ውስብስቡ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርና የቁጥጥር ድክመቶች የደቀኑት አገራዊ ፈተና

ውስብስቡ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርና የቁጥጥር ድክመቶች የደቀኑት አገራዊ ፈተናአፍሪካ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ በግጭቶች ስታናወጥ የኖረችና ያለች አኅጉር ስትሆን፣ ይኼ የተንሰራፋ ግጭትና ብጥብጥ ውስጣዊ ችግር ላላቸውም ሆነ መጠነኛ መረጋጋት ለሚታይባቸው አገሮች ዳፋው መትረፉ ደግሞ አልቀረም፡፡ በተለይ በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ፍላጎቶች የተተበተበውና የግጭቶች መናኸሪያ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ ችግሩ ጐልቶ የሚታይ ነው፡፡ ግጭት፣ ጦርነት፣ ብጥብጥና የመሳሰሉ ቀውሶች የቀጣናው መለያ እስከ መሆንም ደርሰዋል፡፡ ቀጣናውን ያጠኑና የግጭትና የብጥብጥ አዙሪቱ ማለቂያ አልባ ሆኖ ያገኙት ተመራማሪዎች፣ በቀልድ መልክ ቀጣናው ይኼን ያህል ብጥብጥ እያስተናገደና አዳዲስ ግጭቶችና ጦርነቶችን እየተፈለፈሉ ያለው በስሙ ሳቢያ ሊሆን ስለሚችል፣ ‹‹የአፍሪካ ቀንድ ማለቱን እንተው እንዴ?›› ሲሉም ተደምጠው ያውቃሉ፡፡

እነዚህ ደርዛቸው የሰፋ ቀውሶች መዘዛቸው የሰፋና ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ለመስጠት አዳጋች ከመሆኑም ባለፈ፣ ወደ ሌላው አካባቢ በቀላሉ እንዲዘዋወሩና እንዲሰፉ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር ነው፡፡ ‹‹የአነስተኛ የጦር መሣሪያዎች ሥርዓትና ኢተገቢ አጠቃቀም በምሥራቅ ጎጃም›› በሚል ርዕስ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ተቋም የማስተርስ ዲግሪ መርሐ ግብር የመመረቂያ ጥናት የሠሩት አቶ አዕምሮ ጠናው፣ ይኼንን እውነት እንደሚከተለው ያስቀምጡታል፡፡

‹‹የአነስተኛ የጦር መሣሪያዎች ሥርገት በአፍሪካ ቀንድና በታላቁ የሐይቆች ከባቢ ቀጣይና አድብን የሆኑ ጥረቶችን ሲያስከትሉ ይታያሉ፡፡ በተለይም የግጭት ቀጣና በሆኑት እንደ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ሰሜናዊ ኡጋንዳ የአነስተኛ መሣሪያዎች በአመፆች ሳቢያ የሚከሰቱ ሞቶች ምክንያት ናቸው፤›› የሚሉት አቶ አዕምሮ፣ ‹‹የአነስተኛ መሣሪያዎች (Small Arms and Light Weapons) ሕገወጥ ዝውውር ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አካባቢዎች እጅግ የበዛ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ሰላምና መረጋጋት ማምጣት የማይጨበጥና ትልም ብቻ ሆኖ ከእውነታ እየራቀ ነው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ይኼ ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች ሥርገት ለዓለም ማኅበረሰብ በሰላሙም ሆነ በጦርነት ወቅት አደገኛ የሰብዓዊ ልማት ፈተና ይደቅናል በማለት የሚጠቁሙት አቶ አዕምሮ፣ የመቆጣጠር ጥረቶችም በፈተናዎች ተተብትበው የተሰናከሉ ናቸው ይላሉ፡፡

የሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች ሥርገትን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች ዓለም አቀፋዊ፣ አኅጉራዊና አገራዊ መልክ ሲኖራቸው ከዓለም አቀፍ ጥረቶች በዘላቂ የልማት ግቦች በግብ 16 የተመለከተው ሁሉንም ዓይነት ግጭቶችና ተያያዥ ሞቶችን ለማስቀረት፣ እንዲሁም ሕገወጥ የመሣሪያዎችን ዝውውር መግታት የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ ከአኅጉራዊ ጥረቶች የአፍሪካ ኅብረት ያስቀመጠው ግጭቶችንና ጦርነቶችን እ.ኤ.አ. በ2030 ማስቀረት የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡

ከአገራዊ ጥረቶች አንዱ መንግሥት እያዘጋጀ የሚገኘው የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ይጠቀሳል፡፡ ሆኖም በየወቅቱ የሕገወጥ መሣሪያዎች ዝውውር የመገታት ቀርቶ የመቀነስም አዝማሚያ እያሳየ አልመጣም፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 በዓለም አቀፍ የልማት ጥናቶች የድኅረ ምረቃ ተቋም የተዘጋጀው የአነስተኛ መሣሪያዎች ዳሰሳ ጥናት፣ በአፍሪካ በሲቪል ግለሰቦች እጅ የሚገኙ የጦር መሣሪያዎች 40 ሚሊዮን እንደሚሆኑ በመገመት፣ በ100 ሰዎች መካከል በአማካይ 3.2 መሣሪያዎች ይገኛሉ ይላል፡፡ ከእነዚህ መካከል 7.8 ሚሊዮን መሣሪያዎች በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ሲሆኑ፣ በ100 ሰዎች መካከል በአማካይ 1.9 መሣሪያ ይገኛል በማለት ሥሌቱን ያስቀምጣል፡፡

እነዚህ መሣሪያዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ተለያዩ አገሮች በሕገወጥ መንገድ መግባታቸው መጤን እንዳለበት፣ በአኅጉሪቱ ላሉ ሕገወጥ መሣሪያዎች ምንጭም ሆኖ ያገለግላል በማለት የዳሰሳ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

ኢትዮጵያም ድንበር በማቋረጥ የሚመጡ የጦር መሣሪያዎች መዳረሻ ከሆኑ አገሮች አንዷ ስትሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት የሚያዙ የጦር መሣሪያዎችን ዓይነትና ብዛት ፖሊስና የጉምሩክ ኮሚሽን ሲያስታውቁ ቆይተዋል፡፡ መሣሪያዎቹ የሚመጡበት መንገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ እንደሚሄድና አንዴ የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪ፣ አንዴ በመኪና ፍሬቻ ውስጥ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከሌሎች ዕቃዎች ሥር በመደበቅ፣ እንዲሁም የዕቃ ጫኝ መኪኖች ታችኛውን ክፍል በመቁረጥና መሣሪያዎቹን በመሰግሰግ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሥልቶችን መመልከቱ በቂ ነው፡፡ በኤርፖርት በኩል ሲመጡ የሚያዙ መሣሪያዎችና የመሣሪያ አካላት ሲያዙ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በዓረብያን መጅሊስ ውስጥ ተደብቀው ሊገቡ የነበሩ የዘመናዊ ስናይፐር መሣሪያ ተጓዳኝ ዕቃዎች መያዛቸው የቅርብ ጊዜ ዜና ነው፡፡

የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስከ ጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም. በጉምሩክ ኮሚሽን የፍተሻ ጣቢያዎች ከ2,000 በላይ ሽጉጦች፣ 62 ክላሽኒኮቭ ጠመንጃዎችና አራት መትረየሶች፣ ከ900 በላይ የመትረየስ ጥይቶች፣ ከ2,800 በላይ የብሬን ጥይቶችና ከ80 ሺሕ በላይ የሽጉጥ ጥይቶች ተይዘዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል በታኅሳስ ወር 2011 ዓ.ም. 1,291 የቱርክ ሽጉጦችን ይዞ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዝ የተያዘው የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪ ተጠቃሽ ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስም የተለያዩ ተመሳሳይነት ያላቸው መረጃዎችን ሲያወጣ በተደጋጋሚ ይስተዋላል፡፡

ሆኖም የሚያዘው ከባህር የመጨለፍ ያህል ነው እንጂ ወደ አገር ውስጥ ፍተሻዎችን እያለፉ የሚገቡት የላቁ ይሆናሉ የሚለውን ሐሳብ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ ይጋሩታል፡፡

‹‹ከፀጥታ አካላት ያመለጠ የጦር መሣሪያ ምን ያህል እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ የሚያመልጥ አለ የሚል ግምት አለ፡፡ ማምለጡ መች ይቀራል? በተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች በጥይት ተመትተው የሞቱና የተጎዱ ሰዎች ያንን ሊያሳዩ ይችላሉ፤›› ሲሉ አቶ ጄይላን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጦር መሣሪያዎች በሥርጭት ላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ ጄይላን መረጃ ከሆነ ከበርካታ መሣሪያዎች መሀል የቱርክ ሽጉጦች ይበዛሉ፡፡ እነዚህ መሣሪያዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ታይቶ ውሳኔ ሲያገኙ፣ ተወርሰው ወደ ግምጃ ቤት ይገባሉ ሲሉም አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሕገወጥ  የጦር መሣሪያ ቁጥጥሩንና ክትትሉን በጋራ ቢሠሩትም፣ የፌዴራል ፖሊስ የመከላከያ ሠራዊት፣ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት፣ እንዲሁም የጉምሩክ ኮሚሽን የሚይዟቸውን  መሣሪያዎች በተናጠል ወደ ግምጃ ቤት ስለሚያስገቡና የየራሳቸውን መረጃ ስለሚይዙ፣ በማዕከል የተጠናቀረ አገር አቀፉን ገጽታ የሚያሳይ  በማዕከላዊ የመረጃ ቋት የተያዘ መረጃ እንደሌለ አቶ ጄይላን ተናግረዋል፡፡

በነዳጅ ቦቴ በብዛት መሣሪያዎች እንደሚገቡም ያመለከቱት አቶ ጄይላን፣ ቦቴዎች ከቦታቸው ሲነሱ ታሽገው ስለሆነና ፖሊስ አስቁሞ መፈተሽ ስለማይችል የተሻለ ተመራጭነት ማግኘታቸውን አመላክተዋል፡፡

የመሣሪያዎችም የመግቢያ መስመሮች ከሶማሊያ በቶጎ ጫሌ በኩል፣ ከኬንያ በሞያሌ በኩል፣ ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን በጋምቤላና ከኤርትራ በተለያዩ መስመሮች እንደሆነ በመጠቆም፣ እነዚህ ሥፍራዎች ያልተረጋጉ በመሆናቸው በቀላሉ መሣሪያዎች ተገኝተው ይንቀሳቀሳሉ ይላሉ፡፡ በእነዚህ መስመሮች በኬላ ከሚመጡ መሣሪያዎች በተጨማሪ በግመል፣ በባጃጅ፣ በሰውና በፈረስ ተጭነው የሚመጡ እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡

እንደ እሳቸው መረጃ ክላሽኒኮቭ መሣሪያዎች አሁን ላይ ከ130 እስከ 150 ሺሕ ብር እየተሸጡ እንደሚገኙ፣ ለመሣሪያዎቹ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ፣ ኅብረተሰቡ ራሱን ከመጠበቅ አልፎ ለልጆቹ የማውረስ ፍላጎት አንግቦ መሣሪያዎችን እንደሚገዛ ይነገራል፡፡ ሌሎች መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ደግሞ ማካሮቭ ሽጉጦች እስከ 70 ሺሕ ብር ይሸጣሉ፡፡

ሰዎች የደኅንነት ሥጋት ሲሰማቸው ራሳቸውን ለመከላከል ብለው እንደሚገዙ በመግለጽም፣ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችም መሣሪያዎችን እንደሚዙ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሌላ ፍላጎት ከሌላቸው በስተቀር ቦምብና መትረየስ ለምን ይገዛሉ?›› በማለትም ይጠይቃሉ፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ ጥናት ተቋም ተመራማሪና የጂኦ ፖለቲካ ተንታኝና ባለሙያ የሆኑት አቶ ልዑልሰገድ ግርማ፣ በኢትየጵያ ያለው ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ምንጩ የአፍሪካ ቀንድ ትርምስ ውስጥ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የቀጣናው አገሮች አስተማማኝ ፀጥታ የሌላቸው፣ እንዲሁም የብሔር ግጭቶችና የሥልጣን ፉክክሮች የጎሉበት ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡ ይኼ በተለይ በኢትዮጵያ ጠንካራ እንደሆነ በመግለጽም የልሂቃን ቡድኖች ፍላጎት እያየለ መጥቷል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

እነዚህ ቡድኖች ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት በተለያዩ መንገዶች እንደሚሄዱ በመጠቆምና ያልተገራ አስተሳሰብ (Ungoverned Mind) በመኖሩ፣ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጣጣሩ ቡድኖች በጦር መሣሪያ ዝውውር ውስጥ ሊሳተፉ ይችላሉ ይላሉ፡፡

‹‹የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እንደሚችሉ ግምት የሚወስዱ ቡድኖች እንደሚኖሩ እገነዘባለሁ፡፡ የብሔር ፖለቲካ እንዲያይልና የብሔር የበላይነት እንዲሰፋ የሚፈልጉ አሉ፡፡ ካላጋጩ ደግሞ እነዚህን ፍላጎቶች  ማሟላት አይችሉም፤›› የሚሉት አቶ ልዑልሰገድ፣ የቀጣናው መንግሥታት የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅትን (ኢጋድ) ጨምሮ ባሏቸው የትብብር ማዕቀፎች ሊገቱት ያልቻሉት ጉዳይ በመሆኑ፣ ግጭቶች የመሣሪያ ፍላጎትን እየፈጠሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ መሣሪያዎችም አሁን ከነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች አልፈው ወደ ቡድን መሣሪያዎች ከፍ እያሉ መምጣታቸው አሳሳቢ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

እነዚህ ግጭቶች እየሰፉ ሲመጡ የፀጥታ መዋቅሩ በራሱ ሊፈርስ ይችላል የሚሉት አቶ ልዑልሰገድ፣ ‹‹ልልነት ባይኖር ኖሮ በኤርፖርት በኩል መሣሪያ አይገባም ነበር፤›› ሲሉም ያሰምሩበታል፡፡ በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ግጭቶችን ለመግታትና ለመቆጣጠር መንግሥት በፍጥነት በመሥራት፣ የተቋቋሙት የዕርቀ ሰላምና የድንበር ኮሚሽኖች ወደ ተግባር ገብተው ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚኖርባቸው ያመለክታሉ፡፡

‹‹በእነዚህ አካሄዶች ማኅበራዊ ወረቶች (Social Capitals) የሚታከሙበት መንገድ መበጀት አለበት፤›› ሲሉም ምክር ይለግሳሉ፡፡

ለእነዚህ ችግሮች ሕግ ቢበጅላቸው ሙሉ በሙሉ ይቀረፋሉ ማለት እንዳልሆነ፣ ሕጎች ወጥተው ተግባራዊ ሳይሆኑ የቀሩባቸውን ሁኔታዎች በማስታወስ፣ ለዚህ ተግባር የሚሠራው ሕግ በአንዳንድ አካባቢዎች ሊተገበር ይችላል ወይ ብሎ ማጤን እንደሚገባ፣ የመከላከል ጉዳይ አድርገው የሚያዩ እንዳሉም መዘንጋት የለበትም ይላሉ፡፡

‹‹ከሕጉ በፊት ግን አመለካከት ላይ ነው መሠራት ያለበት፡፡ እንደ ኢትዮጵያውያን በመሣሪያ አይደለም መኖር ያለብን፡፡ የተለያዩ እሴቶች አሉን፡፡ እነሱን በማጎልበት ለተሻለ ነገ መሥራት ያሻል፤›› የሚሉት አቶ ልዑልሰገድ፣ የሲቪል ማኅበረሰቡ የተሻለ ሁኔታ ተፈጥሮለታል ብለው ስለሚያምኑ ይኼንን ሚና እንዲጫወት ማድረግና ሥነ ልቦናን ማከም ቀዳሚው ሥራ መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

ከዚህ በዘለለም ደረጃ የወጣለት (Normative) እና ተቋማዊ (Institutional) የሆኑ የደኅንነት ሥራ ትብብሮችን በቀጣናው መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በተመሳሳይ አቶ ጄይላን መንግሥት እያዘጋጀ ያለው ሕግ ይኼንን ችግር ለመፍታት ዓይነተኛ መፍትሔ እንደሆነ እንደሚያምኑ በመጠቆም፣ ሕግ ያግዛል እንጂ ብቻውን አይሠራምና ሕዝቡን ባሳተፈ መንገድ ሊሠራ ይገባል ይላሉ፡፡ የፌዴራል ፖሊስ እያደረገ ባለው ተቋማዊ ሪፎርም የጦር መሣሪያዎች ደረጃ (Standard) እየተሠራ በመሆኑ፣ ማን ምን መታጠቅ እንዳለበትና እንዴት ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት ይኼ ደረጃ ይወስናል ይላሉ፡፡

የአጥፊዎችን የሕግ ተጠያቂነት በተመለከተ ግን በቁጥር ይኼን ያህል ተከሰሱ ወይም ተያዙ ከማለት የዘለለ መረጃ እንደሌለ፣ በተደጋጋሚ በሚወጡ የመንግሥት ሪፖርቶች መረዳት ይችላል፡፡ የአጥፊዎችም ማንነት፣ የትና ለምን ምክንያት መሣሪያዎችን ሲያዘዋውሩ እንደነበርም ሲገለጽ አይታይም፡፡ ይኼ የሆነበትም ምክንያት አቶ ልዑልሰገድ ሲያስረዱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የጀመሩት ሁሉንም ችግሮች በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ እንፍታ የሚለው አካሄድ በመሆኑ፣ ተጠያቂነት ማምጣቱ የተጀመረውን የሰላም ሙከራ ሊያናጥበው ይችላል በሚል ሥጋት የአጥፊዎች  ማንነትና ዓላማቸው አይገለጽም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ታገሉ ተብለው ከትጥቅ ትግል የመጡ ቡድኖች በመሆናቸው ነው መሣሪያዎቹን የሚያዘዋውሩት ይላሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ ግን ያጠፉ ወገኖች ተጠያቂ መሆን አለባቸው ይላሉ አቶ ልዑል ሰገድ፡፡ ‹‹አንድ ዜጋ ከሚሞት የአንድ የፖለቲካ ልሂቅ ፍላጎት ተጠምዝዞ ቢቀየር ይሻላል፡፡ ኢትዮጵያን ማዳን ነው መቅደም ያለበት፤›› ሲሉም የሕግ የበላይነትን አስፈላጊነት አበክረው ያስረዳሉ፡፡

አቶ ጄይላን  መሣሪያውን የሚያዘዋውሩት እነ ማን እንደሆኑ አይታወቅም ይላሉ፡፡ እነ ማን እንደሆኑ ቢታወቅ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ይቻል ነበር ሲሉም ያክላሉ፡፡

ሌሎች ታዛቢዎች ደግሞ መሣሪያዎቹ ከዚህ የዘለለ ግፊት ባለው ምክንያት እንደሚዘዋወሩ ይጠቁማሉ፡፡ በዓለም ካሉ ከፍተኛ የመሣሪያ አምራቾች እ.ኤ.አ. በ2012 ብቻ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሽያጭ ያላቸው አገሮች ግፊት ኃያል ነው በማለትም፣ በእነሱ ጫና ሳቢያም መሣሪያዎች ይዘዋወራሉ ይላሉ፡፡ እነዚህ አገሮችም አሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ብራዚል፣ ኦስትሪያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ቤልጂየም፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ቱርክ፣ ኖርዌይና ጃፓን እንደሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም እነሱ ሊጠቀሙባቸው የማይፈልጓቸውን መሣሪያዎች ለማራገፍ የሚሸጡ እንዳሉም ይታመናል፡፡ ይኼንን ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ በሰጡበት ወቅት ጠቅሰው፣ ከገዛችሁ ደህናውንና መዋጋት የሚችል መሣሪያ ግዙ ብለዋል፡፡

በዓመቱ (2012 ዓ.ም.) በርካታ መሣሪያዎች እንደተያዙ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ጠንካራ ሥራ ካልተሠራ በስተቀር ከአገሮቹ ጋር በየብስ ግንኙነት በመኖሩ ከዋና ዋና ጥበቃ ከሚደረግላቸው መንገዶች በተጓዳኝ በፈረስም በግመልም መሣሪያ ይገባል ብለዋል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሜክሲኮን ድንበር አጥራለሁ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ድንበሮች ካልታጠሩ መቆጣጠር ከባድ መሆኑን በመግለጽ፣ ይኼንን ማድረግ ግን እንደማይቻልና ጉዳት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡ ለመከላከል መንግሥት የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች አዘዋዋሪዎች እያጠኑ እንደሚሠሩም በመናገር ቁጥጥሩን ከባድ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በላይ ግን፣ ‹‹ችግር እየሆነ ያለው ኢትዮጵያ እየገባ ያለው መሣሪያ በሚያመርተው አገር የማይፈለግ ነው፡፡ ክላሽኒኮቭ አንድ ካርታ ከተኮሰ በኋላ የሚቃጠል ነው፡፡ የሚረባ ነገር እየገባ አይደለም፡፡ ማስገባታችሁ ካልቀረ ዘመናዊ ዕቃ አስገቡ፤›› በማለት ሲያማርሩ የፓርላማ አባላት በሳቅ አጅበዋቸዋል፡፡ እሳቸው አክለውም፣ ‹‹ሌላ ቦታ ግምጃ ቤት ያጣ ዕቃ ተዋግቶ ለማሸነፍ የማይሆን ኮተት ከምንሰበስብ ማለት ነው፤›› ሲሉም የሚገባውን መሣሪያ አቅም አጣጥለዋል፡፡

ሆኖም የሚገባው የወገንን ሕይወት እየቀጠፈ በመሆኑ፣ ጥፋቱን ሰፋ አድርጎ በማየት ይኼንን ማረምና ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡