ጅብ ባደረሰው ጉዳት የሦስት ሕጻናት ሕይወት ሲያልፍ አንድ ሰው ክፉኛ ተጎዳ።

DW : በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በወላይታ ዞን ባለፉት ሦስት ተከታታይ ቀናት ጅብ በሰዎች ላይ ጉዳት አደረሰ። ከስፍራው የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ጅብ ባደረሰው ጉዳት የሦስት ሕጻናት ሕይወት ሲያልፍ አንድ የ14 ዓመት ልጅም ክፉኛ ተጎድቷል። የአካባቢው ባለስልጣናት እንዳሉት ጅቡ ጉዳት ያደረሰው በዞኑ ሶዶ ዙሪያ ወረዳ በሾላ ኮዶ ቀበሌ ጋውሎሮ በተባለች መንደር ውስጥ ነው።

አደጋውን ያደረሰውም ንጋት እና ምሽት አካባቢ ወደ መንደሩ ዘልቆ በመግባት መሆኑን የሶዶ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሳምነው አዲሱ ለዶቼ ቬለ (DW) ገልጸዋል። «ጅብ በአካባቢው ኅብረተሰብ ላይ ባረሰው ጉዳት እስካሁን ሦስት ሰው ነው የሞተው፤ አንድ ሰው ሆስፒታል በህክም ርዳታ ላይ ነው ያለው።

ሕጻናት ናቸው ዕድሜ ከስምንት እስከ 14 ዕድሜ ያልሆናቸው፤ አንዱ ሕጻን ነው የሞተው ወደ ዘጠኝ ዓመት ነው፣ አንዷ የ14 ዓመት፣ ሕጻን ናት የሞተችው። በተለያየ ቦታ የጅቡ መልኩ ተመሳሳይ ነው። ለመግደልም ብዙ ሙከራ ተደርጎ እያመለጠ ያስቸገረበት ሁኔታ ነው፤ ያው ከተለያዩ አካባቢዎች እኛ ባረጋገጥነው መረጃ ጅቡ አንድ ነው እስካሁን ጉዳት እያደረሰ ያለው።»

በጅቡ ንክሻ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰበት የዐሥራ አራት ዓመት ልጅ በወላይታ ሶዶ ሆስፒታል የህክምና ርዳታ እየተደረጋለት እንደሚገኝም አክለው ተናግረዋል። ጥቃት ያደረሰውን ጅብ ከአካባቢው ለማስወገድ ቢሞከርም ቦታው እየቀያየረ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆኑ አሰሳ በማድረግ ላይ ይገኛል ::