ያለመታከት ለዘጠኝ አመት የአገር ሀብት እየተዘረፈ ነው ሲሉ የሚጮኹት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ሰሚ አላገኙም ።

በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምጽ
……………..
ሰሚ ሳይኖር ተስፋ ሳይቆርጥ ዝም ብሎ የሚጮህ ሰው ታውቃላችሁ ? እኚህ ሰው እንዲህ ናቸው ። አቶ ገመቹ ዱቢሶ ይባላሉ ።
እናም እኚህ ሰው ላለፉት ሁለት አመታት አይደለም ፡ ሶስት አራት አመታትም አይደለም ። ስድስት ሰባት አመታትም አይደለም ። ይኸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሆነው ከተሾሙ ከዛሬ ዘጠኝ አመት ጀምሮ አንድ ቀን ጩኸቴ ይሰማ ይሆናል እያሉ የኦዲት ሪፖርታቸውን ለምክር ቤቱ ሲያሰሙ ፡ ኸረ የህዝብ ገንዘብ እየጠፋ ነው ፡ ኸረ የመንግስት ሃብት እየተመዘበረ ነው እያሉ በተለያዩ ተቋማት ላይ በሚደረግ ምርመራ ላይ የሚገኘውን ጉድለት አቅርበው እርምጃ እንዲወሰድ አቤት ! እያሉ ይኸው አሉ ።
ስለ እኚህ ሰው ሳስብ ጽናታቸው ይገርመኛል ። ሪፖርት ባቀረቡባቸው ተቋማት ላይ ከአመት አመት እርምጃ እንዳልተወሰደ እያወቁ ተስፋ ባለመቁረጥ ሁሌ እንደተናገሩ ነው ። አሁን አሁን ግን እኚህ ሰው ተስፋ ወደ መቁረጥ ተቃርበዋል ። ላለፉት ዘጠኝ አመታት እጮሃለሁ ነገር ግን ጩኸቴ ፍሬ አላፈራም እያሉ ነው ። በምድረ በዳ እንደሚጮህ ሰው ድምጽ ጩኸታቸው ሰሚ አላገኘም ። አቶ ገመቹ እንግዲህ ምን እንላለን ጽናቱን ይስጦት