የለማ መገርሳ የጠለፋ ፖለቲካ አይሳካም – ስዩም ተሾመ

ኦቦ ለማ መገርሳ የመደመር ፍልስፍናን ሆነ በፓርቲዎች መዋሃድ እንደማይስማሙ ገልፀዋል።

የኦዴፓ ምክር ቤት ውህደቱን በሚያፀድቅበት ግዜ በአካል መገኘታቸውን ጭምር ገልፀዋል። በእርግጥ በውህደቱ ሂደት ላይ ይህን ያህል የጎላ ተፅዕኖ አሊያም ግድፈት ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። በዚህ ረገድ የሰፋ ክፍተት ቢኖር ኖሮ እንደ ድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ አሊያም ደግሞ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም በይፋ መግለፅ ነበረባቸው። በተመሣሣይ በመደመር ፍልስፍና አለማመን መብታቸው ነው። በኦዴፓ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የሃሳብ ልዩነት መኖሩን እንደ ልዩ ክስተት ሊወሰድ አይገባም። ይሁን እንጂ ነገሮች በሂደት አልፈው ጫፍ ላይ ከደረሱ በኋላ “ከመጀመሪያው ጀምሮ አልደግፍም፥ አልስማማም ነበር” ማለት በአጭር ቃል አይነፋም። አሁን ላይ የተቃውሞ ድምፅ ማሰማት ውህደቱን ለማደናቀፍ ካልሆነ በስተቀር መሠረታዊ የሆነ የአቋም ልዩነት መኖሩን አያሳይም። መሠረታዊ የሆነ የአቋም ልዩነት ከነበረ ደግሞ መጀመሪያውኑ አልስማማም ብሎ የራስን መንገድ መከተል ይሻል ነበር። በአለቀ ሰዓት እንዲህ ያለ ነገር ውስጥ መግባት ያው የተለመደ የመጠላለፍ ፖለቲካ ነው። ይሄ ደግሞ ወያኔና ጃዋርን ከማስደሰት በቀር የሚያመጣው ለውጥ ያለ አይመስለኝም። ይሄም ቢሆን የአንድ ሰሞን የጨበራ ተስካር ነው። ዋናው ነገር ውህደቱ እውን ይሆናል። የኢትዮጵያም ሰላምና አንድነት ይረጋገጣል። ሀገርና ህዝብን ዋስትና አስይዞ የፖለቲካ ቁማር መጫወት አብቅቷል።