ሁለት ወዶ አይቻልም – ሕብረብሄራዊ የሸዋ አስተዳደር አስፈላጊነት #ግርማ_ካሳ

አሁን ያለውን በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌዴራል አወቃቀር የሚደግፉ ወገኖች አሉ። በተለይም የትግራይ፣ የሶማሌና የኦሮሞ ብሄረተኞች፣ በድርጅት ደረጃም ኦህዴድና ህወሃት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ኦፌኮ፣ አረና፣ የነአቶ ሌንጮ ኦዴፍ …አወቃቀሩ መቀጠል አለበት ብለው የሚከርከሩ ናቸው።

ይሄ በተወሰነ ደረጃ በቋንቋ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው የሚባለው ፌዴራል አወቃቀር፣ አንደኛ የአማርኛ ተናጋሪዉን ማህበረሰብ ያገለለ፣ በተሰነይ ኤርትራ ደርግ ከመዉደቁ በፊት፣ ዶር ነጋሶ ጊዳዳ እንደገለጹት፣ ሻእቢያው ዶር በረከት ሃብተስላሴ፣ ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊና የብዙ ወገኖች ደም በእጃቸው ያለባቸው የቀድሞ ኦነግ የአሁን ኦዴፍ መሪ አቶ ሌንጮ ለታ የነደፉት፣ በሕዝቡም ላይ በሃይል የተጫነ የአሸናፊዎች አወቃቀር ነው።

ይህ አወቃቀር ፍትሃዊነት የሌለበት፣ በወንድማማቾች መካከል ልዩነት የፈጠረ፣ የዘር ግጭቶችን ያባባሰና ወደፊትም ማሻሻያ ካልተደረበተ ወደ ማያስፈለግ ችግር ውስጥ ሊከተን እንደሚችል እያሳሰብን እና እያስጠነቀቅን ነው።

ፍትሃዊነት የሌለበት አወቃቀር ነው ስንል ያለ ምክንያት አይደለም። እነርሱ ቋንቋን እንደ መስፈርት ወስደናል ቢሉም፣ የራስቸው የሆነውን የቋንቋን መስፈርት እንኳን እንዴት እንደተገበሩት ብናይ ትልቅ ፍትሃዊነት መጓደሉን ብዙ ቦታዎች በግልጽ ማየት እንችላለን። አንድ ምሳሌ ለማስቀመጥ እንሞክር

– ከአስራ ሁለት አመት በፊት በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ መሰረት የአዲስ አበባ ህዝብ ወደ 2.9 ሚሊዮን ነበር። የአዲስ አበባ ሕዝብ አሁን ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይገምታል። ከዚህ ውስጥ 85% የሚሆኑት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አማርኛ ሲሆን እንደተደራቢ ቋንቋ ከ98% በላይ አማርኛን ይናገራሉ። የአዳማና አካባቢዋ ነዋሪ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ነው። ከዚህ ሕዝብ ወደ 80% የሚሆነው አማርኛ ተናጋሪ ነው። የቢሾፍቱና አካባቢዋ ሕዝብ ወደ እሩብ ሚሊዮኑ ሊደርስ ይችላል። ከ80% የሚሆነው ነዋሪ አማርኛ ተናጋሪ ነው።

– ደቡባዊ ቤሬ እና ጊምቢቺን ወረዳዎች አቋርጦ በምስራቅ በኩል፣ ከአዲስ አበባ ድንበር እስከ አማራ ክልል ድንበር ድረስ ወደ 40 ኪሎሚትር ይሆናል። በስተሜን ምስራቅ በኩል ደግሞ የቤሬ ና የአለልቱ ወረዳዎች አቋርጠን ከአዲስ አበባ አማራ ክልል ድንበር 55 ኪሎሚተር ነው። የጊምቢቺ ወረዳ ነዋሪዎች የተወሰኑቱ አማርኛ ተናጋሪ ቢኖሩባቸውም አብዛኞቹ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ናቸው። በአዲስ አበባና በአማራ ክልል መካከል ባሉ ወረዳዎች የሚኖሩ ዜጎች በአብዝኛው ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ናቸው።

– በአዳና ሎሜ ወረዳዎችን አቋርጦ ከቢሾፍቱ አማራ ክልል ያለው ርቀት ወደ 32 ኪሎሚተር ገደማ ነው። ከቢሾፍቱ በስተምስራቅ ባለው የአዳ ወረዳና በሰሜን ሎሜ ወረዳ የሚኖሩ ነዋሪዎች ወደ አምሳ ሺህ ቢጠጉ ነው።

– ከአዳማ ከተማ አማራ ክልል ድንበር 24 ኪሎሜትር ብቻ ነው። አማራ ክልል እስኪደርስ ድረስ ከአዳማ በስተሰሜን የሚኖሩ ነዋሪዎችን ብንደምራቸው እነርሱ ወደ አምሳ ሺህ የሚጠጉ ናቸው።

እንግዲህ የአዲስ አበባ ከተማን ሕዝብ እና የቢሬና አለልቱ ወረዳ ነዋሪዎችን ብናወዳደር ሰማይና ምድር ነው። በሺሆች የሚቆጠሩ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በቤሬና በአልለቱ ቢኖሩም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማርኛ ተናጋሪዎች በሸገር ይኖራሉ። በአዳና በሎሜ ወረዳዎች የሚኖሩ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በቢሾፍቱ ከተማ ከሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎች ቁጥራቸው በጣም ያነሰ ነው። በአዳማና በአማራ ክልል መካከል የሚኖሩ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በሺሆች ቢቆጠሩም፣ በአዳማ ከተማ የሚኖረው አማርኛ ተናጋሪው ግን በመቶ ሺሆች የሚቆጠር ነው።

እንግዲህ አሁን ላለው አወቃቀር ቋንቋ መስፈርት ከሆነ፣ አዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱና አዳማ ወደ አማራ ክልል መጠቃለል ነበረባቸው። ግን አልተጠቃለሉም።

ቋንቋን እንደ ትክክለኝ የአወቃቀር መሰፈርት ነው ካሉ፣ በመስፈርቱ መሰረት አዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ አማርኛ ተናጋሪዎች የበዙበት ስለሆነ ወደ አማራ ክልል እንዲጠቃለሉ መስማማት ይኖርባቸዋል። ” አይ አይሆንም፤ እዚያ አካባቢ የቋንቋ መስፈርት ብቻ መታየት የለበትም፣ እንዴት የአለልቱ፣ የጊምቢቺ፣ የቤሬ፣ የአዳ ወረዳ ኦሮሞ ገበሬዎች ወደ አማራ ክልል ይጠቃለላሉ ?” የሚል ብሶት ከቀረበ ደግሞ፣ አፋቸውን ሞልቶ የቋንቋ አወቃቀር ይስራል እያሉ የሚያደነቁሩንን፣ እኛ የቋንቋ አወቃቀር ብቻውን አይሰራም ብለን ስንከራከር ፣ እንዲሁ በስሜትና በጭፍን “የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች” እያሉ የሚያቀርቡትን ክስ ማቆም አለባቸው። በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱ፣ በአዳማ ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች የሚኖሩ ኦሮሞኛ ተናጋሪዎች ወደ አማራ ክልል እንዲገቡ እንዳልተፈለገው ሁሉ፣ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ…የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎች በኦሮሞ ክልል መቀጠል እንደሌለባቸው ማመን አለባቸው። ሁለት ወዶ አይቻልምና።

እኛ ቋንቋ ብቸኛ ሳይሆን ከሌሎች መስፈርቶች ጋር እንድ አንድ መስፈርት አድርገን ነው የምናየው። ለዚህም ነው ቋንቋን የሕዝብን አሰፋፈር፣ ታሪክን፣ ጂዮግራፊን፣ የአስተዳደር አመችነትን ከግምት በማስገባት ፣ እንደ መፍትሄ፣ በአዲስ አበባ፣ ደብረዘይት/ቢሾፍቱ፣ አዳማ..ዙሪያ ባሉ ወረዳዎች የሚኖሩ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችን፣ እንዲሁም በከተሞች የሚኖሩ አማርኛ ተናጋሪዎች ፣ በፍቅር የሚያያዝ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ የኦሮሞ ክልል፣ የአማራ ክልል ሳይባል፣አማርኛም አፋን ኦሮሞ የስራ ቋንቋ ተደረጎ መኖር የሚቻልበትን፣ አዲስ አበባን ያካተተ ፣ ሕብረ ብሄራዊ አስተዳደር ይቋቋም የምንለው። ይሄ አስተዳደር ታሪካዊ ስሙን ሸዋ ተብሎ ሊጠራ ይችላል።

የኦሮሞ አክራሪዎች ያለ ኦሮሞነት ምንም ነገር አይታያቸውም። በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ የጊምቢቺ ኦሮሞዎች መብት እንጅ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአዲስ አበባ፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ የአዳማና የቢሾፍቱ አማርኛ ተናጋሪ ወገኖች መብት አይታያቸውም። የኛ ዘር ከሚሉት ዉጭ ሌላው ስው አይመስላቸውም። እኛ ግን የጊምቢቺ ኦሮሞ ገበሬዎችን ጨምሮ የሁሉም መብት እንዲከበር ነው የምንሟገተው። የኛና የነርሱ ልዩነት እንግዶህ ይሄ ነው።


► መረጃ ፎረም - JOIN US