የተሰረቁ ቼኮችንና ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ከመንግስትና ከግል ባንክ ደንበኞች ሊጭበረበር የነበረ 28 ሚሊዮን ብር ማዳን ተችሏል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከመንግስትና ከግል ባንክ ደንበኞች ሊጭበረበር የነበረ 28 ሚሊዮን ብር ማዳኑን የአዲሰ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ።

ኮሚሽኑ ለኢዜአ እንዳስታወቀው ከመንግስትና ከግል ባንኮች ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ያጭበረበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የተሰረቁ ቼኮችንና ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ነው ከመንግስትና ከግል ባንክ ደንበኞች ላይ ገንዘቡን ያጭበረበሩት ።

ፖሊስ ከተለያዩ የመንግስትና የግል ባንክ ደንበኞች ላይ ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል እየተፈፀመ ስለመሆኑ ከብሔራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ ነው ክትትል ያደረገው።

በወንጀል ተጠርጥረው ከተያዙት ከ70 በላይ ግለሰቦች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ከተለያዩ የግል ባንክ ደንበኞች የባንክ ሂሳብ ውስጥ 60 ሚሊዮን 843 ሺህ 601 ብር ወጪ ማድረጋቸውም ተረጋግጧል።

በተመሳሳይ መንገድ ወጪ ተደርጎ ሊወሰድ በሂደት ላይ የነበረ ከ28 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን እንደተቻለና ከተጠርጣሪዎቹ እጅም የተለያዩ የባንክ ቼኮችና ለወንጀል መፈፀሚያነት የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች እንደተያዙም ነው የተገለፀው።
www.ena.et/?p=67298