ደብዳቤ ለአቶ ለማ – የኦሮሞ ክልል ሕጎች ዘመናዊ ሆነው ይሻሻሉ ዘንድ ምሁራን ጠየቁ – ክፍለ 1

በኦሮሞ ክልል ኦሮምኛ የማይናገሩ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው ዞኖችና ወረዳዎች፣ እንዲሁም በክልሉ ኣማርኛ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን፣ ኦሮምኛም በግዕዝ ፊደል ትምህርት እንዲሰጥና የሌሎች ማህበረሰባትን መብታቸው ተረግጦ፣ ደህንነታቸው አደጋ ላይ ወድቆ፣ ከኦሮሞው ማህበረሰብ እኩል እንዳያታዩ ያደረጉ  የክልል መንግስቱ አሰራሮች፣ ፖሊሶዎችና ሕጎች እንዲሻሻሉ የሚጠይቅ ለአቶ ለማ መገርሳ ከተሳፈው ደብዳቤና ሰንድ የተወሰደ።

መምህራኑና አክቲቪስቶቹ መምህር ልዑለቃል አካሉ፣  ዶ/ር ኣበራ ሞላ ፣ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ፣  ፕ/ር ማሞ ሙጬ፣  ፕ/ር ባዬ ይማም ፣ ፕ/ር ኀይሌ ላሬቦ፣ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፣  ዶ/ር አበባ ደግፌ፣ የተከበሩ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ፣ አቶ ያሬድ ጥበቡ፣ አቶ ሰይፉ አዳነች ብሻው፣  አቶ ተፈራ ድንበሩ፣ አቶ ብርሃኑ ገመቹ፣  አቶ አብርሃም ቀጄላ፣ አቶ ታደሰ ከበደ፣ ወ/ሮ እስከዳር አውላቸው፣  አቶ ተመስገን መኩሪያ  እና አቶ ግርማ ካሳ ናቸው።


 

ክቡርነትዎና የትግል አጋርዎ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ብዙ ጊዜ ኦሮሞ ክልል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ክልል እንደሆነች ገልጻችኋል። የኦሮሞ ክልል ሕገ መንግሥት ግን እናንተ እየደጋገማችሁ በግልጽና በአደባባይ የገለጻችሁትን የሚያንጸባርቅ አይደለም። የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ስምንት፣ የኦሮሞ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን፣ የሕዝቡ የበላይነትም የሚገለጸው በሚመርጣቸው ተወካዮችና ራሱ በቀጥታ በሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው ይላል። ይህ ማለት የኦሮሞ ክልል ባለቤት የኦሮሞ ሕዝብ እንደሆነ፣ ኦሮሞ ክልል የኦሮሞዎች እንደሆነች፤ ሌላው በክልሉ የሚኖረው ኦሮሞ ያልሆነው ማሕበረሰብ ደግሞ፣ በኦሮሞ ማሕበረሰብ ፍቃድ እንደሚኖር፣ እንግዳ እንደሆነና የክልሉ የባለቤትነት መብት እንደሌለው የሚያመለክት ነው።

ይህ የክልሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ፡ ክቡርነትዎ ኦሮሞ ክልል የሁሉም ኢትዮጵያውያን ናት ያሉትን የሚጻረር ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ በሆነ መልኩ የዜጎችን የሰብአዊና የእኩልነት መብቶችን የሚገፍ ነው። ዜጎች በማንኛውም የአገሪቷ ክፍል የመኖር፣ የመሥራት፣ የመነገድ፣ የመማር፣ የማስተማር፣ የመምረጥ፣ የመመረጥ መብቶቻቸው ሊጠበቁላቸው ይገባል። የክልሉ ሕገ መንግሥት ማንም ኢትዮጵያዊ፣ በሁሉም መስፈርት ከኦሮሞው እኩል እንደሆነ የሚያረጋግጥ፣ የሌሎች ማሕበረሰባት በክልሉ የመኖር ዋስትናን የሚሰጥ ሕገ መንግሥት ሆኖ መሻሻል አለበት ብለን እናምናለን። ከላይ የተጠቀሰው አንቀጽ ስምንት የኦሮሞ ክልል ነዋሪ ሕዝብ የክልሉ የበላይ ሥልጣን ባለቤት ሲሆን፣ የሕዝቡ የበላይነትም የሚገለጸው በሚመርጣቸው ተወካዮችና ራሱ በቀጥታ በሚያደርገው ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው በሚል ቢሻሻል ጥሩ ሊሆን ይችላል ብለን እንመክራለን።


► መረጃ ፎረም - JOIN US