መንግሥት የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል በአስቸኳይ ዕርምጃ ካልወሰደ ከቁጥጥር ውጪ እንደሚሆን ተገለጸ

የአንበጣ መንጋ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

ሪፓርተር

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ)፣ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን እንደሚችል አስጠነቀቀ፡፡ ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል በአስቸኳይ ዕርምጃ እንዲወስድ ማሳሰቡን አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተሠራጨው የአንበጣ መንጋ በማሳ ላይ የሚገኙ ተክሎችን እያወደመ መሆኑን ገልጿል፡፡ በአማራ ክልል ብቻ የተወሰኑ አርሶ አደሮች ያበቀሉት ጤፍ መቶ በመቶ በአንበጣ መንጋው እንደወደመባቸው አስረድቷል፡፡

በኢትዮጵያ የፋኦ ተወካይ ሚስ ፋጡማ ሰይድ፣ ‹‹አስፈላጊዎቹን ነገሮች ሁሉ በማንቀሳቀስ በፍጥነት ምላሽ መስጠት ስላለብን፣ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅማችንን ማሳደግ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

በአንበጣው መንጋ ላይ በመረባረብ የመከላከልና የማስወገድ ሥራው በፍጥነት ካልተከናወነ፣ ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተጨማሪ ወደ ኬንያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ድረስ ሊዛመት እንደሚችል ፋኦ አስታውቋል፡፡

የአንበጣ መንጋው 351 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሆን ሥፍራ መሸፈኑንና በቀን ከ1.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ አረንጓዴ ዕፅዋትን እንደሚያወድም ፋኦ አስታውቋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን ራያና ቆቦ ወረዳ፣ በ30 ቀበሌዎች የአንበጣ መንጋ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በማሽላ ሰብልና በግጦሽ ላይ እያደረሰ ያለው የአንበጣ መንጋ ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተ መሆኑ ታውቋል፡፡

የአንበጣው መንጋ ከወራት በፊት ከየመን ወደ ኢትዮጵያ እንደገባ የፋኦ መረጃ ያመለክታል፡፡