፣ ማህበረሰባዊ ትስስራቸው እንዲላላ ከመደረጉ የተነሳ ብዙ ግጭቶች ተከሰቱ። ሚዔሶ ሶማሌ/ ሚዔሶ ኦሮሞ፣ ባቢሌ ሶማሌ፣ ባቢሌ ኦሮሞ፣ ጉርሱም ሶማሌ/ጉርሱም ኦሮሞ፣ ሞያሌ ሶማሌ፣ ሞያሌ ኦሮሞ፣ ጠለምት አማራ /ጸለመት ትግሬ፤ ጠገዴ አማራ /ጸገዴ አማራ፣ ሰሜን ሸዋ/ኦሮሞ ሰሜን ሸዋ /አማራ፣ ዲላ/ጊዴዎ፤ ዲላ/ኦሮሞ ….ተብሎ ዘር በመለየት ብቻ ከተሞች፣ ወረዳዎች ተበጣጠሱ።

ወገኖች የዘር ፖለቲካው ጎድቶናል። ቆም ብለን ካላሰብን ወደ አላስፈላጊ እልቂት ነው የሚወስደን። ከወዲሁም ችግሮችን እያየን ነው።

– በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች አማራዎችን መጉዳት፣ ማፈናቀል፣ የተለመደ ሆኗል።

– ከቤኔሻንጉል ክልል አማራዎች መጤ ተብለው ተፈናቀለው፣ ተገድለዋል።

– በኦሮሞ ክልል በርካታ ሶማሌዎች ተገድለዋል። ወደ መቶ ሺህ የሚጠጉ ተፈናቅለዋል።

– በሶማሌ ክልል በርካታ ኦሮሞዎች ተገድለዋል። ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል።

_ በጌዲዮ ደቡብ ክልል ዞን እና በኦሞ ክልል ጉጂ ዞኖች መካከል ግጭት ተቀሰቀሶ በሺዎች ተፈናቅለዋል። ብዙ ጉዳት ደርሷል።

_ በሀረሪ ክልል ንፁሃንን መግደል፣ ማሳደድ ተጀምሯል።

_ በምስራቅ አማራ በኩል ከአፋር አዋሳኝ አካባቢዎች በኩል ግጭቶች ተቀስቅሰዋል።

– በበወልቃይት ጠገዴ ግዛቱ የትግሬ ነው የአማራ ነው የሚል ዉዝግብ አለ።

_ በጉራጌ ዞን፣ ጉራጌዎች ወልቂጤ ዙሪያ ያሉ የቀቤና ማህበረሰብ አባላት ላይ ጥቃት እንደፈጸሙ ተዘግቧል። ቀቤዎችም እንደዚሁ።

– በአዋሳ ሲዳማዎች በወላይታና የሌሎች ብሔር ተወላጆች ላይ ድብደባና ወከባ እየደረሰባቸው ነው። በወላይትና ሲዳማ ወጣቶች መካከል በዉቧ አዋሳ የዘር ጭፍጨፋ እየተመለከትን ነው። በወላይታ ሶዶም ተመሳሳይ ነገር አለ።

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ “ ሊያባሉንና ሊያጫርሱን ለተዘጋጁት የቀን ጅቦች ዕድል ልንሰጣቸው አይገባም ” ሲሉ በተለይም በአዋሳ በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ጥሪ አቅርበዋል። “ሁሉም ክልል ከኔ ወሰን ተወስዶብኛል እንጂ እኔ ወሰን ወስጃለሁ የሚል የለም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የክልል ድንበር የሚባል ነገር የለም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአስተዳደር ወሰን ነው “ ያሉት ዶር አብይ የህዝቡን ጥያቄ ለማዳመጥ ወደ ደቡብ ክልል እንደሚያመሩም ተገልጿል።

ዶር አባይ የአስተዳደር ወስን ነው ያለው ያሉት ፍጹም የተሳሳተ አባባል ነው። የአስተሳደር ወሰን ብቻ ቢሆን ኖሮ ያለው፣ በአስተዳደሩም ሁሉም ዜጎች የዘር ልዩነት ሳየደረግባቸው እኩል ቢታዩ፣ አንድ ቀበሌ ከአንድ አስተዳደር ወደ ሌላ አስተዳደር እንዲገባ ቢደረግ ምንም ችግር አይኖርም ነበር። ግን አሁን ያለው የዘር ክልል ስለሆነ፣ አንድ ቀበሌ ወደ ሌላ ቀበሌ ማዞር የአንድን ብሄረሰብ ማንነት እንደ መድፈር ነው የሚቆጠረው። ለዚህ ነው ለምሳሌ በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ ባሉ አካባቢዎች ኦሮሞ ያልሆኑ ቁጥራቸው ቀላል ስላልሆነ፣ አዲስ አበባን ባካተተ ሸዋ የሚባል፣ የኦሮሞ ማህበረሰም ከሌላው እኩል የሚታይበት፣ ኦሮምኛም የስራ ቋንቋ የሆነበት ሕብረ ብሄራዊ አስተዳደር ውስጥ ይካተቱ ስንል ጸረ-ኦሮሞ የምንባለው።

የዘር ክልል ሳይሆን ለአስተዳደር አመች የሆነ የአስተዳደር ወሰን ነው እንዲኖር የሚያስፈለልገው። ለዚህም ነው አሁን ያለው የዘር የክልል ፌዴራል አወቃቀር እንደገና መታየትና መሻሻል አለበት ብለን የምንከራከረው። ምን ችግር ነበረው “ይሄ መሬት የዚህ ዘር ነው” ሳይባል፣ ዜጎች የፈለገ ዘር ይኑራቸው በሁሉም የአገሪቷ ግዛቶች ልዩነት ሳይደረግባቸው ቢኖሩ ? ምን ችግር ነበረው ወልቃይቴው ትግሬም፣ አማራም ሳይባል እንደ ድሮው፣ እንደ በፊቱ፣ በፍቅር እንዲኖር ቢደረግ ? ምን ችግር ነበረው የጋሪ ማህበረሰብ ኦሮሞ ወይም ሶማሌ ከሚባል ኦሮማሌ ማንንቱን ይዞ ቢቀጥል ? ምን ችግር አለው መሬት በዘር ሽንሽኖ በመሬት ይገበኛል ደም ከሚፈስ መሬቱ የጋራ የሁሉም ሆኖ በጋራ ቢኖር ?

(ከዚህ በታች ያለው ፎቶ ልብን የሚያዳማ፣ በዉቢቷ አዋሳ በወላይታና በሲዳማ ወጣቶች መካከል የተከሰተውን የዘር ግጭት የሚያሳይ ነው)


► መረጃ ፎረም - JOIN US