ድሬዳዋ አዲስ ባገረሸው ግጭት በነዋሪዎች ላይ የመሳርያ ጥቃት ደረሰ

DW : በድሬዳዋ ትናንት ዳግም በአዲስ ባገረሸው ግጭት በአራት ሰዎች ላይ የመሳርያ ጥቃት ሲደርስ ከአስር የሚበልጡ በመጠኑ መጎዳታቸውን የድሬደዋ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል አስታወቀ፡፡ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ባይረጋገጥም በትናንቱ ግጭት ቦምብ መፈንዳቱን የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ፡፡

የድሬደዋ ድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር የሺዋስ መኳንንት ለDW በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በትናንትናው ዕለት በከተማው ቀፊራ እና ገንደጋ እና አዲስ ከተማ አካባቢዎች እንደ አዲስ አገርሽቶ የተጀመረውን ግጭት ተከትሎ በርካታ የተጎዱ ሰዎች ወደ ሆስፒታሉ መጥተዋል። ከነዚህም አራቱ በመሳርያ የተመቱ እንደሚመስሉ ገልፀዋል።

ዶ/ር የሺዋስ ተጎድተው ወደ ህክምና ከመጡት እና በመሳርያ ጉዳት የደረሰባቸው እንደሚመስሉ እንደሚመስሉ ከገለፃቸው አራት ተጎጅዎች ሁለቱ በፍንዳታ እና ሁለቱ በጥይት ሳይሆን እንደማይቀር ጠቁመዋል። ምንም የሞተ ሰው አለመኖሩንም አክለዋል።  ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታሉ የሚገኙት ተጎጅዎች ያሉበት የጤና ሁኔታ ጥሩ መሆኑን ዶ/ር የሺዋስ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል።

በሌላ በኩል ትናንት በድሬዳዋ በተቀሰቀሰው ግጭት ቦንብ መፈንዳቱን የተለያዩ መረጃዎች ቢኖሩም ከፖሊስ ወይም ከሚመለከተው አካል ስለ ድርጊቱም ሆነ በማን እንደተፈፀመ ለማረጋገጥ ያደረግነው ጥረት ባለመሳካቱ በዚህ ሪፖርት ማካተት አልተቻለም። ግጭቱ በተከሰተበት አካባቢ አንፃራዊ ሰላም ቢኖርም ዛሬ ጠዋት ድረስ የመሳርያ ተኩስ ድምፅ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ከአመራር ጀምሮ አንዱ አካል አንዱን በሚከስበት ሁኔታ ውስጥ ያለው የድሬዳዋ የፀጥታ ችግር በአንፃሩ በአንዳንድ አካባቢ የተረጋጋ ይምሰል እንጂ በሁሉም ዘንድ ያሰፈነው ስጋት የቀደመው ሞቅ ያለ የከተማዋ ነባራዊ ድባብ እንደራቀው ይታያል። አስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት እየሰራሁ ነው ቢልም ይህን ችግር ለመፍታት ዛሬም ቁርጠኛ የፖለቲካ አቋም እና ውሳኔ የሚሰጥ እንዲሁም የሕግ የበላይነት የሚያስከብር ጠንካራ አስተዳደር  መኖሩ አጠራጣሪ ነው የሚለው አስተያየት የብዙዎች ነው።