‹‹ተለቀቁ ሲባል በመገናኛ ብዙኃን ከመስማታችን የተለዬ ነገር አልሰማንም፡፡›› የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ታጋች ተማሪዎች ወላጆች


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

‹‹ተለቀቁ ሲባል በመገናኛ ብዙኃን ከመስማታችን የተለዬ ነገር አልሰማንም፡፡›› የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ታጋች ተማሪዎች ወላጆች

በታጋቾች ቁጥጥር ሥር ከነበሩ የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል 21 ትናንት መለቀቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

አብመድ ዛሬ ወደ ታጋች ቤተሰቦች ደውሎ ከልጆቻቸው ጋር በስልክ መገናኘት ስለመቻል አለመቻላቸው ጠይቋል፡፡ የተለቀቁም ያልተለቀቁም ተማሪዎች እንዳሉ በመገናኛ ብዙኃን ከመስማታቸው ውጭ አዲስ ተጨባጭ መረጃ እንዳላገኙ ነው ቤተሰቦች የተናገሩት፡፡ ‹‹መግለጫውን በመገናኛ ብዙኃን ከመስማት ውጭ የሰማነው ነገር የለም፤ ቀደም ብሎ አልፎ አልፎ ሲደውሉልን የነበረም በአጋቾች ስልክ ነው፤ ያም ስልክ አይሠራም፤ የልጃችንም ስልክ አይሠራም፡፡ አጋቾች ሲያገናኙንም ልጆቹ ‹‹ደህና ነን› ከማለት በቀር ሌላ መረጃ አልሰጡንም ነበር›› ብለዋል የአንደኛዋ ታጋች ተማሪ ቤተሰብ፡፡

ሌላኛው የታጋች ተማሪ አባት ደግሞ ‹‹እኔ ተለቀቁ ሲባል ስሰማ በጣም ተደስቼ ነበር፤ ግን ይኸው እስከ ዛሬ 6፡00 ድረስ የልጄን ድምጽ አልሠማሁም፡፡ መቼም ልጄ ምን ያህል እንደምንጨነቅ አታጣውም፤ ከተለቀቁ እንዴት የሌላ ሰው ስልክ ለምና እንኳን አትደውልልንም? መንግሥትስ የተለቀቁትን ተማሪዎች ዝርዝር ለምን አይነግረንምና ቁርጣችን አናውቅም?›› ብለዋል፡፡

ሌላኛው የታጋች ቤተሰብም ተመሳሳይ አስተያዬት ነው የሰጡን፤ ‹‹መግለጫውን እንደሰማን በጉጉት መጠበቅ ጀምረን ነበር፤ ግን ይኸው መሽቶ ነጋ፤ አዲስ የሰማነው ነገር የለም፡፡ የልጃችንን ድምጽም አልሰማንም›› ብለዋል፡፡

ልጆቹ ከታገቱ በኋላ በአጋቾች ስልክ ሁለት ጊዜ አገናኝተዋቸው እንደነበረ ያስታወሱት የታጋች ቤተሰብ ‹‹ሌሊት ሌሊት ስለሚያጓጉዙን የት እንዳለን አናውቅም፤ ብቻ ደኅና ነን፤ ምግብም ያቀርቡልናል›› እንዳለቻቸው አስታውሰዋል፡፡ በቅርብ ሳምንታትም ደውላ እንደማታውቅም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ተማሪዎች እንደሚባለው ተለቅቀው ከሆነ ስለምን ስልክ ወደ ቤተሰብ እንዲደውሉ አይደረግም? ወደ ቤተሰቦቻቸውስ ለምን አይልኳቸውም?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

አብመድ ተለቀቁ ስተባሉት ተማሪዎች ዝርዝር መረጃ ለማግኘት በደምቢዶሎ አካባቢ ከሚገኙ የፀጥታ አካላት፣ ከፌዴራል መንግሥትና ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ነው፤ እስካሁን መረጃ ማግኘት አልቻለም፤ እንዳገኘ የሚያደርስ ይሆናል፡፡