የቅማንት የማንነት ኮሚቴ አባላት በክልሉ መንግስት የተደረገላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል ተባለ

130 የቅማንት የማንነት ኮሚቴ አባላት በክልሉ መንግስት የተደረገላቸውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ አካባቢያቸው ተመልሰዋል

(ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል 130 የቅማንት የማንነት ኮሚቴ አባላት የተደረገላቸውን የሰላም ጥሪ ተቀበለው በመግባት በአካባቢው ሠላም ዙሪያ እየመከሩ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ይርሳው በክልሉ ሰላም፣ ደህንነት እና እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ጌትነት በመግለጫቸው በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ ግጭቶችን ለመፍታት በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በዚህም ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ግጭት ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከክልሉ ልዩ ሃይልና ከማህብርሰቡ ጋር በመሆን በውይይት መፍታት መቻሉን አስረድተዋል።

የክልሉ መንግስት ለቅማንት የማንነት ኮሚቴ ባደረገው ጥሪ መሰረት 130 የቅማንት ኮሚቴ አባላት ጥሪውን ተቀብለው በመግባት በአካባቢው ሠላም እና ደህንነት ዙሪያ ከመንግስት ጋር እየመከሩ መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

በተመሳሳይ በሰሜን ሸዋ እና በኦሮም ብሄርሰብ አስተዳደር አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በውይይትና በዕርቀ ሰላም መፈታቱን አንስተዋል።

ከቤኒሻንጉል ጉምዝ እና ከአፋር ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች ጋር ውይይት በማድረግ ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች በሰላም እንዲኖሩ መደረጉንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የግብርና ሰብል ምርትን እንዳያበላሽ ለመከላከል በተሰራ ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በቀጣይ ሰብሎችን በተገቢው ሰዓትና ጊዜ የመሰብሰብ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

በጣና ሃይቅ ላይ የተከሠተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድም የተለያዩ የመከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህ መሰረትም በአሁኑ ወቅት በሰው እና አራት ማሽነሪዎችን በመጠቀም የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌትነት፥ በቀጣይ በስነ-ህይወት እና በኬሚካል ዘዴዎች አረሙን የመከላከል ስራ ይሰራል ብለዋል።

የክልሉን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማስቀጠልም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረትና በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል።