የጠቅላይ ምኒስትሩ ንግግር ከሕወሓት አመራሮች ጋር ያላቸው ግንኙነት የበለጠ መሻከሩን ያሳበቀ ሆኗል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢሕአዴግን ለማዋሐድ የተዘጋጀው ሰነድ ከተጠናቀቀ ከአንድ አመት ከስድስት ወር በላይ ቢሆነውም «ላለመበትን ስንለማመን ከርመናል» ሲሉ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት 28 አመታት ኢትዮጵያን ያስተዳደረውን ግንባር ለማዋሐድ የተጀመረውን ጥረት በተቃወሙ ወገኖች ላይ የሰላ ትችት ሰንዝረዋል። የጠቅላይ ምኒስትሩ ትችት የተደመጠው ኢሕአዴግ የሚመራበትን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮት ይተካል ተብሎ የሚጠበቀውን «የመደመር ፍልስፍና» የሚያብራራ መፅሀፋቸው አዲስ አበባ በሚገኘው የሚሊኒየም አዳራሽ በዛሬው ዕለት ሲመረቅ ባደረጉት ንግግር ነው።

የኢሕአዴግ ውኅደት «ኢትዮጵያን ከፌደራላዊ ሥርዓት ወደ አሃዳዊ ሥርዓት መመለስ ነው» የሚል ተቃውሞ መቅረቡን የጠቀሱት ጠቅላይ ምኒስትሩ በትግራይ፣ በአማራ እና በደቡብ ክልሎች የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦች በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ እየተዳደሩ ለበርካታ አመታት መቆየታቸውን ጠቅሰው ትችቱን አጣጥለዋል።

«የፓርቲ ውኅደት ጉዳይ አላለቀም። እኛ የመደመር ፍልስፍናን የምናምን ሰዎች በዴሞክራሲያዊ ውይይት ስለምናምን አንድ አመት ከስድስት ወር ሙሉ ተጠንቶ ያለቀ ሰነድ ጉዳይ ቢሆንም ላለመበትን ስንለማመን እና ስንወያይ ከርመናል። አሁንም ውይይቱ አልተቋጨም።

ውይይቱ ሳይቋጭ አንዳንዶች ይኸ የፓርቲ ውኅደት ‘መጨፍለቅ ነው፤ ኢትዮጵያን ከፌደራላዊ ሥርዓት ወደ አሃዳዊ ሥርዓት መመለስ ነው ’ የሚል በእኛ ውስጥ ታስቦ የማያውቀውን መርዶ አረዱን። የፓርቲው አንድ መሆን ኢትዮጵያን የሚጨፈለቅ ከሆነ ኢትዮጵያ አልነበረችም፤ ተጨፍልቃለች ማለት ነው። ምክንያቱም ትግራይ ውስጥ ሕወሓት የሚባል ድርጅት እንጂ ኩናማ የራሱ ድርጅት የለውም። ኢሮብ የራሱ ድርጅት የለውም። ኢሮብ የራሱ ልዩ ወረዳ አለው፤ ኩናማ የራሱ ልዩ ወረዳ አለው። በሕወሓት ይተዳደራል፤ ነገር ግን የፌደራል ሥርዓት አልተጨፈለቀም።»

የጠቅላይ ምኒስትሩ  ንግግር ከሕወሓት አመራሮች ጋር ያላቸው ግንኙነት የበለጠ መሻከሩን ያሳበቀ ሆኗል። የኢሕአዴግ መሥራች የሆነው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በዚህ ሳምንት ባወጣው መግለጫ «በውህደት ስም፣ በፍፁም ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መንገድ፣ አዲስ አሃዳዊ ድርጅት ሊመሰረት አይገባም» ብሎ ነበር። የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ «የኢሕአዴግ ውኅደት ሊቆይ የሚገባው ጉዳይ ነው» ሲል አቋሙን በመግለጫው አንጸባርቋል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ግን የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት «አንድ የኤኮኖሚ እና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመፍጠር» ርዕይ እንዳለው በመጥቀስ የውህደቱን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተዋል። እርሳቸው በሊቀ-መንበርነት የሚመሩት ኢሕአዴግ «እንኳን ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ራሱም አንድ መሆን ተስኖት ቆይቷል» ሲሉም ነቅፈዋል። ውኅደትን በተመለከተ በኢህአዴግ አራት አባል ድርጅቶች ተቀባይነት የሚያገኘው ሐሳብ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

«በተሰጠው ዕድል መጠቀም ሳይችል ዕድል ሲነጠቅ በትውልድ ዕድል መቀለድ አይቻልም። ኢሕአዴግ እንዴት ይዋሃዳል? ምን ስም እና ግብር ይኖረዋል? የሚለውን እኔ አልወስንም። እኔ ዴሞክራት መሪ ስለሆንኩ ለውይይት ሐሳቤን አቀርባለሁ። የተሻለ ሐሳብ እና የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ብዙኃን ሐሳብ የሆነውን ግን በቅርቡ ለሕዝባችን እንገልፃለን።» ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጽሐፍ መልክ ያዘጋጁት የመደመር ፍልስፍና የሶማሌ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን ጨምሮ «እያንዳንዱ ዜጋ ሀገሬን ልመራ እችላለሁ» ብሎ አስቦ የሚዘጋጅባት፤ «ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር» የሚያስብ እንደሆነ ጨምረው ገልጸዋል።

ህወሓት ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ ግን በውህደት ስም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶችንም ህልውና የሚያጠፋ እንደሆነ አስጠንቅቆ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው እርሳቸው የሚያቀነቅኑትን መንገድ የሚቃወሙ አማራጭ ሐሳብ እንዲያቀርቡ በዛሬው ንግግራቸው ጠይቀዋል።«መደመር ፍልስፍና ከሆነ እና ፓርቲው ከተዋሀደ ወደ እልቂት እንገባለን የሚለው ጉዳይ-እልቂትን ምን አመጣው? አንድ ፓርቲ መሆን እና መደመር የማያዋጣ ከሆነ ጀግና ሰው ውስኪውን አስቀምጦ መባዛት የሚል አማራጭ ሐሳብ ይዞ ይመጣል።

ያኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ መደመር እና መባዛትን ጎን ለጎን ያይና፤ መደመር አያስፈልገኝም ይላል። ሐሳብ እያለ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ምን ያገዳድለናል? እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚቀጥለው አማራጭ መገዳደል ነው የሚለው የ19ኛው ክፍለ ዘመን የማርክስ እና የሌኒን እሳቤ ነው። መደመር እንደዚህ አያምንም። መደመር ‘እኛ ውስኪ ጠጪ ኢሕአዴጎች እባካችሁን ውሐ የናፈቀው ሕዝብ እንዳለ አትርሱ’ ይላል። ሲሉ ተናግረዋል።ዛሬ አዲስ አበባን ጨምሮ በ65 ከተሞች የተመረቀው የጠቅላይ ምኒስትሩ መፅሐፍ በኦሮምኛ፣ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች በአንድ ሚሊዮን ኮፒ መዘጋጀቱ ተገልጿል።

DW