DW : ከአንድ ወር በፊት በምስራቅ እና ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች አየል ብሎ በተስተዋለው የአካባቢ ግጭት በርካታ ዜጎች ህይወት ሲያልፍ ኩርፋ ጨሌ በሚባል ወረዳ የምትገኘው ገልዲድ ማርያም እና በኩርፋ ጨሌ እና ቀረሳ ወረዳ መካከል የሚገኘው ዋቅጅራ መድኃኒለምን ጨምሮ ሶስት ያህል አብያተ ክርስትያናት መቃጠላቸው መገለፁ የሚታወስ ነው ፡፡
በአካባቢው በአብያተ ክርስትያናት ላይ የደረሰውን ጥቃት ብቻ ሳይሆን በእምነቱ ተከታዮች ላይ “ተፈፀሟል” ያለውን ጥቃት ያወገዘው የምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ከውግዘት ባለፈ አብያተ ክርስትያናቱን መልሶ ለመገንባት እና የተጎዱትን ለመርዳት እንቅስቃሴ ጀምሯል ፡፡ የዚህ እንቅስቃሴ ኮሜቴ አባል በተለይ ለዶይቸ ቬለ DW በስልክ እንደገለፁት ሰሞኑን በምስራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተመራ ቡድን ጉዳት የደረሰባቸውን አብያተ ክርስትያናት እና በአካባቢው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በአስቸጋሪ ሁኔታ ሄዶ ተመልክቷል ፡፡
በዚህም በአካባቢ ምልከታቸው ደረሰ ያሉትን ውድመት ተናግረዋል ፡፡አስተያየት ሰጪው እንዳሉት የተቋቋመው ኮሚቴ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት እና በቃጠሎ የተጎዱ አብያተ ክርስትያናትን መልሶ ለመገንባት እንቅስቃሴ ላይ ሲሆን በቅርቡ በአካባቢው ለተጎዱ ወገኖች አስቸኳይ ጊዜ የሚያስፈልጉ ቁሳቆሶችን ድጋፍ ሲያደርግ የአብያተ ክርስትያናቱን መልሶ ለመገንባት ድጋፉን እያሰባሰበ ይገኛል ፡፡