ዶር አብይን አለመጋበዝ ለሕዝብ ተስፋ ቦታ አለመስጠት ነው #ግርማ_ካሳ

ዶ/ር አብይ አህመድ ዳላስ በሚደረገው አመታዊው የኢትዮጵያዉያን እግር ኳስ ውድድር ላይ ለመገኘት ጥሪ እንዳቀረቡና የፌዲሬሽኑም የቦርድ አባላት በጉዳዩ ላይ እየተነጋገሩ እንደሆነ ሰምተናል። ያንን ተከትሎ አምስት ፣አስር የማይሞሉ፣ ዲሲ የሚኖሩ፣ የአለምቀፍ ግብረሃይል የሚል ስም ለራሳቸው የሰጡ የግንቦት ሰባት ካድሬዎች ፣ የፌዴሪሽኑን የቦርድ አባላት ስም ዝርዝርና የስልክ ቁጥር ይፋ አድርገው ፣ ኢትዮጵያዊያን ደዉለው የዶር አባይን መገነኘት እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን፣ ሃብታሙ አያሌውና የተወሰኑ ከኢሳትና ከግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት ያላቸው ወገኖችም ፌዴሬሽኑ ዶር አባይን እንዳይጋብዝ ጽፈዋል። በተለይም ሃብታሙ አያሌው፣ ዶር ብርሃኑ ነጋስ እሺ፣ ግን ለአንድዋለም አራጌ ግድ የሚሰጠው ይመስል ፡ “ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ ህዝቧ የመስዋዕት በግ ሆኖ ዛሬ ዶክተር አብይ በሚመሩት ድርጅት ስቃይ የተቀበለውን አንዷለም አራጌን ፖለቲከኛ ስለሆነ በሚል ከግብዣው ተርታ አስቀርተን፣ ለጠቅላዩ መፍቀድ ብርቱ ሃጢያት ይሆናል። ስለ ኢትዮጵያ እራሱን የበረሃ ሲሳይ ያደረገውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን አልፈን ጠቅላዩን ቤት ለእንግዳ ብንል የበደል ሁሉ በደል ይሆናል። እናም ፌዴሬሽኑ ያስብበት ” ሲል የጻፈው ባያስገረመኝም ትንሽ አስቆኛል።

በነገራችን ላይ ፌዴሬሽኑ እስክንደር ነጋም አንዱዋለም አራጌን ቢጋብዝ ደስ ይለኝ ነበር። እንደውም ባለኝ መረጃ እነ እስክንደር ሊጋበዙ እንደነበረ ነው የሰማሁት። ሆኖም ግን በመሃከል የዶር አብይ ጥሪ ሲመጣ፣ ለዶር ባይ ቅድሚያ መስጠት የግድ ነው። ካላቸው ሃላፊነትና ቦታ አንጻር። እርግጠኛ ነኝ ወንድም አንዱዋለም አራጌና እስክንደር ነጋ ዶር አብይ ጠንካራ መሪ ሆነው በአገር ቤት ለውጡን የበለጠ እንዲያፋፍሙ ነው የሚፈልጉት። አስፈላጊም ከሆነ ፊዴሬሽኑ እስክንደር ነጋና ዶር አብይ በአንድ መድረክ እንዲገኙ ማድረግም ይችላል። መክፈቻቸውን እስክንደር ነጋ እንዲናገር ተደርጊ፣ ኢትዮጵያ ቀን ላይ እስክንድርም ባለበት ዶር አብይ እንዲናገሩ ማድረግ ይችላል። ከእስክንደር ጋር ቆመው ለሕዝብ ንግግር ቢያደረጉ ዶር አባይ ያስደስታቸዋል እንጅ አያስከፋቸውም።

ላለፉት 27 አመታት የአገዛዙ ባለስልጣናት እየተደበቁ ነበር ስብሰባ የሚያዘጋጁት። በስብሰባው የሚገኙት፣ የነርሱ ደጋፊዎች የሆኑ ብቻ ተለይተው ተጠርተው ነበር። በዳያስፖራ ያለውን አብዛኛውን ማህበረሰብ እንደ ጠላት ነበር የሚያዩት። ዶር አብይ ግን ያንን አጥር በመስበር ነው፣ “የኔን ድርጅት የሚደግፉትን ብቻ ሳይሆን ፣ ያኮረፉ፣ እኛን የሚቃወሙትን እንደ ኢትዮጵያ መሪ ሄጄ ማነጋገር አለብኝ፤ እነርሱም ለአገር ያስፈልጋሉ፤ እነርሱን መስማት አለብኝ” ብለው ወደኛ ለመምጣት የወሰኑት።

ይ ዉሳኔ በግሌ የምደግፈው ብቻ ሳይሆን ልቤን በደስታ ያቀለጠው፣ ለዶክተሩ ያለኝ ጥሩ አመለካከት የበለጠ እንዲጨምር ያደረገ ዉሳኔ ነው። አጼ ሃይለስላሴ ሲሞቱ ገና ሕጻን ነበርኩ። ብዙ አላውቃቸውም ነበር። መንግስቱ ሃይለማሪያም፣ መለስ ዜናዊንና ሃይለማሪያም ደሳለኝ ግን አውቃቸዋለሁ። ዱርዬ፣ ሕዝብን የሚንቁ መሪዎች ነበሩ። ዶክተር አብይ ግን ሕዝብን የሚያከብሩ፣ ትሁት መሪ ሆነው ነው ያገኘኋቸው። ስለርሳቸው እግዚአብሄርን በጣም አመሰግናለሁ። (እዚህ ጋር አንሳሳት፣ ዶር አብይ መልአክ ነው፤ አይሳሳትም፣ መተቸት የለበትም እያልኩ አይደለሁም። እርሱም አትተቹኝ አይልም። ግን በአንጻራዊነት በብዙ እጥፍ ቀደም ሲል ከነበሩ መሪዎች፣ እንደው የተቃዋሚ መሪ ነን ከሚሉት ከነ ዶር ብርሃኑ ሁሉ ሳይቀር በጣም የተሻሉ ነው)

ዶር አብይ በዝግጅቱ ለመገኘት የሚመጡት እንደ ኢህአዴግ መሪነታቸው አይደለም። እንደ ኢትዮጵያ መሪነታቸው ነው። ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው፣ ለምሳሌ “ያንን አስቀያሚ ኮከብ ያለበት ባንዲራ አድርጋችሁ ነው” አላሉም። እኛ ጋር የሚመጡት ራእያቸውን ሊነግሩን፣ ከኛም ሊሰሙ ነው።

አዎን ብዙ ያልተሻሻሉ ችግሮች ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም አሉ። ቀላል ምሳሌ ብሰጥ በኦሮሞ ክልል ኦሮሞ ያልሆኑ ሌሎች ማህበረሰባት አሁንም እንደ መጤ፣ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው የሚቆጠሩት። በአዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ሻሸመኔ ..ከሰማኒያ በመቶ በላይ አማርኛ ተናጋሪ እያለ፣ አማርኛን ስለሚጠሉ ብቻ ኦህዴዶች ዜጎች በአማርኛ የመንግስት አገልግሎት እንዳያገኙ አሁን ድረስ አከላክለዋል። ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ወገኖች ኦሮሞ ስለሆኑ ብቻ ሲቋቋሙ፣ ከኦሮሞ ክልል የተፈናቀሉ ግን ወደ ኦሮሞ ክልል እንዳይገቡ ተደርጎ በወሎ በረሃማ ቦታዎች እየተሰቃዩ ነው። አዎን ብዙ ችግሮች አሉ። አሁንም በአገሪቷ የሰፈነው የዘር ፖለቲካ የሕወሃት/ኦነግ ፖሊሲዎች ጉዳት እያደረሱ ናቸው።

ግን ዶር አባይ ችግር የለም፣ ሁሉም ሰላም ነው ሊሉን አይደለም የሚመጡት። ” ችግሮች አሉ ፣ በአንድ ጀንበር አያፈቱም፤ እናንተም የመፍትሄው አካል ሆናችሁ አብረን ችግሮቻችን እንፍታ፣ እንነጋገር፣ ጉልበታችሁን፣ እውቀታችሁን፣ ገንዘባችሁን አገራችሁና ህዝብናችሁ ላይ እንዳታጠፉ ማነቆ የሆነባችሁን ነገር አብረን እናስወገድ” ሊሉን ነው የሚመጡት።

አስቡት እስረኞች ተፈቱ። በቀናት ውስጥ አንዳርጋቸው ጽጌን ልጆቹንና ባለቤቱን ይቀላቀላል። የወልቃይት ኮሚቴ አባላትን እውቅና ሰጥተውአነጋገሩ። በዉጭ አገር ያሉ ዜጎችን አስፈቱ። ኢትዮጵያዊነትን ሰበከ፤ አጉላ። ቱባ የሕወሃት ሰዎችን በጡረታ አሰናበቱ። ባለኝ መረጃ አሁን በአዲስ አበባ በየታክሲው ሰው የዶር አባይን ፎቶ ነው እየለጠፉ ያለው። አገር፣ ህዝብ ወዷቸዋል። ይሄ ያለምንም ምክንያት አይደለም። ህዝብ ኢትዮጵያ የሚልን ስለሚወድ ነው።

ፌዴሬሽኑ ላለፉት በርካታ አመታት በብዙ ፈታናዎች ውስጥም እያለፈ ኢትጵያውያን ያሰባሰበ ድርጅት ነው። ያንን ድርጅት ለመክፈል ወያኔዎች ብዙ ሲያደቡና ሲዶልቱ እንደነበረ፣ ተደራቢ ፌዴራሺን እስከማቋቋም እንደደረሱ የሚታወቅ ነው። ያ ብቻ አይደለም ፌዴሬሽኑ ብዙዎቻችን ከማናየው ከእርግጫውና ከዳንኪራው ባላፈ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ስፖንሰር አድርጎ ለበጎ አድርጎት ስራዎች ድጋፍ ያደረገ ነው።

ይህ ስብስብ ወደፊት በጥሩ ከተቃኘ፣ እነ ዶር አባይም ሁኔታዎችን ካመቻቹለት፣ በአገር ቤት ብዙ ለአገራ ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ማከናወን ይችላል። ያለምንም ጥርጥር ዶር አብይን በእንግድነት መጋበዝ ለፌዴሪሽኑ ትልቅ ጥቅም ነው የሚያመጣው። ለፌዴሬሽኑ ትልቅ ክብር ነው። ዶ/ር አባይ ኢህአዴግን አይደለም የሚወክሉት። ኦህዴድን ወይንም የኦሮሞ ማህበረሰብን ብቻ አይደለም የሚወክሉት። የሚወክሉት ኢትዮጵያዉያን ለአገራቸው ያላቸውን ትልቅ ተስፋን ነው። ዶር አብይን ሲያስቡ ዜጎች የወያኔዎችን ስቃይ ሳይሆን የሚያስቡት የነገው ብሩህ ተስፋ ነው የሚያስቡት።

ፌዴሬሽኑ ስሜታዊ የሆኑ፣ ጽንፈኛ ዳያስፖራዎች ለማስደሰት ብሎ እኝህን በሕዝብ ተወዳጅ የሆኑ መሪ አለመጋበዙ እኔን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያዉያንን በ እጅጉ የሚያስቀየም ነው። እኛ ወደ ኋላ ከሚጎተትን አንፈለግም። ባለፈው ነገር መታሰር አንፈለግም። ጥላቻን፣ ቂም በቀለን አንፈለግም። ወደፊት መሄዱ፣ ወደፊት መፈንጠሩ ይሻላል ባዮች ነን። አገር ብዙ ችግር አለባት። እንኳን ተከፋፍለን፣ አንድ ሆነንም በአለም ካሉ አገሮች በጣም ወደ ኋላ የቀረን ነው። መንቃት መጀመር አለብን።ገና ብዙ ስራ ወደፊት ይጠበቅብናል።

በመሆኑም ለክብራን የፌዴሬሽን የቦርድ አባላት፣ ግልጽ መል’እክት አለኝ። የምትወስኑት ዉሳኔ ለአገርና ለሕዝብ፣ ለፍቅርና ለአንድነት ያለውን ትልቅ እድምታ ከግምት በማስገባት ዶር አብይን የክብር እንግዳ አድርጋችሁ ጋብዙ እያልኩ አክብሮታዊ ጥሪዬ አቀርባለሁ።አንዳንድ ወገኖች ዶር አባይ ከመጡ ዝግጅቱ ላይ አንገኝም ያሉ አሉ። እመኑኝ እነርሱ ቢቀሩ እነርሱን ተክቶ አስር እጥፍ ሊመጣ ያላሰበ ዜጋ ይመጣል። በጭራሽ አትከስሩም። በገንዘብ፣ በሞራል፣ በሁሉም መስፈርት ታተርፋላችሁ።

በነገራችን ላይ የዶር አብይ በዲሲ መገኘት ተአምር ይሰራል የሚል እምነት የለኝም። ግን ቢያንስ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያሻግር ነው። ዶክተሩን ትልቅ አቀባበል ካደረግንላቸው፣ በጨዋነት ያሉንን ጥያቄዎቻችንን ካቀረብንላቸው፣ እንደዉም የበለጠ የተሻለ ነገር እንዲሰሩ፣ የተናገሩትን እንዲተገብሩ ሃይልና ድጋፍ እንሆናቸዋለን። እርሳቸውን ግን ለመጋበዝ ፍቃደኛ ካልሆንን ፌዴሬሽኑ ክፉኛ ተቀባይነቱ ይሸረሸራል።

እንደ ሃብታሙ አያሌው ያሉ የዳያስፖራ ፖለቲካው ስራቸው ነው። እነ ዶር አባይን መቃወም ስራቸው ነው። አገር ቤጥ የሚቃወሙት ከሌለ ስራ አይኖራቸውም። ቢዝነስ ይሞትባቸዋል። ጉዳዩን ከአገር ጥቅም ጋር አይተዉት ሳይሆን ከራቸው ጥቅም ጋር አይተውት ነው የሚሞግቱት። ሆኖም ግን የፌዴሬሽኑ ቢርድ አባላት በሞያቸው፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ባላቸው ሃላፌነት የተከበሩ እንደመሆናቸው ትክክለኛውን ዉሳኔ ይወስናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።


► መረጃ ፎረም - JOIN US