ኢራን የተከሰከሰውን አውሮፕላን ጥቁር ሳጥን ለቦይንግም ሆነ ለአሜሪካ እንደማትሰጥ ገለጸች

ኢራን በትላንትናው እለት የተከሰከሰውን አውሮፕላን ጥቁር ሳጥን (black box) ለቦይንግም ሆነ ለአሜሪካ እንደማትሰጥ ገለጸች

ንብረትነቱ የዩክሬይን የሆነው 737-800 የሆነው አውሮፕላን ከቴህራን አየር መንገድ በተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ 176 ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ የተከሰከሰ ሲሆን አንድም ሰው በህይወት መትረፍ አለመቻሉ ተገልጿል፡፡

በዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ህግ መሠረት ኢራን ምርመራውን የመምራት መብት ያላት ሲሆን፤ አምራቾች የሚሳተፉ ቢሆንም ጥቂት ሀገራት ጥቁር ሳጥኖችን የመተንተን ችሎታ እንዳላቸውም ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ፡፡

አውሮፕላኑ የተከሰከሰው ኢራን በኢራቅ የሚገኙ ሁለት የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የሚሳኤል ድብደባ ባደረሰችበት ከሰአታት በኋላ ቢሆንም ሁለቱ ክስተቶች የሚገናኙ ስለመሆኑ የተረጋገጠ ነገር የለም ተብሏል፡፡

የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት ደህንነት ቦርድ በአሜሪካ የተሰሩ ቦይንግ አውሮፕላኖችን በሚመለከት በማንኛውም ዓለም አቀፍ ምርመራዎች የሚጫተው ሚና ቢኖርም ቦርዱ ፈቃድ ባለውና በሚመለከታቸው የውጭ ሀገር ሕጎች መሠረት እንደሚሰራም ተጠቅሷል፡፡

የኢራን የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ኃላፊ አሊ አብድዛድህ ለኢራን ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት “ጥቁር ሣጥኑን ለአምራቹ ቦይንግም ሆነ ለአሜሪካ አንሰጥም” ብለዋል ፡፡

አክለውም “ይህ አደጋ በኢራን የአየር መንገድ ድርጅት ምርመራ የሚደረግበት ሲሆን ዩክሬናውያንም እንዲሁ መገኘት ይችላሉ” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።