የሸፈተ ሰራዊት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አለ ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ሐሰት ነው ተባለ

በአሶሳ አቅራቢያ በሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር ዙሪያ የሸፈተ ሰራዊት አለ ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ፍፁም ሀሰት መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስታወቀ፡፡

በአሁኑ ሰዓት በሱዳን ድንበርና አሶሳ ዙሪያ የሸፈተ ሰራዊት አለ ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ፣ የቆየ ታሪክ እንጂ ወቅታዊውን የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ አይደለም ሲል፣ የቤኒሳንጉል ጉምዝ ክልል የመንግስት ኮሚንኬሽን ጉዳይ ፅ/ቤት ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቋል፡፡

ቀደም ሲል ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ የሱዳን አዋሳኝ ድንበር እና በአሶሳ ዙሪያ የሸፈቱ ሀይሎች እንደነበሩ የተናገሩት የኮሚንኬሽን ጉዳይ ፅ/ቤት ሀላፊው አቶ መለሰ በየነ፣ በወቅቱ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ልዩ ሀይል አካባቢዎቹን በመለየት እና ካምፕ በመስራት በጫካ ውስጥ ሸፍተው የነበሩት ላይ ተኩስ በመክፈት ማርኳቸው እንደነበር አንስተዋል፡፡

በመቀጠልም ሸፍተው የነበሩት ምርኮኞች፣ በክልሉ መንግስት ውሳኔ መሰረት ወደ ስልጠና እንዲገቡ ተደርጎ እንደነበር ለጣቢያችን ገልፀዋል፡፡

በኋላም ልዩ ልዩ ስነ-ምግባር ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ወስደዉ፣በአሁኑ ወቅት ግማሾቹ የፖሊስ አባል የሆኑ ሲሆን፣ቀሪዎቹም የቀደመ ሰላማዊ ኑሯቸውን በመምራት ላይ እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡

እናም በሱዳን ድንበርና አሶሳ ዙሪያ የሸፈተ ሰራዊት አለ ተብሎ የሚናፈሰው ወሬ ጊዜውን መሰረት ያላደረገ ፍፁም ሀሰት መሆኑን ተናግረዋል አቶ መለሰ፡፡

ሀላፊው አክለውም የቆየ ታሪክ እያነሱ የክልሉን ስም በአንድም በሌላ የሚያጠፉ ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም