የሽብር ፖለቲካ፡- “እኔ ትክክል ነኝ፣ አንተ ሟች ነህ!”

የሀገራችን ፖለቲካ ጭምልቅልቅ ብሏል። ሁሉም በራሱ እንደ መጣከት ይናገራል፤ በእውን ከሆነው ይልቅ የመሰለውን ይፅፋል። ነባራዊ ሁኔታውን ሳያገናዝብ በቢሆን ዓለም እሳቤ ይጠይቃል፣ ያስባል፣ ይወስናል፣ ይመራል፣… ሁሉ ነገራችን መላ-ቅጡ ጠፍቷል። ይሁን እንጂ ነባራዊ እውነታን ከመቀበል ውጪ ሌላ ምርጫና አማራጭ የለንም። ምክንያቱም እውነትን በራሳችን ፍላጎትና ምርጫ መቀየር ሆነ ማስቀረት አንችልም። በእርግጥ ቀድሞ የነበረው፣ አሁን ያለውና ወደፊት የሚኖረው ነገር አንድና ተመሳሳይ ነው። ሁለትና ሦስት ዓይነት እውነት የለም። በተጨባጭ የነበረው፣ ያለውና የሚኖረው አንድ ዓይነት እውነት ነው። ልዩነቱ በእኛ ሃሳብና አስተሳሰብ፣ ባለን ዕውቀትና ግንዛቤ፣ በምናራምደው አቋምና አመለካከት ምክንያት የተፈጠረ ነው። በጋራ መነጋገርና መግባባት ካለብን፣ ሰላምና መረጋጋት ከፈለግን፣ ለውጥና መሻሻል ካስፈለገን፣… ሌላ ሳይሆን እኛ ነን መቀየር፥ መለወጥ ያለብን።

በዚህ መሰረት ከራሳችን አልፈን የሌሎችን ሃሳብና አስተሳሰብ ለመረዳት ጥረት ማድረግ፤ ያለንን ልምድና ዕውቀት ለሌሎች ማካፈል፤ የሌሎችን አቋምና አመለካከት በትዕግስት ማስተናገድ፣ የራሳችንን አቋምና አመለካከት በኃይል ለመጫን ከመሞከር ይልቅ በምክንያት ማስረዳት አለብን። ለዚህ ግን በቅድሚያ ነባራዊ ሁኔታን መገንዘብ፣ የራሳችንን አቋምና አመለካከት መፈተሸ፣ ማዳበርና ማሻሻል፣ እንዲሁም የሌሎችን ሃሳብና አመለካከከት በዝርዝር ማጥናትና መረዳት ይኖርብናል። የሀገራችን ፖለቲካ ውጥንቅጡ የወጣው እዚህ ጋር ነው። በእውን ስላለው ነባራዊ ሁኔታ በቂ ግንዛቤ የለንም፣ ያለንን ሃሳብና አመለካከት በምክንያታዊ ዕውቀትና በተጨባጭ ማስረጃ ለማስደገፍ ሆነ ለማሻሻል ጥረት አናደርግም። በዚህ ላይ ደግሞ የሌሎችን ሃሳብና ጥያቄ ከመረዳት ይልቅ በጅምላ ለመፈረጅና ለማጣጣል እንጣደፋለን። በእንዲህ ያለ ሁኔታ ታዲያ እንዴት መነጋገርና መግባባት ይቻላል? ሰላምና መረጋጋት ከወደዬት ይመጣል? የእኛ ሃሳብና አመለካከት ሳይቀየር ምን ዓይነት ለውጥና መሻሻል ይመጣል? በዚህ መልኩ ለውጥ ማምጣት ይቅርና ለውጥ ራሱ መጥቶ ከደጃፋችን ላይ ቢቆም አይተን መለየት አንችልም።

ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ሆነ አይቶ ለመለየት በቅድሚያ ትላንት የነበርንበትን፣ ዛሬ ያለንበትን እና ነገ የምንደርስበትን በግልፅ ማወቅና መረዳት ያስፈልጋል። ትላንት ላይ ተገትረን ቆመን የነገውን መገመት ቀርቶ ዛሬ ያለንበትን በቅጡ መረዳት አንችልም። ዛሬ ላይ ብቻ ቆመን ለውጥ ለማምጣት የምናደርገው ጥረት መጨረሻው የትላንቱን ስህተት መድገም ይሆናል። ከትላንቱ ታሪክና ከዛሬው ሁኔታ በተነጠለ መልኩ ነገ ላይ ለውጥ ማምጣት ቀርቶ የሚሆነውን መገመት አንችልም። ስለዚህ ዘላቂ የሆነ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ትላንት የነበርንበትን ማወቅ እና ዛሬ ያለንበትን መረዳት፣ እንዲሁም የወደፊቱን ሁኔታ በትክክል መገመት ያስፈልጋል። በተጨባጭ እውነታና ዕውቀት ላይ የተመሰረተ የተግባር ዕቅድ ማዘጋጀት፣ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር እና የተቀናጀ እንቅስቃሴ በማድረግ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ይቻላል።

በእኛ ሀገር ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ግን ከዚህ ፍፁም የተለየ ነው። አንደኛው ወገን ትላንት ላይ ተገሽሮ ቆሟል። ሌላኛው ወገን ደግሞ ዛሬን ብቻ ያስባል። ዛሬ ላይ ያሉትን ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚጨነቁና የትላንቱን ስህተት ላለመድገም የሚጠነቀቁ በጣም ጥቂቶች ናቸው። የዚህ ሀገር ቀጣይ እጣ-ፈንታ በእነዚህ ሰዎች ትከሻ ላይ የተንጠለጠለ ነው። በዚህ ረገድ ትልቁን ጫና ከተሸከሙ ጥቂት ሰዎች ውስጥ ጠ/ሚ አብይ አህመድ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት ላይ መቆዘም የሚፈልጉትን፣ ዛሬ ላይ ብቻ የቆሙትን እና ወደ ነገ መሻገር የሚፈልጉትን አንድ ላይ አሰባስቦ ለመምራት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በእርግጥ ይህ ከአንድ መሪ የሚጠበቅ ሥራና ኃላፊነት ነው።

አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ሀገርና ህዝብን ወደፊት ለመሻገር የሚደረገው ጥረት የሞት-ሽረት ጣር ነው። ምክንያቱም በተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት ጫፍ የረገጠ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም ሃሳብና ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡት የሀገርና ህዝብን ህልውና መደራደሪያ በማድረግ ነው። የሀገር አንድነት እና የዜጎችን ሕይወት መደራደሪያ አድርጎ ማቅረብ በራሱ ፖለቲካ ሳይሆን ሽብርተኝነት ነው። ሽብርተኝነት የራስን እምነትና አመለካከት በግድ ለመጫን መሞከር ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ደግሞ “እኛ ያልነው ካልሆነ ‘ሀገር ይፈርሳል፣ ግጭት ይነሳል’” በሚሉ ኃይሎች የተሞላ ነው። አንተ የምትፈልገው ምላሽ ካልተሰጠ ሀገር የሚፈርስ ወይም ደም የሚፈስ ከሆነ ሲጀመር ያቀረብከው ጥያቄ ሳይሆን ማስፈራሪያ ነው። ይህ “እኔ ትክክል ነኝ፣ አንተ ተሳስተሃል” (I am right, you are wrong) ከሚለው ምክንያታዊ እሳቤ ውጪ ነው። ከዚያ ይልቅ “እኔ ትክክል ነኝ፣ አንተ ሟች ነህ” (I am right, you are dead!) ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው። ናጄሪያዊው ሎሬት “Wale Soyinka” ደግሞ ይህ ምርጫና አማራጭ የሌለው እሳቤ የሽብርተኝነት መሰረታዊ መለያ ባህሪ እንደሆነ ይገልፃል።

በእርግጥ ሁሉም የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎች የሽብር ፖለቲካ አራማኞች ናቸው ማለት አይቻልም። ሆኖም ግን የአብዛኞቹ አካሄድ በዚህ እሳቤ የተመሰረተ ነው። በተለይ ደግሞ በሀገሪቱ ታሪክና ፖለቲካ ላይ የላቀ ተፅዕኖ ያላቸው የኦሮሞ፣ አማራና ትግራይ ቡድኖች በዋናነት የሽብር ፖለቲካ አራማጆች ናቸው። ለምሳሌ የአብዛኞቹ አቋምና አመለካከት፤ እኛ ያልነው ካልሆነ ሀገሪቱ ትፈርሳለች፣ የሌላው ብሔር ቡድኖች በህዝባችን ላይ የህልውና አደጋ ጋርጠዋል፣ ጥያቄያችን መልስ ካላገኘ አመፅና ሁከት ይቀሰቀሳል፣… ወዘተ በሚሉ ጭፍን እሳቤዎች ላይ የተመሰረተ ነው። ከዚህ አንፃር የሀገሪቱ አንድነት፣ የህዝቡ ሰላምና ደህንነት የሚረጋገጠው ትክክልና አግባብ ስለሆነ ሳይሆን የእነሱ ጥያቄና ፍላጎት ምላሽ ሲያገኝ ብቻ ነው። ይባስ ብሎ እነዚህ ቡድኖች አንዱ ሌላውን ለማጥቃት ሲሆን ይተባበራሉ። በሰላም ተከባብሮ ስለ መኖርና መስራት ሲሆን ግን መተባበር ቀርቶ አይነጋገሩም።

በእንዲህ ያለ የፖለቲካ ማህብረሰብ ዘንድ ሙሉ በሙሉ ትክክል ሆነ ስህተት የሚባል ነገር የለም። ምክንያቱም የአንዱ ስህተት በሌሎች ዘንድ ትክክል ሊሆን ይችላል። በሌሎች ዘንድ ትክክል የተባለውን አንዱ ስህተት ብሎ መግለጫ ሲያወጣ ታገኙታላችሁ። በአጠቃላይ በሽብር ፖለቲካ አንዱ ሌላውን በጉልበት በማስፈራራት እንጂ በውይይትና መግባባት የሚፈታ ነገር የለም። ሌላው ቀርቶ ውይይትና ድርድር ለማድረግ ጥያቄ የሚቀርበው በአመፅና ግድያ ጉልበቱን አሳይቶና አስፈራርቶ ነው። መቼም በማስፈራራት የሚደረግ ነገር ሽብርተኝነት እንጂ ድርድር አሊያም ወይይት ሊባል አይችልም።

ከምንም በላይ ደግሞ የሚገርመው የመንግስት ሥራና ተግባር የሚገመገመው በተቀናቃኝ የብሔር ቡድን ላይ በወሰደው የኃይል እርምጃ አማካኝነት ነው። ስለዚህ መንግስት የኃይል እርምጃ እስካልወሰደ ድረስ በየትኛውም ወገን ዘንድ በቂ ድጋፍና ተቀባይነት አያገኝም። መንግስት ያለውን አቅምና ተቋማዊ አደረጃጀት ተጠቅሞ የኃይል እርምጃ ከወሰደ ከአንዱ ወገን ድጋፍና ተቀባይነት ሲያገኝ በሌላኛው ወገን ላይ ደግሞ የህልውና አደጋ ይጋረጣል። የህልውና አደጋ የተጋረጠበት ማህብረሰብ ሳይወድ በግድ የአፀፋ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል። አንዴ ወደዚህ አዙሪት ከገባን ደግሞ መውጫው ይጠፋናል። በመሆኑም መጨረሻችን የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት ይሆናል። ስለዚህ መንግስት በተቀናቃኝ ቡድኖች ላይ የኃይል እርምጃ እንዲወስድ መወትወት በህዝብ ላይ ሽብርና ዕልቂት ከመደገስ ተለይቶ አይታይም። በአጠቃላይ አሁን በሀገራችን ያለው የሽብር ፖለቲካ ነው። “እኔ ትክክል ነኝ፣ አንተ ተሳስተሃል” በማለት ልዩነትን በምክንያት ከማስረዳት ይልቅ ሁሉም እየተነሳ “እኔ ትክክል ነኝ፣ አንተ ሟች ነህ” የሚል ሆኗል። የቀይ ሽብር ዘመቻ እና የፀረ-ሽብር አዋጅ መንስዔያቸው ይሄው ፅንፈኛ አመለካከት ነው። አሁን የምናነሳቸው ጥያቄዎች እና እያሄድንበት ያለው መንገድ ያን አስቀያሚ ታሪክ ለሦስተኛ ግዜ እንዲደገም የቋመጥን ነው የሚመስለው።