ኢሕአዴግ ግብርና መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ፖሊሲውን በ አዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊተካው መሆኑ ተሰማ

DW : ዐቢይ አሕመድ «ተከታታይና ፈጣን ዕድገት አስመዝግቧል፤ ሚሊዮኖችን ከአስከፊ ድህነት አውጥቷል፤ የመሰረተ ልማት ግንባታ አስፋፍቷል» እያሉ የሚያወድሱትን የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ «የሽርኮች ካፒታሊዝም» ፈጥሯል ሲሉ ይከሱታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መደመር በተባለ መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ የገበያ፣ የመንግሥት እና የሥርዓት ጉድለቶች እንዳሉበት ገልጸዋል

ለመዋሐድ ዝግጅት ላይ የሚገኘው ኢሕአዴግ ከዚህ ቀደም ይከተል የነበረውን ግብርና-መር የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ገሸሽ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። የግንባሩ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው እሁድ ካደረገው ውይይት በኋላ «አንድ ላይ የተመሰረተ ክፍለ-ኤኮኖሚ ብቻ በመከተል የዚህን አገር የኤኮኖሚ ችግር መፍታት አይቻልም» የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ ተናግረዋል።

በአቶ ፍቃዱ ማብራሪያ መሰረት፦ ውኅዱ ፓርቲ ለግብርና፣ ለማዕድን፣ ለቱሪዝም እና ለኢንዱስትሪ ዘርፎች ዕኩል ትኩረት ይሰጣል። በነፃ የገበያ ሥርዓት ፓርቲው «አካታች የሆነ የካፒታሊዝም ሥርዓት» የመፍጠር ዓላማ እንዳለው አቶ ፍቃዱ ገልጸዋል።

በአቶ ፍቃዱ ማብራሪያ መሠረት ውኅዱ ፓርቲ በሥልጣን ከቆየ መንግሥት በገበያው በሚኖረው ጣልቃ ገብነት በኩል ባለፉት ሁለት ዓሥርተ-ዓመታት ኢሕአዴግ ከተከተለው የተለየ አቋም አይኖረውም። ውኅዱ ፓርቲ ይመራበታል ተብሎ በሚጠበቀው እና  መደመር በተሰኘ መጽሐፋቸው ዐቢይ አሕመድ «መንግሥት የገበያ ጉድለትን ለማረም ጣልቃ ከመግባት በዘለለ ገበያውን የመፍጠር እና የማጠናከር ሚና ሊኖረው ይገባል» ይላሉ። ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግሥት በገበያው የሚያድርገው ጣልቃ ገብነት «የገበያውን ፍትሐዊነት የሚያረጋግጡ ሕግጋትን በማውጣትና ማስፈጸም፤ ለግል ዘርፉ አትራፊ ያልሆኑ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ቀድሞ ገብቶ ማልማት፤ የግል ዘርፉን  ማሳተፍና የግል ዘርፉ መንሠራራት ሲጀምር ከዚህ የአምራችነት ሚና በፍጥነት ራሱን ማግለል ይኖርበታል» ሲሉ ያብራራሉ።

ዐቢይ «መንግሥት የሰው ሐብት ክምችትን በማዳበርና መሠረተ-ልማትን በማስፋፋት ረገድ ትልቅ ሚና መጫወት አለበት» የሚል አቋም አላቸው። ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተረከቡት ኢሕአዴግም ይሁን መንግሥት በዚሁ እምነት የሚመራ ሆኖ ቆይቷል። መንግሥት ከሸቀጥ ችርቻሮ እስከ ግዙፍ የመሠረተ-ልማት ግንባታ በገበያው የነበረው ጣልቃ ገብነት በውስብስብ ችግሮች የተተበተበ አገሪቱንም ለከፍተኛ ወጪ የዳረገ ነበር። ጅማ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር እና የልማት ጥናት መምህሩ አቶ ፍሰሐ ሙሉ እንደሚሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ መደመር በተሰኘ መጽሐፋቸው ባቀረቡት ሐሳብ ኢሕአዴግ ከሚያምንበት ገሸሽ የማለት አዝማሚያ ማሳየታቸውን ይናገራሉ።

አቶ ፍሰሐ «በልማታዊ መንግሥት በተለይ ፕሮጀክቶች ማለቅ ሲያቅታቸው፤ በሙስና ነገሮች ሲበላሹ፤ የተጠበቀውን ያክል ውጤታማ ሳይሆኑ ሲቀሩ ቢያንስ የግሉ ዘርፍ ቢሳተፍ ኤኮኖሚውን ሊያግዝ ይችላል፤ ያለው የዕዳ ጫናም ሊቀንስ ይችላል። አንደኛ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል በማዛወር ሁለተኛ ፉክክርም ሊኖር ስለሚችል ያ ኩባንያ ጠቅልሎ ሊይዝበት የሚችል ነገር ስለሚያመቻች ከዚያኛው የመውጣት ነገር ነው እንጂ፤ ይኸኛውም ሙሉ በሙሉ ካፒታሊዝም አይደለም። ቅይጥ አይነት ነገርም አይደለም። ትኩረቱ የልማታዊ መንግሥትን አቅጣጫ በሌላ መንገድ የመሔድ ይመስለኛል» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ አስራ ስድስት ምዕራፎች ባሉት መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ኤኮኖሚ ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶች እና በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት ኢሕአዴግ የተከተላቸው ምጣኔ ሐብታዊ ፖሊሲዎች የነበሩባቸውን ጉድለቶች ይተነትናሉ። በዐቢይ ትንታኔ መሠረት የገበያ፣ የመንግሥት እና የሥርዓት ጉድለቶች የኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት ማነቆዎች ናቸው። የትምህርት እና የሲቪክ ተቋማት ተሳትፎ መገደብ በተጨማሪ ምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

«በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያጋጥመው የገበያ ጉድለት በአመዛኙ ከግብይት ይዘት ጋር በተለይም ከገበያ መረጃ ጋር በተያያዘ ያለው ነው። በተለይም ደግሞ የድለላ ሥራ የገበያ መረጃን ከማዛባት እና የገበያውን ሥርዓት ከማመስ አንፃር ያለው ተጽዕኖ በሀገራችን ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም የግል ባለሀብቶች ከመንግሥት እና ከገዢዎች የተሻለ መረጃ ስላላቸው ይኸን ተጠቅመው ተገቢ ያልሆነ እጥረት ወይም የዋጋ ንረትን ሲፈጥሩ የሚከሠተው የገበያ ጉድለት ከፍተኛ ነው» የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።

«አሁን ባለበት ሁኔታ መንግሥት የራሱን ኃላፊነቶች ሁሉ ተወጥቶ ገበያው ሙሉ በሙሉ የነፃ ገበያ ፍልስፍናን ተከትሎ እንዲሔድ ቢፈቅድ እንኳን፤ አብዛኞቹ ባለሐብቶች የሚፈለገውን ቅልጥፍናና ውጤታማነት በአጭር ጊዜ በማምጣት ገበያውን የማስተካከል ዐቅም አላዳበሩም» ባይ ናቸው።  «ስለዚህ መንግሥት በቀጣይ ጊዜያት የግል ባለሐብቱን እያበረታታ ወደ መሥመር ለማስገባት የሚያደርገው ጥረት ደረጃ በደረጃ ሊሆን ይገባል። በአንድ ጊዜ ሁሉን ነገር ለገበያው ሊለቀው አይገባም» ብለዋል።

ዐቢይ ኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት ባለሐብቶችን በመደገፍ እና አብሮ የመስራት መንገድ በተከተለባቸው ዓመታት «የሽርኮች ካፒታሊዝም» እንዲፈጠር ኾኗል ሲሉ ይወቅሳሉ። «በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑ መልኩም ቢሆን በግል ዘርፉ ዋንኛው የኤኮኖሚው አንቀሳቃሾችና የምርት ኃይሎችን የተቆጣጠሩ ሰዎች ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ በጥቅም ትስስር የተቧደኑ ወይም በዝምድና የተሳሰሩ ግለሰቦች ናቸው» ይላሉ።

በጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚክስ መምህሩ አቶ ሐብታሙ ግርማ «ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰው ኪሳራ ልማታዊ መንግሥት አስተሳሰቡ ያመጣው ሳይሆን አተረጓጎሙ ነው። ፐብሊክ ኢንቨስትመንት የግል መዋዕለ-ንዋይን መደገፍ ሲገባው ከገበያው የሚያስወጣው አካሔድ ተከትሏል። ያ የሆነው ልማታዊ መንግሥት በሚለው አቅጣጫ ተመርቶ ሳይሆን አብዛኞቹ ልኂቃን በፖለቲካ ባላቸው ግንኙነት በመንግሥት ሥራዎች የግሉን ዘርፍ እያስወጣ የራሱን ቢዝነስ እየመሰረተ ነበር። አሁንም መደመር ሊገጥመው የሚችለው አደጋ ይኸ ነው። የተፃፈው ነገር እንደሚለው ወደ ፊት ደግሞ ሲተገበር የምናየው ልዩነት ሊኖረው ይችላል። ስለዚህ ጥብቅ የሆነ ቁርጠኝነት ይፈልጋል» ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ዐቢይ «ባለሐብቶች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር የጥቅም ትስስር በመፍጠራቸው ወይም በሌብነት ላይ በመመስረታቸው» የመንግሥት ጉድለት መፈጠሩን ያስረዳሉ። ለዚህም የልማት ድርጅቶችን እና የኢሕአዴግ አባል ፓርቲ ንብረት የሆኑ ተቋማት (ኢንዶውመንቶችን) በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ዐቢይ እንደሚሉት በመንግሥት ተቋማት አለ የሚሉት ዳተኝነት፤ የተቋማት አቅም እና የአመራር ብቃት ማነስ፤ ቅጥ ያጣና የግሉን ዘርፍ የሚያፍን የቁጥጥር ሥርዓት፤ የተንዛዛ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ለጉድለቱ አስተዋፅዖ አላቸው።

«የመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች በቴክኖሎጂ ፈጠራና አስተዳደር የላቁ አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች አቅም መፍጠሪያና ማጎልበቻ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ያስፈልጋል። የሜጋ ፕሮጀክቶችንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን አፈፃጸም ለማሻሻል፤ ከግምገማና አነስተኛ ለውጥ ባሻገር ስትራቴጂክ መፍትኄ የሚኾነው የግሉ ዘርፍ በልማት ሥራዎች ላይ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ ነው» የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ዐቢይ ለሚመኙት ዘላቂ ዕድገት እና ልማት መንግሥት፣ ባለሐብቶች ሲቪል እና የትምህርት ተቋማት ተባብረው እንዲሠሩ ይመኛሉ። አቶ ፍሰሐ ግን «ሁሉም ሲሰባሰብ ትብብሩ የሆነ ነገር ይፈጥራል የሚል አቋም አላቸው። መንግሥት እንዳለ ሆኖ የግል እና የሲቪክ ዘርፎች ተሰባስበው አብዛኛውን ለመጥቀም የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል የሚል ነው። ነገር ግን ሲቪል ሴክተሩ ምን ያክል ጠንካራ ነው? የግሉንም ዘርፍ ስናየው ለዚያ የሚያመቹ ነገሮች ላይኖሩ ይችላሉ» ሲሉ ጥያቄ ይሰነዝራሉ።
አቶ ሐብታሙ በበኩላቸው «ልማታዊ መንግሥት የሚከተለው የምሥራቁን ዓለም ነበር። መነሻም ያደረገው ታይገር ኤኮኖሚ የሚባሉ በደቡብ ምሥራቅ እስያ ያሉ እንደ ደቡብ ኮሪያ፤ ታይዋን እና ሆንግ ኮንግ ያሉ አገራትን ነው። መሰረቱ ማቴሪያል ካፒታሊዝም ነው። አጠቃላይ ግቡም ዕድገት ማምጣት፤ መሰረተ-ልማት መገንባት እና ድህነትን ማስወገድ ነው። ትኩረት የሚያደርገው የገቢ ድህነት ላይ ነው። ስለዚህ ያለፈው የኤኮኖሚ አቅጣጫ ትኩረቱ ሰው ላይ አልነበረም። ሐብት ክፍፍል ላይ ነው የነበረው። የአሁኑ መደመር ግን መነሻውም መድረሻውም ሰው ላይ ያደረገ ነው» ሲሉ መሠረታዊ ለውጥ መታዘባቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው እሁድ የውኅዱ ፓርቲ ፕሮግራሞች ላይ በተወያየበት ወቅት የሕወሓት ተወካዮች አልነበሩም። ሕወሓት ውኅደቱን በይፋ ቢቃወምም እስካሁን በዝርዝር የፓርቲው ፕሮግራሞች ላይ ያለው ነገር የለም። በዓለም አቀፉ የቀውስ ጥናት ማዕከል የኢትዮጵያ ጉዳዮች ተመራማሪው ዊሊያም ዳቪድሰን «ገዢው ኢሕአዴግ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፅንሰ-ሐሳብን ጥሎ በመደመር እሳቤ ወደ ሚመራ አንድ ፓርቲ ለማዋኃድ ሁኔታዎቹ አጋጣሚዎቹም ትክክል ናቸው የሚል ዕምነት ሕወሓቶች የላቸውም። ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ምኒስትሩ ያቀረቡትን የፖለቲካ ፕሮግራም እና ርዕዮተ- ዓለም አላመኑበትም፣ አይቀበሉትም። ይልቁን ይህ የኅብረ-ብሔራዊው ወይም የብሔር ፌድራሊዝሙ የመጨረሻ መጀመሪያ እንደሆነ ህወሓት ያምናል» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አንድ መቶ ሰማንያ አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ምክር ቤት ነገ ሲሰበሰብ ከሚመክርባቸው ጉዳዮች አንዱ ሥራ አስፈፃሚው ያጸደቀው የብልፅግና ፓርቲ የኤኮኖሚ ፕሮግራም እንደሆነ ይጠበቃል።