የስፖርት ፌዴሬሽኑ ውሳኔ ፤ዶ/ር አብይን እንደዜጋ ተቀብሎ ለማነጋገር አይገታንም፤ (አሰግድ አረጋ)

የስፖርት ፌዴሬሽኑ ውሳኔ ፤ዶ/ር አብይን እንደዜጋ ተቀብሎ ለማነጋገር አይገታንም፤
(አሰግድ አረጋ)

ጠ/ሚኒስትሩን ላለመጋበዝ በስሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን የደረሰበትን ውሳኔ እንደየስሜታችን  አስተናግደነዋል። ከመግለጫው እንደተረዳነው ዶ/ር አብይንና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶችን ባልመጠነ መስተንግዶ ለመቀበል  እንዳልተዘጋጀ ነው ።

ይሁን እንጂ ፤በተለያዩ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች እየወጡ ያሉ መርጃዎችና ( ተዓማኒነት አላቸው ከሚባሉ የሚዲያ አውታሮችና ታዋቂ ግለስቦች ጭምር) እየተነገረ ያለው ዕውነታ ፤ በውሳኔው ላይ ስሜታችን እንዲሻክር ፤ ፌዴሬሽኑ ደረሰበት ለተባለው ውሳኔ አሉታዊ መንፈስ እንዲኖረን የበኩልን ሚና እንደተጫወተ ነው። ለአብነት ለመጥቀስ፤ ጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄውን ለፌዴሬሽኑ እንዲያቀርቡ የተሄደበት መንገድ ቀናነትንና ቀጥተኝነትን ያልተላበሰና ፤ በራሱ ጥያቄ ያስጫረ እንደነበር ተመልክቱዋል።

የዶ/ር አብይ መስተንግዶም በመሃበረሰቡ የመሪነት ሚና ባልታወቁና አመኔታን ባላተረፉ ግለስቦችና ተቁዋማት እንዲመራ የተሞከረብት ሁኔታና ይህም “ግብዣቸው ፈጠነብን” ፤ “አሁንም ኢሕአድግ ናቸው” ከሚሉ ወገኖች ጋር ተዳምሮ በውሳኔው የድምጽ አሰጣጥ ላይ ጥላውን እንደጣለበትም ተደምጡዋል።

በትክክለኛው መንገድ ቢኬድም እንኩዋ ውጤቱ አሁን ካየነው ላይለውጥ ይችላል፤ ነገር ግን የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ያለፈበት ጎዳና  በተቁዋሙ ተዓማኒነት ላይ ሊጥል የሚችለው ጠባሳ በቀላሉ መታየት የለበትም።

በእርግጠኝነት ምን እንደተፈጸመ ለመረዳት በጊዜና  ታሪክ ሂደት ውስጥ አልፎ የምናየው ስለሚሆን፤ ወደሁዋላ ላለመመለስ ለራሳቸን ቃል ገብተን፤ እውቀታችንንና ጉልበታችንን ባሰባሰበ ሂደት፤ ወቅቱን በመጠነና የጊዜውን ፍጥነት በአማከለ ሂደት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን የለውጥ ጉዞ በተጨባጭ ለማገዝ  የምንቀሳቀስበት እንዲሆን ጥሪያችን ነው።

በመሰረቱ፤ ዶ/ር አብይ እያራምዱ ያሉት ኢትዮጵያዊነት ከፌዴሬሽኑ ውሳኔና እርሱም ካስከተለው በጎም ሆነ በጎ-ያልሆነ ስሜት በላይ ነው። እያሳዩን ካለው ባህርያቸው ልንገምት እድምንችለው፤ የፌዴሬሽኑን ግብዣ ለማግኘት በጉዋሮ በር የሚሄዱ ወይም ስነ ስርአቱን ለመምራት ሸፍጥ ያለው ድርጀታዊ ስራ እንዲሰራም የሚጠይቁ አይመስሉንም።

ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ብቅ በሚሉበት አጋጣሚም ኢሳትንና ሌሎች ታዋቂ የሚዲያ አውታሮችን የሚጎብኙ፤ በከተማዋ የከተሙትን የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የሃይማኖት ተቁዋማትና ነዋሪዋን አለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚያነጋግሩ እንደሚሆኑ ተስፋችን ነው፤ እነ የዲሲ ግብረሃይል እያሳደዱ እሚጋፈጡዋችው መሪ ከመሆን የዘለሉ፤ ይልቁንም፤ በራሳቸው ጥያቄ በጠረጴዛ ዙሪያ በጋራ ሀገራቸው ጉዳይ ላይ ለመውያየት ድፍረቱ ያላቸው ይመስሉናል፤ በቅርቡ እየወጡ ካሉ መረጃዎች እንደምንገምተው ፤ዶ/ር አብይ በቅርቡ ወዲህ ወደ ምድረ-አሜሪካ ጉዙዋቸውን እሚያቀኑበት ሁኔታ እንዳለ ነው።

ይህን አጋጣሚ ፍሬያማ ለማድረግ ታዋቂ የማህበረሰቡ መሪዎችና ፤ አክቲቪስቶች፤ የሃይማኖትና የተፎካካሪ ፖለቲካ መሪዎች፤ የብዙሃን መገናኛዎችና ሀገር ወዳድ ዜጎች ተሳታፊ የሆኑበት ግብረሀይል ከወዲሁ ተቁዋቁሞ በሙሉ ሃይላችን ልንቆጣጠርው
በምንችለው ህዝባዊ አዳራሽ እንድንታደም የሚያደርገን ሁኔታ እንዲመቻቸ አክብሮታዊ ጥያቄያችን ነው።

ይህ የጋራ እንቅስቃሴያችን ፤ አንዱ የአጋዥነት ክንዳቸንን ማሳያ መድረክና የዘረጋነው እጅ አለመታጠፉንም ምረጋገጫችን ነው፤ ግንባር ለግንባር እየተያየን ለሀገር የሚበጅ ሀሳብ ለማንሸራሸር፤ ጠያቂና ተጠያቂ ለመሆን፤ ቅሬታ፤ ሂስና ግለሂሳችንን፤ ሰላማዊ ሰልፋችንን ጭምር በጨዋነት መንፈስ  ለማቅርብ ፤ከዚህ የተሻለ መድረክና ወቅቱን የጠበቀ አጋጣሚ ያለ አይመስለንም።