የለየለትን ሃይማኖት ተኮር የዐደባባይ ጥቃትን የእርስ በርስ ግጭት አድርገው ባለሥልጣናት መግለጻቸው አሳዝኖናል

የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የለየለትን ሃይማኖት ተኮር የዐደባባይ ጥቃት፣ “የእርስ በርስ የቡድን ግጭት” አድርገው መግለጻቸው በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡ – የካህናት እና ምእመናን ኅብረት ኮሚቴ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከል እየተንቀሳቀሰ ያለው የአዲስ አበባ አስተባባሪ ኮሚቴ ሣልሳይ ሒደታዊ መግለጫ፤
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች እየደረሰ የሚገኘው ጥቃት እንዲቆም የሚንቀሳቀሰው የአዲስ አበባ አስተባባሪ ኮሚቴ፣ መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከመንግሥት በቀረበለት የእንነጋገር ጥያቄ መሠረት በጉዳዩ ላይ ተነጋግሮ መፍትሔ ለማሰጠት፣ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ቀነ ገደብ አስቀምጦ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ከሚመለከታቸው የክልል እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ጋራ ሲወያይ ቆይቷል።

በዚህም፣ በአብዛኛው ችግሮች መኖራቸውን በማመን የማስተካከያ ርምጃዎችን ለመውሰድ መተማመን ላይ ተደርሷል፤ ይህን ተከትሎም የኮሚቴው ልኡካን የማስተካካያ ርምጃዎቹን ተግባራዊነት ሲከታተሉ ሰንብተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየሰጠ ካለው ተግባራዊ ምላሽ እና በአንጻራዊነት በደቡብ ክልል እና፣ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር ከተጀመሩ ሥራዎች በተጨማሪ በአማራ፣ ሶማሌ፣ ሐረሪ እና ቢንሻንጉል ክልሎች ከተሰጡ በጎ ምላሽ በቀር ስምምነቱ በተሟላ ሁኔታ ሊተገበር አልቻለም።

እንዲያውም፣ በአንዳንድ ክልሎች ከውይይቱም በኋላ ጥቃቶቹ እና በደሎቹ ከቀድሞው በከፋ ኹኔታ ተባብሰው ቀጥለዋል። ባለፈው መግለጫችን እንዳስታወቅነው፣ የተፈጠሩና እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ለዘብተኝነት ያሳየው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በያዘው አቋሙ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሰሞኑን በክልሉ ከ40 በላይ ኦርቶዶክሳውያን በአሠቃቂ ኹኔታ አንገታቸው በገጀራ ተቀልቶ፣ ሰውነታቸው ተቆራርጦ፣ በእሳት ተቃጥለው እና በዱላ ተቀጥቅጠው ተገድለዋል፤ እምነታቸውን በግዳጅ እንዲለውጡ ተደርገዋል፤ አስከሬኖቻቸው መቃብር ተነፍገው ከኢትዮጵያዊ ባህል እና ሰብአዊ ክብር በተፃራሪ በየመንገዱ ተጎትተዋል፤ እንደ አልባሌ ተጥለዋል፤ መኖርያ ቤቶቻቸው እና ንብረቶቻቸው ሙሉ በሙሉ የተዘረፉባቸውና የተቃጠሉባቸው በሺሕዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ለመፈናቀል እና ለእንግልት ተዳርገዋል።

በውይይታችን እንደተስማማነው፣ የክልሉ የጸጥታ አካላት፣ ጥቃቶችን አስቀድመው ሊገቱ ይቅርና በዐይናቸው እያዩ እንኳ ለመከላከል እና ጉዳትን ለመቀነስ ያልሞከሩበት ይብሱኑ አንዳንዶቹ ከነውጠኞች ጋር የተባበሩበት ሁኔታ አሳዛኝ ክሥተት ኾኖ ዐልፏል። ይህም፣ መንግሥት ኀይልን በብቸኝነት በመጠቀም ሥልጣኑ መሠረት የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ እና ሕግን ለማስከበር ባለው ዐቅም እና ፈቃደኝነት ላይ ብርቱ ጥርጣሬ እንዲኖረን አድርጓል። ይልቁንም፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የለየለትን ሃይማኖት ተኮር የዐደባባይ ጥቃት፣ “የእርስ በርስ የቡድን ግጭት” አድርገው መግለጻቸው በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡ በእውነቱ፣ የሟቾቹን ሰማዕትነት ከማቃለል እና የሐዘንተኞችን ጉዳት ከማባባስም ለይተን የምናየው አይኾንም።

የዜጎች ሕይወት መጥፋት እና የንብረት መውደም በእጅጉ ያሳዘነው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የጥፋት መልእክተኞች በተደጋጋሚ የሚያደርሱት ጥቃት እና መከራ፣ ጎልቶ እየታየ ያለው በክርስቲያኖች እና በአብያተ ክርስቲያን ላይ እንደ ኾነ በሰሞኑ መግለጫው አስታውቋል። ክቡር የኾነው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ መጥፋት የሌለበት መኾኑን በመግለጫው የጠቀሰው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ መንግሥት የአገርን ሰላም እና ደኅንነት የመጠበቅ ሓላፊነቱን እንዲወጣ፣ የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው እንዲመልስ፣ ለጠፋው ንብረታቸውም ማቋቋሚያ እንዲሰጣቸው፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ የጥፋት መልእክተኞችን በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ በአጽንዖት አሳስቧል። ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚሁ መደበኛ ስብሰባው፣ የሰላም እና ዕርቅ ዐቢይ ኮሚቴው አካል ያደረገው አስተባባሪ ኮሚቴያችን፣ የምልአተ ጉባኤውን መግለጫ በጽኑ በመደገፍ፣ መንግሥት ዜጎችን በእኩል ዐይን እንዲያይና ሕግ የማስከበር ግዴታውን እንዲወጣ በጥብቅ ያሳስባል።

ቀደም ሲል አስተባባሪ ኮሚቴው፣ ከመንግሥት ጋራ ባደረጋቸው ውይይቶች፣ በቃል የተሰጡት ተስፋዎች እና በቃለ ጉባኤ የተፈራረመባቸው ስምምነቶች ቢኖሩም፣ በተግባር ተተርጉመው የቤተ ክርስቲያን መብት እና የምእመናን የእምነት ነፃነት ካልተከበረ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄ አመርቂ ምላሽ ያገኛል ብሎ ለማመን ያዳግታል። የጥቃቶቹ ተባብሰው መቀጠልም ይህንኑ ጥርጣሬያችንን የሚያጠናክረው በመኾኑ፣ የካህናት እና ወጣቶች ኅብረት ኮሚቴው (ከዚህ በኋላ የሰማዕቱ ቅዱስ ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን መብት እና ክብር አስጠባቂ የካህናት እና ወጣቶች ኅብረት ኮሚቴ) ፣ አካሔዱን ከሰላማዊ ሰልፍ በዘለለ መንግሥት ላይ ጫና ሊያሳድሩ የሚችሉ ሰላማዊ የመብት ማስከበሪያ መንገዶችን ጭምር እንዲያጤንና እንዲቃኝ እያስገደደው ይገኛል።

በኮሚቴው እምነት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጥያቄ አመርቂ ምላሽ ሊገኝ የሚችለው መንግሥት ለቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ እና ሥርዓታዊ የደኅንነት ዋስትና የሚያረጋግጡ ርምጃዎችን በመውሰድ ሕግን የማስከበር ግዴታውን በብቃት ሲወጣ ብቻ ነው።
በመሆኑም ርምጃዎቹ እውን እስከሚሆኑ እና በተግባር ተገልጠው እስከሚታዩ ድረስ የካህናት እና ወጣቶች ኅብረት ኮሚቴው በመንግሥት ላይ ሰላማዊ ግፊቶችን ለማድረግ ወስኗል።

የካህናት እና ምእመናን ኅብረት ኮሚቴው፣ በመስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም. መግለጫው፣ የጥያቄዎቹን ምላሽ በመገምገም ከጥቅምት 30 ቀነ ገደብ በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሔድ ዕቅድ ይዞ እንደ ነበር መግለጹ ይታወሳል። ኾኖም በአንድ በኩል፣ ያለንበትን የሱባኤ ወቅት ግምት ውስጥ በማስገባት ምእመናን የተወሰነውን ጊዜ በጥሞና እንዲያሳልፉ በማሰብ በተጨማሪም፣ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በ38ኛ ዓመታዊ ስብሰባ የጋራ መግለጫው፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ ዓለም አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ በመወሰኑ በጋራ ለማከናወን የሰላማዊ ሰልፉ ቀን ተወስኖ ጥሪው እስከሚተላለፍ ድረስ መጠበቅ አስፈልጓል። ይህንም በመንግሥት ላይ ብርቱ ግፊት ከሚፈጥሩ እና ህልውናን ለማስከበር ከሚያስችሉ የተለያዩ ሰላማዊ ስልቶች ጋራ ማቀናጀቱ ውጤታማነትን ስለሚያረጋግጥ፣ ኦርቶዶክሳውያን ጥሪያችንን በንቃት እንድትጠባበቁ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን።

ጥቅምት 30 ቀን የሱባኤው ሳምንት ማጠናቀቂያ በመኾኑ፣ እንዳለፉት ቀናት ኹሉ ምእመናን በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው ተገኝተው በአባቶች አመራር ከአባቶች ጋራ ጸሎተ ምሕላውን እንዲያደርሱ እያስታወስን፣ በዚሁ አጋጣሚ በቤተ ክርስቲያናችንና በምእመናን ላይ ሰሞኑን በተፈጸሙ አሠቃቂ ጥቃቶች፣ ብሔር እና ሃይማኖት ሳይለዩ፣ በጥላቻ የተሞሉ አክራሪዎችን እየተከላከሉና በቤታቸው ከለላ እየሰጡ ኢትዮጵያዊ ወገንተኝነትንና ሰብአዊ ርኅራኄን ላሳዩ ወጣቶች፣ እናቶች፣ አባቶች እና የማኅበረሰብ ልሂቃን የላቀ ልባዊ ምስጋናችንንና አክብሮታችንን ለመግለጽ እንወዳለን፤ በዚሁም ሳቢያ መሥዋዕት ለኾኑ ወገኖቻችን፣ እግዚአብሔር ዕረፍተ ነፍስን እንዲሰጥልን፣ ለቤተ ሰቦቻቸውም መጽናናትን እንዲያድልልን እንመኛለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ