ኢህአዴግ ከውህደቱ ጋር ተያይዞ የአደረጃጃት ለውጥ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ በፓርቲው ውህደት ዙሪያ ውሳኔ ያሳልፋል

(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ማዕከላዊ ኮሚቴ በቅርቡ በፓርቲው ውህደት ዙሪያ ውሳኔ የሚያሳልፍ መሆኑ ተገልጿል።

ግንባርነቱን ትቶ ወደ ፓርቲነት ለማደግ ሂዳት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ውህድ ፓርቲ ለመሆን ያስጠናው ሳይንሳዊ ጥናት በብሄራዊ ድርጅቶች ውይይት ሲደረግበት ቆይቷል።

አሁን ላይም አብዛኛዎቹ ብሄራዊ ድርጅቶች በጥናቱ ላይ ባደረጉት ውይይት የውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ሙሉ እምነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የከተማ ፖለቲካ ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ካሳሁን ጎፌ ውህደቱ በፓርቲያቸው በኩል ይሁንታ ማግኘቱን ተናግረዋል።

በተደረገው የውህደት ጥናት ላይ በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ውይይት ያደረገው የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በቅርቡ ውህደቱ ፍሬ እንደሚያፈራ እምነቱ መሆኑን የፓርቲው አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ ተናግረዋል።

ኢህአዴግ አሁን ካለበት ግንባርነት ተላቆ ወደ አንድ ሀገራዊ ፓርቲነት ማደጉም ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን በማረም ጠንካራ ፓርቲ እንዲሆን ያስችለዋል ነው ያሉት ።

የኦዴፓ የከተማ ፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ካሳሁን ጎፌ ኢህአዴግ በተቋም እንጂ በግለሰብ ደረጃ አባልነት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል።

ተሳትፎ ሳይኖር ዴሞክራሲ የማይኖር በመሆኑ ትክክለኛ እና እውነተኛ ዴሞክራሲ ለማስፈን ውህደቱ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑንም አክለዋል።

አቶ አብርሃም አለኸኝ በበኩላቸው ውህደቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ ላይ በጋራ እንዲወስን የሚያስችል መሆኑን ነው የሚያብራሩት።

በሌላ በኩል የውህደቱ ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑ ቢገለፅም፥ውህደቱ መጨፍለቅ በማምጣት አሃዳዊነት ይፈጥራል የሚሉ ሃሳቦች ይደመጣሉ።

ይሁን እንጂ ይህ ሃሳብ የመንግስት አስተዳደር ስርዓትን ከፓርቲ ጋር አንድ አድረጎ ከማየት አባዜ የመጣ መሆኑን ነው የፓርቲ የስራ ሃላፊዎቹ የሚገልጹት።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ አለሙ ውህደቱ አሃዳዊነትን የማያመጣ መሆኑን ግንባሩ በአሁኑ ወቅት እየተከተለ ያለውን አሰራር በማንሳት አብራርተዋል።

ኢህአዴግ ከውህደቱ ጋር ተያይዞ የአደረጃጃት ለውጥ እንደሚያደርግም ይጠበቃል።

ይህን ተከትሎም ግንባሩ የሚከናወነው የአደረጃጀት ለውጥ የፕሮግራም ለውጥን ያስከትላል የሚል ጥያቄ ሲነሳበት ይስተዋላል።

አቶ መለሰ አለሙና አቶ ካሳሁን ጎፌ የፓርቲው ሪፎርም የፕሮግራም ማሻሻያ የሚያስፈልገው ከሆነ የማድረግ ዕድል እንዳለው ጠቁመዋል።

የአዴፓ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ በበኩላቸው የአደረጃጀት ለውጡን ወቅቱን ከሚዋጅ ፕሮግራም ጋር ማቀናጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የፕሮግራም ለውጡ ግን በፓርቲውም ሆነ ከፓርቲው ውጪ በሚኖር ፍላጎት ይወሰናል ነው ያሉት።

አሁን ኢህአዴግ የሚያደርገው ውህደት በአራት እህትና በአምስት አጋር ብሄራዊ ድርጅቶች ነው ወደ አንድ ሀገራዊ ፓርቲነት የሚያድጉት ።

በሌላ በኩል ከዘጠኙ ብሄራዊ ድርጅት ውጪ በግለሰብም ሆነ በፓርቲ ደረጃ ቀጣይ ውህደት እንደሚፈፅም የሚጠበቀውን ኢህአዴግ የሚቀላቀል ይኖራል ወይ የሚለው ጥያቄ ይነሳል?

የውህደቱ ጥናት በብሄራዊ ድርጅቶች ውይይት ተደርጎበት የተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ በማዕከላዊ ኮሚቴው መቋጫ ያገኛል ያሉት አቶ መለሰ፥የግንባሩ ውህደት ከተወሰነ ሌሎች ፓርቲዎችን ይሁን ግለሰቦችን ወደ ፓርቲው የመቀላቀል ዕድሉ ዝግ አለመሆኑን ጠቁመዋል።