የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች የአፋር ክልል ልዩ ኃይል በሕዝብ ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው ሲሉ ተቃውሞ አሰሙ

በአፋር እና ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በሚነሳው ግጭት በሶማሌ አርብቶ አደር ህዝብ ላይ እየተፈፀመ ነው የሚሉትን ጥቃት በመቃወም በሶማሌ ክልል የተለያዩ ዞን እና ወረዳዎች ሰላማዊ ሰልፎች ተካሄዱ፡፡

DW : በሶማሌ ከልል ሲቲ ዞን ሽንሌ ወረዳ እና በድሬደዋ ከተማ ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ነዋሪዎች በአፋር ክልል ልዩ ኃይል እና በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አነሳሽነት በሶማሌ አርብቶ አደር ኅብረተሰብ ላይ እየተፈፀመ ነው ያሉት ጥቃት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ ሰልፈኞች አንዱ ለዶይቼ ቬለ «DW» በሰጡት አስተያየት ችግሩን ለመሸፋፈን የሚደረገው ጥረት መቆም እናዳለበት ገልፀው የፌደራል መንግሥት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።ሰሞኑን በአፋር ክልል ታጣቂዎች የተፈፀመ ጥቃትን ተከትሎ በአንዳንድ የሀገር ውስጥ እና የውጭ መገናኛ ብዙሃን የቀረበው ዘገባ ትክክለኛ አይደለም ሊታረም ይገባል በሚል ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።

በተለይ የሀገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሰሞኑን ግጭት አስመልክቶ የሚያቀርበው መረጃ ትክክለኛ አይደለም በሚል ቅሬታቸውን በመግለፅም ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡ከክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባገኘነው መረጃ በዛሬው ዕለት በጅግጅጋ ፣ ቀብሪበያህ ፣ ጉርሱም ፣ ቱሉጉሌድ እና ሌሎች ከተሞች ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን ለማወቅ መቻሉን የድሬደዋዉ ወኪላችን የላከልን ዘገባ ያመለክታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሶማሌ እና አፋር ክልል አመራር አካላት ጋር በዛሬው ዕለት በአካባቢው ስላለው የፀጥታ ጉዳይ መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በፌስ ቡክ ባሰራጨው አጭር መረጃ አመልክቷል።