የአንበጣ መንጋ በምሥራቅና ምዕራብ ሀረርጌ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በምሥራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖችም በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በስድት ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ላይ ባለ ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ኃላፊ ለዶቼ ቬለ DW ገልፀዋል።

ከሳምንታት ወዲህ በኢትዮጵያ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ የተገኘው የአንበበጣ መንጋ ወረርሽኝ በምሥራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ባሉ በርካታ ወረዳዎች መከሰቱን ታውቋል። በመንጋው በተለይ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ የሚረዱ ባህላዊና ዘመናዊ የመከላከል ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው ተገልፃል።

ለDW አስተያየት የሰጡ የምዕራብና ምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ኃላፊዎችና ባለሞያዎች እንደናገሩት ከሰሞኑ በየዞኑ ባሉ በርካታ ወረዳዎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ የተለያየ ጉዳት በማድረስ ላይ ይገኛል። በተለይ የምዕራብ ሀርጌ ዞን የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ኃላፊ አቶ አነስ አልይ በዞኑ ስድስት ወረዳዎች ላይ ተከስቷል ያሉት የአንበጣ መንጋ ከአንድ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በሚገኝ ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተናግረዋል።

በምሥራቅ ሀረርጌ ዞን ስምንት ወረዳዎች ላይ የተከሰተው አንበጣ በርካታ ሄክታር በሸፈነ የዕፅዋት እና የደረሰ ምርት ላይ ማረፉን የተናገሩት በዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ኃብት ፅ/ቤት ባለሞያ የሆኑት አቶ አሸብር ለማ በበኩላቸው ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል። በሁሉቱም ዞኖች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ጉዳትን ለመከላከል ተማሪዎች ጭምር የተሳተፉበት ባህላዊና ዘመናዊ የመከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሀገሪቱ በአብዛኞቹ አካባቢዎች የተከሰተውን ይህን የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ አስቀድሞ መከላከል አይቻልም ነበር ወይ በሚል ላቀረብነው ጥያቄ ሞያዊ ምላሽም ሰጥተዋል። የአንበጣ መንጋ በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ድሬደዋን ጨምሮ በሶማሌ ክልል እና አሁን ደግሞ በምሥራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች የተከሰተ ሲሆን እየተደረገ ካለው የመከላከል ሥራ ባለፈ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አለመዋሉ ታውቋል።