ከኦነጎች ጋር ቁጭ እየተባለ የአማራ ብሄረተኝነት መቃወም ነውር ነው – (ግርማ ካሳ)

ከግርማ ካሳ

አቶ ኤፍሬም ማዴቦ፣ የግንቦት ሰባት አመራር ናቸው። የአማራ ብሄረተኝነትን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብሄረተኝኘትን እንደሚቃወሙና ለአገር አደጋ እንደሆኑ በትዊተር ገልጸዋል። አቶ ኤፍሬም ትክክል ናቸው።እኔም የርሳቸውን ሐሳብ ነው የምጋራው። በዘር መደራጀት አደጋ አለው።

ሆኖም ግን በባህር ዳር የአማራ ፓርቲ መቋቋሙን ተከትሎ ይሄን አስተያየት መስጠታቸው ግን ያስገምታቸዋል። ከለየላቸው የኦሮሞ ብሄርተኝነት ቁንጮ ከሆኑት ጋር በየመድረኩ ሲቀመጡና ዲስኩር ሲሰጡ፣ ግንባር፣ ሕብረት ንቅናቄ ወዘተረፈ ሲፈጥሩ፣ ያኔ ለምን ተመሳሳይ አስተያየት አልሰጡም? ይሄ ግብዝነት ካልሆነ ምን ሊባል ይችላል?

ለኔ ከሁሉም በላይ አደገኛው የኦሮሞ ብሄረተኝነት ነው። ምክንያቱም ቀላል ነው። አሁን ያለው የዘርና የጎጥ ፌዴራል አወቃቀር ፈርሶ፣ ሁሉም እኩል የሆኑበት ፌዴራላዊ አስተዳደራዊ አወቃቀር ቢኖር የአማራ ብሄረተኞች ከማንም በላይ ደስተኞች ናቸው። ያኔ የአማራ ብሄረትኝነት ይከስማል ባይ ነኝ። የኦሮሞ ብሄረተኞች ግን አሁን ያለው አወቃቀር ፣ ከተቀየረ ደም መፋሰስ ነው ብለው የሚያስፈራሩና የሚዝቱ ናቸው። ፖለቲካቸው በመስፋፋትና ኦሮምነትን በሌላው ላይ በመጫን ላይ ያተኮረ ነው። ለዚህም ነው በኦሮሞ ብሄረተኛ ፖለቲከኞች ፣ በኦሮሞ ክልል አማርኛ እንዳይነገር፣ የስራ ቋንቋ እንዳይሆን፣ አማርኛ ተናጋሪዎች በብዛት ባሉባቸው ቦታዎች በአማርኛ አገልግሎት እንዳያገኙ እየተደረገ ያለው።

አቶ ኤፍሬም አንድ ነገር መዘንጋት የለባቸው። የአማራ ብሄረተኝነት ያልነበረ ግን በሕወሃትና በኦሮሞ ብሄረተኞች የተወለደ መሆኑን ነው። አሁን ያለው ፣ የአማራዉንና የአማርኛ ተናጋሪ ማህበረሰብ ያገለለ፣ የጎዳ፣ አንገት ያስደፋ ሁኔታ ከቀጠለ አሁን ካለው ሁለት፣ ሶስት፣ .. አስር እጥፍ የአማራ ብሄረተኝነት ያድጋል። ልንቆጣጠረው የምንችለው ነገር አይደለም። ብሲት የደረሰበት፣ የተገፋ ማህበረሰብን ራስህን አትከላከል ማለት አስቸጋሪ ነው።

ስለዚህ አቶ ኤፍሬም ለይተው አንዱን ወገን ከሚያጠቁ ፣ አማራጮችን በማቅረብ፣ ወደ አገር ቤት በሰላም በመግባት፣ እዚያ ካሉ የአንድነት ሃይሎች ጋር በመተባበር ቢሰሩ የተሻለ ነው። እኛ ጽፈናል መፍትሄው ይሄ መሬት የኦሮሞ፣ ያ መሬት የትግሬ፣ እዚያ ማዶ የአማራ እየተባለ …ዜጎችን በዘር አጥር ማጠር ይቁም ብለናል። አሁን ያለው የዘር አወቃቀር ፈርሶ ወይንም ተሻሽሎ(ቢያንስ ሕብረብሄራዊ ዜጎች በብዛት የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሕብረብሄራዊ አስተዳደር ውስጥ እንዲካተቱ ተደረጎ)፣ ማንም ዜጋ በማንኛው የአገሪቷ ክፍል ዘሩና ሃይማኖቱ ሳይጠየቅ መኖር፣ መስራት፣ መነገድ፣ መዉጣት፣ መግባት፣ መመረጥ የሚችልበት አገር ትኑረን እያልን ጮኸናል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US