“በወልዲያ ለተፈጸመው ድርጊት መንግስት ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰድ አለበት” -ፕ/ር መረራ ጉዲና

“በወልዲያ ለተፈጸመው ድርጊት መንግስት ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰድ አለበት” -ፕ/ር  መረራ ጉዲና

(ኢፕድ) በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሞ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ድርጊት ፓርቲያቸው ማውገዙን ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ገልጸው መንግስት እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን በፍጥነት እልባት እንዲያገኙ ማድረግ ካልቻለ የህዝቦችን አብሮነት ይጎዳል ብለዋል።

እንድህ ያሉ ድርጊቶች አሁን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜ ሲፈጸሙ እንደነበር የገለጹት ፕሮፈሰሩ መንግስት ተማሪዎችን የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት፣ ይህንንም በተግባር ማሳየት ይገባዋል ብለዋል።

ሰሞኑን በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተው ነገር ተገቢነት የሌለው ድርጊት ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ሁኔታውን በእርጋታ በመመልከት ትምህርታቸውን መቀጠል ይገባቸዋል ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።

ፕሮፌሰሩ አክለውም እንዲህ ያሉ ነገሮች ዳግም እንዳይከሰቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

እንዲህ ያሉ ድርጊቶች የሚከሰቱት የፌዴራልና የክልል መንግስታት ተናበው መስራት ባለመቻላቸው እንደሆነ የገለጹት ፕሮፈሰር መረራ በቀጣይ እንዲህ ያሉ ነገሮች እንዳይከሰቱ ሁለቱ መንግስታት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እጃቸው አለበት የተባሉ አካሎችን ወደ ህግ ማምጣት አለባቸው ብለዋል።