በኢትዮጵያ የሚመረቱ ዘይቶች በአብዛኛው ለኦክስጂን በተጋለጠ ሁኔታ የሚጨመቁ መሆናቸው ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ያጋልጣሉ ተባለ

በኢትዮጵያ የምግብ ዘይት ጥራት ላይ ያሉት እውነታዎች — በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8

በአገራችን ለምግብነት የምንጠቀመው የምግብ ዘይት ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መበራከት አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡

በህገወጥ መንገድ እና በግል አስመጪዎች በኩል የሚገባውን ሳይጨምር መንግስት ብቻውን ከውጭ ዘይትን ለማስገባት በአመት እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያደርግ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

እነዚህም በምን ያህል መጠን ለጤና ተስማሚ መሆናቸው የሚረጋገጥበት ሂደት በራሱ ችግሮች እንዳሉበት ይነገራል፡፡

ከዚህ ባለፈ በሀገር ውስጥ የሚመረተው ወይም የሚጨመቀው የምግብ ዘይት የባሰ ችግሮች ያሉበት እንደሆነ ይሰማል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የአገራችን የምግብ ዘይት ጥራት ላይ ያሉት እውነታዎች ምንድን ናቸው? ሲል ከዘርፉ ተመራማሪ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

በሆለታ ግብርና ማዕከል የወይና ደጋ የቅባት ሰብሎች ከፍተኛ ተመራማሪ ሚስጢሩ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የሚመረቱ ዘይቶች በአብዛኛው ለኦክስጂን በተጋለጠ ሁኔታ የሚጨመቁ መሆናቸው ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ያጋልጣሉ ይላሉ፡፡

በተለይ በሀገር ውስጥ የሚመረቱት እንደ ኑግ እና ተልባ የመሳሰሉ ዘይቶች ለኦክስጂን ተጋልጠው የሚመረቱ አልያም የሚሸጡ ከሆነ ከፍተኛ ለሆነ የጤና እክል ያጋልጣሉ፡፡

እንደ ካንሰር እና ስኳር የመሳሰሉ በሽታዎች በምርትና በሽያጭ ጊዜ ለኦክስጂን በመጋለጣቸው ጥራታቸውን ባጡ ዘይቶች የሚከሰቱ መሆናቸውን የሆለታ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪው ነግረውናል፡፡

በኢትዮጵያ ምን ያህሉ ናቸው ጤናማ ዘይት በማምረት ላይ የሚገኙት ስንል ጥናት ጠቅሰው እንዲያብራሩልን ተመራማሪውን ጠይቀናል፡፡

እሳቸው በዛ ደረጃ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ባውቅም በጥናት የተለየ ነገር የለም፡፡ ወደ ፊት ግን መሰራት ያለበት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ጤናማ ዘይት ለማምረት አስቸጋሪ የሆኑ እና በአምራቾች እንደቅሬታ የሚቀርቡ ጉዳዮች ምንድናቸው የሚለው ሌላኛው ጥያቄችን ነበር፡፡

ተመራማሪው እንደሚሉት ከሆነ እንደ ሱፍ እና የፈረንጅ ነጭ ሱፍ እንዲሁም አኩሪ አተር የመሳሰሉ ሰብሎችን ያለማግኘት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እነዚህን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በሀገር ውስጥ የሚገኙትን እንደ ኑግ እና ተልባ የመሳሰሉትን ሰብሎች የምርት ጥራት በመጨመር የሚመረቱበት ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆናቸውን ተናግረዋል አቶ ሚስጢሩ።

ዘይት ጨማቂዎች የቀረቡ መመዘኛዎችን ጠብቀው እንዲያመርቱ ጥረቶች ተጀምረዋል ያሉት ተመራማሪው ባህርዳር እና አዳማ ላይ በጥቂቱም ቢሆን ተግባራዊ እየተደረገ ነው ይላሉ፡፡