የሀገሪቱን ፖለቲካ በሚፈለገው ፍጥነት ወደፊት ለማስኬድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መካከል ያለው መግባባት ወሳኝ ነው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


“የሀገሪቱን ፖለቲካ በሚፈለገው ፍጥነት ወደፊት ለማስኬድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መካከል ያለው መግባባት ወሳኝ ነው”

“ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይና አቶ ለማ አንድ ባህል እና አንድ ቋንቋ ኖሯቸው፣ ለተመሳሳይ ሕዝብ እየታገሉ፣ በመግባባት አብሮ መሥራት ካቃታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ አስቸጋሪ ነው ብዬ አምናለሁ” ዶ/ር ሔኖክ

BBC Amharic : የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትርና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ፤ የኢሕአዴግን ውህደት እንደማያምኑበት ለቪኦኤ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ገልፀዋል።

“መዋሀዱ ትክክል አይደለም። ከሆነም በችኮላ መሆን የለበትም፤ ወቅቱም አይደለም” ያሉት አቶ ለማ፤ በመደመር ፍልስፍናም እንደማይስማሙ ከራድዮ ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ መናገራቸው ተዘግቧል።

አቶ ለማ፤ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የፓርቲዎችን ውህደት ባፀደቀ ጊዜ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተገኝተው እንደነበር አስታውቀው ስለ ሂደቱ ግን ለጣቢያው ከማብራራት ተቆጥበዋል።

አቶ ለማ መደመርን የተቃወሙበትን ምክንያት ለቪኦኤ ሲያስረዱም፤ በአጠቃላይ ከመጀመሪያ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ድረስ የፓርቲዎች ውህደትን በተመለከተ የተለየ ሀሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ይህንንም ለሥራ አስፈጻሚውና ለሁሉም መናገራቸውን መግለፃቸው በጣቢያው ላይ ተላልፏል።

አቶ ታየ ደንደኣ ስለ ብልፅግና ፓርቲ አመሠራረት ሂደት፣ ፋይዳዎቹና የአቶ ለማ በውህደቱ አላምንም ማለትን አስመልክተው ከኤስቢኤስ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ማድረጋቸውን በፌስቡክ ገፁ ላይ አስነብቧል።

ሬዲዮው አክሎም አቶ ታዬ፣ “አቶ ለማ በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ውህደቱ አስፈላጊ እንደሆነና የመደመር ዕሳቤ ከኢትዮጵያ ዐልፎ ለምሥራቅ አፍሪካም ጠቃሚ ሃሳብ እንደሆነ ተስማምተው ነው ያጸደቁት፤ የልዩነት ሃሳብ አልሰማንም። ከዚያም አልፎ በኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴና ጉባኤ፣ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ ሁሉ የተለየ አቋም አላንጸባረቁም። በዚህ መሄድ አለብን የሚል የተለየ አማራጭ ሃሳብም አላቀረቡም” ማለታቸውን አስታውቋል።

ይህንን የአቶ ለማ አቋም አስመልክተን ያነጋገርናቸው በዋሺንግተንና ሊ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት ሔኖክ ገቢሳ (ዶ/ር) ውህደት ብለን የምንናገር ከሆነ ለዚች አገር ከፍተኛ ውለታ ዋሉ እንደ አቶ ለማ መገርሳ ያሉትን ሰዎች እየቀነስን ውህደቱን እውን ማድረግ አስቸጋሪ ነው ብለውናል።

ዶ/ር ሔኖክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎችን፣ ሀሳባቸውንና እምነታቸውን ሳያካትቱ ውህደቱን ማካሄድ ከባድ ይሆናል።

በውህደቱ ላይ አቶ ለማ እንደማይስማሙ በተባራሪ ወሬ ሲሰሙ መቆየታቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ሔኖክ፤ እንዲህ ዓይነት መከፋፈል በአሁኑ ሰዓት መፈጠር አልነበረበትም ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ።

ለዚህም ምክንያት ነው ያሉትን ሲጠቅሱም፤ “በእነርሱ መካከል በሚፈጠር አለመግባባት የኦሮሞ ትግል መከፋፈል የለበትም ብዬ ስለማምን ነው” ብለዋል።

“አቶ ለማም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ትልቅ ውለታ የዋሉ ሰዎች ስለሆኑ ሃሳባቸውን ወደ አንድ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል” በማለትም፤ “የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ እንመልሳለን ብለው ካመኑ፤ የኦሮሞ ሕዝብ መሪዎች ነን ብለው ካሉ፤ መደማመጥ አስፈላጊ ነው” ሲሉ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል።

የኢትዮጵያ መሪዎች ዲሞክራሲን አንገነባለን ሲሉ ተቃራኒ ሀሳቦችንም ማስታገድ አለባቸው ብዬ አምናለሁ የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ አሁንም ያለመግባባት መንስዔ የሆነው የውህደት ውሳኔ እንደገና መታየት አለበት ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

አቶ ለማ ኦዲፒን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በማስታረቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም በማንሳት፤ የእርሳቸው አቋም የደጋፊዎቻቸውንም አቋም እንደሚለውጠው ዶ/ር ሔኖክ ይገልጻሉ።

ከዚህም በመነሳት የአቶ ለማ አስተያየት ወደኋላ ከተተወ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ዶ/ር ሔኖክ “ለማ መገርሳን የቀነሰ መደመር፣ መደመር አይሆንም” ሲሉም አስረድተዋል።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዶ/ር ዐቢይ ይህንን የሚቀበሉ አይመስሉም የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ የኦሮሞና ሌሎች የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ እንዲመለስ የሚፈልጉ ከሆነ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይና አቶ ለማ የግድ በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ያሰምሩበታል።

‘ፖለቲካ የሰቶ መቀበል በብ ነው’

“ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይና አቶ ለማ አንድ ባህል እና አንድ ቋንቋ ኖሯቸው፣ ለተመሳሳይ ሕዝብ እየታገሉ፣ በመግባባት አብሮ መሥራት ካቃታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ አስቸጋሪ ነው ብዬ አምናለሁ” ብለዋል ዶ/ር ሔኖክ።

ፖለቲካ በራሱ የሰጥቶ መቀበል ጥበብ ነው የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ በፖለቲካ አካሄድ ውስጥ መደማመጥና ሚዛን ለሚደፋ ተፎካካሪ ሀሳብ መሸነፍ ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ።

ውህደት የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ የሚመልስ እስከሆነ ድረስ ምንም ችግር የለበትም የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ ይሁን እንጂ አዲሱ መዋቅር እንደ ሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ይሰጣል መባሉ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ይናገራሉ።

በመሆኑም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባትን ለማምጣት፣ ቆም ብለው ግልፅና ፍትሀዊ የሆነ ምክክር ከአቶ ለማ ጋር ቢያደርጉ የበለጠ ጠቀሜታ አለው ብለው እንደሚያምኑ አብራርተዋል።

አለመግባበቱ ቢቀል ምን ሊፈር ይችላል?

የአገሪቱን ፖለቲካ በሚፈለገው ፍጥነት ወደፊት ለማስኬድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መካከል ያለው መግባባት ወሳኝ ነው የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ ይህንንም መግባባት ለማምጣት ትልቁ ሚና የሚጠበቀው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑን ይናገራሉ።

በመካከላቸው መግባባት ባይፈጠር ግን የአገሪቱ ፖለቲካ ወዳልተፈለገ ጎዳና ሊሄድ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም።

ይህንንም ሲያብራሩም፤ “ምናልባትም አቶ ለማ ሥልጣን ወደ መልቀቅ እርምጃ ሊያመሩ ይችላሉ” በማለት፤ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትሩ ወደ ተቃዋሚነት ተሸጋገሩ ማለት ነው ሲሉ ያብራራሉ።

ከዚህም በተጨማሪ አቶ ለማ የተቃዋሚነትን አቋም የሚከተሉ ከሆነ በእርሳቸው አመራር የሚያምኑ አካላት ስላሉ ትልቅ የፖለቲካ ክፍፍል ይፈጥራል ብለዋል።

ይህም በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ላይ የራሱ ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ። በተለይም በመጪው ምርጫ ላይ የሕዝብ ድምጽ መከፋፈልን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሃላፊዎች በወቅታዊ የፓርቲው ሁኔታ ላይ እየመከሩ መሆኑን የኢህአዴግ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ ላይ ተጽፏል።