በአማራ ክልል አስር ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ሰላም እንዲደፈርስ አልመውና አቅደው የሚሰሩ ኃይሎች አሉ ተባለ

ሁለት ተማሪዎች በሞቱበት የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ግጭት የተሳተፉ ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

DW : የአማራ ክልል ሰላም እና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር ዛሬ መደበኛ ጉባኤውን እየካሄደ ለሚገኘው የአማራ ክልል ምክር ቤት እንደተናገሩት በክልሉ የግለሰቦች ግጭቶች ወደ ብሔር ግጭት እየተሸጋገረ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። ትላንት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ያጋጠመውም ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል።

“ትላንትና ማታ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ላይ ተማሪዎች ኳስ ሲመለከቱ አመሹ። በኳስ ጨዋታ መደገፍ፤ በሀገራችን ክለቦች አይደለም በውጭ ሀገር ክለቦች አደጋገፍ ላይ፤ በተማሪዎች መካከል ግጭት ተነሳ። ይህን ግጭት የሚፈልጉት ኃይሎች ስላሉ ወዲያውኑ የብሔር ግጭት አደረጉት። በግጭቱ ተማሪዎች፤ ወጣቶች ተጎዱ” ብለዋል።

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ አስናቀ ለዶይቼ ቬለ (DW) በስልክ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ትናንት ምሽት አምስት ሰዓት በተነሳ ግጭት ሁለት የሶሻል ሳይንስ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ህይወታቸው ሲያልፍ አስሩ ደግሞ ቆስለዋል። የሟች ተማሪዎችን ማንነት ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

“ተማሪዎቹ ህንጻ ቁጥር ሰባት ላይ እና ግጭቱ እንደተነሳ የሚናገሩበት ሁኔታ አለ። በሌላ በኩል የአውሮፓ ሊጎች የእግር ኳስ ጨዋታ ምሽት ነበረ። እዚያ ኳስ ሲመለከቱ፣ ከDSTV አምሽተው ሲወጡ፤ ‘ችግሩ እዚያ ነው የተነሳው፤ ከዚያ ጠንከር ብሎ ነው ወደ ዶርም የገባው’ የሚሉም አሉ” ሲሉ የግጭቱ መንስኤ ነው የሚባለውን አብራርተዋል።

በግጭቱ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው አስር ተማሪዎች ከተለያየ አካባቢ የመጡ እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ተፈራ አሁን በወልዲያ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ገልጸዋል። ለተማሪዎች ግጭት መነሻ የሚሆን ምክንያት ቀደም ሲል እንዳልታዬ የሚናገሩት የዩኒቨርሲቲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ተማሪዎቹ በአንበጣ መከላከል ሥራ ተጠምደው እንደዋሉ አመልክተዋል።

ዛሬ ረፋዱን ለአማራ ምክር ቤት አባላት በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ የሰላም እና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ግን በክልሉ በሚገኙ አስር ዩኒቨርስቲዎች ላይ ሰላም እንዲደፈርስ አልመው እና አቅደው የሚሰሩ ኃይሎች እንዳሉ ጠቁመዋል። ቢሮአቸው እነዚህን ኃይሎች ለይቶ እርምጃ ለመውሰድ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም አመልክተዋል። በወልዲያ ዩኒቨርስቲ ትላንት የተፈጠረውን ግጭት በአሁኑ ወቅት ማረጋጋታቸውን ለምክር ቤት አባላት የተናገሩት አቶ አገኘሁ “በዚህ ወንጀል ላይ የተሳተፉ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል” ብለዋል።