የህዳሴ ግድቡ ለኢትዮጵያ ምን ያደርግላታል? – ፕሬዚዳንት ትራምፕ

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ምን እንደሚያደርግላትና ሌላ  አማራጭ ለምን እንዳልተጠቀመች ጥያቄ አቅርበው ነበር

ሱዳን የህዳሴ ግድቡ የሚያስገኝላትን ጥቅም በዝርዝር በማቅረብ ከኢትዮጵያ ጎን መቆሟን ዳግም አረጋግጣለች

ግብፅ ሦስተኛ ወገን አሸማጋይ እንዲሰየም ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎባታል

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን አሜሪካ ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወያየችበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ምን እንደሚያደርግላትና ከዓባይ ውኃ ይልቅ ሌላ የኃይል አማራጭ ለምን እንዳልተጠቀመች ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ተገለጸ፡፡

ሦስቱ አገሮች ግድቡን በተመለከተ ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ አሜሪካ በአዘጋጀችው የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የውይይቱ መጠናቀቅን ተከትሎ በአሜሪካ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ ዋናው ውይይት ከመጀመሩ አስቀድሞ የሦስቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ተገናኝተው እንደነበር አስረድቷል፡፡

በዚህ ወቅት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስለህዳሴ ግድቡ ግንባታ መረዳት የሚፈልጓቸውን ጥያቄዎች፣ ለየአገሮቹ ሚኒስትሮች አቅርበው እንደነበር ተገልጿል፡፡

ለኢትዮጵያ ያቀረቡዋቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ “ኢትዮጵያ ግድቡ ምን ያደርግላታል?” የሚል ጥያቄ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አንስተው እንደነበር፣ ከዚህ በተጨማሪም የዓባይን ውኃ ከመጠቀም ይልቅ “አትዮጵያ ለምን ሌላ የኃይል አማራጭ አትጠቀምም?” የሚል ጥያቄም አንስተው እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ግድቡ የታችኞቹን አገሮች ማለትም ግብፅንና ሱዳንን ምን ያህል እንደሚጎዳቸው፣ እንዲሁም ምን ዓይነት ጥቅምስ ሊሰጣቸው እንደሚችል ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀው እንደነበር አቶ ገዱ አስረድተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ካነሷቸው ጥያቄዎች ስለህዳሴ ግድቡ ግንባታ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርጉ መረጃዎች ብቻ ደርሰዋቸው እንደነበረ ለኢትዮጵያ ልዑክ ካነሷቸው ጥያቄዎች መረዳት እንደሚቻል የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ፣ በተነገራቸው መጥፎ ትርክት ስለህዳሴ ግድቡ የነበራቸውን የተሳሳተ አረዳድ ለመቅረፍ ለኢትዮጵያ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በወቅቱም ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሕዝብ ቁጥር ውስጥ 70 ሚሊዮን የሚሆነው  የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደሌለው፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ልማት አንፃርም የኤሌክትሪክ ኃይል በከፍተኛ ደረጃ የአቅርቦት ጉድለት የሚስተዋልበት ስለመሆኑና ይህንን ክፍተት የመሙላት ጉዳይ ወሳኝ የኢኮኖሚ ጥያቄን መመለስ እንደሆነ ለትራምፕ ማብራሪያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የኢኮኖሚ ደረጃ የኃይል ምንጭ አድርጋ ልትጠቀምበት የምትችለው ያላትን የውኃ ሀብት ብቻ ስለመሆኑ መብራራቱን አክለዋል፡፡

በአጠቃላይ ፕሬዚዳንቱ ከነበራቸው ግንዛቤ የሚመስለው ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ በሙሉ ይዛ ግብፅን ለመጉዳት የግድቡን ግንባታ እንደጀመረች ተደርጎ መረጃ እንደቀረበላቸው፣ ከእሳቸው ጋር በነበራቸው ውይይትም ይህንን ግንዛቤ ለማጥራትና ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታን በግልጽነት፣ በትብብርና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ የምታከናውነው ስለመሆኑ ለማብራራት ዕድል የሰጠ አጋጣሚ እንደነበር አቶ ገዱ አስረድተዋል፡፡

ግብፅ ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ መንካት የለባትም የሚል ክርክር ዘወትር የምታነሳው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም እንደ መከራከሪያ የምታቀርበው ኢትዮጵያ ሌሎች በርካታ የውኃ ምንጮች እንዳሏት፣ እንዲሁም ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውኃ ሀብት ባለቤት እንደሆነች መሆኑ ይታወቃል፡፡ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር የነበረው ውይይት ሱዳን በኃያሏ አሜሪካ ፊት የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ለኢትዮጵያ ታማኝነቷን ያረጋገጠችበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

አንዳንዶች ሱዳንን በጥርጣሬ ማየት እንደሚገባ የሚገልጹ ቢሆንም፣ ልዑካኑ ግን የህዳሴ ግድቡ መገንባት ለአገራቸው ስለሚሰጠው ፋይዳ በዝርዝር ማስረዳታቸውን፣ ካነሷቸው ጠቃሚ ጉዳዮች መካካል በሱዳን ላይ በየዓመቱ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ በማስቀረት፣ ዓመቱን ሙሉ የተመጣጠነ የውኃ ለሱዳን በማቅረብ በማንኛውም ወቅት የመስኖ ልማት እንድታከናውን፣ የኃይል ማመንጫ ግድቦቿም ሳይስተጓጎሉ ኃይል እንዲያመነጩ ዕድል እንደሚሰጣቸው ማስረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ከተደረገው ውይይት በኋላ ሦስቱ አገሮች በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቨን መንቺን አወያይነትና በዓለም ባንክ ኃላፊ ታዛቢነት ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት በሚችሉበት መንገድ ላይ ውይይት አድርገው የጋራ መግባባት ላይ እንደተደረሰ፣ ሁለቱም የኢትዮጵያ ተወካይ ኃላፊዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተዋል፡፡

በዚህ ውይይት የደረሱበት ስምምነትም ሦስቱ አገሮች ያላቸውን ልዩነት ለመፍታት የሚስችሉ አራት ስብሰባዎችን በማድረግ እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የጊዜ ማዕቀፍ የተቀመጠ መሆኑን፣ በሚያደርጓቸው ውይይቶችም የዓለም ባንክና አሜሪካ በታዛቢነት ተገኝተው ድጋፍ እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሦስቱ አገሮች ከሚያደርጓቸው ውይይቶች በተጨማሪ ኅዳር 28 ቀን 2012 ዓ.ም. እና ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የውይይት ሒደታቸውን ለመገምገምና ለመደገፍ፣ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ሁለት ስብሰባዎችን ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡ የዓለም ባንክም ሆነ የአሜሪካ መንግሥት በሚደረጉት ውይይች ላይ በታዛቢነት መገኘታቸው ልዩነቶችን ለመፍታት የሚያስችል ድጋፍ ሊያስገኝ የሚችል ከመሆኑም ባለፈ፣ ግብፅ ባለፉት ጊዜያት ስምምነቶች ከተደረሱ በኋላ እንደገና የተደረሰውን ስምምነት የማስተጓጎልና የማፍረስ ተግባሯ እንዲገታ የሚያደርግ መሆኑን ሚኒስትር ስለሺ (ዶ/ር)  አስረድተዋል፡፡

አገሮቹ ከኅዳር ወር መጀመሪያ አንስቶ እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በሚያደርጓቸው ውይይቶች ስምምነት ላይ ካልደረሱ፣ በ2008 ዓ.ም. ባደረጉት የትብብር መገለጫ ስምምነት አንቀጽ 10 መሠረት በጋራ ስምምነት ሦስተኛ ወገን እንዲያሸማግላቸው ሊመርጡ፣ ወይም ጉዳዩን ለሦስቱ አገሮች መሪዎች ለመምራት ስምምነት መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡

ግብፅ በአሜሪካ በነበረው ውይይት ወቅት ሦስተኛ ወገን አሸማጋይ እዚያው እንዲመረጥ ጥያቄ አቅርባ የነበረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያና በሱዳን ተቀባይነት ባለማግኘቱ ውድቅ እንደተደረገባት ስለሺ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

“በአሜሪካ በነበረው ውይይት የግድቡ ግንባታንም ሆነ፣ ኢትዮጵያ ከግድቡ ልታገኝ የምትችለውን ሙሉ ተጠቃሚነት የሚነካ ውይይት አልተደረገም፡፡ ወደፊት ቢመጣም አንቀበለውም፤” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ ተናግረዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. የሦስቱ አገሮች መሪዎች በተፈራረሙት የትብብር መገለጫ ስምምነት መሠረት በህዳሴ ግድቡ ላይ የሚኖራቸውን ልዩነቶች በውይይት መፍታት ካልቻሉ ሦስተኛ ወገን እንዲያሸማግላቸው መፈራረማቸውን ያስታወሱት ስለሺ (ዶ/ር)፣ መግባባት ላይ መድረስ እስካልተቻለ ድረስ ኢትዮጵያ የሦስተኛ ወገን አሸማጋይነትን ለመቀበል እንደማትችል አስረድተዋል፡፡