በሽብር የተጠረጠሩ ሰዎች በመታወቂያ ዋስ መፈታታቸው የፍትሕ ስርዓቱን መነጋገሪያ አድርጎታል።


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በሽብር ጠርጥሮ በመታወቂያ ዋስ መልቀቅና የፍትህ ሥርዓቱ ማሻሻያ

BBC Amharic በለውጡ ዋዜማ ስለ አፋኝነቱ ብዙ ብዙ የተባለለት የፀረ ሽብር አዋጁን በሚመለከት “…አሸባሪው መንግሥት ነው” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የፓርላማ ንግግር ለብዙዎች አይረሴ ነው።

የፀረ ሽብር አዋጁ መንግሥታቸው ትኩረት ሰጥቶ ከሚያሻሽላቸው ህጎች ቀዳሚው እንደሚሆን በተናገሩት መሰረት ህጉን የማሻሻል ሥራው ተጠናቆ ረቂቁ ለመፅደቅ የፓርላማ ተራ እየጠበቀ ይገኛል።

በዚህ መሃል ይህ ህግ ተጠቅሶ ሰዎች በሽብር መጠርጠራቸው ሲያነጋገር፤ መንግሥት በእርግጥም የፍትህ ሥርዓቱን የማሻሻል መልካም ፍቃድ አለው ወይ? የሚል ከባድ ጥያቄንም ማስነሳቱ ይታወቃል።

ከሰኔ 15ቱ “የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ” ጋር በተያያዘ በሽብር የተጠረጠሩ ሰዎች ከአራት ወራት እስር በኋላ በመታወቂያ ዋስ ከቀናት በፊት መፈታታቸውም እንደገና የፍትህ ስርዓቱን መነጋገሪያ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መሱድ ገበየሁ “መንግሥት አሸባሪው እኔው ራሴ ነኝ ባለ ማግስት ይህን ህግ የተጠቀመው ሆን ብሎ የሰዎችን ሰብአዊ መብት ለመጣስ ነው” ይላሉ።

“ለቀጣይ ዓመት ይሻሻላል ተብሎ ሼልፍ ላይ ያደረን ህግ ተጠቅሞ መጠርጠር በራሱ ጤነኛ አደለም” የሚሉት አቶ መሱድ ሰዎችን በመፈንቅለ መንግሥት መጠርጠር ካስፈለገ በፀረ ሽብር ህጉ ሳይሆን በመደበኛ የወንጀል ሥነ ሥርዓት እና በወንጀል ህግ መሰረት መጠርጠር እንደነበር ትክክለኛው አካሄድ ያስረዳሉ።

ሰዎችን በፀረ ሽብር ህጉ መጠርጠር ሙሉ በሙሉ ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሆነ ይደመድማሉ።

በሽብር በተጠረጠሩ ሰዎች ከሃያ በላይ መዝገቦች ላይ ጠበቃ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ መሱድ ተጠርጣሪዎቹ ላይ በተለይም በመጀመሪያዎቹ 26 ቀናት መሰረታዊ መብቶቻቸው ተጥሰው ነበር ይላሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር የሆኑት አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ የፍትህ ወር በሚል ከፍተኛ የፍትህ ተቋማት ባለስልጣናትና የህግ ባለሙያዎች ለውይይት በተሰባሰቡበት መድረክ “ለምድን ነው እስካሁን በፀረ ሽብር ህጉ የምትከሱት?” የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር።

እስካሁንም የፀረ ሽብር ህጉ በህግ ስላልተሻረ ይህን ህግ ጥቅም ላይ ማዋል ምንም አይነት ህጋዊ ችግር እንደሌለበት “ከህግ አንፃር ይችላሉ፤ ከፖለቲካ አንጻር ግን አጥፊ ነው” በማለት ነገሩ ፖለቲካዊ እንደሆነ ያስረዳሉ።

“በአንድ ቀጠሮ 28 ቀን አስሮ ማቆየት እድል ይሰጣል። የወንጀል ህጉ የሚፈቅደው 14 ቀን ነው። ስለዚህ ዳኞች የተጠቀሰውን ህግ ብቻ በማየት ፖሊስ ወይም አቃቤ ህግ የጠየቀውን ያልተገባ ቀን ይፈቅዳሉ” የሚሉት አቶ ሙሉጌታ በዚሁ መሰረት መንግሥትም አስሮ ማቆየት የሚፈልጋቸውን ሰዎች ለማሰር የሽብር ህጉን እንደመረጠው ያምናሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የፀረ ሽብር ህጉ ከአራት ወር በላይ ሳይከሱ ማሰርን ስለማይፈቅድ ተጠርጣሪዎቹ በመጨረሻ ከእስር ተለቀዋል።

ህጎችን በማሻሻል ሂደት ላይም ተሳታፊ በመሆናቸው አዲሱ ረቂቅ ህግ በቅርቡ ፀድቆ አሁን እየተጠቀሰ ያለው የፀረ ሽብር ህጉ የሚሻር ይመስልዎታል ወይ? የሚል ጥያቄ ለአቶ ሙሉጌታ አንስተን ነበር።

ተሻሽሎ የፀደቀውን የማህበራትና የሲቪል ሶሳይቲ ህግን በመጥቀስ አሁንም እየተሻሻሉ ያሉ ህጎችን በመጥስ ይህ ህጎችን የማሻሻል ሥራ በጣም አዎንታዊ እንደሆነ ያስረዳሉ።

“ቢሆንም ግን በፖለቲካው መንግሥት ችግር እየገጠመው ነው፤ የፖለቲካ ማሻሻያውና የህግ ሥርዓቱን ማሻሻል ጎን ለጎን እየሄዱ አይደለም። የፖለቲካ ማሻሻያው ወደ ኋላ ቀርቷል” ይላሉ አቶ ሙልጌታ።

በመጨረሻም ጉዳዩ የፖለቲካና የፖሊሲ ጉዳይ እንጂ የህግ እንዳልሆነ፤ ስለዚህም ፖለቲካዊ መልካም ፍቃድ ከሌለ ህግ ቢወጣም ህጉን ያወጣው መንግሥት ራሱ ህጉ እንዳይፈፀም እንደሚያደርግ የሚያስረዱት አቶ ሙሉጌታ አሁን በአገሪቱ የፖለቲካና የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያዎች ላይ እየሆነ ያለውም ይኸው እንደሆነ ይደመድማሉ።

“የተጣለ ህግ አንስቶ ህይወት ሲዘራበት ይታያል። የፀረ ሽብር ህጉ ለእኔ ሆስፒታል የተኛ ህግ ነው፤ ይህ ህግ እንዴት ፍርድ ቤት ይጠቀሳል?” ሲሉ አጥብቀው ይጠይቃሉ።