ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ያደረገው ፌዴራላዊ ስርዓቱ የተተገበረበት መንገድና የፌዴራል ስርዓቱ የመንግስት አወቃቀር ነው ተባለ

ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ያደረገው ፌዴራላዊ ስርዓቱ የተተገበረበት መንገድና የፌዴራል ስርዓቱ የመንግስት አወቃቀር አንዱ ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ተናገሩ::

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ፌዴራላዊ ስርዐቱ የተተገበረበት መንገድ ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ተጋላጭ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ተናገሩ::

ዶክተር ዳንኤል በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳብራሩት፤ ዜጎችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ያደረገው ፌዴራላዊ ስርዓቱ የተተገበረበት መንገድና የፌዴራል ስርዓቱ የመንግስት አወቃቀር አንዱ ችግር መሆኑን አሰረድተዋል:: የፖለቲካ ፓርቲ አወቃቀሩም ሌላው ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመው በተለየ ማንነት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱም ለግጭት መዳረጉንም ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች አወቃቀር፣ የመንግስት አወቃቀርና ህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ መፈተሽ አለብን፣የፖለቲካ አወቃቀራችን በተፈጥሯቸው የአግላይነት ጸባይ ስላላቸው በውጤታቸው ደግሞ ለግጭት፣ ለብጥብጥና ለእርስ በእርስ አመጽ የሚጋብዙ ሆነው የሚታዩ ስለሚመስሉ ጉዳዩ ሊመረመር፣ ሊጠና እና ሊታይ ይገባዋል ያሉት ኮሚሽነሩ የፖለቲካ መሪዎችም በእዚህ ጉዳይ መወያየት መጀመር የሚገባቸው ይመስለኛል ብለዋል፡፡

በእኔ እምነት ለሰብአዊ መብት ተጋላጭ ያደረገው ራሱ ፌዴራላዊ ስርዓቱ ሳይሆን ፌዴራላዊ ስርዓቱ የተተገበረበት መንገድና የፌዴራል ስርዓቱ የመንግስት አወቃቀር አንዱ ሊሆን ይችላል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የፖለቲካ ፓርቲ አወቃቀሩ፣ በተለየ ማንነት ላይ (የዘር ማንነት፣ የብሄር ብሄረሰብ ማንነት፣ የአካባቢ፣ የሃይማኖት ማንነት ላይ የተመሰረቱ አደረጃጀቶች) የተመሰረተ ፓርቲ ለግጭት ስለሚዳርግ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች እንዲህ አይነት የፖለቲካ አደረጃጀት በህጎቻቸው አልፈቀዱም ወይም በግልጽ ከልክለዋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት የፖለቲካ አስተዳደር እንዳለን ይታወቃል፡፡ ታሪካዊ መሰረትና ምክንያት አለው›› ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን የመጣንበት መንገድ ያስገኘው ውጤትና የፈጠሩት ተግዳሮቶችም አሉት ያሉት ዶክተር ዳንኤል፤ ከተደረሰበት የፖለቲካ ምዕራፍ አንጻር ሂደቱን መርምሮ ችግሮችና ያስገኘውን ውጤት በማስመልከት ግልጽ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ያደረገ የመንግስት አወቃቀር ካለውም አወቃቀሩን መፈተሽ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ይህ ማለት ግን የፌዴራላዊ አስተዳደርን ማፍረስ ማለት አይደለም፣ ኢትዮጵያ ካላት ብዝሃነት አንጻር እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ብሄር ብሄረሰብ ላላቸው አገራት የፌዴራላዊ አስተዳደር ተገቢ አስተዳደር ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

ፌዴራላዊ አወቃቀር ህዝቦች፣ ሰዎች፣ ዜጎች በየአካባቢያቸው የራሳቸውን ጉዳይ በእየራሳቸው የሚያስተዳድሩበት መንገድ መሆኑን በመጠቆምም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የሆነው አስተዳደር ግን በተለይ ከብሄር ብሄረሰብ ማንነት ጋር በጣም የተቆራኘ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ በተለያዩ ክልሎችና በክልሎቹ ውስጥ ባሉ የተለያዩ የማንነት ጥያቄዎች እና የድንበርና የወሰን ልዩነት ላይ እጅግ አወዛጋቢ ክርክር የፈጠረ መሆኑ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ ማድረጉንም አልሸሸጉም፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታዩ ግጭቶች ከማንነት ጥያቄና ከአካባቢ እና ከድንበር ጉዳይ ጋር ተያይዞ ‹‹ይህ የእኔ አካባቢ ነው፣ ይህ አካባቢ የአንተ አይደለምና ከእዚህ ትወጣለህ፣ የአንተ ድንበር እዛ ጋር ነው›› ከሚሉ ጥያቄዎች ጋር የተያያዘ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አገራችን ውስጥ በየክልሎቹ ብቻ ሳይሆን በየቀበሌዎቹና በየወረዳዎቹ ደረጃ ያለ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን፤ የአስተዳደር ወሰን መሆኑ ቀርቶ ልክ ከአጎራባች አገሮች ጋር እንዳለ አይነት የድንበር ወሰን ጋራ የሚመሳሰል እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡

አሁን የተፈጠሩት ግጭቶችም በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የአስተዳደር ወሰኖችን እንደ ድንበር በመቁጠር ከሌላ አገር ጋር የተፈጠረ ችግር አይነት አዝማሚያ እንደሚታይበት ኮሚሽነሩ ገልጽው የፌዴራል ስርዓቱን በሚያጠንክር መልኩ የአስተዳደር ወሰኖችና የማንነት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ተወያይቶ የፖለቲካ መፍትሄ መፈለግ ይሻላል ሲሉ መክረዋል፡፡

አዲስ ዘመን