በህገ መንግስቱ ላይ ማሻሻያ ሳይደረግ እና ስር ነቀል የአመራር ለውጥ ሳይኖር የሚደረገው ውህደት ዘላቂነትን አያመጣም ተባለ

DW : የኢትየጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ውህደት መፍጠሩ እኩል የፖለቲካ ተሳትፎን እንደሚረጋግጥ ዶይቼ ቬለ (DW) ያነጋገራቸው የአማራ እና የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ግን ከውህደት አስቀድሞ “የህገ መንግስት ማሻሻያ መደረግ ነበረበት” ብለዋል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባ የግንባሩን አባል ፓርቲዎች ለማዋሃድ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ከየአቅጣጫው የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛሉ። ከኢህአዴግ ጋር በአጋርነት ሲሰሩ የቆዩ የአምስት ክልል ፓርቲዎች የአዲሱ ውህድ ፓርቲ አካል እንደሚሆኑም እያነጋገረ ይገኛል።

ላለፉት 28 ዓመታት የኢህአዴግ አጋር ድርጅት ሆነው ሲሰሩ ከነበሩ ድርጅቶች መካከል የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህአዴን) አንዱ ነው። የኢህአዴግ ውህደት ለጋምቤላ ህዝቦች ምን ፋይዳ እንዳለው የተጠየቁ የክልሉ ነዋሪዎች አዎንታዊ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። በስልክ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ካካፈሉ የጋምቤላ ነዋሪዎች ውስጥ አቶ ኡጁሉ ኡጋላ የክልሉ ህዝብ ባለፉት ዓመታት በፖለቲካው ዘርፍ እምብዛም ተጠቃሚ እንዳልነበሩ አስታውሰዋል። የጋምቤላ ህዝብ የግንባሩ አባል ድርጅቶችን ውህደት “በሙሉ ልብ ተቀብሎታል” ሲሉም ድጋፋቸውን ገልጸዋል።

ሌላው ጋምቤላ ክልል ነዋሪ አቶ ኦሞድ ጆን “ከበፊትም ቢሆን መስራች እና አጋር ድርጅት ብሎ መክፈሉ ትክክል አልነበረም” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። “ውህደቱ የአገሪቱን አንድነት ከማስጠበቅም ባለፈ አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ አገሪቱን የመምራት እድል እንዲኖረው ያስችላል” ሲሉም አክለዋል።

በአማራ ክልል ዋግኸምራ ዞን የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ አቶ እሸቱ ታደሰ በበኩላቸው ውህደቱ “አሁን ያለውን የተበታተነ ሀሳብ ወደ አንድ ያመጣል” የሚል እምነት አላቸው። በዚሁ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በምትገኘው በላሊበላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ዲያቆን መለሰ አክብሮም ውህደቱ “እኩል የመሪነት ሚናን የሚያረጋግጥ ነው” ይላሉ። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ግን ከሁለቱ አስተያየት ሰጪዎች የሚቃረን ሀሳብ አላቸው። የጎንደሩ ነዋሪ “በህገ መንግስቱ ላይ ማሻሻያ ሳይደረግ እና ስር ነቀል የአመራር ለውጥ ሳይኖር የሚደረገው ውህደት ዘላቂነትን አያመጣም” በሚል ተችተዋል፡፡

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባደረገው ውይይት የውህደቱን ጥያቄ በአብላጫ ድምጽ ከመደገፍ ባሻገር የአዲሱን ውህድ ስያሜ እና የመተዳደሪያ ደንብ አጽድቆ ለግንባሩ ምክር ቤት መርቷል። መቶ ሰማንያ አባላት ያሉት የኢህአዴግ ምክር ቤት ከዛሬ ሀሙስ ህዳር 11 ጀምሮ ውህድ ፓርቲውን በተመለከተ ለስብሰባ ተቀምጧል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።