“አሁን ያለው የፌደራሊዝም ሥርዓት የአማራውን ህዝባዊ አንድነት የሚገረስስ ሆኖ ነው ያገኘነው” – የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ

ላለፉት ቀናት የመስራች ጉባዔውን በባህር ዳር ከተማ ሲያከናውን የቆየው የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ፤ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ተጠናቅቋል። በዚህም መሠረት በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔን የፓርቲ ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል።

የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ክርስቲያን ታደለን በፓርቲው ምስረታ፥ ቀጣይ እርምጃዎች እንዲሁም በተነሱ ትችቶች ዙሪያ ቢቢሲ አነጋግሯቸዋል።

ቢቢሲ- በቅርቡ መስራች ጉባኤያችሁን አካሂዳችኋል፤ ምን ይመስል ነበር?

አቶ ክርስቲያን ታደለ- ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላ የስራ አስፈጻሚው ቁጭ ብሎ ተወያይቶ ነበር። ምስረታው ከጠበቅነው በላይ እጅግ ስኬታማ ነበር። ምስረታውም ትክክለኛ እንደነበረ አረጋግጦልናል። ይህ ጉዳይ የተወሰኑ አባላት ብቻ ጉዳይ አይደለም፤ በትንሹ ከ40 እስከ 45 ሚሊየን የሚገመተው የሁሉም አማራ ተወላጅ ጉዳይ ነው ብለን ነው የምናምነው።

በሃገራችን ህግ መሰረት አንድ ሃገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሰረት ቢያንስ 1500 አባላት ከአምስት ክልሎች ማስመዝገብ ስለሚጠበቅበት፤ እነሱን ነው ለምርጫ ቦርድ በመስራች አባልነት ያስመዘገብነው።

ቢቢሲ- የአጭር፤መካከለኛ እና የረጅም ጊዜ እቅዶቻችሁ ምንድናቸው?

አቶ ክርስቲያን ታደለ- እንግዲህ ሁሉም ሰው እንደሚከታተለው፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በየጊዜው ተለዋዋጭ እና እጅግ ፈጣን፤ ጊዜ የማይሰጥና ሌት ከቀን መስራት የሚጠይቅ ነው ብለን እናምናለን።

የአጭር ጊዜ ግባችን ድርጅቱን ለህዝቡ ማስተዋወቅ ነው። አደረጃጀቱን በከተማ፤ በገጠር እንዲሁም ምሁራን አካባቢ ማጠናከር እናስባለን። በሃገር ውስጥም ከሃገር ውጪም ያለውን የአማራ ተወላጅ እናደራጃለን። ከዚያም ቀጥሎ ሊመጣ የሚችለው፤ እንደ ሃገር በአሁኑ ሰአት በጣም ፈጣን የሚባሉ ውሳኔዎች እየተወሰኑ ስለሆነ፤ አማራውን በቁመቱ እና በወርዱ ሊወክለው የሚችል የፖለቲካ ፓርቲ የለም ብለን እናምናለን።

ከዚህ በኋላ ማንኛውም አማራውን የሚመለከቱ ድርድሮች እና ጉዳዮች ላይ ህዝቡን ወክለን የመካፈል እንዲሁም የአማራውን ዘላቂ ጥቅሞች፤ፍላጎቶች እና መብቶችን ለማስከበር ጥረት እናደርጋለን።

በቀጣይ ደግሞ 2012 ላይ በሚካሄደው ሃገር አቀፍ ምርጫ ላይ እንሳተፋለን። በኛ እምነት የፖለቲካ ስልጣን ላይ ያለው ስርአት፤ አማራው እያጋጠመው ላለው የህልውና አደጋ ዋናው ምንጩ ነው ብለን ነው የምናስበው።

ስለዚህ በምርጫ የፖለቲካ ስልጣን ይዘን ይህንን የተዛባ ግንኙነት የማስተካከል ስራዎችን ለመስራት ነው የምናስበው።

ላፉት ሶስት አስርት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ስርአቱ ከተቀዳበት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌው ጀምሮ አማራ ጠል እና ያገለለ እንዲሁም ህልውናውን የሚፈታተን ነው።

የረዥም ጊዜ እቅዳችን እነዚህን የህልውና ጥያቄዎች ማስከበር እና መሰል ተግባራት ወደፊት እንዳይፈጸሙበት የሚያስችል መዋቅራዊ ስርአት መገንባት ነው።

ቢቢሲ- በአጠቃላይ ህዝቡን ከመወከል አንጻር ምን አቋም አላችሁ? ምክንያቱም በስራ አስፈጻሚ ምርጫችሁ ወቅት ለሴቶች ብዙ እድል አልሰጣችሁም በሚል ቅሬታ እና ትችት ተነስቶባችሁ ነበር።

አቶ ክርስቲያን ታደለ- ይህ ቅሬታ በተለያየ መንገድ ለኛም ደርሶናል። በመሰረታዊነት የ13 ስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ነው የተደረገው። ከአስራ ሶስቱ ደግሞ አንዷ ብቻ ሴት ናት። ሌላው ደግሞ የሃይማኖት ጉዳይ ነው እየተነሳ የነበረው። መታወቅ ያለበት በመሰረታዊነት የህልውና ጉዳይ መሆኑ ነው።

ስለዚህ ሁሉም የተመረጠው በችሎታ እና በችሎታ ብቻ ነው። መሰረት ያደረግነው እሱን ነው። አንዱ አማራ ሁሉንም አማራ ይወክላል፤ ሁሉም አማራ ለአንዱ አማራ ዘብ ይቆማል በሚለው መርሃችን መሰረት ነው የምንሰራው። ለእያንዳንዱ የስራ ዘርፍ ብቃት ያላቸውን ሰዎች ነው የመለመልነው። የሴቶች ተሳትፎም ቢሆን፤ ከስራ አስፈጻሚዎች መካከል አንዷ ብቻ ሴት ብትሆንም፤ በርካታ ሴት መስራች አባላት እንዳሉን እንዲታወቅልን እንፈልጋለን።

ቢቢሲ- አሁን ኢትዮጰያ ውስጥ ያለው ቋንቋ እና ብሄርን መሰረት ያደረገው ፌደራላዊ ስርአት ዙሪያ ምን አይነት አቋም ነው ያላችሁ? አማራ ክልልን እያስተዳደረ ካለው ፓርቲ ጋር ምን አይነት ግንኙነት እንዲኖራቹ ትጠብቃላችሁ?

አቶ ክርስቲያን ታደለ- የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ በመሰረታዊነት ፌደራላዊ ስርአትን አይቃወምም። ይህ ማለት ግን የአማራ ህዝብ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ፌደራሊዝም ይደግፋል ማለት አይደለም። ለአብነት አሁን ያለው የፌደራሊዝም ስርአት የአማራውን ህዝባዊ አንድነት የሚገረስስ ሆኖ ነው ያገኘነው።

በዋነኛነት የመታገያ ጥያቄያችን የአማራን ህዝብ እንደ ህዝብ አንድነቱን እና የታሪካዊ ግዛት መብቶቹ እንዳይገረሰሱ እና እንዲጠበቅ ማድረግ ነው።