ክፉውንም ሆነ ደጉን ታሪክ በመቀበል ያለፈውን ታሪክ በይቅርታ መዝጋት ይገባል – ዶ/ር አብይ አህመድ

በኢትዮጵያ ወደ በረከት ሊቀየሩ የሚገባቸው ብዙ ሃብቶች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ የ’እንኳን አደረሳችሁ’ መልዕክት አስተላልፈዋል። (ኢዜአ)

በመልዕክታቸውም ‘’በአገራችን በጠላት ግፊት ለመዓት የዋሉና ለበረከት ልንቀይራቸው የሚገቡን ብዙ ሀብቶች አሉን’’ ብለዋል።

ለአብነትም የመለያያና የመከፋፈያ ምክንያት እየሆነ ያለው ብዝኀነት ከታወቀበት በረከት መሆኑን አስገንዝበዋል።

‘’ብዙኀነት ማለት ብዙ እሴት ብዙ ጸጋ፣ ብዙ ሃብት ብዙ ቅርስ ብዙ ታሪክና ብዙ ቋንቋ ብዙ ባህል ማለት ነው። የሌላውን ዓለም ሰዎች ይህን እኛ ያለንን ብዙ ሃብት ፍለጋ ዓለምን ይዞራል።’’ ሲሉም አመልክተዋል።

‘’በረከት የምናገኘው ከዳር ቆመን አይደለም መሐል ገብተን እንጂ ከሩቅ ሆነን አይደለም’’ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወደህዝብ መውረድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ክፉውንም ሆነ ደጉን ታሪክ በመቀበል ያለፈውን ታሪክ በይቅርታ መዝጋት እንደሚገባ ገልጸዋል።

Image result for abiy ahmed  in Gonder

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስተላለፉት የ’እንኳን አደረሳችሁ’ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል

ኢየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከመጠመቁ በፊት የሰው ልጅ ውሃን የሚያውቀው በመዓትነቱና በእንቅፋቱ ነበር ። በኖህ ዘመን የሰው ልጅ የጠፋው በውሃ ነው። እስራኤላውያን ከግብጽ ወጥተው ወደ ከነዓን ሲጓዙ መንገድ የዘጋባቸው የኤርትራ ባሕር ነበር። ኢያሪኮን ተሻግረው ወደ ምድረ ርስት ሲገቡ የዘጋባቸው የዮርዳኖስ ወንዝ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በማዕከል ዮርዳኖስ ሲቆም ግን ለመዓት የነበረው ውሃ ለበረከት ሆነ። ይሄም ዛሬ በየዓመቱ ወደ ውኃ ወርደን የጥምቀት በዓልን እናከብራል።

በዓለም ላይ አዲስ ሃብት ይፈጠራል ብለን መጠበቅ የለብንም ። ለችግር፣ ለመከራና ለመዓት ሲውሉ የነበሩ ነገሮችን ነው ወደ በረከት መቀየር ያለብን። የሰው ልጅ በጥንት ጠላቱ ምክንያት በጥፋቱና በስንፍናው ውሃን የመዓት ማዝነቢያ አድርጎት ነበር። ክርስቶስ ያንኑ ውሃ ለበረከት እንዲሆን አድርጎ ለውጦታል።

በአገራችን በጠላት ግፊት ለመዓት የዋሉና ለበረከት ልንቀይራቸው የሚገቡን ብዙ ሀብቶች አሉን። ለምሳሌ ብዙኀነታችንን ብንወስድ የመለያያና የመከፋፈያ ምክንያት እየሆነብን ነው። ካወቅንበት ግን ብዙኀነታችን ለበረከት ማድረግ እንችላለን። ብዙኀነት ማለት ብዙ እሴት ብዙ ጸጋ፣ ብዙ ሃብት ብዙ ቅርስ ብዙ ታሪክና ብዙ ቋንቋ ብዙ ባህል ማለት ነው። የሌላውን ዓለም ሰዎች ይህን እኛ ያለንን ብዙ ሃብት ፍለጋ ዓለምን ይዞራል። እኛ ግን በአገራችን ውስጥ ዓለምን የሚያስደንቅ ብዙኀነት አለን አጠቃቀማችን በጥበብ ብናደርገው ኢትዮጵያችን የሰው ልጅ ሀብቶችን መናኸሪያ ናት።

ክርስቶስ ውሃን የቀደሰው ከሰማያት ወርዶ ነው። ወደ ውሃ ሄዶ ነው ማዕከለ ባሕር ቆሞ ነው። በውኃ ተጠምቆ ነው። እኛም መከተል ያለብን ይሄንን ነው። ራሳችንን ከሰቀልንበት ማውረድ አንዳችን ወደ ሌላኛችን መሄድ በሰላም መካካል መገኘት። የሌላውን የራሳችን ማድረግ አንዳችን ከሌላችንም መማር። በረከት የምናገኘው ከዳር ቆመን አይደለም መሐል ገብተን እንጂ ከሩቅ ሆነን አይደለም ወደዚያው ተጉዘን እንጂ እላይ ነን ብለን አይደለም ወደ ሕዝብ ወረድ ብለን እንጂ።

ለመሆኑ ሰፈሮቻችን ክልሎቻችን የአስተዳደር ወሰኖቻችን የጉዳት ምክንያት እንዲሆኑ ለምን እንፈቅድላቸዋለን። ለምን የበረከት ምክንያት አናደርጋቸውም ለምን የግጭትና የመለያየት መንስኤ ይሆኑብናል ለምን የእኔ የእኔ እንባባልባቸዋልን ለምን የመገዳደያ አውዶች እናደርጋቸዋለን ኢትዮጵያ የሁላችንም መሆኗ ብናምንም በወሰኖቻችን ላይ ሰፋፊ ገበያዎችን ብንዘረጋ አንዱን ክልል ከሌላው የሚያገናኙ አካባቢዎችን በጋራ ብናለማ አንዳችን ወደ ሌላችን ሰፈር ሄደን አብረን የመኖር ነባር እሴቶቻችን ብናጠናከር የሁላችንም የሆነውን ሜዳ ለጋራ እርሻ ወንዙን ለጋራ መዋኛ ተራራውን ለጋራ መዝናኛ ጫካውን ለጋራ መናፈሻ ብናውለው መዓቱን በረከት አደረግነው ማለት ነው። የሚያጣላን ሀብቱ አይደለም አስተሳሰባችን እንጂ አንምሮአችን ውስጥ የገነባነው ግድግዳ ካፈረስነው መሬት ላይ ያለው አጥር ገድቦ አይገድበንም። በአዕምሮአችን ያስቀመጥነው ክልል ካልሆነ በቀር መሬት ላይ ያለው በፍቅር ከኖርንብት ጠቦ አይጠበንም።

በታሪኮቻችንና በቅርሶቻችን፣ በጀግኖቻችንና በታሪካዊ ኩነቶቻችን ለምን እንጣላለን? እነዚህን ነገሮች መዓት ማውረጃ ለምን እናደርጋቸዋለን? ለምን ወደ በረከት አንቀይራቸውም? ክፉውንም ደጉንም ታሪክ እንቀበለው፣ ያለፈውን በይቅርታ እንዝጋው፣ ታሪካዊ ቦታዎቻችንን የቱሪስት መስህቦች እናድርጋቸው ጀግኖቻችንን ለሚያከብሯቸው እንተውላቸው፡፡ ግድ ሁላችንም ካልተስማማንባቸው ብለን አንቆራቆስባቸው፣ ታሪካዊ ሁነቶችን አዳዲስ እሴቶች ጨምረን እንዘክራቸው፣ ያልተሟሉ ታሪኮቻችንን ጥናትና ምርምር አድርገን እናሙላቸው እያፈረስን መስራቱን ትተን እሞላን እንሂድ ያን ጊዜ ለመአት እየዋሉ ያሉት ታሪካዊ ሀብቶቻችን በረከት የምንጮች ይሆናሉ፡፡

አደጉ የምንላቸው ህዝቦች ሁሉ ያደጉት መዓቱን ወደ በረከት መቀየር በመቻላቸው ነው፡፡ የበለጸጉ ህዝቦች የብልጽግናቸው ምስጢር ሌላ ሳይሆን ችግርን ወደ እድል የመቀየር ችሎታቸው ነው፡፡ እነዚህ ህዝቦች በረዶውና ሙቀቱ ያስቸገራቸው፣ ረሀቡና ወረርሽኙ ያስመረራቸው ጦርነትና ስደት ያሰቃያቸው ነበሩ፡፡ ችሎታቸውን በመጠቀም የሚያስመርረውን አየር ንብረት፣ ፈታኙን መልክአ-ምድርና አስቸጋሪውን ተፈጥሮ ወደ በረከት ቀይረው ዛሬ ምቹ አገር ገንብተዋል፡፡ ያለ ችግር መፍትሄ፣ ያለፈተና ጥንካሬ ያለ ጨለማ ብርሃን አይኖርም፡፡ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ያሳደገው ዘመናዊነትን ያመጣውና ስልጣኔን የወለደው ችግርና ፈተና ነው፡፡ ሰዎች በብልሃት ከያዙት ከመአት ውስጥ በረከት የሚሆን ነገር ማውጣት ይችላሉ፡፡

ሺህ ጊዜ ጨለማን መውቀስ ብርሃንን አያመጣም እንደሚባለው ባለንበት ተተክለን መአቱን ብንረግመው በረከት አይሆንም። ከቁልሉ ላይ እንውረድ፣ ከከፍታው ዝቅ እንበል ወደ ውሃው እንሂድ በውሃው እንሂድ በውሃው መካከልም እንቁም ራሳችንን እላይ ሰቅለን ከተደላደልን የሚመጣ ለውጥ የለም። ሌላው ወደ እኛ እንዲመጣ ብቻ ከተመኘን የሚመጣ ለውጥ የለም። ውጡ ማለትን ትተን እኛ ራሳችን እንውረድ ኑ ማለትን ትተን እንሂድ። ከዳር መሆንን ትተን መሃል እንግባ። ያን ጊዜ የምንፈልገው በረከት ይሆናል።
የሰው ልጅ ሊያየው የሚገባ የኖረው ሚስጥር በጥምቀት የተገለጠው በዚህ ምክንያት ነው። ከላይ መውረድ ወደ ውሃውም በመሄድ ውሃው ውስጥም በመግባት ኢጲፋንያ መገለጥ የተባለውም ለዚህ ነው። አብ በደመና መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወልድ በዮርዳኖስ አስደናቂው ሚስጥር የተገለጠው በዚህ ነው።

አንድ በምንሆንበት፣ የምንሰለጥንበት፣ የምንበለጽግበት፣ የምንዘምንበት፣ የምንፋቀርበት ሚስጥር እንዲገለጥልን ኑ ሁላችንም ከላይ እንውረድ የችግርና የፈተና ምንጭ በመሰለን ነገር መካከል እንገኝ። ከሩቅ መመልከታችን አቁመን መካከል ላይ እንቁም በቋንቋው፣ በባህሉ፣ በታሪኩ፣ በወጉ መካከል እንሁን። በጥምቀት በዓል ህዝቡ ሁሉ ቤቱን ትቶ፣ ሰፈሩን ትቶ፣ ጎጡን ትቶ ሁሉን ወደሚያካትተው ባህር ይወርዳል። ሁሉን ወደሚያካትተው ሜዳ ይሰባሰባል። ኑ እኛም ምሽጎቻችንን ትተን ሁላችንም ወደምንገናኝበት ወደ ሰፊው ሜዳ እንሄድ። የራሳችን የምንለውን ሁሉ ይዘን ከሌላው ጋር አብረን ለመሆን ወደ ሰፊው ሜዳ እንሄድ።

በጥምቀት ጊዜ ሁሉም ያለውን ይዞ በየወጉ ለብሶ በየቋንቋው እየተናገረ በየባህሉ እየጨፈረ በአንድ የጥምቀት ሜዳ ይገናኛል። ኢትዮጰያ ዓይነተ ብዙ ጸጋ፣ ብዙ ሀብት፣ ብዙ መሆኗን ይመሰክራል። ሁሉም ይወርዳል፣ አንዱ በሌላው ሙዚቃ ይዋባል። አንዱ በሌላው ቋንቋ ያወጋል በሌላው ልብስ ያጌጣል አንዱ የሌላውን ባህል ያወርሳል። ጠላታችን ለመዓት ሊያደርግብን የነበረውን ነገር ሕዝባችን ለምህረት ያደርገዋል። የሚያዋጣንም ይኸ ነው።

መልካም የከተራና የጥምቅት በዓል ይሁንልን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፈራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር

ፈጣሪያችን ሀገራችንና ሕዝቦቿን ይባርክ

አመሰግናለሁ

(ኢዜአ)