ሥራ አጥነትና ሥራ ፈትነት፤ የሕግ ሚናዎች – (አበበ አሳመረ – የሕግ ባለሙያና ጠበቃ)

በሌሎች፣ በተለይም በበለጸጉት አገራት ሥራ አጥነትን በተወሰነ ቁጥር እቀንሳለሁ ብሎ የፖለቲካ መደራደሪያ በማቅረብ መራጩን ለማሳመንና ድምጹን ለማግኘት መሞከር የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሥራ ላይ ያለው የሰው ኀይልም የሥራ ዋስትናው የተጠበቀ፣ የተሻለ ገቢ የሚያገኝ እንዲሆን፣ በግል ሥራ እራሳቸውን የሚያስተዳድሩም ያለባቸው ችግር ካለ እንዲፈታ በማድረግ የግል ንግዳቸው ላይ እንዲቆዩና ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ እርከን እንዲያድጉ ለማድረግ በርካታ የፖሲሲ አማራጮችንና የሚወሰዱ የሕግ እርምጃዎችን ለመወዳደሪያና በማቅረብ ሥልጣን ላይ መውጣት የተለመደ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ሠርቶ ማደር (the right to work) መሠረታዊ መብት ስለሆነና ይህን መብት ማስከበር የመንግሥት ኀላፊነት ስለሆነ ነው፡፡

በአገራችን የሥራ አጥነትና የሥራ ፈትነት ችግር በተለይ የወጣቶች ሥራ አጥነት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ትኩረት እንደተሰጠው እየሰማን ነው፡፡ በተለይ በከፍተኛ ቁጥር እያደረገ ከመጣው የመንግሥትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን ሥራ ማጣት ጋር ተያይዞም በርካታ የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ተፈጥረዋል፡፡ በሌላ በኩል የሥራ ፈትነትን ችግር በተመለከተ ምንም ነገር አይነሳም፡፡ ቀጣሪ ድርጅቶች በተለያዩ ምክንያቶች በመዘጋታቸው ምክንያት ከሥራ የሚሰናበቱትና በግል ትናንሽ ንግድ ተሰማርተው በተለያዩ ምክንያቶች ንግዳቸው ስለሚዘጉ ሰዎች ምንም የሚባል ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ ማኅበራዊ ደኅንነትን የማስፈን ጉዳይ ለሁለቱም ጉዳዮች የተመዛዘነ ትኩረት መስጠትን ይፈልጋል፡፡ ዛሬ ላይ ተቀጠረ ብለን ወይም በራሱ የንግድ ሥራ እራሱን ቻለ የምንለው ሰው ነገ ሥራውን ካጣ ውጤቱ ዜሮ ድምር ይሆናል፡፡ ስለሆነም ለሥራ አጥነት የሚሰጠውን ትኩረት ያክል ለሥራ ፈትነትም ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ሁለቱንም ችግሮች ለመቅረፍ ጥልቅና ሰፊ ጉዳዮችን መመልከት የሚገባ ቢሆንም ከነዚህ ውስጥ ሕግ ያለውን ሚና በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡

የታክስ ሕጐች
***

የታክስ ሕጐች፣ የፖሊሲ መሠረታቸውና አፈጻጸማቸው ሥራ አጥነትንና ሥራ ፈትነትን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አላቸው፡፡ በተለይ አነስተኛ የግል ንግዶች እንደግል ቅጥር ተቆጥረው እራሳቸውን ከቻሉ በቂ ነው የሚል አስተሳሰብ ከተያዘና የግብር ጫና ከሌለባቸው ዘላቂ ሆኖ የመቀጠል፣ ወደላይ የማደግና በተመሳሳይ ሁኔታም ሥራ አጦችንም ወደግል ሥራ እንዲገቡ የማነቃቃት አዎንታዊ ተጽዕኖ ስላላቸው እነሱ ላይ የሚኖረው የታክስ ሕግ አፈጻጸም ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በርካታ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን በአነስተኛ ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን የግብር ጫና ይለባቸውም፡፡ ለምን ጫና እንደሌለባቸው በወቅቱ ሥልጠና የሰጠንን ከፍተኛ ባለሥልጣን ጠይቄው ነበር፡፡ የሰጠኝ ምክንያቶች በትናንሽ ንግድ ሥራዎች እራሳቸውን የሚችሉ ሰዎች የራሳቸው ተቀጣሪ ስለሚሆኑ ይህ በራሱ ለመንግሥት ከፍተኛ እገዛ ነው፣ የግብር አሰባሰብ ብቃትን በማሳደግ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ላይ በማተኮር ግብር መሰብሰብ የግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቱን የገቢ አሰባሰብ ብቃት ይጨምራል፣ አነስተኛ ግብር ከፋዮች በመንግሥት ላይ የሚያቀርቡትን ምሬትና ብሶት ስለሚቀንስ የተሻለ መልካም አስተዳደር ያሰፍናል፣ መንግሥት ተናንሽ ነጋዴዎችን በመደገፍ ወደከፍተኛ ግብር ከፋይነት እንዲሽጋገሩ የማድረግ ሥራን እንዲሠራ ያደርገዋል፣ ትናንሽ ነጋዴዎች በግብር ምክንያት እንጠየቃለን ብለው የሚያስቡትን ግብር ወደሸማቹ ስለሚያዞሩት እቃዎች በአነስተኛ ዋጋ ለሸማቹ አይደርስም፣ ይህ ደግሞ የፋብሪካ ምርቶች በብዛትና በስፋት ለሸማቹ እንዳይደርስ ስለሚያደርግ ሸማቹ ይጐዳል፣ በግብር ምክንያት ከሥራ የሚወጡ ነጋደዎች ተመልሰው የመንግሥት ሸክም የመሆን እድላቸው ይጨምራል ወዘተ. በማለት በርካታ ምክንያቶችን ዘረዘረልኝ፡፡ በዚህ ምክንያትም ደቡብ አፍሪካ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከፍተኛ መዳረሻ ከሆኑት አገሮች መካከል ግንባር ቀደም ናት ለማለት ይቻላል፡፡ በአጋጣሚ ያናገርኳቸው ኢትዮጵያውያን “በግብር ስለማንማረር ጥሩ ነው” በማለት መልስ ሰጥተውኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሕግ አፈጻጸም መልካም (regulatory good governance) አስተዳደር ሌላው መሠረታዊ ትኩረት ነው፡፡ የታክስ አስተዳደሩ ድርጅቶች ሲዘጉ፣ ከሥራ ሲወጡ፣ ወዘተ. ለምን ትዘጋላችሁ ማለት አለበት፡፡ ይህ ዓይነት ትኩረት ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረ ሲሆን አሁን አሁን ግን የለም ለማለት ይቻላል፡፡ በ1989 ዓ.ም. አካባቢ የታክስ ኦፊሰር ሆኖ የሥራ ሰው እንደነገረኝ “ድርጅታቸውን በግብር ምክንያት” እንደሚዘጉ ሲያመለክቱ ችግራቸውን በሚገባ ጠይቀን እንረዳና እንዳይዘጉ እናግዛቸው ነበር በማለት ልምዱን አጋርቶኛል፡፡ ይህ አሠራር ነጋዴዎች ድርጅታቸውን ዘግተው ሥራ ፈት እንዳይሆኑና የቀጠሯቸው ሠራተኞችም ካሉ እንዳይበትኑ ስለሚያስችላቸው ጥሩ አሠራር ነው፡፡ ስለሆነም የታክስ አስተዳደሩ እንደዚህ ዓይነት የሕግ አፈጻጸም መልካም አስተዳደር ሥራዎችን ቢሠራ የግሉ ዘርፍ የተሻለ ሥራ ፈጣሪ የሚያደርገው ከመሆኑ በተጨማሪ ወደ ሥራ ፈትነት የሚሸጋገረውን የሰው ኃይል ይቀንሰዋል፡፡

የተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች የሕግ አፈጻጸም
***

በየዓመቱ የንግድ ፈቃዳቸውን የሚመልሱ ነጋዴታች በርካታ ቢሆኑም ለምን እንደሚመለሱ ግን በግልጽ አይታወቅም፡፡ በተገቢው መረጃ ላይ የተመሠረተ ጥናትም አላጋጠመኝም፡፡ የንግድ ፈቃድና የሙያ ማረጋገጫ ፈቃድ ሰጪ ተቋማት ነጋዴዎች በሥራ ላይ እንዲቆዩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጣሪ መሆን አለባቸው፡፡ በተለይ የንግድ ቢሮዎች ከቁጥጥር ባለፈ በራሳቸው አዳዲስ የንግድ ሥራ ዕድሎችን በማጥናት ወደ ንግድ ሥራ ለሚገቡ አዳዲስ ነጋዴዎች እገዛ ማድረግ፣ ምክር የመስጠት የሕግ ኀላፊነት ሊኖርባቸው ይገባል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ቀድሞ “የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ” ይባል በነበረበት ጊዜ አዳዲስና አዋጪ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ፕሮጀክቶችን በማጥናት ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምባቸው ዝርዝራቸውን በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ይለጥፍ ነበር፡፡ አነስተኛ እና አዲስ ነጋዴ የአዋጭነት ጥናት ለማስጠናት ግንዛቤውም የገንዘብ አቅሙም ስለማይኖረው በዚህ መልክ ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል፡፡

ስለሆነም አዳዲስ የንግድ ሥራዎች እንዲሰፋ ማድረግና ያሉትም በተረጋጋ ሁኔታ በሥራቸው ላይ እንዲቆዩ ማድረግ መሠረታዊ ግዴታቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ለወጣቱ ሥራ ፈጣሪ የተበጀተውን በጀት በተመለከተ ወጣቶቹ በጋራና በተናጠል ምን ቢሠሩ ያዋጣቸዋል የሚለውን ለማማከርና ለመወሰን ከንግድ ቢሮዎች የተሻለ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የለም፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት ቢችሉም በተለያዩ ምክንያቶች አስተዋጽዖ ማድረግ የሚገባቸውን ያክል እያደረጉ ግን አይደለም፡፡

ይሁን እንጂ ቢሮዎቹ በዚህ መልክ ተግባራቸውን ማከናወን ይችላሉ የሚለው አጠያያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ አለበለዚያ አሁን የተመደበው ገንዘብ ውጤት ማምጣት ካልቻለ ወጣቶቹ ወደሥራ ፈትነት ሊሸጋገሩ ስለሚችሉ የንግድ ቢሮዎችን ተግባርና ኀላፊነት በሚገባ መቃኘት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አስተዳደር ጋር በጋራ መሥራት ይገባዋል፡፡ ስለሆነም የንግድ ቢሮዎች የሥራቸው ውጤት ሊመዘን የሚገባው በሰጡትና በሰረዙት ንግድ ፈቃድ ቁጥር ሳይሆን ንግድ እንዲስፋፋና ያለውም ነጋዴ በሥራ ላይ እንዲቆይ ባደረጉትና በውጤቱም ለአዲስ ሥራ ዕድልና ሥራ ፈትነት እንዳይኖር ባደረጉት አስተዋጽዖ መጠን ልክ መሆን አለበት፡፡

ይህ ዓይነት የሕግ አፈጻጸም መልካም አስተዳደር ለኢንቨስትመንት መሥሪያ ቤቶችና ለከተማ አስተዳደሮችም ይሆናል፡፡ ኢንቨስተሮች በፕሮፖዛላቸው መሠረት ሠራተኛ መቅጠራቸውን፣ ሥራ ላይ ያሉት ኢንቨስተሮች በሥራ ላይ እንዲቆዩ ማድረግ የእነዚህ ተቋማት ኃላፊነት ሲሆን በዚህ መልክ ሲፈጸም ግን አይታይም፡፡ የኢንቨስትመንት ሰርተፊኬት መስጠት ብቻ በራሱ የተዋጣለት ሥራ ሊሆን አይችልም፡፡ የከተማ መስተዳደሮች የሥራ ዕድል የመፍጠር ተፈጥሯዊ ኀላፊነት ቢኖርባቸውም ከንቲባዎች ሊፈጥሩት በሚገባው የሥራ ዕድል መጠን ኀላፊነት ተለክቶ አይሰጣቸውም፡፡ የትላልቅ ከተሞች ከንቲባዎች ይህን ኀላፊነታቸውን በብቃት መወጣት የቻሉ ናቸው፡፡ በከተሞች የማስተር ፕላን ጥናት ውስጥ በርካታ የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮችም ታሳቢ የሚደረጉ ቢሆንም እነሱን መሠረት ያደረጉ ትግበራ ግን አያጋጥምም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብቃት ማረጋገጫ በሚል መመዘኛ ከወጣ በኋላ በርካታ የተዘጉ ጋራዦች አሉ፡፡ ጋራዦቻቸውን ዘግተው የተቀመጡ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ የብቃት ማረጋገጫ ተገቢ ቢሆንም የየሥራ መስኩን ነባራዊ ሁኔታ፣ የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ ባላገናዘበ ሁኔታ የተፈፀመ ስላለ እርምጃው ለሥራ ፈትነት የራሱን አስተዋጽዖ አድርጓል፡፡ ስለሆነም ተቆጣጣሪ ተቋማት ከቁጥጥርና ከክልከላ በዘለለ ድርጅቶቹ በሥራ ላይ እንዲቆዩ የእገዛ ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ሥራቸውን እንደዋና ሥራ ስለማይቆጥሩት ችግሮች ይከሰታሉ፡፡

ብቃት ያለው ተቋም፣ ሕግና ቁጥጥር
***

ከዚህ ጋር በተያያዘ በሕዝብ መዋጮ የሚቋቋሙትን የአክሲዮን ማኅበራትን መመልከት በቂ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ዋና ማሳያ ሆነው ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል ዋናዎቹ የፋይናንስ ተቋማት የሆኑት የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ለግል ባንኮችና ለኢንሹራንስ ኩባንያች ሥርዓትን የተከተለ ወጥ ዕድገት አንዱና ምናልባትም ዋናው ምክንያት የብሔራዊ ባንክ ቁጥጥርና ክትትል ነው ለማለት እችላለሁ፡፡ እነዚህ ተቋማት ሕጋዊ ይዘታቸው የአክሲዮን ማኀበርነት ሲሆን የተቋቋሙትን በአብዛኛው ለሕዝብ በተሸጠ አክሲዩን አማካኝነት ነው፡፡

ሌሎች በርካታ ለሕዝብ በተሸጡ አክሲዮኖች የተቋቋሙ የአክሲዮን ማኅበራት ቢኖሩም እንደብሔራዊ ባንክ ጠንካራ ጥርስ ያለው ተቆጣጣሪ የመንግሥት ተቋም ስላልነበራቸው በቢሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ ሳይውል ቀርቷል፡፡ ኀላፊነት በሚሰማቸው እጅ ወድቀው ከነበሩት ጥቂት የአክሲዩን ማኀበራት ውጪ ብዙዎቹ ለባለአክሲዮኖቻቸው ያተረፉላቸው የትርፍ ድርሻን ሳይሆን ቁጭትና ፀፀትን ብቻ ነው፡፡ እነዚህ የአክሲዮን ማኅበራት ከአመሠራረታቸው ጀምሮ እስከፕሮጀክት አፈጻጸማቸው ድረስ ጥብቅ የክንውን ክትትል ቢደረግባቸው ኖሮ በሺሕዎች ለሚቆጠሩ ዜጐች የሥራ ዕድል ይፈጥሩ ነበር፡፡

ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የቀጠሯቸውን ባለሙያዎች ብዛት ስንመለከት በምሩቃን ቅጥር ውስጥ ያላቸውን ከፍተኛ ሚና እናደንቃለን፡፡ በሕዝብ መዋጮ የተቋቋሙትና የመከኑት የአክስዮን ማኅበራትም ተመሳሳይ አስተዋጽዖ ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ በሌሎችም መስኮች ተገቢውን ተቋም፣ አግባብ ያለውን ሕግና ቁጥጥር አቀናጅቶ አለመጠቀም በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ስንመለከት በርካታ ዕድሎች እንዳመለጡት ግልጽ ነው፡፡ ካለበት መሠረታዊ ችግር ጋር ተደምሮ የሪል እስቴት ሕግ አለመውጣትን እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሁንም እየተቋቋሙ ያሉት ግዙፍ ካፒታል ለሕዝብ በሚሸጥ አክሲዮን በመሰብሰብ ሥራዎችን እንከውናለን የሚሉትም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ላለማለፋቸውስ ምን ዋስትና አለ?

ኢትዮጵያ ከሕዝብ በሚሰበሰብ አክስዮን የሚቋቋሙ ባለግዙፍ ካፒታልና ባለብዙ ባለአክሲዮን የንግድ/ቢዝነስ ድርጅቶች ያስፈልጓታል፡፡ ሐበሻ ቢራ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ዘርና ሃይማኖት የሌላቸው የበርካታ ሺሕዎች ባለአክስዮንኖች ንብረት የሆኑ ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች በርካታ ጠቀሜታ አላቸው፡፡ እምነት የሚጣልባቸው አደራጆችን በማበረታታትና መንግሥት ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ የአክሲዮን ማኅበራት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዲገቡና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ቁጥጥርና ክትትል እንጂ ገንዘብ ማሰባሰቡ ችግር እንዳልሆነ በርካታ የመከኑ የአክሲዮን ማኅበራት ምስክር ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የብሔራዊ ባንክን ሞዴል በመከተል ቁጥጥሩንና ክትትሉን የሚያደርግ ተቋም እንዲቋቋም ለረዥም ጊዜ ጉትጐታ ሲደረግ ነበር፡፡ በዚህ መሃል ብዙ ጉዳት ደርሷል፡፡

በአጠቃላይ ሥራ ፈጠራ ገንዘብ በመስጠት ብቻ የሚፈታ ሳይሆን በርካታ ዘርፈ ብዙ መፍትሔዎችን በማቀናጀት ማስፈጸም የሚፈልግ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አንዱ ሕግን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል፣ ተቋማት በሕግ የተሰጣቸውን ኀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ማድረግና ቁጥጥርና ክትትል ነው፡፡